Friday, March 31, 2023

በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ ማስነሳት እርምጃ የመኖሪያ ቤት አልባነትን አባብሷል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተደራጀው የሸገር ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት (Demolition and Forced Eviction) እየተከናወነባቸው ካሉ አካባቢዎች መካከል ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ እና በዙሪያው ከሚገኙ አካባቢዎች ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በግል እና በቡድን ለኮሚሽኑ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም መሠረት ለኮሚሽኑ ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎችን፣ የሚመለከታቸውን የከተማ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት በማነጋገር፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት ሂደቱ የሚከናወንበትን ሁኔታ እንዲሁም ቀደም ሲል የፈረሱ ቤቶችን የመስክ ምልከታ በማድረግ መረጃ እና ማስረጃ አሰባስቧል።

#image_title

#image_title

ለኢሰመኮ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሰዎች ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ በየአካባቢው ከቀድሞ/ነባር ባለ ይዞታዎች ቦታ ወይም ቤት በመግዛት ኑሮ መሥርተው ሲኖሩ የነበሩ መሆናቸውን፣ በየአካባቢው ከሚገኙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውሃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸውን፣ ለተለያዩ የአካባቢው የልማት ሥራዎች እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ክፍያዎችን ሲከፍሉ መቆየታቸውን በመጥቀስ መኖሪያ ቤቶቻቸው ያለ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከሕግ አግባብ ውጭ እንደፈረሱባቸው ይገልጻሉ።

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የሸገር ከተማ ኃላፊዎች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እንደ አዲስ መመሥረቱን ተከትሎ “ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸውን” ግንባታዎች በማፍረስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የአየር ካርታን ጨምሮ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው፣ ከነባር የአርሶ አደር ይዞታ ውጪ የሆኑ እና በተለይም ከ2005 ዓ.ም. በኋላ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ በተወሰነው መሠረት የተከናወነ መሆኑን፣ ቤቶቹን የማፍረስ ሂደቱን በተመለከተም ከቤቶቹ ባለቤቶች ጋር በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ውይይት ተደርጎ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር በማድረግ እና በሚፈርሱ ቤቶች ላይ በቅድሚያ ምልክት ከተደረገ በኋላ እራሳቸው ግንባታውን እንዲያፈርሱ ጊዜ የሚሰጣቸው መሆኑን፣ በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ግንባታውን ሳያነሱ የቀሩ ሰዎች ካሉ ግንባታዎችን በአፍራሽ ግብረ ኃይል እንደሚያፈርሱ፣ የፈረሰውን የግንባታ ቁሳቁስም በሕግ የተቀመጠውን አሠራር በመከተል ወደ ከተማ አስተዳደሩ ተወስዶ ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ ጨምረው አስረድተዋል።

ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ በለገጣፎ ለገዳዲ፣ በሰበታ አካባቢ ፉሪ እና ለቡ ተክለሃይማኖት እንዲሁም በቡራዩ ገፈርሳ ኖኖ አካባቢዎች በመዘዋወር ቀደም ሲል የፈረሱ እና የማፍረስ ተግባሩ እየተከናወነ የነበረባቸውን አካባቢዎች ተመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ በመገኘት እየፈረሱ የነበሩ ቤቶችንም ለመመልከት ችሏል። በምልከታው የቤት ማፍረሱ እና በግዳጅ ማስነሳቱ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንደነበረ እና በቦታው ከፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም ተመልክቷል።

የክትትልና የምርመራ ሥራው ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም እስካሁን በተገኙት መረጃዎች እና ማስረጃዎች መሠረት የቤት ማፍረስ እና በግዳጅ የማንሳት እርምጃው ከሰብአዊ መብቶች አኳያ የታዩበትን ክፍተቶች እና ሊወሰዱ የሚገባቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች በተመለከተ ኢሰመኮ የሚከተለውን ይገልጻል።

በዓለም አቀፍ ሕግ እና የሰብአዊ መብቶች መርሆች መሠረት በግዳጅ ማንሳት (Forced Eviction) ማለት አንድን ሰው ወይም ቤተሰብ ወይም ማኅበረሰብ ከሚኖርበት ቤት ወይም ቦታ ላይ ያለ ፈቃዱ፣ አማራጭ መፍትሔ ሳይሰጠው ወይም ሕጋዊ ጥበቃ ሳይደረግለት በጊዜያዊነት ወይም በዘላቂነት በኃይል አስገድዶ ማንሳትን የሚመለከት ነው።
https://amharic-zehabesha.com/archives/181404

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...