Tuesday, April 18, 2023

ጉድ በል ጎንደር ማለት አሁን ነው!! - ይነጋል በላቸው
በነዚህ ሰዎች ዕኩይ ተግባር መላዋ ሀገርና በተለይ ደግሞ የፈረደበት አማራ፣ በነዚሁ ሰዎች - ሰዎች ማለት ከቻልኩ ነው ለዚያውም - ለምን ብትል ድርጊታቸው ሁሉ ከዐውሬም የባሰ ነውና - አዎ፣ በነዚሁ “ሰዎች” ንግግር እኔን መሰል የኢንትርኔት አርበኛ ዕረፍት እንዳጣን ሰሞነኛው ፖለቲካዊ ድባብ አፍ አውጥቶ በግልጽ ይናገራል፡፡ ሁላችንም ዕረፍት አጥተናል፡፡ አገር ቤት ያለው ወገናችን በነዚሁ ሰዎች  የጎሣ ፖለቲካ ምክንያት አሣሩን እየበላ ሲሆን በትላልቅ ከተሞች ያለነው እኔን መሰሉ የድረ ገጽ ተከታታይና የወሬ ሱሰኛ ደግሞ እንቅልፉን አጥቶ እየሆነ ያለውን በብስጭትና በቁጭት ሌት ተቀን ይከታተላል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ነገረ ሥራቸው ሁሉ ቅጥ አጥቶ የሚያደርጉትን ብቻ ሣይሆን የሚናገሩትንም ጭምር ወዳለማወቅ ተሸጋግረዋል፡፡ የሚሉት ነገር ምን ያምጣ ምን ግድ የላቸውም፡፡ አፋቸው ዝም አይበል እንጂ ስለሚናገሩት ነገር ትክክለኝነት አይጨነቁም፡፡

የወታደር ብርሃኑ ጁላን ንግግር አድምጬ መታገስ አቃተኝና በደረቅ ሌሊት ተነስቼ መጫጫር ጀመርኩ፡፡ በእውነቱ እኛ ብቻ ሳንሆን እነሱም ተረግመዋል፡፡ ባይረገሙ ኖሮ አንደኛ በትምህርትም፣ በጀግንነት ሙያም፣ በልምድና በችሎታም እዚህ ግባ የማይባል አንድ የወያኔ ዘመን ምርኮኛ ወታደር፣ ከትግራይ አንስቶ ጣልማ በር ድረስ ሸሽቶ መምጣቱና በፋኖና በአማራ ልዩ ኃይል ነፍሱን ማትረፉ ሳያንስ ዘረኛው አቢይ አህመድ ኦሮሞን ከፍ በማድረግ የጠቀመ፣ አማራንና ሌሎችን ደግሞ ዝቅ በማድረግ ያንኳሰሰና የጎዳ መስሎት ከመሬት ተነስቶ በአፍሪካ ቀርቶ በዓለም እጅግ ውድ የሆነውን የመጨረሻውን ወታደራዊ ማዕረግ ሰውዬው ትከሻው ላይ ጭኖ ትርጉሙን እንኳን በቅጡ በማያውቀው ሁኔታ ትከሻውን ባላንቀጠቀጠው ነበር - ትከሻ አፍ የለውምና አልችልም አይልም መቼም፡፡ ሁለተኛ  የአቢይ ሸኔ አጣዬ አካባቢ መንገድ ዳር ጠብቆ ሰሞኑን የገደላቸውን ወደ ሲቪልነት የተለወጡ የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይሎችን ፋኖ እንደገደላቸው አድርጎ ይሄው ጉደኛ የኦነግ አባል - ብርሃኑ ጁላ የሚባለው ኦነግ/ኦህዲድ - ያለ አንዳች ሀፍረት መናገሩ የሰዎቹ ሥሪት ከሰው ሥጋና ደም ይሁን ከሌላ ከምን እንደሆነ መገመት እንኳን እንዳንችል አድርጎናል፡፡ የአማሮቹን መገደል ከሚገልጸው ከቦታው ከተሰራጨ ቪዲዮ እንደምንረዳው ገዳዮቹ የሚነጋገሩትና በአማሮቹ መሞት እየተሳለቁ ደስታቸውን የሚገልጹት በኦሮምኛ እንጂ በሌላ ቋንቋ አይደለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ በአማራ መገደል በደስታ የሚቦርቁ በሥፍራው የነበሩ ገዳዮች ኦሮምኛ ተናጋሪ የጎንደር ፋኖዎች ናቸው ማለት ነው - እያሳዘነ ያስቃል፡፡ ይህን ውሸት ጁላ የሚባለው ጅል ለመናገር እንዴት እንደደፈረና የውሸቱ ደራሲ ሊሆን እንደሚችል የምጠረጥረው አለቃው አቢይ አህመድ እንዴት ይህን ነጭ ውሸት ሊፈበርክ እንደቻለ በጣም ገርሞኛል፡፡ አንድ ሰው ላመነበት መጥፎ ነገር እንዴቱን ያህል ኅሊናውን ለገንዘብና ለሥልጣን እንደሚሸጥ ከዚህ በላይ ዋቢ የለም፡፡ ኦሮሙማዎች ከምር አሳዘኑኝ፡፡ የከፋ ጭንቀት ውስጥ ሳይገቡ አልቀሩም፡፡ ውሸት እኮ ለከት አለው፡፡ በዚህ ደረጃ መውረድ ግን ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን ነጭ ጥቁር ሳይል መላውን የሰው ዘር የሚያሳስብ ነው፡፡

በሥነ ልቦናው ዘርፍ “ፓቶሎጂካል ላየር” የሚባል ነገር አለ - በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ የተጠናወተው ሰው ካልዋሸ ጭንቅላቱን እንደሚያመውና የጤነኝነት ስሜት እንደሚርቀው ይታመናል፡፡ መዋሸት በሚሰጠው ደስታ እየተዝናና መኖር ለዚህ ዓይነቱ ህመምተኛ ትልቅ የኅልውና መሠረት ነው፡፡ የሀሰተኞቹ የነአቢይ ሰሞነኛው ፋኖ ፋኖን ገደለ ዜና ግን ከፓቶሎጂካል ላየርነት እጅግ የተለዬ ነው፡፡ ከነሱ ይልቅ አባቱ ውሸት ሊያስተምረው “በሰማይ ላይ ገበሬዎች በነጫጭ በሬዎች ጤፍ እያበራዩ አየሃቸው?” ብሎ የትምህርቱን ሀሁ ሊያስጀምረው ሲል፣ ልጁ “ውይ፣ አባዬ እብቁ ዐይኔ ውስጥ ገባ!” በማለት ገና ከጅምሩ አባቱን በውሸት ትምህርት የበለጠው ሕጻን ልጅ የበለጠ ተኣማኒነት አለው፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ፋኖ በኦሮሞ ልዩ ዞን መጥቶ ትጥቃቸውን በኦሮሞ ሸኔ የተነጠቁ ወይንም በግልጽ አማርኛ ትጥቃቸውን ለኦሮሙማ ባስረከቡ ሰላማዊ የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ላይ የመትረየስ ጥይት ሲያርከፈክፍና በኦሮምኛ ደስታውን ሲገልጽ ይታያችሁ፡፡ እባካችሁን ይህችን ውሸት በድንቃ ድንቅ መዝገብ እንድትመዘገብ ለማድረግ ለተቋሙ ቀረቤታ ያላችሁ ወገኖች ጥረት አድርጉ፡፡ አቤት! ምድር ስንቱን ችላዋለች ግን!!

ስለዚሁ ማርሻል ተብዬ የኢትዮጵያ ኤታ ማጆር ሹም አንድ አስደናቂ ሰሞነኛ መረጃ ብናገር ደስ ይለኛል፡፡ ይህ ሰው ትግሬዎችን ሰብስቦ “ከእናንተ መፈጠሬ ያኮራኛል” በማለት ልክ ምድረ ዘረኛን እንዳስጨበጨበው እንደመለስ ዜናዊ ሁሉ፣ የጨፌ ባለሥልጣናትን ሰብስቦ “አማራን ሥልጣኑን፣ ትግሬን ሀብቱን ቀምተናል” ብሎ ናዝሬት ላይ ዘረኛ ኦሮሞን በጋለ ስሜት እንዳስጨበጨበው እንደአቢይ አህመድ ሁሉ አሥር አለቅነት የሚበዛበት ይህ ብርሃኑ ጁላም ሰሞኑን ደብረ ዘይት ላይ ለተሰበሰበው የኦሮሞ ልሂቃንና ቄሮ  የሚከተለውን እንደተናገረ ተተርጉሞ ወጥቷል፡-

“እኔ ወታደር ነኝ፡፡ ጄኔራል ነኝ፡፡ መለዮየን ጥዬ ሲቭል ለብሼ ነው የመጣሁት፡፡ ለምንድን ነው? እንደ አንድ የኦሮሞ ልጅ መሣተፍ ስለምፈልግ ነው፡፡ እኛ እየሠራን ያለነው ለኦሮሞ ጥቅምና ክብር ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ‹ዶር.‹ አቢይም የሚሠራው ለኦሮሞ ጥቅምና ክብር ነው፡፡ የሚቻል ከሆነ በምሥራቅ አፍሪካ በወታደራዊ አደረጃጀት፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በፖለቲካው የታፈረችና የተከበረች ታላቋን ኦሮምያ ሀገር ለመመሥረት ነው የምንሠራው፡፡ ይህንን ካልቻልን ግን በኦሮሞ ፍላጎት የምትተዳደር ኢትዮጵያን እንመሠርታለን፡፡ ሁላችሁም የኦሮሞ ልጆች አግዙን፡፡…”

መሽቶ ከመንጋቱና እሁድን በሰኞ ከመለወጡ ውጭ ምንም ደንታ የሌለን የምንመስለው ሌላው ነገድና ጎሣ እንግዲህ ከዚህ የብርሃኑ ጁላ ንግግር ምን እንደምንገነዘብ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ እነሱ ጨርሰዋል፡፡ ሌሎቻችን ግን ምናልባትም በ“ ማንም ምንም አያመጣም” የተለመደ የዘወትር ንቀት ተጋድመን ማለትም በጥልቅ እንቅልፍ ለሽ ብለን የኦሮምያን ምሥረታ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ እነሱ ሥራ ላይ ናቸው ወንድሜ፡፡ ሀፍረትንና ይሉኝታን ባወጡ ሸጠው በኢትዮጵያ ስምና አጠቃላይ ወጪ ኦሮምያ የምትባል አዲስ ሀገር ለመመሥረት እየተጣደፉ ነው፡፡ የኢትዮጵያን መፈራረስ የሚፈልገውና በአዲስ የዓለም ሥርዓት (NWO) ግምባታ ላይ የሚገኘው የምዕራቡ ዓለምም ከጎናቸው ነው፡፡ በመጨረሻው መጨረሻ ምን ሊፈጠር እንደሚችልና የግፍ ዕንባ ጥርቅም ከፈጣሪ ምን ሊያስከትል እንደሚችል የቆዬ የሚያየው ሆኖ አሁን የታሰርንበት አካልንና ኅሊናን ሰርሳሪ ገመድና የተጣድንበት እቶን ኃያል መሆኑ ግን አይካድም፡፡

ግዴላችሁም ጤናማ ኦሮሞዎች ካላችሁ ከዚህም ሳይብስባቸው እነዚህን ሰዎች ምከሯቸው - ከምንም ዓይነት ሃይማኖት የራቁ በመሆናቸው እንጂ ወደጠበል ውሰዷቸው ብዬ መምከርም በቻልኩ ነበር፡፡ ሰው እኮ ጥርሱን ተነቅሶ እየሣቀባቸው ነው፡፡ ወገኖቼ፣ ዝምታም እኮ ወርቅ ነው፡፡ ይህን በእንግሊዝኛው አነጋገር “Adding an insult to injury” (እርግጫና ቡጢ ላይ ስድብን እንደመጨመር ዓይነት) ምን ይሉታል? ወዴት ወዴት እየሄዱስ ነው? ምን ዓይነት አስተዳደግ ውስጥስ ቢያልፉ ይሆን እስከዚህን ድረስ ቀዳዳ በርሜል ሊሆኑ የቻሉት? እርግጥ ነው - የዚህ ውሸታቸው ዓላማ ግልጽ ነው፡፡ አንደኛ አማራውን እርስ በርስ ለማጋጨት ሲሆን ሁለተኛ ሸኔያቸውን ከደሙ ንጹሕ ለማድረግ ነው፡፡ ግን የበለጠ ከሰሩበት እንጂ አላተረፉም፡፡ ሸኔነታቸውን በማይደበዝዝ ቀለምና ፊርማ አጸደቁበት፡፡

ለማጠቃለል ያህል ከፍ ሲል የጠቀስኳቸውን ሁለት ጉዳዮች በመጠኑ ላብራራቸውና ጅምሬን ልቋጭ፡፡ አንደኛ የሰዎቹ ንግግር እንትን እንትን እያለኝ መምጣቱን በአንክሮ ሳልገልጽ ማለፍ አልፈልግም፡፡ የነሱን ጆሮን የሚሰቀጥጥ የሀሰት ንግግር ላለማዳመጥ መቼም የጆሮ ታምቡሬን አልሸነቁረው ነገር ሌላ ስንት የሚደመጥ መልካም ነገር አለ፡፡ እንጂ እንደነሱ ቢሆን ኖሮ አንድም ቀን አላቆዬውም ነበር፡፡ “ፋኖ መንገድ ላይ ጠብቆ አማራዎችን ገደለ” ይበሉን ውሸት ቢያጡ? ወይ ድንቁርና!! ለመሆኑ ሌላውን ኦሮሞ ተውትና ሸኔዎቹ ራሳቸው ከት ብለው አይስቁባቸውምን?

የጁላን ተፈጥሮ በቀጥታ የሚገልጽ አንድ ብሂል ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ሙሽራ አማቱ ቤት ከነሚስቱ ሄደ አሉ - ለቅልቅል፡፡ ማፈር የለም፡፡ እውነቱን ነው የምናገረው፡፡ እናላችሁ ሌሎች የቤተሰብ አባላት እየበሉ እየጠጡ ሲጫወቱ ሙሽራ ሆዬ ፀጥ ረጭ ይላል፡፡ ይህን የታዘቡት የሙሽሪት እናት “ምነው ዝም አልክ ልጄ? ተጫወት እንጂ” ቢሉት - በጅል ሰው ንግግር ጎተት እያደረጋችሁ አንብቡልኝ ታዲያ “ አይ፣ እ…ማ..ዬ፣ አ.ል.ጫ.ወ.ት.ም፡፡ እናቴ ‹ንግግርህ አር አር ስለሚል አትናገር› ብላኛለች… እህ.. እህ ..እህ…” ይላቸዋል፡፡ ያኔ የገልቱው ሙሽራ የሚስቱ እናት “ውይ በሞትኩት፤ ምን ያሉ ሴት ናቸው በል? ልጄ ለኔስ ንግግርህ ማር ማር ነው የሚለኝና ተጫወትልኝ፤ በል ተናገር ልጄ፤ አፌ ቁርጥ ይበልልህ” ይሉትና እንደምንም አግባብተው እንዲናገር ያደርጉታል፡፡ ልጁ ጨዋታውን ጀመረልሃ ወንድማለም!! “እሽ … እ.ማ.ዬ … ያ ልጅ የማነው ልጅ” ይልና ከተቀመጡት አንዱን በሌባ ጣቱ በመጠቆም ይጠይቃቸዋል፡፡ አማትም ዝምተኛው የልጃቸው ባል ንግግር በመጀመሩ ምክንያት በደስታ እየተፍለቀለቁ “አዎ፣እንዲያ ነው እንጂ … የኔ ነው ልጄ” ይሉታል፡፡ ጅሉ ሙሽራም ቀጠለ፤ “ያኛው እዚያ ወዲያ ያለውስ …” ብሎ ሌላኛውንና ሴትዮዋ ስልችት እስኪላቸው ሌሎቹም ልጆች የማን እንደሆኑ በማከታተል ይጠይቃቸው ገባ፡፡ በመጨረሻም “ሆ..ሆ..ሆ … ይሄን ሁሉ የወለዱበት ‹መውለጃዎ› እንዴት ይሰፋ!!” ሲላቸው ሒሣባቸውን ያገኙት አማት የሚገቡበትን አጡ፤ አትሣቁ ወገኖቼ! “አያድርስ” ነው እሚባል፡፡ ያኔ ሴትዮዋ ይገቡበትን አጡ፡፡ ቀጠሉናም “ውይ ውይ እውነትም ከአርም አር “ በማለት ልጁን እንዲናገር ለማድረግ የወሰዱትን ተነሳሽነት ተራገሙ ይባላል፡፡ የብርሃኑ ጁላ ንግግርም ከዚህ አማች የሚተናነስ አይደለም፡፡ አልጨከንኩበትም፡፡

ሌላኛው ነጥቤ ስለዚሁ ዘረኛ የአቢይ ካድሬ ወታደራዊ ማዕረግ ከፍ ሲል የጠቀስኩት ነውረኝነት ነው፡፡ በዓለም ደረጃ 141 የሚሆኑ ፊልድ ማርሻሎች እንዳሉ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ እጅግ ብዙ ሀገሮች ይህ ማዕረግ ከናካቴው የላቸውም፡፡ ማዕረጉ የሚሰጠው ብዙ መሥፈርትን ለሚያሟላ እንጂ በዘረኝነት በተቆላለፈ የማይማን ሬቻ ማኅበር እንደቡና ቁርስ ለወደድከው የምትሰጠው ለጠላኸው የምትነሣው አይደለም፤ እንዲያ ብታደርግ እንደኦሮሙማ መሣቂያ ነው እምትሆን፡፡ በትምህርት መግፋትን ይጠይቃል፡፡ በተለያዩ ዐውደ ግምባሮች የጦር ሜዳ ውሎ እጅግ አንጸባራቂ ድሎችን ማስመዝገብን ይጠይቃል፡፡ ሀፍረተቢስ ካልሆንክ በስተቀር ነፍስ አውጪኙን እየፈረጠጠ የመጣን ፈሪ ጦር የሚመራ የጦር መኮንን የነበረውንም ማዕረግ ሳይቀር ትገፈዋለህ እንጂ ከፍተኛ ማዕረግ መስጠት ቀርቶ ባለበት ማዕረግ እንኳን አታስቀጥለውም፡፡ ወታደራዊ ሣይንስ ባንማርም በግምት ብዙ እናውቃለንና የአቢይ ሹመት ሽህ-ሞት እንጂ ሹመት ሊባል አይችልም፡፡ አቢይ በሰጠው በዚህ ሹመት የራሱን ግብዝነት ገለጠ፤ ለሰውዬውም የሀፍረት ካባ አጠለቀለት - ጁላ ማፈርን አያውቅም እንጂ ቢያውቅ ኖሮ “በማይመጥነኝ ሹመት ሰው ከሚያሾፍብኝ እባክህን ይቅርብኝ” ቢል ያዋጣው ነበር፤ በገንዘብ ለውጦለት ቢሆን በተሻለው፡፡ ለኔማ መዝናኛየ ነው፡፡ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ! ፐ!ፐ!ፐ! አልቀረበትም፤ አልቀረባቸውም፡፡ “ፉልዱረቲ ኡመታ ኦሮሞ፡፡” “ጀምበር ሳለ ሩጥ፤አባት ሳለ አጊጥ፣” ነው ነገሩ፡፡

አስገራሚነቱ ደግሞ አንድም ሀገራዊም ይሁን ዓለማቀፋዊ አካል አቢይን ሲገስጸውና ወደጤናማ አሠራር እንዲገባ ሲገፋፋው አለመታየቱ ነው፡፡ በዚያ ላይ በተደረገው ጦርነት ድል አስገኘ እንኳን ቢባል በወንድማማቾች መካከል በተደረገ ጦርነት በሚገኝ ድልና ሽንፈት የተነሣ ይህ ዓለም አቀፍ ትልቅ ወታደራዊ ማዕረግ ሊሰጥ ባልተገባ ነበር፡፡ ይህች አገር ምን ዓይነት ደናቁርት ሙሰኞችና የቆሸሸ ኅሊና ያላቸው ሰዎች እጅ እንደገባች አንዱ ማሳያ ይህ ሹመት ነው፡፡ በዚህ መልክ የተሾመ ሰው በዚህ ጽሑፌ ውስጥ የተጠቀሰውን የሀሰት ምስክርነት ቢሰጥ አይፈረድበትም፡፡ ኢትዮጵያ በጤናማ ሰዎች እጅ ገብታ እንዲያሳየኝ አምላኬን ዘወትር እማጠናለሁ፡፡ እናንተስ? በእንደነዚህ ዓይነት ሰው ሊሆኑ ብዙ የሰውነት ንጥረ ነገሮችና ጤናማ ሕዋሳት በጎደላቸው ተናጋሪ እንስሳት በመመራቴ በእውነቱ እጅግ፣ እጅግ በጣም አፍራለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይሁነን፡፡ ከደገሱልን የዕልቂት ድግስም አንድዬ ያውጣን፡፡ ሰው እንደናፈቀኝ አልሙት፡፡
https://amharic-zehabesha.com/archives/181950

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...