Tuesday, March 28, 2023

ግንጊልቻ (Gingilchaa)- የጠቅላዩ የፓርላማ ውሎ ትዝብት... በ-ሙሉዓለም ገ/መድኀን 
የሀገረ-መንግሥቱ ትርክት የሚነገረንም ሆነ በንባብና በዐይን እማኝነት የያዝነው ግንዛቤ የሚያስረግጥልን፣ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ ከኔጋቲቭ ወደ ዜሮ ማደጉን ነው፡፡ ይህ “እድገት” የተመዘገበውም ኢሕአዴግ ቢያንስ በመርህ ደረጃ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን እና እንደ ድመት መልሶ የበላውን የሚዲያ ነፃነት በመፍቀዱ ነበር፡፡ በዚህም፣ ትልቁን የፖለቲካ ተቋም ፓርላማውን የመጥፎ ገጽታ ምልክት እንዲመስል አድርጎታል፡፡

በተለየ ከምርጫ-2002 ጀምሮ በተከታታይ በተመሰረቱት ምክር ቤቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት የግድ የሚለውን የፖለቲካ ብዝሃነት ጨርሶ እንዳይታይ ስለመጨፍለቁ አብዝተን መሟገታችን የትላንት ትውስታ ነው፡፡ በተረፈ፣ እነዚህን ሂደቶች እና አስመሳይ (façade) አዋጆቹን ተመርኩዞ ‹ሥልጣን በብቸኝነት ይገባኛል› ወደሚል የአውራ ፓርቲ ጉዞ መቀየሩን ስናስታውስ፣ ፓርላሜንታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የማይቻል ዳገት (Uphill Stride) አድርጎት ለመዝለቁ አስረጂ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ርግጥ ነው፣ ኢሕአዴግን ወደ አውራ ፓርቲነት ያመጡት እነዚህ ሲዶ መሰላሎች ውድቀቱንም አፋጥነውታል፡፡

በሀገራችን ባህል ሙታንን ከዚህ በላይ መውቀሱ ነውር ነውና፤ ኢሕአዴግን አሰናብትን በወራሹ እንጀራ ልጁ እንደበራለን፤ (መቼም፣ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ከዐቢይ አህመድ፣ ሙክታር ከድር፤ ከአይናለም ንጉሴ፣ አለምነው መኮንን፤ ከአብራሃም በላይ፣ ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል፤ ከፍፁም አሰፋ፣ ሽፈራው ሽጉጤ… “ተወላጆች” እንደነበሩ አትዘነጋውም?! በአናቱም፣ የመተካካቱ ባቡር እንዲህ ሃዲድ በመሳቱ ይመስላል ለአክሱም ፂዮን ቪዛ የተጠያየቅነው፤ ለጎንደር ጥምቅት ዲቪ የሞላነው፤ ለቁልቢው ገብርኤል ፓስፖርት ያወጣነው፤ አዋሳ ለመዝናናት ትራንዚት የጠየቅነው…¡፡፡)

ወደ ርዕሰ-ጉዳያችን እንመለስ፤

ከገዥው ፓርቲ በተቃራኒ የተሰለፉ የምክር ቤት አባላት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ላይ የደቦ ሳቅና ሁካታ ማሰማቱ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለመዘርዘር የሚቸግሩ አሳፋሪ መንጋነት የተጫናቸው ሁነቶች የምክር ቤቱ የተለመደ ተውኔት ሆነዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው ገፊ-ምክንያት የፓርላማው የፖለቲካ ብዝሃነት ድቀት ከኑሮ ውድነቱም በላይ መናሩ ነው፡፡

ዛሬ በምክር ቤቱ የጎነው ቅጥ አምባሩ የጠፋበት ትምክህት (በርግጥ፣ ትምክህት የራሱ ወግ አለው! ቃሉን የተጠቀምኩት ለመግባባት እንዲረዳን ብቻ ነው) መነሻው ፋሽዝምንና ብሔርተኝነትን መቀላቀሉ ብቻ ሳይሆን፤ ሊገራ የሚችል (check and balance) የፖለቲካ ብዝሃነት ያለው ፓርላማ አለመኖሩ ነው፡፡ ይህም ቢያንስ ምክር ቤቱ ለአስፈፃሚው አካል ልጓም መሆን የሚችልበት ዕድልን አሁንም አምክኖ እያዘገመ መሆኑን ለመታዘብ አስችሎናል፡፡ ልብ በሉ? እያወራው ያለሁት ስለ አውራ ፓርቲ አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ የአውራ ፓርቲ የሕይወት ታሪክ በእንጀራ ልጁ ተዘግቶ፤ የአውራ ብሔር ዘመን ተገልጧልና፡፡ (በዚህ ድምዳሜ ካልተስማማህ፡- የቅርብ ጊዜዎቹን የኦሮሚያ፣ የዐማራ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የጋምቤላ… ብልፅግና ቅርንጫፎችን የመግለጫ “እንካ ሰላምታ” መልሰህ ትገርበው ዘንድ አስታውስሃለሁ፡፡)

የሆነው ሆኖ፣ ዘመነ-አውራ ብሔር (a.k.a የድኀረ-2010ሩ ‹‹ለውጥ››) በአምስት ዓመት ቆይታው ሲመዘን የሀገረ-መንግሥቱን ቀጣይነት የሚያስረገጡ ዐምዶችን እየናደ፣ የሀገረ-መንግሥት ምስረታ (State formation) ላይ ተጠምዷል፡፡ በዚህም ነው፣ በስሁት ትርክት የተበጀውና ዝንፈት የተጫነው ሕገ-መንግሥት (An original sin of Ethiopian Federalism) እንዳይሻሻል ወጥሮ፤ ከሽግግር ፍትሕ ይልቅ፣ የተረኝነት ሽግሽግ ማንገሡ ውሃ እንደመጠጣት የቀለለው፡፡

በተረፈ፣ የዜጎችን የአገር ባለቤትነት ድርሻ የዘነጋው ሕገ-መንግሥት፣ የሥርዓት ወለድ ችግሮች ሁሉ እናት መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ ‹ለአንድ ክልል ብለን ሕገ-መንግሥት አንቀይርም!› ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ‹ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል በምርጫ የተመረጠ መንግሥት የግድ ያስፈልጋል› የሚለውን ክርክር አርቀው መሰቀላቸውንም አልዘነጋሁትም፡፡ በርግጥ፣ ይህ ርቀት “ከሥልጣን ይውረዱ?” የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ እንደ ሸሚዝ ኪሳቸው ሲቀርባቸው ደጋግሜ አስተውያለሁ፡፡

(የቅንፍ ጥያቄ፡- ሕገ-መንግሥቱ በትሕነግ ዘመን ቢያንስ ‹ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተቀዳ ነው› በሚል ኢንተለክቸዋል ትችት ለማቅረብ ያስችል ነበር፡፡ ዛሬስ፣ እነ ዐቢይ ‹ሕገ-መንግሥት› ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? የገዳ ሥርዐት ነው? የብልጽግና ወንጌል ነው? የመደመር አርቲ-ቡርቲ ነው? ቄሮ ነው? የሌንጮ ለታ ምክር ነው? በተቃርኖ የታጨቀው የጀዋር መሀመድ ጽሑፍ ነው? የአህመዲን ጀበል ኃይማኖ-ቲካ ነው? የእነ ሳውሮስ ሸኔያ’ዊ-ሲኖዶስ ነው? …ወይስ ማን ነው? ይህ ጥያቄ የቀረበበት መግፍኤን በአያሌ ማስረጃ መደግፉ ቀላል ነው፡፡ ዋና አጀንዳ ባለመሆኑ እናልፈዋለን እንጂ፡፡)

ዐቢይ አሕመድ  የዘመን መንፈስ ሆነዋልና ጎልማሳው መሪ "መለኮታዊ ተልዕኮ አለው" እንዳሉላቸው ወንጌላዊ ቤተኞቹ ሳይሆን፤ ተልዕኮው ከማንም ሆነ ከማን… ለሥልጣናቸው ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለሱ በዛሬው የፓርላማ ውሎ አራምባና ቆቦ እየረገጡ ተናግረዋል፡፡

ወትሮውንም ቢሆን የሰውየው የቀውስ ጊዜ አመራር ከንግግራቸው ይልቅ፤ በተግባራቸው እንዲመዘኑ የሚያስገድድ ነበር።

ዛሬ በተዳፈነ እሳት ውስጥ ስለ ድኀረ-ጦርነት ባህሪያት ሊያወሩን የሞከሩት የአራተኛ ዙር ጦርነት ማስነሻ የዝግጅት ጊዜ መሆኑን ለመጋረድ (ሽፋን ለመስጠት) እንደሆነ የሚያውቅ ያውቃል፡፡ ከጥፋቱም ከቅጥፈቱም መማር የተሳነው ትሕነግ በትግራይ ባሉ ማሰልጠኛዎች ሠራዊቱን “ለልዩ ተልዕኮ” በሚል እየሰጠ ላለው ከባድ ስልጠና ስፖንሰሩ ማን እንደሆነ እናውቃለንና፡፡ ለዚህ ነው፣ ማዘናጋት፣ ማሰልቸት፣ ማጭበርበር… የአመራር ዘይቤ ሆነው በተግባር ሲገለጡ እያየን ነው የምንለው፡፡

(ወይ ረስቼው? የጽሑፌ ርዕስ “ግንጊልቻ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ሲሆን፤ የዐማርኛ ትርጓሜው “ወንፊት” ማለት ነው፡፡)

ከዚህ በተጨማሪ፣ ‹መንግሥታዊ መዋቅራቸው ተጠልፏል› ከሚለው መላምት ባለፈ፤ በልሂቃኑ ሲነሳ የኖረውን የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች ጽንፍ የረገጡ ጥያቄዎችን ‹‹በሰመመናዊ ሳይንስ›› ለማስመለስ በዕቅድ እየተጓዙ ነው ወደሚል ድምዳሜ መገፋታችን ስህተት አይደለም፡፡ ለሀገሬው የሚፍልገውን እየተናገሩ፣ የሚፍልጉትን የመሥራት የደከረተ ሴራን ስለመከተላቸው ዐደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነውና፡፡ (በተረፈ ‹‹ሰመመናዊ ሳይንስ››ን የ16ኛው ክፍለ ዘመን ‹ሌጋሲ› ብለህ ወደ ዐማርኛ ልትተረጉመው ትችላለህ፡፡ ወይም፣ በፈረንጅኛው የራሱን “hidden empire” ጠርዝ በረገጠ ስግብግብነት ለማዋለድ የሚተጋ ልትለው ትችላለህ፡፡)

እነዚህና መሰል ድርጊቶቻቸው፣ በኢትዮጵያ ያሉ ሁኔታዎች ከድርጅት በላይ በመሆናቸው፤ ለአንድ አውራ-ብሔር ቀርቶ፣ ለአንድ ገዥ ፓርቲም ለብቻ በአደራ የሚሰጥ እንዳልሆነ በተግባር ያስተምረናል፡፡ ምክንያቱም፣ ስቴት ማሽነሪውን የተቆጣጠረው ኃይል ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የሀገረ-መንግሥት ምስረታ ተልዕኮውን አንድ ብሎ የጀመረ በመሆኑ፣ ለሁሉም የአገሪቱ የማንነት ቡድኖች የህልውና አደጋ ደቅኗል፡፡ ይሁንና፣ በተለመደው የአለቃና ምንዝር (patron-client) አካሄድ አመራሩን ቀይዶ በመያዝ አስፈፃሚውን ገባሪ አድርጎታል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ፡- ‹rubber stamp› የሆነ ሚና የተዋረሰውን ምክር ቤትም እንደፈለገ በመጠምዘዝ ለዚሁ ተልዕኮ ማስፈጸሚያነት እየተጠቀመበት ነው፡፡ በዚያው ሰሞን ትሕነግን ከአሸባሪነት መዝገብ ለመፋቅ የነበረውን ድራማ ለምክርቤቱ ሱፐር ‹rubber stamp› ነት ዐቢይ አስረጅ አድርገን እንጠቅሳለን፡፡ ገራሚው ተረክ አማራን ወከልን ያሉ ጉሊቶችም እጃቸውን ለአውራ-ብሔር ፖለቲካው ማከራየታቸው፤ ጥንተ-ጠላታቸውን ትሕነግን ደግፈው መታየታቸው ነው፡፡

ዛሬ ጠቅላዩ በነበራቸው የፓርላማ ውሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታና ለዛ ባጣ ትምክህት የሰጧቸው ምላሾች ግን፡- ከውጭ ምንዛሬ ክምችቷ ባሻገር የድንገተኛ አደጋ መጠባበቂያ የእህል ክምችቷ አራግፋ የጨረሰች፣ ዓለም ዐቀፍ ውጥረት የፈጠረው የህዳሴ ግድብ እንደ ስቢስቴ ነጋሢ ዘመን የተረሳ መስሎ ሥራው የቆመበት፣ ካዝናዋ ተራቁቶ አየር መንገዷንና ቴሌዋን እንድትሸጥ በደላሎች የምትዋከብ፣ ማንነት-ተኮር ግጭትና መፈናቀል የተንሰራፋባት፣ ኑሮ “በሚራክል መኒ” የሚገፋባት፣ እጅግ የተጋነነውን ሥራ-እጥነት ከመቅረፍ የንጹሃንን አንገት መቀንጠስ የቀለለባት… ሀገር እየመሩ እንደሆነ አለመምሰላቸውን አስረግጠዋል፡፡

ኧረ እንዴውም “ሰላም እየተስፋፋ ነው” ሲሉ ተሳልቀዋል፤ (የሰላምን አንፃራዊነት ብናምንም፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ “ኢትዮጵያ ሰላም ነች” ለማለት ግን የግድ ወዳጅነት ፓርክ ውሎ ማደርን ይጠይቃል፡፡)

የተቀረውን ንግራቸውን እንኳ “ሰውየው” በሚል መጽሐፍ ከእምለኮም የገዘፈ ውዳሴ ደርድሮ ዋልታን ለተሸለመው ሰው ትተህለት፤ በበኩልህ የዛሬውን ውሎ “ግንጊልቻ” ብለህ እለፈው!!!

ሁለት የግርጌ ማስታወሻዎች፡-

፩. ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን የለቀቀው፣ ከጠቅላይ ሚንስትርነቱ ነው እንጂ፤ “ሕዝብ መረጠኝ” ብሎ ከያዘው የፓርላማ ወንበር አይደለም፡፡ የሥራ-አስፈጻሚውን አለቃም ሆነ ግብረ-አበሮቹን የመረጣቸው ይህ ምክር ቤት ሲሆን፤ “አልቻልክም ውረድ!” የማለት ሥልጣኑም የእሱ ነው፡፡ የምክር ቤቱን አባላት የሚሸረው (ውክልናን የሚያነሳው) ደግሞ የመረጣቸው ሕዝብ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት ተራ ጉዳዮችን ጭምር እየጠቀስን ለመምከር የተገደድነው፣ ጨዋታውን ወደ ሕፃናት መዋያ /ኪንደር ጋርተን/ ደረጃ ስላወረዱት በመሆኑ ነውና፤ አንባቢያን “አፉ” በሉኝ፡፡)

፪. ይህ ጽሑፍ አላለቀም፡፡ ከሰላም፣ በአገሪቱ በተለያያ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች፣ ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር እና ከቀጠናው ችግሮች አኳያ ነባራዊ ሁኔታዎችን ተመልሰን እንዳስስበታለን፡፡
https://amharic-zehabesha.com/archives/181234

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...