Wednesday, March 8, 2023
መሰረት ተስፉ (Meserettesfu4@gmail.com)
ለሁላችንም ግልፅ ነው ብየ እንደማስበው አብዛኛዎቹ የአለም ሃገራት እንደ ሃገር የተመሰረቱት፤ እንዲሁም የተረጋጋ መንግስት የፈጠሩት ከተለያዩ ግጭቶችና እልህ አስጨራሽ ጦርነቶች በኋላ ነው። አሁን ላይ በአለም ደረጃ የዴሞክራሲ “ጳጳስ|” ተደርጋ የምትገለፀው አሜርካ እንኳ እንደሃገር የቆመችው አንዱ ሌላውን አሸንፎ ለመውጣት ከተደርጉ ጦርነቶች በኋላ ነበር። ለምሳሌ ነባሮቹ አሜሪካኖች የመጀመሪያውን ጦርነት አድርገው ድል የተቀዳጁት ከቅኝ ገዣቸው ከብሪታኒያ ጋ ነበር። ከዚህ ቆየት ብለው የርስ በርስ ግጭት ያካሄዱት ደግሞ የአንድነት ሃይሎች ተብለው በሚታወቁት የሰሜናዊ ግዛቶቹ እና ራሳቸውን ለመቻል ይፈልጉ በነበሩት የደቡብ ግዛቶች መካከል ነበር። በዚህ ጦርነት አንድነት ፈላጊዎቹ ተሳክቶላቸው የደቡቦቹን ግዛቶች በሃይል የአሜሪካ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ ችለዋል። እንደአሜሪካ ሁሉ ዴሞክራሲ በልፅጎባታል ተብላ የምትታወቀው ብሪታኒያም ብትሆን የተመሰረተቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ አልነበረም። ይህች ሃገር እንደሃገር ተረጋግታ መቆም የጀመረችው በእንግሊዝ ንጉሳዉያንና በወቅቱ Parliament ተብሎ ይታወቅ በነበረው ሃይል መካከል ከተካሄደው ጦርነት በኋላ እንደሆነ የታሪክ መዛግብቶች ያስረዳሉ። ፈረንሳይ ውስጥም በዘር ላይ የተመሰረተ ጦርነትን ለመከላከል ሲባል ሁሉንም የማመሳሰል (Assimilation ) ስራ የተሰራውም በአስገዳጅ ሁኔታ እንጅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ነበር የሚል ክርክር ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። እነዚህ ሃገራት የተረጋጋ መንግስት ያቆሙት ከላይ በተገለፀው የጦርነት ወይም አስገዳጅ የሆነ መንገድ ቢሆንም ግን በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በደረሰባችው በደል ምክንያት የኋላ ታሪካቸው ቁርሾ ሆኖ እርስ በርስ ሲያባላቸው አይታይም። በእርግጥ በገዥዎቹ ስርዓታዊ የሆነ ስግብግብ ባህሪ ምክንያት አንደኛ ደረጃ (First Class) ተብለው በሚታወቁት የገዥው መደብ አባላትና በደሃው መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ የነበረ ቢሆንም ይህን ስርዓታዊ በደል ለማስተካከል አልህ አስጨራሽ ትግል አደረጉ እንጅ በየሃገሮቻቸው ላይ የቂምና የበቀል ስሜት ቋጥረው እንዲበታተኑ መስራታቸውን የሚገልፅ ማስረጃም አላየሁም።
ኢትዮጵያም ብትሆን እንደሌሎቹ የአለም ሃገራት ሁሉ የተመሰረተችበትና የተረጋጋ መንግስት የፈጠረችበት ሂደት አልጋ በአልጋ አልነበረም። ይልቁንም በሃገረ መንግስት ምስረታው ሂደት በየአከባቢው የነበሩ መሳፍንቶች አንዳቸው ሌላውን ለማስገበር በተደረጉ ፍትጊያዎችና ግጭቶች የተሞላ ነበር። ራቅ ያለውን ትተን የቅርቡን እንኳ ብንወስድ አፄ ቴዎድሮስ ደጅዝማች ውቤን፤ ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥሎ ደግሞ አፄ ዮሃንስ ወንድማቸው የሆኑትን ተክለጊዮርጊስን በጦርነት አስገብረው ነው ንግስናቸውን ያፀኑትና ኢትዮጵያን የመሩት። ከአፄ የኋንስ በኋላ አፄ ሚኒሊክ በየቦታው የነበሩ ሌሎች መሳፍንቶችን እና ንጉሶችን አስገብረው ግዛታቸውን በማስፋፋት ኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል አሁን ያለውን መልኳን እንድትይዝ ያደረጉት በጦርነትና በግጭት እንደህነ ለማንም ግልፅ ነው።
እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ ከላይ የተገለፁትና ሌሎቹ የኢትዮጵያ መሳፍንቶች ይከተሉት የነበረው ስርዓተ-ማህበር ፊውዳላዊ መሆኑ ነው። በፊውዳሊዝም ስርዓት ደግሞ በስርዓቱ ልዩ ባህሪ ምክንያት ስልጣን ላይ ያለው ሃይል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታዎችን ጠቅልሎ በመያዝ የራሱንና በዙሪያው ያሉ አባላቶቹን ጥቅም የሚያስከብር እንደሆነ ይታወቃል።
ከታሪካችን እንደምንረዳው የኢትዮጵያ መሳፍንቶች ከላይ እንደተገለፀው ገና በፊውዳሉ ስርዓተ-ማህበር ውስጥ የነበሩ እንደመሆናቸው መጠን ከስርዓቱ ባህሪ ተነስተው የፈፀሟቸው በጎም በጎ ያልሆኑም ተግባራት ነበሩ ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከበጎዎቹ ተግባራቶቻቸው ውስጥ አገር መስርተው የተረጋጋ መንግስት ለመፍጠር ያደረጉት ሙከራ የሚናቅ አይደለም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሃገር ሉአላዊነትን ለማስከበር ያደረጓቸው ቆራጥ ተጋድሎዎችና መሰል ተግባራት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ በአገር ሏዓላዊነትና ዘመናዊነትን በማስተዋወቅ ረገድ አፄ ሚኒሊክ የነበራችውን ሚና መካድ አይቻልም። የአደዋ ድልም የሳችድው ጥበበኛ አመራር ወሳኝ እንደነበር አለም የመሰከረው ሃቅ ነው።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መሳፍንቶች አሁንም ከላይ እንደተገለፀው ገና በፊውዳሉ ስርዓተ-ማህበር ውስጥ የነበሩ እንደመሆናቸው መጠን ከስርዓቱ ባህሪ ተነስተው ከፈፀሟቸው በጎ ያልሆኑ ተግባራቶቻቸው ውስጥ አንዱ በመደብ ክፍፍሉ ምክንያት በየቦታው የነበሩ “ባላባቶችና” በዙሪያቸው ያሉ አባላቶቻቸው በሃገሪቷ ሃብትና ንብረት ላይ እንደፈለጉ የሚያዙበትና ጭሰኛ ተብሎ የተፈረጀው አብዛኛው ህዝብ ግን ለፍቶ፣ ጥሮና ግሮ በሚያመርተው ምርት ተጠቃሚ ያልነበረ መሆኑ ነው። ከዚህ አልፎም የጭሰኛው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረገጥ ሌላው መሰረታዊ ችግር ነበር።
እየቆየ ሲሄድ የፊውዳሉ ስርዓት የሁሉንም ህዝቦች ፍትሃዊ የሆነ ጥቅም የሚያስከብር ሆኖ ባለመገኘቱ የባላባቶቹ ስርዓተ መንግስታት በርካታ አብዮቶን አስተናግደዋል። ለምሳሌ በደርግ ወታደራዊ ጁንታ ተጠልፎ ለስኬት ሳይበቃ ቀረ እንጅ የአስራ ዘጠኝ ስልሳ ስድስቱ ህዝባዊ አብዮት ዋነኛው ነው። በርግጥ ደርግም ቢሆን አብዮቱ እንደተካሄደ መሬት ላራሹን የመሳሰሉ አዋጆችን በማውጣ የፊውዳሉን ስርዓት ለማዳከም የወሰዳቸው እርምጃዎች አወንታዊ ነበሩ ማለት ይቻላል። ነገር ግን ወታደራዊ ጁንታው ለሃገር አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር እንጅ ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ምንም አይነት ደንታ ስላልነበረው ለአስራ ሰባት አመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ገሃነም ውስጥ እንዲኖር ፈርዶበት ነበር ቢባል ማጋነን የሚሆን አይመስለኝም። ለዛም ነው ህዝቡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የነበረውን የከረረ ጥላቻ እንደግባዓት ተጠቅሞ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ደርግን ያስወገደው።
ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በበኩሉ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ የቡድን መብቶች እውቅና እንዲያገኙ ጥረት አድርጓል። ምንም እንኳ ወደ መጨረሻ ቢሆንም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከነበረበት የኋልዮሽ ጉዞ ወጥቶ የተሻለ እድገት ያስመዘገበውም በዚሁ በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ወቅት ነበር። ይሁን እንጅ ይህ ፓርቲ ጥሏቸው ያለፉትን ጠባሳዎች ቆጥሮ መጨረስ የሚቻል አይመስለኝም። ሲጀመር ሃቀኛ ፌዴራሊዝም ሳይኖር ግን በፌዴራሊዝም ስም እየማለና እተገዘተ ብሄሮችን በማንነት በመሸንሸን ከፋፍሎ ለመግዛት ያደረገው ጥረት መሰሪነት የተሞላበት እንደነበረ ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደም። በአጠቃላይ የህወሓት ሰዎች ሲፈፅሟቸው የነበሩ ተግባራቶቻቸው ሁሉ የሚያመላክቱት ከቻሉ የበላይነታቸውን በሌላው ላይ ጭነው አብሮ ለመኖር ካልሆነ ደግሞ የራሳቸውን አገር መስርተው ራሳቸውን ለመቻል ነበር። ይህን ታሳቢ አድርገውም የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች ለመቆጣጠር ለከት የለሽ ሙከራዎች አድርገዋል። በመጨረሻም በህዝብ ቆራጥ ተጋድሎ ምክንያት አልተሳካላቸውም እንጅ ሰሜን እዝን አጥቅተው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሞከሩት በዚሁ እሳቤያቸው እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም።
ከኢህአዴግ መክሰም በተለይም ደግሞ ከህወሃት ሰዎች ሃይል መዳከም በኋላ የመንግስት ስልጣን የያዘው ብልፅግና ፓርቲም ያስገኛቸው ለውጦች እንዳሉ መካድ አይቻልም። በተለይ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ውጭም ሆነ ውስጥ ለነበሩ እንዲሁም እንደ አዲስ ለተፈጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እድል መስጠቱና ሚዲያ በነፃነት እንዲስፋፋ እያደረገ ያለው ሙከራ ተጠቃሾች ናቸው። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ስራዎች ናቸው ወይ የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ በደን ልማትና የመዝናኛ ስፍራዎችን በማስፋፋት ረገድም እየፈፀማቸው ያሉ ተግባራት በቀላሉ የሚታዩ ናቸው ብየ አላስብም። አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ ሌሎችንም መግለፅ ይቻል ነበር።
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ፓርቲው ከተመሰረተ ጀምሮ የፈፀማቸው በርካታ ስህተቶች አሉ። እነዚህ ስህተቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መልክ አላቸው። ችግሮቹ በርካታ ቢሆኑም በዚህ ፅጽሁፍ ላተኩርባቸው የፈለኩት ግን ኢትዮጵያ እንደሃገር ለመቀጠል እንቅፋት ሊሆኗት ይችላሉ ብየ በማስባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ከዚህ አንፃር መጀመሪያ ረድፍ ላይ ሊነሳ የሚገባው መሰረታዊ ችግር “stuck in the past” እንደሚሉት ፈረንጆቹ በታሪካ ላይ መቸንከር ነው። ይህ ችግር በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የማህብረሰብ አባላት ዘንድ በስፋት የሚስተዋል መሆኑ አሳሳቢ ቢሆንም ሁኔታዎችን የበለጠ ውስብስብ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ያለው ግን አገር እየመራ ባለው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥም ስር እየሰደደ መሆኑ ነው። ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ችግሩ የሚገለፅባቸው የተለያዩ መልኮች አሉት። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ታሪክን መሰረት አድርገው የሚታዩ ፍትጊያዎች እና ፅንፈኝነት ናቸው ብየ አምናለሁ።
ከታሪክ አንፃር እየታየ ያለው ዋነኛው ችግር አንዳንድ ወገኖች ከመቶ አመት በፊት የነበሩ ገዥዎች ፈጽመዋቸዋል ብለው የሚያስቧቸውን ክፋት ብቻ መርጠው እነሱ የወጡበት ነው ብለው የሚያስቡትን ማህበረሰብ በሙሉ ባለ እዳ አድርገው የመመልከት ዝንባሌ ያላቸው መሆኑ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜስ ቂም በቀልን ለመወጣት በሚመስል አኳኋን ይህንኑ ማህበረሰብ ሊያቀጭጭ ይችላል ብለው ያሰቡትን ሴራ ሁሉ በድብቅ ሲነጋገሩበት አፈትልኮ እየወጣ እየሰማነው ነው። ይህ ሌላውን አሳምኖ ወይም አደናግሮ በተለይ አንድን ማህበረሰብ በመነጠል የራስን ቡድን የበላይነት ለመጫን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የተናጋሪው ሃሳብ ብቻ ነው ብሎ መውሰድ በጣም ያስቸግራል። ምን አልባትም በደንብ ውይይት ተደርጎበት በድብቅ አቋም የተያዘበት የስራ መመሪያ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በሌላ በኩልም በታሪክ አጋጣሚ ተገዝተናልና አሁን እኛ ብቻ በተራችን ካልገዛን እኩልነታችን አይረጋገጥም የሚል በሚመስል መልኩ የሚገለፁ እንቅስቃሴዎችን እያየንና እየሰማን ነው። ይህ በመሆኑም ፓርቲው ከተመሰረተ በኋላ በርካታ ንጿን ዜጎች እየሞቱ፣ ከቀያቸው እየተፈናቀሉና ንብረታቸው እየደመ ቢሆንም ይህን ለማስቆም ቆርጠኝነት ሊያሳይ አልቻለም።
በሌላ ወገን እየተስተዋለ ያለው ችግር ደግሞ የፊውዳሉ ስርዓት ተከታይ በነበሩ መሳፍንቶች የተከናወኑ ጥሩ ጥሩ ስራዎችን የራስ አድርጎ በመኩራራት እነሱ የፈፀሟቸውን ችግሮች ግን disown የማድረግ ዝንባሌ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑ ነው። በዚህ ፅሁፍ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው የፌውዳሉን ስርዓተ ማህበር የሚከተሉ መሳፍንቶች ከስርዓቱ ባህሪ ተነስተው የፈፀሟቸው ጥሩ ጥሩ ስራዎች የነበሩትን ያህል በርካታ ስህተቶች እንደፈፀሙም እውቅና አለመስጠት በስርዓቱ ምክንያት በደል በደረሰባቸው ዜጎች ቁስል ላይ ጨው እንደመነስነስ ሊያስቆጥር የሚችል ዝንባሌ ነው።
ከዚሁ የታሪክ ውዝግብ ሳንወጣ መጠቀስ የሚገባው ሌላው ችግር ደግሞ የብልፅግና ፓርቲን አደረጃጀት በህዝብ ቁጥር ብዛት ለመቃኘት እየተደረግ ያለው ጥረት ነው። በእርግጥ የዚህ ጉዳይ መነሻ ከፍተኛ ቁጥር ይዞ ግን በታሪክ ግፍ ከደረሰበት ማህበረሰብ የወጣሁ ነኝ የሚል ሃይል ፖለቲካውን ጨምሮ ሁሉንም የመጠቅለል ፍላጎት እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። በእኔ እምነት ግን ፖለቲካ ማለት ማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኝ ሃሳብ ነው። ፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ ይህን ሃሳብ በርእዮተ-አለም (Ideology) መልክ ቀርፆ አጉልቶ በማውጣት ያቀፋቸውን ሁሉንም አባላት በእኩልነት በማሳተፍ ወደፖለቲካ ስልጣን ለመምጣት የሚንቀሳቀስ ስብስብ እንጅ በምርጫ የህዝብ ይሁንታ እስከሚያገኝ ድረስ የህዝብ ውክልና የሌለው ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲን የተለያዩ አደረጃጀቶች የሚያንቀሳቅሱ አመራሮች ማለትም የማእከላዊ ኮሚቴ፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ የምክር ቤትና የቁጥጥር ኮሚቴ አባላት ድልድል ሁሉም በፓርቲው የታቀፉ የብሄር ብሄረሰብ ክልሎች በእኩል ቁጥር የሚወከሉበት እንጅ ከምርጫ በኋላ እንደሚያዙ የተወካዮች ም/ቤት ወንበሮች ወይም የሌሎች የፌዴራል መንግስት ሹመቶች በህዝብ ቁጥር ብዛት ለማመጣጠን ጥረት የሚደረግበት ሁኔታ እንዳይኖር ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብየ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም ርዕዮተ-አለማዊ ጉዳዮች መወሰን ያለባቸው ቢቻል ችሎታና ብቃትን መሰረት ባደረገ መልኩ በተመረጡ፤ ካልተቻለ ደግሞ ሁሉም በድርጅቱ ውስጥ የታቀፉ ክልሎች እኩል ቁጥር ይዘው በተወከሉ አመራሮች እንጅ በዛ ያለ ቁጥር ካለው ብሄር/ብሄረሰብ የፈለቀ ሃይል አናሳ ቁጥር ካለው ብሄር/ብሄረሰብ የወጣን ሃይል ሊጨፈልቅ በሚችልበት አኳኋን ሊሆን ፈፅሞ አይገባም ባይ ነኝ፡፡
ከርዕዮተ-አለም ጋ ተያይዞ ያለኝ ግንዛቤ ይህ ሆኖ እያለ የብልፅግና ፓርቲ ህገደንብ ውስጥ (ይፅደቅ አይፅደቅ እርግጠኛ መሆን ባልችልም) የማእከላዊ ኮሚቴ፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ የኦዲት ኮሚሽንና የሌሎች የድርጅት ኮሚቴዎች አመርር አባላት ውክልና የህዝብ ብዛትን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት የሚል ድንጋጌ ያነበብኩ መሰለኝ። ይህ ህገደንብ ፀድቆ ከሆነ በተነፃፃሪ ቁጥራቸው አነስ ካሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የወጡ አመራሮችን አፍኖ ቁጥሩ በዛ ካለ ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ የወጣ ሃይልን ፍላጎትና ጥቅም (ኢ-ፍትሃዊ ቢሆንም) ሊያሳካ ይችላል ተብሎ በሚታሰብ አኩኋን ለማስወሰንና ለማስፈፀም የታቀደ እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም። የዚህ አይነት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን (Veto Power) የሚመስል ጡንቻ ለአንድ ቡድን የሚሰጥ አካሄድ ደግሞ እጅግ በጣም አደገኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ቁጥራቸው በተነፃፃሪ አነስ ካለ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የወጡ ሃይሎች ራሳቸውን ብዙ ቁጥር ካለው ህዝብ የወጣ ሃይል ተገዥ የሚያደርግ ፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመሆኑ ነው። በፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ ይህን አሰራር ለመሰንቀር መሞከር ከፀረ ዴሞክራሲያዊነት አልፎ ፍፁም አንባገነንነትን ሊፈጥር የሚችል አደገኛ ዝንባሌ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ይህ ሲባል ግን ፓርቲው በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ሲቆጣጠር የፌዴራሉ መንግስታዊ መዋቅር የብሄር ብሄረሰቦች ነፀብራቅ መሆን ይችል ዘንድ የህዝብ ቁጥርን መሰረት በማድረግ የማመጣጠን ስራ ሊኖር አይገባም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ይህን በማድረግ “Majority rules with minority rights” የሚለውን የዴሞክራሲ አንድ መርህ ተግባራዊ ማድረግ ነው የሚሆነው፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የሚታየው ሁለተኛው ችግር ደግሞ ፅንፈኝነት ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ይህ ችግርም ቢሆን ከታሪክ ጋ ሊያያዝ የሚችል ቢሆንም ከአሳሳቢነቱ አንፃር ራሱን አስችየ ላስቀምጠው ወድጃለሁ፡፡ ፅንፈኝነት ታሪካዊ ወይም አሁናዊ መነሻ ኖሮት ግን ከገደብ ባለፈ መንገድ እኛና እነሱ የሚል መስመር የሚያበጅ አደገኛ የሆነ የግለሰበኝነት ዝንባሌ ነው፡፡ ፅንፈኝነት የጎጥ፣ የሃይማኖት፣ የፆታ ወዘተ መልክ ያለው ሲሆን በባህሪው በመቻቻል ላይ ለተመሰረተ ውይይት በር የማይከፍት፤ እየከፋ ሲሄድ ደግሞ መጠቅለልን ወይም መነጠልን ሊያስከትል የሚችል አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ በተለይ የጎጥ መልክ ይዞ ብልፅግና ፓርቲን እየናጠው እንደሆነ ምልክቶችን ማየት ከጀመርን ዋል አደር ብለናል፡፡ በተለይ ፓርቲው በጊዜ እመርታዊ በሚያስብል ደረጃ የችግሩን ሰንኮፍ ነቅሎ መጣል የማይችል ከሆነ መዘዙ ከራሱ አልፎ ለህዝብ ሊተርፍ እንደሚችል መገንዘብ ጠቃሚ ነው ብየ አምናለሁ፡፡
ችግሮቹ ከላይ በተገለፀው መልኩ የሚታዩ ከሆነ መፍትሄያቸውስ ምን ይሁን ብሎ መጠየቅ ደግሞ እግባብነት አለው። በ’ኔ እምነት መፍትሄ ሲታሰብ ወደኋላ እያዩ ወደፊት መሄድ በእንቅፋት ተመቶ ለመወደቅ ወይም ከሌላ ነገር ጋ ተላትሞ ለመንኮታኮት በር ይከፍታል የሚለውን ፍሬ ነገር እንደመነሻ መውሰድ ጠቃሚ ነው እላለሁ። በዚህ መነሻ ሃሳብ መሰረት በተለይ ብልፅግና ፓርቲ ወደኋላ ሄዶ በታሪክ ላይ ከሚቀዝፍ ይልቅ አሁናዊ በሆኑ ተራማጅ አስተሳሰቦች በመመራት ለውጥ ለማምጣት ከመጣር የተሻለ አማራጭ ሊኖረው እንደማይችል መገንዘብ ይኖርበታል። በተለይ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርጎ ቢንቀሳቀስ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነዚህም፤
በሌላው ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ ራስን ወደውስጥ አይቶ መፈተሽና ማፅዳት፣
ራስን ፈትሾ ካፀዱ በኋላ ሌላውን በውንጀላ መልክ ሳይሆን ቅንነት በተሞላበት ጓዳዊ መንፈስ ለማረም ጥረት ማድረግ፣
ግልፅነትና ቅንነት በተሞላበት ሁኔታ ውይይቶችን በማካሄድ በታሪካችን ላይ መግባባት ለመድረስ ጥረት ማድረግ። በሂደትም ውይይቶቹን ወደ ህዝብ ማውረድ፣
በታሪካችን ላይ መተማመን ለመድረስ የሚሻክር ነገር ካለ ደግሞ አግባብ ካላቸው ባለሙያዎች የተውጣጣ ቡድን ጥናት አድርጎ የምፍትሄ ሃሳቦችን እንዲያቀርብ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
ኣመራሩም ሆነ አባሉ የሚመዘነው አያቶቹ ወይም ቅድመ አያቶቹ በፈፀሟቸው በጎና በጎ ያልሆኑ ተግባራት ሳይሆን በራሱ ስራ መሆኑን በሚገባ መረዳትና ማመን፣
በመሃል ሰፋሪነትና በመሃል ፖለቲክ አራማጅነትን መካከል ያለውን ልቱነት በሚገባ አንጥሮ በመለየት የመህል ፖለቲካን አጠንክሮ መያዝ፣
ፕሮግራምንና ህገደንብን በሚገባ ፈትሾ የሁሉንም ህዝቦች እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊያሟሉ የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ። በማንኛውም አይነት ምክንያት አድሎና ያለአግባብ መጠቃቀም እንዳይኖር ጠንክሮ መታገል፣
ሁሉም የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል እይታ እንዲኖራቸው የሚያሳችል ስራ መስራት፣
የፓርቲ አሰራሮች ከህዝብ ቁጥር መብዛትና ማነስ ጋ መቆራኘት የሌለባቸው መሆኑን ከልብ ማመን።
ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ እንደሆኑ በተግባር ማሳየት፣
ሴራና ተንኮልን አምርሮ መታገልና በመርህ፣ በግልፅነትና ቅንነት ላይ የተመሰረት ግንኙነት እንዲኖር ማስቻል፣
በጎጥ ወይም በሃይማኖት ሊፈጠር የሚችልን ዋልታ ረገጥነት መከላከል፤ ሲከሰትም ታግሎ ማስተካከል፣
ታሪክን የእርስ በርስ መናቆሪያ በማድረግ ጭብጨባ ከመፈለግና ደጋፊ ከማብዛት ብሎም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ከመጣር ፈፅሞ መቆጠብ ናቸው።
ቸር እንሰንብት!!!
https://amharic-zehabesha.com/archives/180583
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment