Saturday, April 1, 2023

አማካሪ የሌለው መንግስት አገር እያፈረሰ ነው - ገለታው ዘለቀ
አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ልዩ ሃይል እንዲፈርስ መንግስት መወሰኑን ሲግለጹ አዳመጥኩ። መቼስ በአንድ ሉዓላዊት ሃገር ስር መደበኛ ያልሆኑ ወታደራዊ አደረጃጀቶችና ልዩ የሚባሉ የክልል ሃይሎች መኖር እንደሌለባቸው የታወቀ ነገር ነው። ክልሎች የየራሳቸው የፍትህ አካል የሆነ ፖሊስ የሚኖራቸው ቢሆንም፣ ነገር ግን ሚሊተሪ የሚገነቡበት ሁኔታ አይኖርም። ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጊዚያት በተለምዶ ልዩ ሃይል የሚባል አደረጃጀት ተፈጥሮ ሁሉም ክልሎች ይህንን ሃይል ገንብተዋል። አንዳንድ ክልሎች ከፍ ያሉ ሚሳየሎችን ሳይቀር ታጥቀዋል ይባላል።

#image_title

ስለ እነዚህ ልዩ ሃይሎች ስናወራ እነዚህ ሃይሎች ወታደራዊ ተቋም እንደመሆናቸው የየራሳቸውን የሚሊተሪ ኢንተለጀንስ ገንብተዋል። ይህ ማለት በክልሎች መካከል የእርስ በርስ የስለላ ስራዎች ይካሄድሉ ማለት ነው። እነዚህ የክልል ሃይሎችና ሌሎች አደረጃጀቶች የሚሊተሪ ኢንተለጀንስ ስራ ውስጥ ለውስጥ ሲሰሩ በቆዩባቸው በነዚያ ጊዚያት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፍክክር ውስጥ ገብተው ከህዝባቸው ጉሮሮ እየነጠቁ እንዲያውም አንዳንድ ክልሎች በተለይ የፌደራሉን መንግስት የሚገዳደር ሃይል ገንብተዋል። ከሁሉም በላይ የክልሎች ልዩ ሃይሎችና ሌሎች መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች በየክልሉ ህዝብ ዘንድ የመከታነት ስሜትን አዳብረዋል።

ታዲያ  ዛሬ ላይ ይህንን ሃይል ድንገት ልናፈርስ ነው የሚባል ነገር ሲመጣ መጀመሪያ መነሳት ያለበት ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ሃይል የሚባለው አደረጃጀት በኢትዮጵያ ውስጥ አንዴት ተፈጠረ? እንዴት ተጸንሶ እንዴት ተወለደ? እንዴትስ ነው ይህ ሃይል ነውጥና ሽብር ሳይፈጠር የሚፈርሰው? የሚለውን ጉዳይ ማንሳትና በጽሞና ነገሩን ማጤን ያስፈልጋል። ይህንን ሃይል ማፍረስ እንዳለብን ብናውቅም መቼና እንዴት የሚለውን ጉዳይ መለየት ቁልፍ ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ሃይል የተጠነሰሰው በሃገራችን ውስጥ ሽግግር ይመራል የተባለው የፖለቲካ ሃይል መክሸፍ መክሸፍ ሲሸት ነው። ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ሃገሪቱ ትጠብቃቸው የነበሩ የሽግግር ስራዎች በቅደም ተከተል መከናወን ሳይችሉ ሲቀሩና በገዢው ሃይል ውስጥ መከፋፈል ሲመጣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ አለመተማመን (uncertainty) ረበበ። ከዚህም በላይ አሻገሪው ሃይል ከከሸፈባቸው ዋና ዋን ምክንያቶች መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የህዝቡን ዋስትና (security) መጠበቅ አለመቻል አገሩን ለትጥቅ አነሳስቷል።  ነገሮች እየከፉ ሲሄዱ ክልሎች ይህንን ክፍተት ለመሙላትና ወደፊት ክፉ ጊዜ ከመጣ ሁላችንም ጠመንጃችንን ወልውለን ራሳችንን መጠበቅ አለብን ከሚል ስሜት የተነሳ ታጥቀዋል። የፌደራል መንግስት የፖለቲካ ቁጥጥር ማነስ ያመጣው ስርዐታዊ ሽብር ክልሎችን እያስበረገገ ጠብመንጃ እንዲያነሱ አድርጓል። የሽግግር ክሽፈት ሲመጣ መደበኛ ያልሆኑ የትጥቅ አደረጃጀቶች ማቆጥቆጣቸው የሚጠበቅና በሌሎች ሃገሮችም የታየ ነገር ነው። በመሆኑም ከፍ ሲል እንደገለጽነው ልዩ ሃይል የፌደራል መንግስት ቁመና በተግባር ሲመዘን የሃገሪቱን ወፍራም ችግሮች ለመፍታት ሲበዛ መቅጠኑ ያመጣው የመተማመን (uncertainty) ውጤት የወለደው ሃይል ነው ማለት ነው። ልዩ ሃይል በተለይ በገዢው ፓርቲ ለሂቃን መካከል ያለን የፖለቲካ ክፍፍል የሚያሳይ ተግባራዊ መገለጫም ነው። ዞሮ ዞሮ የፖለቲካው መከፋፈልና ሆድና ጀርባ መሆንም ያው የፖለቲካ ክሽፈት ውጤት ነው።

በዚያም በዚህም ይህ የፖለቲካ ክሽፈት የወለደው ልዩ ሃይል ዛሬ ላይ ፈርጥሞ በተለይም በህዝቡ ልብ ውስጥ አያሌ ቦታ አግኝቶ ይታያል። ለምሳሌ በአማሮች ዘንድ ባህላቸውን ተከትሎ የመጣ ፋኖነት በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ንቅናቄ አይደለም። አማሮች ብሶት ሲበዛባቸው የመጨረሻ ምርጫቸው የሆነውን የፋኖነት ባህል ተከትለው ተደራጅተዋል። ይህ ንቅናቄ ጠመንጃ ያነገተውን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን በአማሮች ልብ ውስጥ የገባ ጊዚያዊ ራስን የመከላከል ክተት ነው። ደቡቦች፣ ኦሮሞዎች፣ሲዳማዎች፣ ወዘተ እንደዚሁ ስርዓታዊ ክሽፈት ሲሸታቸው ለራስ መከላከያ በሚል ተደራጅተዋል። እነዚህ አደረጃጀቶች ደግሞ በአካባቢው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸዋል። ይህ አደረጃጀት ለሃገሪቱ ህልውና የተቀበረ ፈንጂ መሆኑ የታወቀ ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው እነዚህ ሃይሎች የአሻጋሪው የፖለቲካ ሃይል ክሽፈት ጸንሶ የወለዳቸው ሃይሎች ሲሆኑ እነዚህ ሃይሎች የፌደራል መንግስት ጸጥታ የማስከበር አቅም የለውም ብለው ያምናሉ፣ ፌደራል መንግስት የሚታመን አይደለም ሙሉ ልባችንን የምንሰጠው ሃይል አይደለም ብለው ያምናሉ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሃገር የመፍረስ አደጋ ላይ ናት ብለው ያምናሉ። ምክንያቶቻቸው እንደዚህ ከሆነና የተፈጠሩበት መነሻ የፖለቲካ ክሽፈት ከሆነ እነዚህ ሃይሎች መቼና እንዴት ነው የሚፈርሱት? አንዴት ነው እጅ የሚሰጡት? እንዴት ነው ሃገራዊ ቀውስ ሳይመጣ በደስታና በሰላም በሃገሪቱ አንድ ወታደራዊ ሃይል የምንገነባው? የሚለው ላይ መነጋገር ተገቢ ነው።

ጎበዝ፣ ይህ መንግስት መካሪ የሌለው መንግስት ነው። ተቋም ሲገነባ ድንገት፣ ሲያፈርስ ድንገት ነው። የሃገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ያለው ቅደም ተከተል አወሳሰድ ችግሮችን የሚፈታ ሳይሆን የበለጠ የሚያወሳስብ ነው። በዚህ ወቅት ልዩ ሃይሎችን ትጥቅ ፍቱ ለማለት በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የመንግስት አካሄድ ራሱን ፌደራል መንግስቱን  አንዳያፈርሰው ከባድ ስጋት አለኝ። ድንገት በአዋጅ ትጥቅ ማስፈታት ቀላል ነገር አይደለም። ከሁሉ በላይ የክልሎቹን ውስጣዊ ሰላምን የሚያውክና በአመራሩና በህዝቡ መካከል ከፍተኛ ግጭትን ያመጣል።ይህ ደግሞ ተደምሮ ከፍተኛ ሃገራዊ የጸጥታ ችግር ያመጣል። ከሁሉ በላይ ጠመንጃህን አምጣ የለም አላመጣም ከሚለው ግብግብ ባሻገር በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅራኔን ያመጣል።ደም ይፈሳል። በግልጽ የተደራጁ ሃይሎች ወደ ህቡእ ትግል ያመሩና ነገሮች ጨርሰው ከቁጥጥር ይወጣሉ።

ስለዚህ ሃገራችን ልዩ ሃይልን አፍርሳ አንድ ጠንካራ ብሄራዊ ስሜት ያለው የመከላከያ ሃይል ለመገንባት በመጀመሪያ የፖለቲካ ለውጦችን ማምጣትና ሁሉን አቀፍ የሽግ ግር ጊዜ መፍጠር ይገባል። ይህንን ማድረግ የወቅቱ መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ስለሆነም መንግስት በየክልሉ ገብቶ ደረጃውንና ወቅቱን ያልጠበቀ ነገር ውስጥ ገብቶ የሃገርን ሰላም ከሚያምስ በመጀመሪያ ከራስ በላይ ለሃገር በማሰብ የተውጣጣ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ቆራጥ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ይድረስ። ጠቅላይ ሚንስትሩ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ስልጣናቸውን ያስረክቡና የሽግግር ጊዜ ጥሪ ይደረግ። ከዚህ በሁዋላ ሃገሪቱ መዋቅራዊ ለውጦችን ለማምጣት ሁሉን አቀፍ ምክክር አድርጋ ስታበቃ የህገ መንግስት ማሻሻያ ስራዎችን የሚሰራ ኮሚሽን ፈጥራ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት የመጀመሪያው ተግባር ነው። ከዚህ በኋላ ለመሃላው የሃገራችን ህዝብ ዋስታንዎችን እናሰፋለን። ደግሞ ዋስትናዎች ሲሰፉና ስጋቶች ሲቀንሱ በቀጥታ ወደ ህዝባዊ ግንዛቤ (public awareness) ስራ መግባት ያስፈልጋል። የህዝባዊ ግንዛቤዎችን ስራ ሰርቶ ልዩ ሃይሉን ማፍረስ ቀላል ይሆናል። መደበኛ ያልሆኑ ወታደራዊ አደረጃጀቶች ፈርሰው መከላከያ ሰራዊታችንን አጠንክረን ወደፊት መራመድ የምንችለው ችግሮችን በቅደም ተከተል ስንፈታ፣ በጥልቀት በተጠና ፍኖተ ካርታ እየታገዝን ስንሰራ ነው።

ይህ መስንግት ስራው ሁሉ አደገኛ ሆኖ ይታያል። አደገኛ ውሳኔዎችን ድንገት ይወስናል። ይህ ችግር ሄዶ ሄዶ ፌደራል መንግስቱን እያንገዳገደው እዚህ ደርሰናል። ስለዚህ ድንገት ተነስቶ ልዩ ሃይሎችን ከዛሬ ጀምሮ ልናፈርስነው.......... ሳይሆን መጀመሪያ የተፈጠሩበትን ስጋቶች ማጥፋት፣ መተማመን መገንባትና ህዝባዊ ግንዛቤ ማድረግ መቅደም አለበት። ይህ የከሸፈ የፖለቲካ ሃይል ከአንድ ክሽፈት ወደ ሌላው ክሽፈት እየዘለለ ሃገሪቱን ብዙ ዋጋ ባያስከፍላት ጥሩ ነው። ሃይ ሊባል ይገባል።
https://amharic-zehabesha.com/archives/181446

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...