Thursday, May 4, 2023

ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ‘ዘ ዊክኤንድ’ በእናቱ ስም የሰየመውን የኢትዮጵያ ቡና ለገበያ ሊያቀርብ ነው
4 ግንቦት 2023

#image_title

ታዋቂው ድምጻዊ “ዘ ዊክኤንድ” እናቱን እና የቤተሰቡን ትውልድ አገር ለማክበር በሚል የኢትዮጵያ ቡና ሽያጭ ሊጀምር ነው።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ “ዘ ዊክኤንድ” በእናቱ ስም ሳምራ ሲል የሰየመውን ቡና፣ ከ“ብሉ ቦትል ኮፊ” ጋር በመተባባር ለሽያጭ ማቅረቡን በትዊተር ገፁ ላይ ይፋ አድርጓል።

አቤል ተስፋዬ እና የሪከርድ ኩባንያው በጋራ በመሆን “ብሉ ቦትል ኮፊ” በሚል ስም ባቋቋሙት ድርጅት ስር የኢትዮጵያን ባሕል እና የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ደረጃ ለመሸጥ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በድረገፁ ላይ ይፋ ተደርጓል።

“የኢትዮጵያ ባሕል ወሳኙ የማንነቴ አካል ነው. . .” ሲል የተናገረው አቤል፣ የኢትዮጵያ ባህል፣ እሴቶች እና ቡና ላይ የዓለም ዐይኖች እንዲያርፉ ለማድረግ ከብሉ ቦትል ኮፊ ጋር በመተባባር እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል።

አቤል በልጅነቱ እናቱ በኢትዮጵያ ባህል መሰረት ቡና አፍልተው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ሲጠጡ ይመለከት እንደነበር ገልጾ፣ ይህም “የመጣበትን ማኅበረሰብ እና ማንነቱ ሁል ጊዜም እንዲያከብር” እንዳደረገው ገልጿል።

ሳምራ ቡና የሚለው ሃሳብ በአቤል እና በስራ ሸሪኮቹ ከተጠነሰሰበት እኤአ ከ2002 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ቡና እንደሚያስመጡ በድረገፁ ላይ የሰፈረው መረጃ ያሳያል።

ከሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ለገበያ እንደሚቀርብ የተነገረውን ቡና በመቅመስ አቤል እና እናቱ ተሳትፈዋል።

ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ቡናውን በእናቱ ስም የሰየመበትን ምክንያት ሲያስረዳ ለእናቱ እና ለኢትዮጵያዊ የዘር ግንዱ ያለውን ክብር ለመግለጽ መሆኑን አክሎ በድረገፁ ላይ አስፍሯል።

ይህ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳየት እንዲሁም ለእናቱ መታሰቢያነት ለሽያጭ ከቀረበው ቡና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ አቅዷል።

ብሉ ቦትል ከሚያገኘው ሽያጭ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሀያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በዩኤስ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል እርዳታ እንዲደርሳቸው ለማድረግ እንደሚለግስም በመግለጫው ላይ ተካትቷል።

ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊክኤንድ) ከዚህ በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሥራ ለመደገፍ የአንድ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መለገሱ ይታወሳል።

በወቅቱ ድምጻዊው በይፋዊ የትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት “በኢትዮጵያ ከጨቅላ ሕጻናት እስከ አዛውንቶች በጭካኔ ሲገደሉ እና ከፍርሃት የተነሳ ቤታቸውን ጥለው ሲፈናቀሉ ስሰማ ልቤ ይሰበራል” ብሏል።

ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች በካናዳ ተወልዶ ያደገው ዘ ዊክኤንድ (አቤል ተስፋዬ) በሙዚቃው ዘርፍ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ኤምቲቪ፣ ቪኤምኤ እና የአሜሪካ የሙዚቃ ሽልማቶችን አግኝቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በአሜሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጠው ሱፐር ቦውል የእግር ኳስ ጨዋታ በእረፍት ሰዓት ላይ በመዝፈን አድናቆት ተቸሮታል።

bbc
https://amharic-zehabesha.com/archives/182250

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...