Wednesday, March 1, 2023

አደገኛው የከተማ ላይ ከተማ ፕሮጀክት (መርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ)

አደገኛው የከተማ ላይ ከተማ ፕሮጀክት (መርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ)
ከግማሽ ክፍለ-ዘመን አስቀድሞ በባእዳን ቅኝ ገዢዎች ሴራ የተወጠነውና በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ) (ህ.ወ.ሀ.ት) ተልእኮ አስፈጻሚነት የተመራው ነገደ-አማራን አንገት የማስደፋቱና፣ ከተቻለም ህልውናውን ከምድረ-ኢትዮጵያ ጨርሶ የማጥፋቱ ፕሮጀክት በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚገኘውን የብልጽግና ፓርቲ የኦሮምያ ክንፍ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ተቋቁመው በኦሮሞ ስም በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አማካኝነት ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉን እያስተዋልን ነው፡፡

በመሰረቱ ወያኔ በስሙ ከከለለለት አካባቢ ይልቅ የአማራው ማሕበረ-ሰብ የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የዎርቅ ባድማዬ ነው በሚል መተማመን በመላዋ ኢትዮጵያ ከጽንፍ እስከአጽናፍ በሰፊው ተሰራጭቶ ነው የሚኖረው፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን መነሻውን አማራ ክልል ያደረገና የዚህኑ ክልል መታወቂያ የያዘ ማንኛውም ዜጋ ሌላው ቀርቶ ወደመዲናዋ አዲስ አበባ እንኳ ድርሽ እንዳይል ግልጽ የሆነ እገዳ የተጣለበት ይመስላል፡፡ ሁሉም የየብስ ጎዳናዎች ጥርቅም ተደርገው ተዘግተዉበታል፡፡ ከዚህም የተነሳ በኦሮምያ ፖሊስና ጸጥታ ሀይሎች አስገዳጂነት ጉዟቸውን እያቋረጡ ወደኋላ እንዲመለሱ የሚደረጉት ወይም አውላላ ሜዳ ላይ የሚፈሱት ንጹሃን መንገደኞች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እዚያው አዲስ አበባ ውስጥና በዙሪያዋ መዲናዋን ያለሀፍረት ለመሰልቀጥ ታስቦ በመደራጀት ላይ ከሚገኘው ከሸገር ከተማ ምስረታ ጋር በተያያዘ እንደሱሉልታ፣ ለገጣፎና ሰበታ ባሉት አነስተኛ የኦሮምያ አዋሳኝ ከተሞች የአማራ ብሔር ተወላጆች የሰሯቸው መኖሪያ ቤቶችና ጥረው ግረው ያፈሯቸው ሀብቶች እየተመረጡ በዘፈቀደ በሚወሰድ እርምጃ ሲፈራርሱና ሲወድሙ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡

እኛ እስከምናውቀው ድረስ ሸገር የሚለው ቃል ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ስትንቆለጳጰስ የምትጠራበት የቁልምጫ ስያሜ ነበር፡፡ ኦፊሴላዊ መቀመጫው በራሷ በአዲስ አበባ እንብርት ላይ እንዲሆን የተደረገው የነዶ/ር ተሾመ አዱኛ ሸገር ግን ቀድሞ ነገር መዲናዋን በሁሉም አቅጣጫዎች አፍኖ ለማስጨነቅና ዘላቂ ባለዋጋነቷን ለመቀነስ በስሌት ታቅዶ የተጠነሰሰ አደገኛ የከተማ ላይ ከተማ ፕሮጀክት መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ በነባር ከተማ ወገብ ላይ ዙሪያውን እንደእባብ ተጠምጥሞ አዲስ የቁጩ ከተማን መቆርቆር ፈጽሞ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡

እነሆ ሸገር በተሰኘው ከተማ መልክኣ-ምድራዊ አፈና ምክንያት መዲናችን አዲስ አበባ ሀገረ-ሌሶቶን መስላላችኋለች፡፡ ዙሪያዋን በደቡብ አፍሪካ ሪፓብሊክ የተከበበችው ትንሽቱ አፍሪካዊት አገር ሌሶቶ የከባቢዋን አገር ፈቃድና ይሁንታ ካላገኘች በስተቀር ከውጪው አለም ጋር የመገናኘት እድሏ የመነመነ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

አዲስ አበባችንም ብትሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ከእንግዲህ በኋላ በሸገር በኩል ካልሆነ በስተቀር ከሌሎች አቻ ከተሞችም ሆነ አጎራባች ክልሎች ጋር እንዳሻት የመገናኘት እድል አይኖራትም፡፡

ይልቁንም ሕገ-መንግሥቱ ተሻሽሎ በዚህ አገር የሚሰራበት መርዘኛው የብሔር ፖለቲካ አንዳች ለውጥ እስካልተደረገበት ድረስ ሸገር ቀስ በቀስ አዲስ አበባን ትውጣት/ትሰለቅጣት እንደሆነ ነው እንጂ አዲስ አበባ ትኩስ አቅም ኖሯት የሸገርን አደገኛ የብረት አጥር ሰብራ ትወጣለች ተብሎ በጭራሽ አይታመንም፡፡

በባንቱስታናይዜሽን ጋኔን ተይዘው አለቅጥ የሚቅበዘበዙት ስግብግብና ጽንፈኞቹ የኦሮምያ ገዢዎችም ከመነሻው የፈለጉት ይህንኑ የአዲስ አበባ ውድቀት ስለነበር ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል ለማለት ያስደፍራል፡፡

በርግጥ ፊንፊኔ የኛና የኛ ብቻ ናት ሲሉ ጉሮሯቸው እስኪነቃ ድረስ ደጋግመው በአደባባይ የሚወተውቱት ወገኖች ዙሪያዋን በሌላ ፌክ ከተማ ክርችም አድርጎ ማጠር ለምን እንዳስፈለጋቸው አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡

 

--
https://amharic-zehabesha.com/archives/180289

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...