Saturday, April 15, 2023

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
#image_title

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወኃምስቱ ዓመቱ ምሕረት

በስመ አብ፣ወወልድ፣ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣

• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፋ የቆማችሁ፣

• በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣

• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵውያት በሙሉ!

ትንሣኤና ሕይወት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

“እሙታን ተንሢኦ ሲኦለ ከይዶ በሞቱ ለሞት ደምሰሶ፡- ከሙታን ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ በሞቱ ሞትን ደመሰሰው” /መጽሐፈ ኪዳን/

ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሥጋ ሰብእ ተገልፆ ዓለምን ከሞተ ኃጢአት እንደሚታደግ ከጥንት ጀምሮ ነቢያት ሲያስተምሩና ሲመክሩ ኖረዋል፡፡

እግዚአብሔር በጠባዩ በደለኛውን ከቶ የማያነጻ አምላክ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንጻሩ ደግሞ ለፍጥረቱ ፈጽሞ የማይጨክን አምላክ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እግዚአብሔር ሰውን በፈጸመው በደል ምክንያት ቢቀጣውም የኋላ ኋላ ቅጣቱን ወደ ራሱ አዙሮ በመቀበል ሰውን በሚያስደንቅ ምሕረቱ ተቀብሎታል፡፡ በዚህም አድራጎቱ እግዚአብሔር ሕግን በማክበር፣ ፍርድን በመጠበቅ፣ ምሕረትን በማድረግ ትክክለኛነቱን በሚገርም ሁኔታ ፈጽሞ እናየዋለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያመሰጥር እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡-

• “ሁሉም ኃጢአትን ሰርተዋልና የእግዚአብሔር ክብር ጐድሎአቸዋል በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፤ እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስርያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎት ስለመተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፤ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው” ይለናል (ሮሜ. 3፡23-26)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!!

ለጌታችን መሰቀልና መሞት መንሥኤ የሆነው የእኛው በደል ነው፡፡ በደላችን እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ አሳጥቶ ኃጢአተኞች እንድንሆን አድርጎናል፡፡ የኃጢአት ደመወዝ ደግሞ ሞት ስለሆነ በኃጢአታችን ለሞት ተዳርገናል፡፡

በዚህ ምክንያት ከተጫነብን የሞት ዕዳ ሊገላግለን ጌታችን በእኛ ፈንታ ተሰቅሎ፣ ንጹህ ደሙንም መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ የሞት ዕዳ ከኛ እንዲነሣ አደረገልን፡፡

እግዚአብሔርም በኢየሱስ ክርስቶስ ንጹህ ደም ምክንያት ሙሉ ይቅርታን ሰጥቶ ታረቀን፤ ወደ እሱም አቀረበን፤ ተቀበለንም፡፡ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስን ደም በፊት ለተደረገውም ሆነ ለወደፊት ለሚሆነው ኃጢአት መደምሰሻ ወይም ማስተሰረያ አድርጎ በቀዋሚነት አጸናው፡፡

በመሆኑም ቀደምት አበውም ሆኑ ደኃርት ውሉድ የሚድኑት በኢየሱስ ክርስቶስ ንጹህ ደም መሆኑን ክርስቲያኖች ሁሉ ሊገነዘቡት፣ ሊቀበሉትና ሊያምኑበት ይገባል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔር በዚህ መሥዋዕት እኛን በማጽደቁ ፍጹም ጻድቅ ወይም እውነተኛ መሆኑን አሳየ” በማለት ያረጋግጣልና ነው፡፡

እንግዲህ ጌታችን በዚህ መሥዋዕትነቱ የቀደመውን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ስላስወገደው በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ቀጥሎም ከአዳም ጀምሮ እስከ ዕለተ ስቅለቱ ድረስ በሰቆቃና በስቃይ የነበሩ ነፍሳተ አበውን ወደ ጥንተ ሀገራቸው ወደ ገነት መለሳቸው፡፡

በዚህም በደልና ፍዳ ኃጢአት ሲኦልና ዲያብሎስ ተሸንፈው ባዶ እጃቸው ስለቀሩ ሲኦልን ረግጦ በሞቱ ሞትን ደመሰሰው ተብሎ የምስራቹ ተነገረን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!!

ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን በከፍተኛ ደረጃ የምታከብረው በዓለ ትንሣኤ በእግዚአብሔር ችሎት የሚያስፈርድብንና የሚያስቀጣን በደላችን ስለተሰረዘ፣ ቅጣታችንም ስለተነሣ፣ እኛን ለመዋጥ አፋቸውን ከፍተው የሚጠብቁትን ሞትና መቃብርም ባዶአቸው የቀሩበት አምላካዊ ድል የተፈጸመበት በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫችን የጌታችን ትንሣኤ ነው፡፡

ጌታችንም ከመሞቱ በፊት በቃልና በተግባር ያረጋገጠልን ይህንን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በቅዱስ ወንጌል፡- “ኃጢአትህ ተሰረየልህ ወይም ተሰረየልሽ” በማለት ኃጢአትን ሲሰርዝ አይተናል፡፡

በሰው ሁሉ ላይ የበላይነት አግኝተው በመርዛም ተግባራቸው ሰውን ሲያሰቃዩ የኖሩ ሰይጣንና ሠራዊቱ “አንተ ርኩስ መንፈስ እልሃለሁ ከሱ ውጣ” እያለ በማስወጣት ወደ ጥልቁ ሲያሠጥማቸው አይተናል፡፡

በአጋንንት ጠንቅ በልዩ ልዩ ደዌና በሽታ ተይዘው ሲሠቃዩ የነበሩ ሰዎችንም ከበሽታቸው ገላግሎ ፍጹም ጤንነት ሲሰጣቸው አይተናል፡፡

መቃብርን ቤታቸው አድርገው የነበሩትንም ሙታን “ና ውጣ ከመቃብር” እያለ ከመቃብር ሲያስነሣቸው አይተናል፡፡ የሞቱትንም “ተነሥ፤ ተነሽ” እያለ ሲያስነሣቸው ተመልክተናል፡፡ በተሰቀለበት ዕለትም በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም አምስት መቶ ሙታን ተነሥተው በከተማው ውስጥ ለብዙ ጊዜ መቆየታቸውን ተምረናል፡፡

ታድያ እነዚህ አምላካዊ ድርጊቶች በሙሉ በደልና ፍዳ ኃጢአት፣ ሞትና ሲኦል፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የእነዚህ አጋፋሪ የሆነው ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ ተሸንፎ ባዶውን ወደ ጥልቅ መስመጡ የሚያሳዩን አይደሉምን; ልብ ብለን ከተመለከትነውና ካስተዋልነውስ ትንሣኤው የጌታችንን እውነተኝነት፣ የዲያብሎስና ሠራዊቱን ተሸናፊነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩን አይደሉምን;

የዚህ ሁሉ ማረጋገጫ ማተምስ የጌታችን ከሞት መነሣት አይደለምን ከዚህ አኳያ ጌታችን ሲነሣ ብቻውን አልተነሣም እንላለን፡፡

ነገር ግን እሱ ሲነሣ ገና ሳይሞት ያስተማረው ትምህርትና የፈጸመው ተአምራት ሁሉ አብሮ ተነሥቶአል፤ ምክንያቱም ትንሣኤው የእውነተኝነቱ ማረጋገጫ ነውና፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!!

እኛ የትንሣኤ ልጆች ነን፤ ጌታችን ሞትንና መቃብርን ድል ነሥቶ የተነሣው እኛም እሱን ተከትለን ሞትንና መቃብርን ድል እንድንነሣ እንጂ የእነሱ ሢሣይ ሆነን እንድንቀጥል አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ እንዳለመታደል ሆኖ የሰው ልጆች ዛሬም ምርጫቸው ትንሣኤ ሳይሆን ሞት ሆኖ መገኘቱ እጅግ በጣም የሚቈጭና የሚያሳዝን ነው፡፡

ዛሬም ሰዎች እርስ በርሳቸው እየተጣሉና እየተገዳደሉ የሞትና የመቃብር ሢሣይ በመሆን ቀጥለዋል፤ ከዚህ አስከፊና ጎጂ ድርጊታቸው ለመቆጠብም ዝንባሌ አይታይባቸውም፤ ታድያ እኛ ሰዎች የሞትንና መቃብርን ጎጂነት፣ የትንሣኤንና የጤናማ ሕይወትን ጠቃሚነት ለይተን በማወቅ ለጥቅማችን መቆም የማንችል ከሆነ የጌታችን ትንሣኤ አከበርን ማለቱ ጥቅሙ የቱ ላይ ነው

ከመገዳደልና ከመጨካከን ሳንመለስ የምናከብረው በዓልስ እግዚአብሔር ይወድልናል ወይ; ይቀበለዋል ወይ

ይህ ፍጹም ሊሆን እንደማይችል ሕሊናችን ሳይቀር ይመሰክርብናል፡፡ ታድያ መፍትሔው ምንድን ነው ያልን እንደ ሆነ መፍትሔውማ ንስሐ መግባት ነው እንላለን፡፡

ንስሐ መግባት ማለት ይከተሉት የነበረውን ክ ተግባር ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጎ በመተው ወደ ደገኛው ተግባር መመለስ ማለት ነው፡፡ ንስሐ ማለት ትናንት በጥይት ሲጠፋፉ የነበሩ ወገኖች ዛሬ እሱን አቆመውና በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ችግራቸውን በፍቅር ለመፍታት መወያየት መቻል ማለት ነው፡፡

ትክክለኛው ንስሐ እንዲህ ያለው ነው፡፡

ይህንን የመሰለ ጥሩ አርአያ ያለው ንስሐ በሀገራችን በቅርቡ ሲፈጸም አይተናል፤ ይህንን ያደረጉ ወገኖች በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናቸዋለን፤ ይህን ያደረጉ ወገኖች ትክክለኛውን ትንሣኤ ተነሥተዋል፤ የትንሣኤውንም በዓል በትክክል አክብረዋል፡፡

ሆኖም ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የሚያስገኘው ከእምነት ሲነሣ ነውና ነገሩ ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ተብሎ በእምነት ሊደረግ ይገባል፤ ገና ወደ ጠረጴዛ ያልመጣችሁ ወገኖችም ንስሐ ገብታችሁ ወደ ውይይት እንድትመጡና የጋራ ሀገራችንን በጋራ እንድናገለግል በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናቀርባለን፡፡

ከእንግዲህ ወዲህ መፎካከር ይቁም፤ መወያየት ይቅደም፤ ከሰላም፣ ከአንድነትና ከፍቅር ተጠቃሚ መሆናችንን አንዘንጋ፤ ኢትዮጵያ ለሁላችንም በቂ ብቻ ሳትሆን፤ ከበቂም በላይ ናት፡፡

ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፤ ይህ የኔ ነው ይህ የኔ ነው በሚል ደካማ አመለካከት ራሳችንን በራሳችን አንጉዳ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የጥይት ድምፅ ይብቃ፤ የዕለቱ ዓቢይ መልእክታችን ይህ ነው፡፡

በመጨረሻም፡-

የትንሣኤውን በዓል ስናከብር የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጨነቁትን በማጽናናት፣ እንደዚሁም የተገኘውን የሰላም ጭላንጭል ይበልጥ ለማስፋትና የሀገር አንድነቱን በዕርቅ ዘላቂ ለማድረግ ቃል በመግባት የፋሲካን በዓል እንድናከብር በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ

ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ 8 ቀን ፳፻፲፭ዓመተ ምሕረት

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
https://amharic-zehabesha.com/archives/181868

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...