Saturday, April 1, 2023

የወዳጆቻችን "ትንፋሻችሁን እንዳልሰማ  የፖለቲካ ዘዬ (intimidation tactics) - ሸንቁጤ- ከካናዳ
“ If you pluck a chicken one feather at a time nobody will notice it.”

Mussolini

የዛሬ አመት አካባቢ  "FASCISM: A Warning from Madeleine Albright “  በሚል ርዕስ  ለንባብ    ያበቁትን መፅሃፍ አስመልክቶ   የቀድሞዋ  የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ  ሚ/ር  ወ/ሮ  ኦልብራይት  VOX ከተባለ  መፅሄት ጋር ያደርጉትን የዳሰሳ    ቃለ  መጠይቅ  በአገራችን እየታዩ ካሉ ጥቂት ነባራዊ ሁነቶች ጋር    በማነፃጸር  አጋርቼ  ነበር::

ህዝቡ  "ሙሴዎቻችን "  ብሎ  እርካብ ሆኖ ካቆናጠጣቸው መንበር ቁብ ብለው ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩት "መሪዎች”  በጭፍሮቻችው "ግፋ በለው !" እየታገዙ ፖለቲካውን ከድጡ ወደማጡ አገሪቱንም የቁልቁሊት ይዘዋት እየነጏዱ ነውና  “ቀጥሎስ   ወዴት ?”   ብለን ቆም ብለን ማሰላሰሉ የግድ ይላል::

"ወዳጆቻችን" ይህን የፈቀዱልን አይመስልም ! ... እንደ ወ/ሮ  ኦልብራይት እይታ ደግሞ የዶሮዋን ላባ ነቀላ  አሀዱ ብሎ የሚጀምረው  በዚሁ  ዝም ፀጥ በማስኘት (intimidation  tactic) ነው:: አስረን  :ደብድበን : አፈናቅለን : በጅምላ አርደን ገለን እስክንጨርሳችሁ ድረስ “እህህ" እያላችሁ ከመብከንከን  ወይ ዳር ቆሞ ከመመልከት ውጪ አልተፈቀደላችሁም ካሉን ሰነባብተዋል::

በተረኞቻችን ምናባዊ  አለም  ስለኢትዮጵያ ስለ በፍቅር አብሮ መኖር ወይም ስለ አማራ ጭፍጨፋ የሚናገር ብቅ ካለ ከያሉበት ጎሬ ተጠራርተው  የማስፈራሪያ  እና ዛቻ ናዳቸውን ለማውረድ አፍታም አይፈጅባቸው::

ጥቂት ማሳያዎች:-

በእ.ኢ.አ 2012  የአዲስ አመት ዋዜማ   ኮለኔሉ  በ4 ኪሎው ቤተመንግስት  ባዘጋጀው " የመደመር ጷግሜ "  በተሰኘ  የእራት ምሽት ህሊና ደሰሳለኝ  የምትባል ወጣት  ገጣሚ " የማጀት ስር ወንጌል " የተሰኘ  በወቅቱ  ይፈፀሙ የነበሩ አሰቃቂ ድርጊቶችን የሚነቅፍ  ዘለግ  ያለ ግጥም ታቀርባለች::በማግስቱ  ይኸው ግጥም  ያልተመቻቸው ሁለቱ  ዝነኛ የሰውዬው  የቀኝ ክንፎች በቴሌቪዥን  ጣቢያቸው ቀርበው " አንድን ብሄር ተሳድባለች !... ያውም በቤተ መንግስቱ! ..በጠቅላይ ሚንስትሩ ፊት!" የሚል የማስፈራሪያ ውርጅብኝ እያወረዱ ቡራ ከርዩ  ይላሉ :: እነኚህ  ሁለት ግለሰቦችም ሆነ ስብስባቸው በወቅቱ  ፍፁም ይጠፏቸዋል ብዬ የማላስባቸው ሁለት ሀቆች ነበሩ:-

ልጅቱ የግጥሟ አንኳር  ያጠነጠነው  አስፀያፊ እና አስቃቂ በሆነው “ ድርጊት"  ላይ የነበረ መሆኑን መካድ  አይቻልም :: ሆኖም በገና ለገና   ድርጊቱን የፈፀመው አካል  የኛ የሚሉት ቡድን በመሆኑ  " ህዝብ ተሳድባለች” ወደሚል  የተሳሳተ መደምደሚያ  በመውሰድ  ቁጣ  ቀስቅሶ የማስደንገጥ  እና  ዝም በማሰኘት(intimidation tactic)  እንዲህ አይነቱ  ትችት እና ነቀፌታ እንዳይደገም ማድረግ  ነበር::

ዛሬ  ለፍሬ የበቃላቸው የዘውግ ፖለቲካ ጥንስስ  ግብዓት አንዱ የሆነው  " ኢትዮጵያዊ  ማነው ?" የተሰኘው ግጥም ተፅፎ የቀረበው  በንጉሱ ዘመን በራሳቸው በአፄ ሃይለስላሴ በጎ ፈቃድ እና ድጋፍ  ይዘጋጅ በነበረ  የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  የግጥም  ምሽት  ላይ እንደነበር  ይዘነጉታል  ተብሎ  አይገመትም :: በተለይ ደግሞ የዚህ ግጥም  ፀሀፊ  የ ኦ.ነ.ግ  ጎምቱ መስራች  ኢብሳ ጉተማ  መሆኑ  እነኚህ ግለሰቦች ይህን ታሪክ አያውቁትም ለማለት የሚያስደፍር በቂ ምክንያት አይኖርም:: ነገሩን የወለፈንድ የሚያደርገው ታዲያ ከዛሬ 50 አመት በፊት የነበረ የመፃፍ እና የመናገር ነፃነትን  በወጉ የተጠቀመ የፖለቲካ አስተሳሰብ "..አሁን በኔ ዘመን እንዴት ተደርጎ!"  በሚል እብሪት  አፍ የማዘጋት ዘመቻው መጀመሪያው ያደረገው ወጣት ገጣሚዋን ህሊና ደሳለኝን መሆኑ ነበር::

ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ የመፃፍና የመናገር መብቶች  ከለውጡ ማግስት መልሶ ማቆጥቆጥ የጀመረ ቢስልም የለውጥ ሀዋሪያ የተባለለት ስርዓት ወደ አፈና ተግባሩ የተመለሰው  በጥቂት ወራት ውስጥ ነበር:: በተለይም የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን ኢላማ በማድረግ  በግልፅም ሆነ  በስውር  የሚያራምዷቸው አጀንዳዎች እና ፓሊሲዎች ላይ አስተያየት የሰጠ  የተቸ ወይም በማስረጃ የተደገፈ  ሪፖርታዥ  ለመስራት የሞከረም ሆነ ተሳክቶለት የሰራ  ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ  ማደሪያው እስር ቤት ሆነ:: የዚህ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት መካከል ጥቂቶቹ:-

የፍትህ መፅሄት አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ የኦህዴድ አገዛዝ እና አጋሮቹ ን የስውር አጀንዳ  አጋላጭ እና የማስጠንቀቂያ ደወል  በሆኑት በተለይ የመከላካያ  ሀይሉን ጏዳ  አብጠርጥረው በፈተሹ ፅሑፎቹ  ምክንያት  ዛሬም ድረስ እስርቤት እና ፍርድቤት ከመመላለስ አላረፈም::

ላለፉት 30  አመታት  በግል  የሚያምኑበትን  ሀሳብ እና ምልከታ በግላጭ ከመፃፍና ከመናገር ተቆጥበው የማያውቁት አቶ  ታዲዮስ  ታንቱ  በኦህዴድ አገዛዝ  የተጋረጠውን   የህልውና  አደጋ ደጋግመው በመናገራቸው  እና  ዝም  ለማለት  ፈፅሞ ባለመፍቀዳቸው የሽምግልና እድሜያቸውን በኦህዴድ እስር  ቤት  እየማቀቁ  ይገኛሉ::

ቀደም  ባሉት አመታት በቁም ነገር መፅሄት ባልደረባነቱ  በቅርቡ ደግሞ  በርዕዮት እና ተራራ ኔትወርክ በተባሉ የዩቲዩብ  መገናኛ መድረኮች  የምናውቀው  ታምራት ነገራ          በ ኦህዴድ እና አጋሮቹ  የነፃ አገር  ህልመኞች ላይ በሚያቀርበው የሰላ ትችቱ ምክንያት  ፍዳውን ለማሳየት እንዲመቻቸው  ኦሮሚያ ክልል  ውስጥ ወደሚገኝ ወይህኒ ቤት  ወስደው ሲያማቅቁት  አቆይተው በመጨረሻ ቢፈቱትም   አገር ጥሎ ለስደት ተዳርጏል::

ልክ እንደ ታዴዎስ ታንቱ  ሁሉ በተለይ በአማራው ማህበረሰብ ላይ  እየደረሰ ያለውን የጅምላ ግድያ  ስደት የኢኮኖሚና የስነልቡና ሰቆቃ ሳትታክት በመወትወቷ ምክንያት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህሯ መስከረም አበራ  ዛሬም ድረስ ከኦህዴድ አገዛዝ  የእስር  ኢላማነት  አልተረፈችም:: ኮሽ ባለ ቁጥር ወደ እስር  ቤት ከሚጎተቱት ቀዳሚዋ ሆናለች::

መአዛ  መሃመድ  ሌላዋ የኦህዴድ  ዋንኛ  ኢላማ ነች :: ሮሃ የተባለው የዩቲዩብ መገናኛ መድረክ መስራች ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ  የሆነችው መዓዛ መሃመድ  በተለይም  በ አማራነታቸው ብቻ ከወለጋ በግፍ የታረዱ እና  ከቀዬአቸው የትሰደዱ  ዜጎችን በአግባቡ በመሰነድ እና  ሪፖርታዥ  ከማዘጋጀት  ባሻገር  በህይወት ተርፈው ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉት ወገኖች የሰብአዊ   እርዳታ  በማቅረቧ ነበር ከኦህዴድ ጥርስ የገባችው ::  የኦህዴድ እስር  ቤቶች ቅንጣት ታህል እንኳ ፍራቻ ያልፈጠረባት ይህች እህት ልክ እንደሌሎቹ ዛሬም ድረስ ወይ እስር ቤት አልያም ፍርድ ቤት ተመላላሽ  ሆናለች::

እንዳው ለአብነት ያህል ከላይ የተጠቀሱት ጋዜጠኞች ተነሱ እንጂ  ቅጥ ያጣው የኦህዴድ  አፈና  እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት ሲፒጄ ሂዩማን ራይትስ ዋች  ኢሰመኮ እና የመሳሰሉት ተቋማት በየወቅቱ የኦህዴድ አገዛዝን አደገኛ አካሄድ ከመውቀስ እና አሳሳቢነቱን ከመግለፅ አልተቆጠቡም::

በአዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿ  ላይ የተጋረጠው የመሰልቀጥ አደጋ አሳስቦኛል ያለው እስክንድር ነጋ  የ አዲስ አበባ ባለ አደራ የተባለውን  ንቅናቄ  እንደመሰረተ ገና ከጅምሩ  ነበር  የማዋከብ  የዛቻ እና ማስፈራሪያ ዘመቻው  ከየአቅጣጫው ነገር ግን በተሰናሰለ መንገድ የተከፈተበት::  ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን ብንመለከት

“Election  have consequences “-  ይህን ያለው የሰሞኑ የኪሊማንጃሮው የ"ሰላም" ተጏዥ የአዲስ አበባን ህዝብ  በግልፅ  እየዛተና እያስፈራራ  በራሱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ነበር:: በዚህ ንግግሩ አዲስአበቤው አርፎ ካልተቀመጠ  ጭፍሮቹ በተጠንቀቅ እየጠበቁ መሆኑን እንዲያውም ለሱ ስራ እንደሚቀልልትና ከሱ የሚጠበቀው  " ተነስ" የሚል ቀጭን ትዕዛዝ እንደሆነ ጭፍሮቹ" ስራውን “ እንደሚጨርሱ በአደባባይ ነገረን

ፕሬዝዳንት ማሜ- የእስክንድርን የባላደራ ንቅናቄ ለማኮስመን (undermine) ለማድረግ ተልዕኮ የወሰደው ይህ ከእውቀት ፈፅሞ ነፃ የሆነ የፌስቡክ መሳለቂያ የሆነ እንጭጭ እስክንድርን ካልደበደብኩ እያለ  በፌስቡክ live ቀረርቶ ሲያሰማ  የዋለበትን ቀን አይተናል- ያው የጫት ሰዓቱ እስኪደርስ ድረስ:: በዚህ ያላበቃው ይኼ ልጅ ምርጫ ምልክቱን ጭልፊት ያደረግ "የፊንፊኔ ባላደራ" የሚል ፓርቲ አቋቁማለሁ ብሎ ምርጫ ቦርድ እስከ መሄድ እናም ይህንኑ "ፓርቲውን" ለማስተዋወቅ  ከOMN  ሰፋ ያለ የአየር ሰዓት ለቃለመጠይቅ ተሰጥቶት እንደነበር እናስተውላለን:: የልጁን ስብዕና በጥቂቱ ላየ ድርጊቶቹ በግብታዊነት የፈፀማቸው የቀልድ ይምሰሉ እንጂ  ሆን ብለው የተቀናበሩ እና  ለእስክንድር  እና ለአዲስ አበቤው "ንቅናቄያችሁ ከስላቅ ፖለቲካ  አያልፍም” የሚል መልእክት  ያዘለ  ነበር

ዶ/ር ሃንጋሳ  ኢብራሂም የሚባል (ዶክተርነቱን ከየት እንዳገኘው ባናውቅም ) ሌላው የፌስቡክ አርበኛ አዲስአበቤውን " የሴተኛ አዳሪ ልጆች" እያለ  በፀያፍ ቋንቋ ከመሳደቡም በላይ በርከት ያሉ  ስብዕናን የሚነኩ እና የሚያዋርዱ መልእክቶችን ሲያስተላልፍ ነበር:: የሚገርመውና " አይ ኢትዮጵያ!" ያስባለን ታዲያ ብልፅግና ይህን ግለሰብ  እጩ ተወዳዳሪ አድርጏ ለፓርላማ  ማስመረጡ የነበረ ሲሆን ያዳቆነ ሰይጣን እንደሚባለው  የለመደ ረዥም ምላሱ ለነ ሸመልስ አብዲሳም አልተመለሰ

"ጦርነት ይነሳል" - ይህን ያለው ኮለኔሉ በአንድ የፓርላማ ንግግሩ  እስክንድር  ነጋ እና ባልደራስን አስመልክቶ በሰነዘረው ዛቻ ሲሆን የቀኝ  ክንፎቹ ዛቻና ማስፈራራት   በተጨማሪ እርሱም የድርሻውን  ለመወጣት  በሚመራው  የአገዛዙ apparatus በኩል  እነ እስክንድር ነጋን ቢሮ እና የስብሰባ  አዳራሽ እንዳይከራዩ ከማድረግ አንስቶ በየሄዱበት እየተከተሉ ማዋከቡ ማስፈራራቱ እና በእስር  ማንገላታቱ ያለመታከት በመቀጠሉ  " መንግስት ሊያፈናፍነኝ አልቻለም "  በማለት ባልደራስን ለተቀሩት አባላቱ አስረክቦ ገለል ብሎ ሰንብቷል :: ሆኖም  የትግሉን  ስልቱን ሳይቀይር እንዳልቀረ በቅርቡ ታዝበናል::

ባለፈው ሳምንትም ይኸው "የወዳጆቻችን"  በዛቻና ማስፈራራት አፍን የማዘጋት ፋሽታዊ ስትራቴጂ ቀጥሎ ፀጋዬ  አራርሳ  የሚባል ፍጥረት ምን ሲደረግልደቱ  አያሌው  የመሰለውን አማራጭ የፖለቲካ ትግል ስልት አቀረበ? እንዴት ቢደፍር ነው  " የኛን" ፖለቲካ የሚተች ብሎ ልደቱን በሃሳብ  ሙግት ከመግጠም ይልቅ ስብእናውን በማጠልሸት ላይ አተኩሮ ሲያላዝን ዋለ አሉ:: የፀጋዬን አካኪ ዘራፍ አጠቃለን ስናየው -

ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ ባዘጋጀልን አዲስ የአማርኛ ቋንቋችን መዝገበ ቃላት መሰረት

ግሳንግስ- በጣም SERIOUS የሆነ ማለት ነው:: ልደቱ ያቀረበውን ፅሁፍ ግሳንግስ ብሎ ሲያበቃ በዛው አርፍተነገር ውስጥ በጣም "ሲሪየስ የሆነ" ይለዋል መልሶ:: አንድን አረፍተነገር እንኳ አስማምቶ  ያለተቃርኖ መጨረስ ያቃተው በሀሳብ ድርቅ የተመታ ከእብሪት እና ቡራከርዩ ሊዘል ያልቻለ መሆኑን አያሳብቅም ትላላችሁ?

ዶ/ር ፀጋዬ የርትዕ ሀሳብ  ድኚው ሲጨስበት  አብይ ወይም ሞት እያለ ለፈለፈ ...

በኢትዮጵያዊነት የተሳሰረ ተገዳዳሪ ሃይል ከመጣ መደበቂያ ዋሻቸው አንድ እንደሚሆን ለፍልፏል - እሰየው ነው!... ግን..ግን .. በአንድ ሰው እና በ 5 ገፅ እንዲህ እየተርገፈገፈ  የሚቀዝን የ አሸዋ ላይ ስሪት ፖለቲካቸውን  እርቃኑን አስጥቶ ስላሳየን  እናመሰግናለን::  ልደቱ በ5 ገፅ መነሻ ሀሳብ  እንዲህ ቆፈን ካስመታቸው    ድርጅት ያቋቋመ ቀን በያሉበት አገር ጫካ እንዳይገቡ!

 

በመጨረሻም የልደቱ የመታገያ መነሻ ሃሳብ( ፅሁፍ)  አንድ እውነት አረጋገጠልኝ:: ልደቱ የእነ”ተረኛ ጌቶችን” መንደር አሸብሯል!

 

ጤና ይስጥልኝ!!
https://amharic-zehabesha.com/archives/181430

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...