ወደ ወገኖቼ! ብዙዎቻችሁ ጽሁፍህ ባይረዝም ትሉኛላችሁ። እኔም ባይረዝም ፍላጎት አለኝ። ስንፍናዬ የሚመኘው ማሳጠሩን እንጂ ማርዘሙን አይደለም። ግን የማነሳቸው ጉዳዮች ሰፋ ተደርገው መቅረብ ስላለባቸው ብቻ ነው ጽሁፌን የሚያረዝሙት። በሃገሩ ጉዳይ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ የሚል የተማረ ሃይል፣፣ ሞልቶ ክተረፈው ጊዜው ጥቂት ደቂቃዎችን ሰውቶ ጽሁፍ ማንበብ ሊከብደው አይገባም ባይ ነኝ። ሰፋ አድርገን ነገሮችን ማየት ካልቻልን እንዴት መግባባት በመረጃና በምክንያት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መወሰን እንችላለን። በዚህ መንፈስ ይህን ፌስ ቡክ በሁለት ክፍል እንድከፍል ያስገደደኝን ጽሁፍ በትእግስት እንድታነቡ በትህትና እጋብዛችኋለሁ።
ቀን - የካቲት 2015
ክፍል 1
ወደ ሰላም ወይም ወደ ቀውስ፤ የትግራይ - ኢትዮጵያ ጉዳይ
ማሳሰቢያ፣ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የሚከተለው ምክንያት እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ማለቂያ በሌለው ቀውስ እየታመሰች ነው። ከእነዚህ ቀውሶች መሃከል አንዱ በወያኔ የተቀሰቅሰው የሰሜን ጦርነት ነው። ይህ ጦርነት ለጊዜው ቆሟል። ሆኖም ግን በደንብ በታሰበበትና በጥንቃቄ ሁኔታው ካልተያዘ ይህ ያልጠና ሰላም በቀላሉ መደፍረስ የሚችል፣ እስካሁን ህዝብ ከቀመሰው መከራ በላይ የከፋ መከራ ሊያመጣበት እንደሚችል፣ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቀጠናው የሚያናጋ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል በጊዜ ለማመላከት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጽሁፉ እንደሚያመላክተው በትግራይ ውስጥ ድምጻችን እየተሰማ አይደልም የሚሉ ለሰላም የቆሙ አካላት ድምጽ ባስችኳይ እንዲሰማ የማድረግ ግፊት በመፈጠሩ ነው። አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የሉም ወይ? አዎ አሉ። ሞልተው ተርፈዋል። አቅሜ በፈቀደ መጠን ወደ እነሱ እመለሳለሁ።
1) እንደ መነሻ!
ትንሽ እውቀት፣ ትንሽ ተመክሮ ያለው ራሱን የፖለቲካ ሰው አድርጎ የሚቆጥር ዜጋ፣ በዘርና በሃገር ጥላቻ፣ በነዋይ ፍቅር፣ በግል ስምና ዝና ስካር፣ በስነልቦና ቀውስ፣ በስልጣን ሱስ፣ በፍራቻ ቆፈን፣ ስንፍና በወለደው ግድየለሽነት እና በሌሎችም የማሰላሰል እና የመተንተን አቅምን በሚገሉ እንከኖች እስካልተሰለበ ድረስ የአንድን ሃገር እውነታ በፍጹም ነጻነትና ገለልተኛነት ለማጤን የወደፊቱንም ለመተንበይ የሚቸገር አይሆንም።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ በተከታታይ ስልጣን ከያዙት የቅርብ ጊዜ ሁለት መንግስታት፣ የወያኔ እና የብልጽግና መንግስታት ወይም የመንግስት አመራሮች ጋር በነበረኝ ግንኙነት ሊመጡ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ችግሮችና የሃገሪቱ ፖለቲካ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የሚመስለኝን ከመጠቆም ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም። በዚህ ጽሁፍ የቀረቡ መረጃዎችና እይታዎች በስልጣን ላይ ላለው መንግስት እንግዳ ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም። አቅሜ፣ ልምዴ እውቀቴ በፈቀደ መጠን ያለምንም ይሉኝታ፣ ግብዝነትና አድርባይነት በድፍረት ሃሳቤን በቃል፣ በጽሁፍ አቅርቤያለሁ። ህዝብ በአደባባይ ከሚያውቀው ይበልጥ በግል የሰጠኋቸው አስተያየቶች ይበዛሉ።
በተለይ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ፣ ከወያኔ ሰዎች ጋር በተለይ ትግራይን በተመለከተ ያደረግኋቸው ክርክሮች “ከፓፓሱ በላይ ቄሱ እስኪሉኝ ድረስ” ከየትኛውም የኢትዮጵያ አርሶ አደር ይበልጥ ለማውቀው የትግራይ አርሶ አደር ወገንተኛነቴን አሳይቻለሁ።
የወያኔ መሪዎች የትግራይ ህዝብ ከደርግ ጋር በተደረገው ትግል የከፈለውን ከፍተኛ መስዋእትነት ለግል ስልጣናቸውና ጥቅማቸው እንዴት እየመነዘሩ እያባከኑት እንደሆነ፣ እንዴት የእነሱ መጨረሻ የማያማር እንደሚሆን፣ የትግራይም ህዝብ የእነሱ እብሪት ብልግና እና ዘረፋ የመጨረሻው እዳ ከፋይ እንደሚሆን ያለማታከት አስጠንቅቄያለሁ። አክረው ሲገፉት የነበረው የዘር ፖለቲካ ህዝብን ለመከፋፈል ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ካልሆነ በስተቀር “በቁጥሩ አነስተኛ ለሆነው፣ በመላው ሃገሪቱ ተበትኖ ለሚኖረውና ለሚሰራው በኢትዮጵያዊነቱ ቀናኢ ለነበረው የትግራይ ህዝብ አይጠቅመውም” በማለት ተሟግቻለሁ። የቋንቋን እና የባህልን እኩልነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን በዘር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ክልሎች ሳያስፈልጉ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል መሆኑን፤ የዘር ፖለቲካው ሁሉንም ዘሮች እርስ በርሳቸው እንዲባሉ አድርጎ ሃገር አውድሞ እንደሚጠቃለል ለማሳየት ሞክሪያለሁ። የቪዲዮ የድምጽና የሰነድ መረጃዎቹ በወያኔና በወቅቱ ኢህዴን ተብሎ በሚጠራው በኋላ ብአዴን በተባለው ድርጅቶችና በየሚድያ ተቋማቱ እጅ እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ። ይህን ያደረግሁት ወያኔ እየወደቀ ባላበት የመጨረሻው ሰአት ላይ አይደለም። ወያኔ ስልጣን ከያዘ ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ጀመሮ ነበር። ከወያኔና ከተላላኪዎቻቸው የኢህዴንና የኦህዴድ ሰዎች ጋር ያደረግሁት ጭቅጭቅ ከአንድ አመት በላይ ቀጥሎ በመጨረሻም ከወያኔ/ ኢህአዴግ ጋር ለመለያየትና በ1985 አ.ም ለሁለተኛ ዙር የስደት ህይወት መጀመር ምክንያት ሆኖኛል።
ዛሬ በህይወት ያሉ ከወያኔዎቹ ወገን፣ እነተወልደ ወልደማሪያም፣ አለምሰገድ ገብረአምላክ፣ ከብአዴኖቹ እነበረከት ሰምኦን፣ እነተፈራ ዋልዋ፣ እነአዲሱ ለገሰና ታምራት ላይኜ፣ በምን ጉዳይ ምን እንደተነጋገርን ያውቁታል። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
በተለይ ተወልደ የኢህአዴግ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የወያኔ የፖሊት ቢሮ አባል በመሆኑና
በወቅቱ የድርጅት ጉድይ ትልቅ ተጽእኖ በሃገሪቱ ላይ የሚያደርግ ስለነበር፣ እኔም የዛ ኮሚቴ አባል በመሆን ካየኋቸው ችግሮች በመነሳት የዛሬ ሰላሳ አመት፣ በ1984 አ.ም፣ ቀኑን እና ሰአቱን ባልረሳሁት አንድ ማክሰኞ እለት ከጠዋቱ 4.30 ላይ፣ ቢሮው ቀጠሮ በመያዝ የኢህዴን እና የኦህዴድ ድርጅቶች ደካማ መሆን ወያኔን ራሱን ለከፍተኛ አደጋ የሚዳርገው መሆኑን በማንሳት ሰፊ ውይይት አድርጌያለሁ። የክርከሬ ጭብጥ “የእነዚህ ድርጅቶች ደካማነት በጊዜያዊንት ለእናንተ የሚያመች ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ስታጠፉ ማረም አለመቻላቸው፣ ድርጅታችሁ በስህተት ላይ ስህተት እየሰራ ገደል እንዲገባ ያደርጋል” የሚል ነበር። የተወልደ መልስ “ድርጅቶች በሰው ሃይል ደካማ እንደሆኑ እናውቃለን፤ ግን ነጻ ድርጅቶች ስለሆኑ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ወደ ድርጅታቸው እንዲያመጡ ህወሃት ማዘዝ አንችልም” የሚል ነበር። በወቅቱ ይህ መልስ እንደማያሳምነኝ ነግሬው ተለያይተናል።
ከወያኔዎች ጋር ወልቃይትና ራያንም በተመለከተ ብዙ ተባብለናል። በተለይ ገብሩ አስራት በ1995 አ.ም እንግሊዝ ሃገር በመጣበት ወቅት ወልቃይትና ራያን በተመለከተ ያደረግነውን ውይይት ይረሳዋል ብዬ አላስብም። የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ እልቂት እንደሚያስከትል፣ በመጨረሻም ወያኔዎች ተሸናፊ እንደሚሆኑ ነበር ለማስረዳት የሞከርኩት።
ያ ወቅት ገብሩና ጥቂት ጓደኞቹ በመለስ ዜናዊ ትእዛዝ ከህወሃት አመራርነት የተባረሩበት ነበር። እቤቴ እራት ጋብዠው በጫወታችን መሃከል ለገብሩ አንድ ጥያቄ አነሳሁለት።
“ያን ሁሉ ዘመን በረሃ ለበረሃ ተንከራታችሁ ይሄው አሁን መለስ ከድርጅቱ አባረራቸሁ ድካማችሁ መና ቀረ። ምን አተረፋችሁ?” አልኩት።
ለዚህ አባባሌ ገብሩ እንዲህ ብሎ መለሰለኝ። “መና አልቀረንም አንቀጽ 39ን በህገ መንግስቱ እንዲካተት አድርገናል።”
ይህ መልሱ በጣም ስላስገረመኝ። በተናገረው ላይ ሌላ ጥያቄ ጠየቅሁት። “ለመሆኑ ትግራይ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 አማካይነት የመገንጠል መብት ብታገኝ የትኛውን ድንበር ይዛ ነው ነጻ ሃገር የምትሆነው?” በማለት፤
ገብሩም መለሰ፣ “የድንበር ጉዳይ ችግር አይደለም። ትግራይ በህገ መንግስቱ የጸደቀ ድንበር አላት” አለኝ
እኔም “ይህ ህገ መንግስታዊ የምትለው ድንበር በጉልበት ከወሎና ከጎንደር የጠቀለላችሁትን ወልቃይትና እና ራያን የሚያካትት ከሆነ ችግር ይፈጠራል” አልኩት።
“ምን ችግር” አለኝ።
ለማስረዳትም እንዲህ አልኩት፣
“በአንድ ሃገር ውስጥ የአስተዳደር ወሰን አድርጎ ክልል መመስረትና የአንድ ነጻ ሃገር ድንበር መመስረት ሁለቱ ይለያያሉ። ትግራይ ኢትዮጵያ አካል ስለሆነች የወልቃይትና የራያ ነገር እስከ አሁን የሚገባውን ትኩረት አላገኘ ይሆናል። ግን ወልቃይትን እና ራያን የነጻ ትግራይ ሪፓብሊክ አካል አድርጌ ድንበር አሰምራለሁ ብለህ ስትነሳ ችግር ይፈጠራል” አልኩት።
ምን ችግር ? አለኝ በድጋሚ
“ጦርነት” አልኩት
የበለጠ ለማስረዳትም የኤትራን ጉዳይ አነሳሁ። “ኤርትራ ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩት ግልጽ የሆነ ድንበር ኖሯት በባድመ ሰበብ የደረሰውን እልቂትና ውድመት አስበው። እንዲህ አይነት ግልጽ የሆነ ነባር ድንበር የሌላቸውን ትናንትና ወያኔ ክልሎች አድርጎ የፈጠራቸውን አካላት አስተዳደራዊ ወሰኖች ወደ ቋሚና ነጻ ድንበርነት እቀይራለሁ ብለህ ስተነሳ፣ አጎራባችህ ያለውና ከዛም ውጭ ያለው ህዝብ ዝም ብሎ የሚያይህ ይመስልሃል? ሁሉም ለእያንዳንዷ ሳንቲሜትር መሬት መዋጋቱ አይቀርም። ይህ ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ራሱን ነጻ ሃገር አደርጋለሁ ብሎ ለሚያስብ የትኛውም ትልቅ ሆነ ትንሽ ክልል የሚሰራ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከቅኝ ገዥዎችና ከሌሎች ወረራዎች ራሷን ተከላክላ የተረፈችውና የቆየቸውም ከሁሉም አካባቢ ዜጎቿ በሁሉም የሃገሪቱ ምድር ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ነው። እንደ ብሄር ወይም ህዝብ ብቻውን ራሱን ከውጭ ወራሪዎች ተከላክሎ ያተረፈ ህዝብና ግዛት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት የትም ቦታ ሰርቼ መኖር እችላለሁ በሚል እምነት የህዝቡን ቁጥር በማይመጥን መሬት ላይ የተቀመጠው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ አጎራባች የሆነውን ሰፊ መሬት የኔ ነው ብሎ ለሚነሳ ተገንጣይ በህገ መንግስቱ መሰረት ያሻህን አድርግ ብሎ የሚተወው ይመስልሃል። ትግራይም የሚገጥማት ችግር ይህ ነው” አልኩት።
ዝምታ ሰፈነ
ቀጥዬም ወያኔዎች በጦርነት እንዴት ራሳቸውን እንደሚያዩ ስለማውቅ፣
“ግጭት የሚነሳ ከሆነ የምትዋጉት በሁሉም መንገድ የውጊያ ታሪክ አቅምና ስነልቦና ካለው የአማራ ህዝብ ጋር ነው።” አልኩት።
የራት ግብዣው በዚህ ቆምጣጣ ውይይት ተዘግቶ ገብሩን ወደሚሄድበት ሸኘሁት።
በግንቦት 7 ንቅናቄ የጸሃፊነት ሃላፊነቴ “የወያኔ ቅጣ ያጣ እብሪትና ዘረፋ ሌላው ህዝብ የትግራይን ህዝብ በበጎ እንዳይመለከተው ማድረጉ አይቀርም” የሚል ስጋት ስለነበረኝ፣ በግሌ የትግራይ ህዝብና የትግራይ ገዥ ጉጅሌ የሚል ስያሜ የሰጠሁትን የጥቂቶች ስብስብ ያላቸውን ልዩነት በየመድረኩ ለማሰረዳት ሞክሪያለሁ። በተለይ ከወያኔ ጋር ትስስር ያልነበራቸው የትግራይ ምሁራን የወያኔን የግፍና የዘረፋ ስርአት በመቃወም ከፊተኛው እረድፍ ላይ ለምን መገኘት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ማብራሪያ በመስጠት ጥሪ አቅርቤያለሁ። “ህዝብ ሁሉም ትግሬዎች ወያኔዎች አይደሉም” የሚል ጠንካራ አቋም እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው “እናንተ የትግራይ ልጆች ወያኔን በመቃወም ትግሉን ስትመሩት ብቻ ነው። እኔ የትግራይ ሰው ያልሆንኩት ከምናገረው እናንተ ብትናገሩት የበለጠ ተደማጭነት ታገኛላችሁ” ብያለሁ። በጣት የሚቆጠሩ ትግራዋይ ይህን ያደረጉ ቢኖሩም የእነዚህ ጥቂቶች ተሳትፎ ብቻውን እየገጠመን ከነበረው ፈተና ጋር ሲነጻጸር እርባና አልነበረውም።
በኢትዮጵያ ወያኔን ከስልጣን ያስወገደው ለውጥ ከመጣና እኔም ከእስር ከተፈታሁ በኋላም ከተለያዩ የሚድያ ተቋማት ጋር ባደረግኋቸው ቃለ መጠይቆች ህዝብ በወያኔ መሪዎችና በትግራይ ህዝብ መሃከል ያለውን ልዩነት እንዲያውቅ ስራዬ ብዬ ስለትግራይ ህዝብ የማውቀውን የህዝቡን ስብእና እና ደግነት የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘብ ለማድረግ የቻልኩትን ጥረት አድርጌያለሁ። ለብቻዬ ከሰው ሁሉ ተገልዬ በታሰርኩበት ቦታ ጠባቂዎቼ ተመርጠው ሁሉም የትግራይ ተወላጆች የነበሩ ቢሆኑም ከነሱ መሃከል ከፍተኛ ስብእና የነበራቸው፣ ወያኔ ከሰጣቸው መመሪያ ወጭ ወጥተው ደግነትና ርህራሄ ያሳዩኝን እንደ ለተማርያም ያሉትን ሰዎች በአደባባይ ህዝብ እንዲያውቃቸው ያደረግሁት “የዘር መጥፎ የለውም የግለሰብ እንጂ” የሚል መልእክት ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስተላለፍ በመፈለጌ ነበር።
በአንድ ቃለ መጠይቅ በኢትዮጵያ ደም መፋሰስን፣ የበቀል አዙሪትን ለማስቆም፣ ጌታቸው አሰፋን ጋር ተቃቅፌ ሰላም ለመባባል እንደማይቸግረኝ የተናገርኩት ጌታቸው በወያኔ ዘመን ለተፈጸሙ አሰቃቂ የስብአዊ መብት ጥሰቶች ዋናው ተጠያቂ እንደሆነ አጥቼው አልነበረም። ሌሎችም የወያኔ አመራሮች ከኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ የዘረፉት አስደንጋጭ መጠን ያለው ሃብት ለሚሊዮን ህፃናት በአጭር መቀጨት፣ በመቶ ሽዎች ለሚቆጠሩ እናቶች በወሊድ እንክብካቤ እጥረት መሞት፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ አጥነትና ተስፋ መቁረጥ፣ በሃገር ውስጥ በዜጎች መሃል እንደሰደድ እሳት ለተስፋፋው ሌብነትን ነወር አድርጎ የማያይ ባህል ተጠያቂ እንደሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም። በሃገሪቱ ሰላም ከወረደ መጪው ዘመን ብሩህ ይሆናል ከሚል ተስፋ ብቻ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝም የወያኔዎች አስተሳሰብና አካሄድ በደንብ ስለሚገባኝ በወቅቱ መጥቶ የነበረውን ለውጥ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት በሚታደግበት መንገድ መስመር ለማስያዝ፣ በተለይ ወያኔዎች ለውጡን በስጋት እንዳያዩትና ወደሌላ አላስፈላጊ መንገድ እንዳይጓዙ ለጻድቃን (ጄ/ል) ሆነ ለአበበ ተክላይሃማኖት ግንቦት 7 ንቅናቄ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ነበር በአካል ተገናኝተን እንምከር የሚል ጥያቄ እራሴ ስልካቸውን አፈላልጌ የደወልኩላቸው። የስልክ ጥሪዬን በጨዋነት ቢመልሱልኝም ከዛ በኋላ ለመገናኘት ያደረግሁት ጥረት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።
በማአከላዊ መንግስትና በወያኔ መሃከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ፣ ቱባ የወያኔ መሪዎችና ሌሎችም የወያኔ ሁነኛ ሰዎች ትግራይ ላይ ሲሰባሰቡ ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ ወያኔዎችን በደንብ ለሚያውቃቸው ለኔ አይነቱ ሰው ከባድ አልነበረም።
ቀደም ብሎ በትግሉ ወቅትና በኋላም ከወያኔዎች ጋር በሰራሁባቸው የተወሰኑ ወራቶች የተረዳሁት፣ ወያኔዎች በተከታታይ የገጠሟቸውን ባላንጣዎች በውጊያ ስላሸነፉ “ከኛ በላይ ጀግና ተዋጊ፣ የሚሊተሪ ሳይንስና ስትራተጂ አዋቂ የለም” የሚል ሰለራሳቸው እጅግ የተጋነነ ግምት እንዳለቸው አውቅ ነበር። ከዛም አልፎ ወታደራዊ ድሎቻቸው የመጡት በበሳልና ሳይናሳዊ በሆነ የፖለቲካ አመራር ነው ብለው ከልባቸው ያምኑ ነበር።
ከወያኔ ጋር በሰራሁበት አጭር ጊዜ ወስጥ በተደጋጋሚ በሚደረጉ ግምገማዎች፣ “አሸናፊነትና ተሸናፊነትን የሚወስኑ በርካታ ጉዳዮች ስለሆኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ብቃታችሁን ከሚገባው በላይ አጋናችሁ አትዩ። ከደርግ ጋር በተደረገው ትግል የሻብያ እርዳታ፣ ከደርግ ጋር ሆድና ጀርባ
የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ደርግ ራሱን ሶሺያሊስት ነኝ በማለቱ እንዲፈርስ የሚፈልጉ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የአረብና የጎረቤት አገራት ድጋፍ ለድላችሁ የነበራቸውን ሚና አትርሱ። ከዛም በተጨማሪ በአንድ ወቅት የሰራ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስትራተጂ በሌላ ወቅት ላይሰራ ይችላል። እንዲያውም ስልጣን ከያዛችሁ በኋላ በሀገር ውስጥና በድርጅታችሁ ውስጥ የሚታየው ቀውስ ጨብጠናዋል የምትሉት ሳይንሳዊ የፖለቲካ አመራር እንደምትሉት ያልተጨበጠ መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ ልተፈትሹት ይገባል” በሚል ተሟግቻቸዋለሁ። በአንድ ግምገማ ላይ ይህን አባባሌን ከምር እንመልከተው የሚሉ ደጋፊዎችም አግኝቼ ነበር። ጌዜው ሁሉም በድል አድራጊነት የስከረበት ወቅት ስለነበር የትም ሳይደርስ ቀርቷል።
ባለፉት ሁለት ንኡስ ምእራፎች ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች በመነሳት ነበር የወያኔዎች ሰዎች አዲስ አበባን እየተው መቀሌ ላይ መሰባሰባቸው ያሳሰበኝ። በተለይ ስዩም መስፍን እና ስዬ አብረሃን የመሳሰሉ ጉምቱ የወያኔ መሪዎች ከመቀሌው ድምጸ ወያኔ የትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች የሰጧቸው አስተያየቶች የወያኔ ሰዎች አሁንም ከድሮ የአዋቂነትና የጀግንነት የበላይነት ቅዥታቸው እንዳልተላቀቁ በሚያሳዩ ቃላቶች የተሞሉ መሆናቸውና በትግራይ የጦርነት ድግስ እየተደገሰ መሆኑን ግልጽ ያደረጉ ነበሩ። እነዚህ ቃለ ምልልሶች ጦርነት ቢከፍቱ የውጭ መንግስታት የሚያግዟቸው እንደሆነ ቃል የተገባላቸው እንደሆነ የሚያሳዩ አነጋገሮች ነበሩባቸው። “ጦርነት ከተነሳ ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ሃይሎች የሚሳተፉበት ይሆናል የሚለው” የስዬ እና የስዩም አባባል ከጎናቸው ከሚቆሙ የውጭ ሃይሎች ጋር ስምምነት መድረሳቸውን ያሳይ ነበር። በዚህ ላይ የወታደራዊ ሰልፉ፣ የትጥቅ ማስጣቱ (ኤግዚብሽኑ)፣ የፉከራውና የቀረርቶው ጉዳይ ሲታከልበት ሁኔታው ወደ ጦርነት እንደሚያመራ ገሃድ ሆኖ ነበር።
በዚህም ወቅትም ቢሆን፣ ስዬ አብረሃ ከ28 አመት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ የተጠቀመባቸውን ቃላቶች ሳይቀይር “ጦርነት መስራት እንችልበታለን፣ ክፍለጦር አፍርሰን ክፍለጦር መገንባት ሜካናይዝድ አፍርሰን ሜካናይዝድ መገንባት እናውቅበታለን።” የሚል በእብሪት የተሞላ ንግግር በትግራይ ቴሌቪዥን ሲናገር በሰማሁብት ጊዜ ዝም ብዬ አላለፍኩም። የስዬና የጓደኞቹ የዛን ወቅት አነጋገርና አስተሳሰብ፣ የተቀየረውን የአለም፣ የቀጠናውን፣ የሃገርና የትግራይም ሁኔታ በደንብ ያላገናዘበ፣ የትግራይን ህዝብ ለከፋ ችግር ሊዳርግ የሚችል መሆኑን የሚገልጽ መልእክት እንዲደራሳቸው በአደባባይ የስዬን ስምና ንግግሩን ጠቅሼ መልእክቴን አስተላፌያለሁ። “ተው ይህ የጦርነት መንገድ አያዋጣም” ብያለሁ።
ወያኔዎች ለራሳቸው በሰጡት የተጋነነ የአይበገሬነትና የአዋቂነት ቅዥትና በውጭ ደጋፊዎቻቸው ቃል በተገባላቸው ድጋፍ ታውረው ወያኔዎች ጦርነት ከፈቱ። ለትግራይ ህዝብ ይህን ጦርነት ለምን እንደከፈቱ “የሰጡት ማብራሪያ የትግራይን ህዝብ ከጥፋት ለማዳን” የሚል ማጭበርበሪያ ብቻ ነው። በተሳሳተ የራስ ጥንካሬና የሌላው ደካማነት ትንተና እና በአሜሪካ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ባሉ ከረጅም ዘመን ጀመረው በገንዘብ በገዟቸው ባልስልጣናት ሸሪኮቻቸው አበረታችነትና የአሜሪካ ጥቅም ለማስከበር የተከፈተ ጦርነት እንደሆነ ለትግራይ ህዝብ አልነገሩትም። የወያኔ መሪዎች አብይን ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት በቀላሉ አሽቀንጥረው ከጃቸው ያመለጠውን ስልጣን በዚህ ስልጣን አማካይነት የተቀዳጁትን የመዝረፍ መብት መልሶ መያዝ ይቻላል በሚል የጀብደኝነት ስሌት የተጀመረ ጦርነት እንደሆነ ለትግራይ ህዝብ የነገረው የለም። ስልጣን ተይዞ ምን ሲሰራበት እንደነበር የሚያውቀው የትግራይ ህዝብ ይህን ሃቅ አውቆ ቢሆን ኖሮ ለሶስተኛ ዙር ልጆቹን የመስዋትነት ጭዳ በማድረግ የወያኔ መሪዎችን ህልውና እና የኢትዮጵያን ጠላቶች ጥቅም ለማስከበር ሆ ብሎ አይነሳም ነበር። የትግራይ ህዝብ እንደርሱ በድህነት ተቆራምደው በሚኖሩ ደሃ የአማራ እና የአፋር ወንድሞቹንና እህቶቹ ላይ በአረመኔያዊ ጭካኔ አይዘምትም ነበር።
አሁንም በዚህ ሰአት ይህ የወያኔዎች የጦርነት አጀማመር ትርክት ከአንድ ጉዳይ በስተቀር ብዙም የተቀየረ ነገር የለውም። በአደባባይ ጦርነቱን በመብረቃዊ ጥቃት ጀመርነው ብለው እንዳልተናገሩ፣ ዛሬ ወያኔዎች ጀማሪዎቹ እነሱ እንዳልሆኑ አድርገው እያቀረቡት ነው። “የትግራይን ህዝብ ከጥፋት ለማዳን” የሚለው የሃሰት ትርክት ግን ዛሬም በወያኔ አባላት መሃከል ብቻ ሳይሆን በመላው ትግራይ እንደታመነ እንዲቀጥል አድርገዋል። ይህን ትርክት ለማስቀጠል እንዲቻል ወያኔዎች ከጦርነቱ በፊት ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡ የዲፕሎማሲ ስራቸው ግብአት እንዲሆን የተዘጋጁበትን የጄኖሳይድ ትርክትና ሰበብ በማጠናከር፣ የጄኖሳይድ ኮሚሽን አቋቁመው በትግራይ ውስጥ ብቸኛው ስራ የሚሰራ፣ በቂ በጀት የተመደበለት የመንግስት ተቋም አድርገው ገንብተውታል።
ኮሚሽኑ ወያኔዎች ከመደቡለት በጀት በተጨማሪ፣ አለም አቀፍ የትግራይ ምሁራን ድርጅት በሚያሰባስበው ገንዘብና ራሱ የኢትዮጵያ መንግስት በሚያቀረበው ገንዘብና እርዳታ ተደግፎ የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግስት በአለም ፊት የሚያሳጣ፣ ምእራባውያኑ መውሰድ ለሚፈልጉት ጸረ ኢትዮጵያና ኤርትራ እርምጃ ሽፋን የሚሆን በሚገባ የታቀደና የተደራጀ፣ ወደፊት ወያኔ ለሚያደርገው የዲፕሎማሲ ዘመቻ የሚያገለግል የተቀነባበረ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
ኮሚሽኑ በየቤቱ ሰራተኞቹን እየላከ ለጄኖሳይድ ክስና ለካሳ ማሰባሰቢያ የሚሆን መረጃ እየሰብሰብኩ ነው በማለት የትግራይ ህዝብ ጄኖሳይድ ሊፈጸምብኝ ተሞክሮ ነበር በሚል እምነት ውስጥ እንዲኖር እያደረገው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን “አሁንም የትግራይን ህዝብ ከወያኔ ውጭ ከጄኖሳይድ የሚያተርፈው የለም የሚል” ሰበካውን ቀጥሎበታል። አሁንም የወያኔ መሪዎች የሰላም ስምምነቱ በጦርነት አስገድደው ያገኙት ድል አድርገው ለትግራይ ህዝብ እያቀረቡለት ነው። ህዝቡ “የዚህ ድል ባለቤት ወያኔ ስለሆነ፤ ከህልውና ጥፋት የታደገህ ወያኔ ስለሆነ፤ እጣህን ከወያኔ ጋር አቆራኝተህ መቀጠል አለብህ” እየተባለ ነው።
ወያኔዎች ያሻቸውን ቢሉ ይህ አላስፈላጊ የነበረ ጦርነት በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱን የደሃ ልጆች ህይወት ቀጥፎ የዚችን ደሃ ሃገር ሃብትና ጥሪት አራቁቶ በነሱ ወታደራዊ ሽንፈት ለጊዜው ቆሟል። ከጦርነት ጋር በተያያዘ የሆነው ሁሉ ጸሃይ የሞቀው ጉዳይ ስለሆነ ብዙ ማተት አያስፈልግም። ከዚህ በላይ ያቀረብኩት መንደርደሪያ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውን ዘመን በጥንቃቄ እንድንመለከት የእይታ ማእቀፍ ለመስጠት ብቻ ነው። የወያኔ መሪዎችን እና ከእነዚህ መሪዎች ጋር የተጣበቀውን የትግራይ ልሂቅ የአእምሮ ውቅር በሚገባ ማወቅ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እውነተኛ ሰላም ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ የትግራይን ህዝብ ጨመሮ ከዛም አልፎ ለቀጠናው እንዲያመጣ ከተፈለገ በስርአት መሰራት ያለባቸውን ነገሮች ለመዘርዘር ያግዛል በሚል እምነት ነው።
ከዚህ ቀጥሎ አሁናዊ የትግራይ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? ይህ ሁኔታ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራል፣ የሰላም ስምምነቱ አንኳር በሆኑት የስምምነት ነጥቦች ዙሪያ በምን ደረጃ ይገኛል? እውነተኛ ሰላም በትግራይ ሆነ በተቀረው ኢትዮጵያ ለማስፈን ምን መደረግ ይኖርበታል? የሚሉ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት መንግስት ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳዩ በዋንኛነት ለሚመለከተው ህዝብ መስጠት የሚገባቸውን ነገር ግን እያደረጉት ያልሆነው ምልከታ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
2) የወቅቱ የትግራይ የፖለቲካ ሁኔታ ከሰላም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ፤
በትግራይ ውስጥ የሰላም ስምምነቱ ከመፈረሙ ከወራት በፊት ወያኔ የጀመረው ጦርነት በትግራይ ህዝብ ላይ ያሳደረውን እልቂትና ጥፋት የሚቃወሙ የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች በከተማው ጎዳናዎችና በየቤተክርስቲያኑ ይበተኑ ነበር። (የሰንድ ማስረጃዎች አሉ) ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በጥቂት ሰዎች የሚደረግ ቢሆንም በራሱ በወያኔ ውስጥ ያሉ ጦርነቱ እንዲቆም በሚፈልጉ የአመራር አካላት ጭምር የሚደገፍ ነበር።
ይህ እንቅስቃሴ ያሳሰባቸው የወያኔ አመራሮች “ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት አላቸው፣ የወያኔ መሪዎችን ለመግደል አሲረዋል፤ እንዲሁም መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አስበዋል ” በሚል በወዲ ሃጎስ የምትመራዋን በመቀሌ ዙሪያ ለጥበቃ የተመደበች ወደ አምስት መቶ የሰራዊት ብዛት የነበራትን አሉላ የተባለች ብርጌድ ላይ እርምጃ ወስደዋል። ወዲ ሃጎስ ለእስር ተዳረገ። በመፈንቅለ መንግስት ክስ ተከሶ ዛሬም እስር ቤት ነው ። የሰራዊቱ አባላት ትጥቅ አውርደው መቀሌ ቢዝነስ ኮሌጅ ውስጥ በተሃድሶ ስም በጥበቃ ላይ ነበሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን እንዴት አታውቅም በሚል የመቀሌው የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ተስፋዬ ከስራው ተነስቶ ለቁም እስር ተዳርጎ ነበር። ኮሚሽነር ኪሮስ የተባለው የጸጥታ ሃላፊም ተመሳሳይ እጣ ገጥሞት ነበር። የመቀሌው ከንቲባ ዶ/ር ገብረመድህን ከሃላፊነቱ በማንሳት ለእስር ተዳርጓል። በወያኔ ውስጥ ጦርነቱን የሚቃወሙ የአመራር አካላት ቁጥራቸው እየተበራከተ በማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ አቅም እየፈጠሩ በመሄድ ላይ ነበሩ።
በዚህ ወቅት በጦር ሜዳ በኩል የሎጂስቲክ ችግር እያደገ፣ በሰራዊቱ ውስጥ የመንደርተኛነት ክፍፍል እየሰፋ፣ ወያኔ በገፍ በቅርቡ ያሰባሰባቸው ወጣቶችና ከእስር ፈትቶ ወታደር ያደረጋቸው ወንጀለኞችና የድርጅቱ የቆዩ አባላቶች ተጣጥመው መስራት እየተሳናቸው በሰራዊቱ ውስጥ ለጋራ አላማ መሰለፍ አዳጋች የሆነበት ሁኔታ በስፋት መስተዋል ጀመሮ ነበር። በርካታ የሰራዊት አባላት ሰራዊቱን እየከዱ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። እነዚህን ተመላሾች ስራዬ ብሎ እያሳደደ የሚለቅም በኮማንድ ፖስት በኩል ሰፊ የተደራጀ ስራም ተጀምሮ ነበር። የሰራዊቱ መሪዎች የሙስና ድርጊት እየባሰበት፣ ሙስናው የሰራዊቱን ቀለብ ከመሸጥ አንስቶ እንዲሁም አብዛኞቹ ወታደራዊ መኮንኖች (እንደወዲ እምበይትይ የመሳሰሉ ጀነራሎች) ወደ ትግራይ የሚያስገቡ ኬላዎች እየዘጉ ከአፋር ፌዴራል ሃይሎች ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ በሆነ የጨው ንግድ በመስማራታቸው በሰራዊቱ ውስጥ ትልቅ መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከአማራና ከአፋር ክልል የተዘረፈውን ሃብት የግል እስከማድረግ ድረስ የሚያካትት ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ራሱ ወያኔ፣ ኮነኔል ጉና (ገብሩ) የአዋሽ አርባ አዲስ ራእይ ማሰልጠኛ ሰራ አስኪያጅና በነበረው በሌሎችም ወታደራዊ አመራሮች ላይ የእስራት እርምጃ እስከመውሰድ ደርሶ ነበር።
በራሱ በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ትግራይ ለገባችበት አሰቃቂ ሁኔታ ተጠያቂዎች መሆን የሚገባቸውን ሰዎች ለይተው ሊጠየቁ ይገባል የሚል ድምጻቸውን ማሰማት የጀመሩ አባላት ብቅ ያሉበት ሁኔታ ተፈጠሮ ነበር። ወያኔ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ጠጋግኖ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ለማለት ነበር የሶስተኛ ዙር የወረራ ጥቃቱን በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ የከፈተው። የሶስተኛው ዙር ወረራ አላማ ቀደም ብሎ እንደታሰበው አዲስ አበባ ለመግባትና የመንግስት ስልጣን ለመቆጣጠር ሳይሆን ከወያኔ መሪዎች አቅምና ቁጥጥር ውጭ እየወጣ የነበረን መጨረሻው የማያምረውን የወያኔን የውስጥ ድርጅታዊ እና የትግራይን ፈተናዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደራደር ለመፍታት የሚያስችል የተወሰነ የመደራደሪያ አቅም ለመፍጠር የተደረገ ነበር። የትግራይ ህዝብና ወጣት የወያኔ አመራሮች ለጦርነቱና ለእልቂቱ የወያኔን ነባር መሪዎች ተጠያቂ እንዳያደርጋቸው ከመስጋት የተደረገ የማደናገሪያ ወረራ ነበር። ወረራው ወያኔዎች እንዳሰቡት ሳይሆን የኢትዮጵያ ጦር ሰፊ የትግራይን ክልል ተቆጣጥሮ ጭራሽኑ ትግራይ ወስጥ ገበቶ መቀሌን በቅርብ ርቀት የሚያይበት ሁኔታ ተከሰተ።
ይህ ወታደራዊ ሽንፈት በአንድ በኩል ወያኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲቀበል ያደረገው ቢሆንም ከዚሁ ያልተናነሰ ጫና ያሳደረው በራሱ በወያኔ ውስጥ የተነሳው ነባር መሪዎቹን ሊበላ ወደሚችልበት ደረጃ እያደገ በመሄድ ላይ የነበረው የውስጥ ትግል መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
ወያኔዎች ከአሜሪካን መንግስት ባላስልጣናት ጋር በቅርበት እየተመካከሩ የሚሰሩ በመሆናቸው ወታደራዊ ሁኔታውን የተረዳው የአሜሪካ መንግስት የወያኔ መሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደራደር ራሳቸውን ከጥፋት እንዲያድኑ ተጸእኖ ሳያደርግባቸው እንዳልቀረ መገመት ከባድ አይሆንም። የአሜሪካ ተጽእኖ በወያኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ መንግስትም ላይ የተደረገ ለመሆኑ ፕሬዚደንት ኢሳያስ በጥር 2015 በሰጠው ቃለ ምልልስ ጥቆማ ሰጥቶናል። በሌላ መንገድም ይህ ተጽእኖ ቀላል እንዳልነበር መረዳት ተችሏል። ይህም ሃቅ እንዳለ ሆኖ የወያኔ የውስጥ ሽኩቻን ያሳደረውን ከፍተኛ ተጽእኖ አሳንሰን ማየት አይገባንም።
የውስጥ ሽኩቻው ከሰላም ስምምነቱ በፊት በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ በነባር አመራሮችና በወጣት አመራሮች መሃከል ይካሄድ ነበር። ሽኩቻው ወጣቶች በጎደሉ የስራ አስፈጻሚ አባላት ምትክ አዳዲስ አባላት እንሙላ ሲሉ፣ ነባሮቹ ወቅቱ አዲስ አባላት ለመሙላት አይፈቅድልንም የሚል ነበር። ወጣቶቹ አዲሶቹ አባላት ከወጣት መሪዎቹ ጎን ይቆማሉ ብለው ስለሚያስቡ ሃሳቡን ሲገፉ ነበር። ነባሮች ይህን ስላወቁ ሃሳቡን ሲቃወሙ ነበር። ሌላው የሽኩቻ ነጥብ በስልጣን የሚታየው ያልተቀየረው የአሻአ (የአክሱም ሽሬ እና አድዋ) ሰዎች በፖለቲካውም፣ በአስተዳደርም በወታደራዊ መስኮች የነበራቸው የበላይነት አሁንም በከፋ መልኩ እየቀጠለ ከመሆኑ ጋር ተያያዞ የሚነሳ ነበር። በተደጋጋሚ በማእከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ይህ ጉዳይ እየተነሳ ያወዛግብ እንደነበር ይታወቃል። ማወዛገቡ ብቻ ሳይሆን ሰዎች የመጡበትን አውራጃ እየጠቀሱ በታማኝነት በከሃዲነት የመፈረጅ ንትርክ ጭምር የተለመደ ሆኖ ነበር።
ከሰላም ስምምነቱ በፊት በነበሩ ጥቂት ወራት በአጠቃላይ በወያኔ አመራር ካምፕ ውስጥ የነበረው ክፍፍል ለተፈጸመው ሁሉ በተጠያቂነት እንያዛለን የሚሉ ጥቂት አመራሮችና ሊጠየቁ ይገባል በሚሉ በርካታ አባላት መካከል እያደገ የመጣ ክፍፍል ነበር። እጣቸውን ከተጠያቂነት ጋር የሚያስተሳስሩ መሪዎች ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ራሳቸውን ለማዳን ሴራ በመሽረብ፣ እቅድ በማውጣት ነበር።
በዛን ወቅት የማእከላዊ ኮሚቴው ለሁለት እንደተከፈለ ሁሉ የሰራ አስፈጻሚውም ለሁለት
ተከፈሎ ነበር። ጌታቸው ረዳ እና ደብረጽዮን በአንድ ወገን፣ ጌታቸው አሰፋና ፈትለወርቅ አለም ገብረዋህድ በሌላው ጎራ ቆመው ነበር። የጌታቸው ረዳ ነገር መቼም አስገራሚ ነው መባሉ አይቀርም። በዚህ የውስጥ ሽኩቻ በትግራይ ውስጥ ከሚገኙ ከ35ቱ (ከ37ቱ ሁለቱ ውጭ ሃገር ናቸው) የወያኔ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መሃል በየቀኑ አቋማቸው የሚለዋውጡ አስራ አራት አባላት ያሉት ሲሆን የተቀሩት በሁለት ጎራ ተከፍለው የእነዚህ የ14 ኮሚቴ አባላት ድጋፍ በማሰባሰብ የሚተናነቁባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ነበሩ።
የውስጥ ሽኩቻው የደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳየው ሃቅ በጥር 2015 ውስጥ ተከስተ። የወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ እና ከእያንዳንዱ አርሚ ሶሶት ሶሶት ሰው የተወከለበት በደጀን የርእሰ መስተዳደሩ ቢሮ፣ ከጥር 7 እስከ ጥር 10 በተደረገው ስብሰባ ኮሚቴው በወሰነው ውሳኔ መሰረት ደብረጽዮን ገብረሚካኢኤል፣ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አለም ገብረዋህድና ጌታቸው ረዳ፣ ሁሉም የህወሃት የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት፣ በትግራይ ለሆነው ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው በሚል ከስልጣናቸው ታግደው እንዲቆዩ እስከመወሰን እና ይህ ውሳኔ በምክር ቤት እንዲጸድቅ ጥያቄ እሰከማቅረብ ደርሶ ነበር።
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የጥቂት የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የአቋም መገለባበጥ ከሚታይበት ሁኔታ በስተቀር በወያኔ ውስጥ በትግራይ ለውጥ እንዲመጣ በሚፈልጉ እና በማይፈልጉ፣ የሰላም ስምምነቱን በሚደግፉና በሚቃወሙ ሁለት ዋና ቡድኖች የማእከላዊ ኮሚቴው እንደተሰነጠቀ ነው።
አንዱ ቡድን የሞንጀሪኖ ቡድን በመባል የሚታወቀው ሲሆን የውናትና የባይቶና (በስም የተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸው ነገር ሁኔታዎች ሲከፉ ከዚህ ቡድን ጋር የሚለጠፉ እንደሆነ ይታወቃል) ድጋፍ ሲኖረው፣ ከወታደራዊ ተቋሙም ጋር ከተወሰኑ አካላት ጋር ቁርኝት ያለው ቡድን ነው። የዚህ ቡድን አባላት ጌታቸው አሰፋ ራሷ ሞንጀሪኖ (ፈትለ ወርቅ ገ/እግዚአብሄር )አለም ገብረዋህድ፣ አልማዝ ገ/ጻድቅ የክልሉ የትራንስፖርት ሃላፊ፣ ገነት አረፈ የማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ፣ ሃጎስ ጎድፋይ ጤና ቢሮ ሃላፊ ( አሁን የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት ሃላፊ)፣ ፍስሃ ሃፍተፅዮን ፣ ሃዱሽ ዘነብ ፣ አማኑኤል አሰፋ ፣ ይትባረክ አምሃ የመቀሌው አዲሱ ከንቲባ፣ አርአያ ግርማይ፣ ዶ/ር አማኑኤል ሃይሌ፣ ሊያ ካሳ የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ፣ እነዚህ የሰላም ስምምነቱ በመቃወም በጋራ የቆሙ ሲሆን፤ በሌላ ወገን ከጌታቸው ረዳና ሌሎች ሰላሙን የሚደግፉ አባላት፣ ብርሃነ ገብረየሱስን፣ የአሁኑ የምእራብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ነጋ አሰፋ፣ የህብረት ስራ ማህበር የክልሉ ሃላፊ፣ ሰብለ ካህሳይ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊ፣ በየነ ሙክሩ የፋይናንስ ሃላፊ፣ ሃብቱ ኪሮስ ቆይቶ የተቀላቀለ የደቡብ ዞን አስተዳዳሪ፣ ዶ/ር አትንኩት መዝገበ፣ ረዳኢ ሃለፎም የትግራይ ኮምኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ለምለም ሃድጉ ባህልና ቱሪዝም ሃላፊ የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ተከራክረው ያሸነፉ ናቸው። አንዲሁም ከተለያዩ አርሚዎች የተወከሉ የጦር መሪዎች አብዛኞቹ የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ ከእነዚህ የለውጥ ሃይሎች ጋር በመሆን የቆሙ ነበሩ፡፡ በዚህ ስብሰባ ጌታቸው አስፋ አሞኛል በሚል ሰበብ ስብሰባውን አቋርጦ አስከመሄድ ደርሷል። በተጨማሪም ጄነራል ወዲ እምበይተይ በስብሰባው ሊገኝ አልቻለም ፡፡
ይህም ሆኖ የሰላም ስምምነቱን ያልተቀበለው ቡድን በጁ ባለው የገንዘብና አሰተዳደራዊ አቅም እና በሰራዊቱ አመራር ውስጥ ባለው ድጋፍ የተለያዩ እንቃስቃሴዎችን ማድረጉን አላቆመም። ይህን አቅም በመጠቀም ጥር 24 እና 25 /2015 ከመላው ትግራይ የቡድኑ ደጋፊዎች ናቸው የሚላቸውን እስከ 600 የሚደርሱ ወጣት ካድሬዎች መቀሌ በሃውልት ሰማእትታ አዳራሽ በማሰባሰብ፣ “ህወሃት ታሪካዊ ድርጅት ነው መፍረስ የለበትም፣ ይህን ታሪካዊ ድርጅት ለማፍረስ ከሚሰሩ ተንበርካኪዎች ጋር መታገል አለብን” የሚል አጀንዳ መወያያ እንዲሆን አድርጓል። (በዚሁ አጋጣሚ ተንበርካኪዎች በሚባሉ ግለሰቦች ላይ ግድያ፣ የግድያ ሙከራ መፈጸም መጀመሩን፣ ወደፊት ይህ የወንጀል ድርጊት እየጨመረ እንደሚመጣ መታወቅ አለበት።) በዚህ ስብሰባ ላይ ሁሉም የማእከላዊ ክሚቴ አባላት ተገኝተው ነበር። አላማው ለውጥ ፈላጊ አመራሮችን ለማሸማቀቅ ከተቻለም ከዚህ በፊት በ1993 መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎቹን በካድሬዎች አማካይነት አዋክቦ ከድርጅቱ እንዲባረሩ ያደረገውን አሰራር ለመድገም ነበር። እንዲህም ሆኖ ስብሰባው ለወጥ በሚፈልገው ወገን አሸናፊነት ተጠናቋል።
ይህ መንገድ አላዋጣ ያለው ጸረ ሰላም ቡድን ከለውጡ በኋላም ስምምነቱን የማጨናገፍ በኢትዮጵያ ደረጃም ሃገር የማናጋት እቅዱን በስራ ለመተርጎም የራሱን እንቅስቃሴዎች ማድረጉን ቀጥሏል። ለስራ ገንዘብ ያስፈልገናል በሚል 350 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅድ አውጥቶ ይህን ገንዝብ የመቀሌን ከተማ መሬት በመቸብቸብ ገንዘቡን ማሰባሰብ ችሏል። የመቀሌን መሬት የገዙት ግለሰቦች ከአማራና ከአፋር ክልል እንዲሁም ከራሱ ከትግራይ ህዝብ ገንዘብና ንብረት የዘረፉ የሰራዊቱ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ናቸው።
ይህን ገንዘብ በመጠቀም ለውጥ የማይፈልገው ቡድን ሰራዊቱ ውስጥ ካሉት አጋሮቹ ጋር በመሆን በልዩ ሁኔታ ለተመለመሉና ለሚያስለጥናቸው እስከ 7000 የሚደርሱ የሽብር ስራ በመላው ኢትዮጵያ ለማካሄድ ለሚሰለጥኑ ሴትና ወንድ አሸባሪዎች ማሰልጠኛ በተግባር ላይ እያዋለው ነው(የመሰልጠኛ
https://amharic-zehabesha.com/archives/180658
No comments:
Post a Comment