Friday, March 31, 2023

ከሸፍጥ ነፃ የሆነ ህዝበ ውሳኔ ይልቅ ፣ ፖለቲካዊ ሤራን ማጫጫስ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እጅግ ይበዛል - መኮንን ሻውል
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ልዩ ኃይልና ወጣት እና ጤነኛ ሚሊሻዎች ወደ መከላከያ ሠራዊት እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ ህጋዊ  አዋጅ ሳይወጣ እና የክልልች ያበጠው ጡንቻ ሳይላላ ፣ ወልቃይት ና ራያን በትግራይ ክልል ውሥጥ በመመለሥ ነፃ ና ገለልተኛ የሆነ ሪፈረንደም ማድረግ የሚቻል አይመሥለኝም ።

ነፃና ገለልተኛ ህዝበ ውሳኔ በማድረግ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩት ከጠብ መንጃ ነፃ ሆነው ያለፍርሃት ያለአንዳች ተፅእኖ ግልፅ ፣ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ የህነ የህዝበ ውሳኔ ድምፅ ለመሥጠት የሚያሥችል ግልፅ ና ገለልተኛ መድረክ ሲኖር  ብቻ ነው ። እኔ አውቅልሃለሁ በሚሉት ኮሚኒሥታዊ አካሄድ ትላንት ወልቃይትና ራያ በትግራይ ክልል ሥር ነበሩ ።

እርግጥ ነው ፣ ከጦርነቱ በፊት ወልቃይትና ራያ በትግራይ ክልል ሥር ነበሩ ። ከ1983 ዓ/ም በፊት ግን አልነበሩም ። ከዘመነ ወያኔ በፊት በዘመነ

ደርግ በጎንደር ክፍለሀገር ሥር እንደነበሩ ይታወቃል ። ከዘመነ ደረግ በፊትም የጠበቀ እና ከአካባቢያቸው   ባህል ጋር የተዋሃደ ማንነት  ነበራቸው ።  ህኖም ትላንት በኃይል  አሥተዳደራቸው ሥለተወሰነላቸው ዛሬም ዜጎችን ያለፈቃዳቸው “ ኃይል ይግዛቸው ። “ ብዬ ሃሳብ ለመሥጠት አይዳዳኝም ። ይሁን እንጂ ያለአሻጥር ፣ በነፃ ና ግልፅ በሆነ መድረክ የሚያሥተዳድራቸውን ክልል ወይም “ ረሥ ገዝ አሥተዳደር  “ ራሳቸው ይወስኑ ። ልዩ የፊደራል ክልል  የመሆንም መብት እንዳላቸውም መዘንጋት የለብንም ። በዘመነ ከፋፍሊት የሆነውም ይኸው ነው ።

በበኩሌበነገራችን ላይ ፣  " ዘመነ ከፋፍልቲን" አገር እንደ ዳቦ የሚቆራርስ እና ለተራው ህዝብ የማይጠቅም የቆዳ ማዋደድ እና ጋብቻ ከልክል በመሆኑ ነፍሴ ይጠየፈዋል ። ኤርትራን ያሳጣንም ይሄ ግትር አቋም ነው ። የግድ ጨካኝ መሪ ያሸንፋል ብሎ ነገር በዛሬው ዓለም የለም ። ሃያል እና ጅምላ ጨረሻ የባዮሎጂ ጦር መሣሪያ ካለህ አንድ አገርን ለማጥፋት ትችላለህና ! በእኛ ሁኔታ ይህንን የሚያደርግ አቅም የለንም ። ከዓለም የምንበልጣቸው አገሮች 24 ናቸው ። በድህነት 25ኛ አገር ነን ። የዛሬ ታሪካችንን ከጎግል መጎልጎል ይቻላል ።  ዕውቀት እንደ ሠፈር ብቅል ሆናለችና ማንም ለማወቅ የፈለገ የተማረ ሰው ሥለ እኛ አገር ክፉና በጎ ሁኔታ ለማወቅ የታሪክ ምሁራንን መጠየቅ አያሥፈልገውም ።

ኤርትራዊያንን ከጉያችን የቀማን ፣ የአንደ እናት ልጆችን የለያየን የቀዝቃዘው ጦርነት ሤራ ነው  ። ካፒታሊስት አሜሪካ ከመሰሎቿ ከአውሮፓውያኑ ጋር በማበር ፤ ሶሻሊስቷን ሩሲያ አሥራ አንድ አገር አድርጋ ሥትበታትናት ፣ በ1982 የደርግ ፍፃሜ እውን መሆኑ ተረጋግጧል ። ደርግ የሶሻሊዝም አቀንቃኝና የአሜሪካን ኢምፐርያሊዝምን ክፉኛ መጥላቱን  በአብዮት አደባባይ ሦሥት በቀይ ቀለም የተሞሉ ጠርሙስችን በመከሥከሥ በተጨባጭ ያረጋገጠ ነበርና ! ( ፊልሙን ዛሬ በእዝን ልቦናዬ ሣሥታውሰው የጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም  ወኔ ያሥደንቀኛል ።

ዛሬ የኃያሏ አሜሪካ ጡንቻ ተገዳዳሪ ቢኖረውም ፣ አሜሪካ የዜጎቿን ጥቅም ለማሥጠበቅ ሥትል የማትወጣው ዳገት እንደሌለ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል ። እንዲህም ሲባል አሜሪካ የብልሃት ፖለቲካን የማይመርጥ መንግሥት የላትም ብለን አናምንም ።

በኢትዮጵያ ውሥጥ የተረጋጋ ጠንካራ ህግ አሥከባሪ መንግሥት እንዲኖር  የአሜሪካ መንግሥት ይፈልጋል ። ከወቅቱ ሥልጣኔ ጋር የማይራመድ የህፃን ጨዋታን የመሠለ ኢ_ዴሞክራሲያዊ ድርጊትንም አይደግፍም ።  በመላው ኢትዮጵያ ግጭቶች ጠፍተው ዜጎች እንዳሻቸው በዜግነታችው በአገራቸው ምድር ሁሉ ተዘዋውረው የሚሠሩበት  አውድ ቢፈጠር እጅግ ደሥ ይላቸዋል ። እነሱም መዋለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ ላይ ያለፍርሃት በማፍሰስ ህዝቡን ጠቅመው የአገራቸውን ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርጉት ሠላም ሲኖር ብቻ እንደህነ ያምናሉ ። ከዚህ እምነታቸው ተነሥተው ነው ፣ ዛሬ እያራመድነው ያለውን የቋንቋና የዘር ፕለቲካ የማይደግፉት ።

የእኛ ፖለቲካ ለህብረት ፣ ለአድነት ፣ ለወንድማማችነት ና ለመልካም ጓደኝነት ፍፁም የተመቸ አይደለም ። ዜጎች ተከፋፍለው ፣ ተለያዬተውተነጣጥለው ፤ ልክ እንደባላንጣ በጎሪጥ እየተያዩ ይህቺን አጭር ህይወት እንዲኖሩ የሚያሥገድድ ነው ።

ለዚህም ነው ዛሬ አማራ ያለመደበትን  " አማራ ነኝ " ብሎ የተደራጀው ። እርግጥ  ኢትዮጵያ 80 ቦታ እንዳትቆራረጥ የአማራ  በአማራነት መደራጀት ይጠቅማል  የሚል ሃሳብ በምሁራን ዘንድ አለ  ። በዘር እና በቋንቋ መደራጀት እና የፖለቲካ ፖርቲ መሆን በህግ እሥካልተወገደ ጊዜ ድረስ አማራ በአማራነቱ በወጉ መደራጀት ግዴታው ነው ።

ይህን የምለው  በሚገባ የተደራጀ እና የታጠቀ ከ 20 ሚሊዮን የማያንስ ወጣትና ጎልማሳ አማራ ካለ ማንም ጉልበት አለኝ ብሎ በዘር   የተደራጀ እና የታጠቀ ህዝብ ሊጨፈጭፈው  እንደማይችል ሥለተገነዘብኩ ነው ። ይህም ብቻ አይደለም እንደ ጨው ዘር በመላው ኢትዮጵያ የተበተነው እና በጋብቻ የተዋለደው  ህብር  ኢትዮጵያዊ ዜጋ ( ጎሣዬ፣ነገዴ፣ብሔር ብሔረሰቤ ... ይኼነው ለማለት የሚቸገር ፤ ልክ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ልጆች  የበዙ ዜጎችን  አማራ ክልል ካለው ጋር   ሥትደምሩ ኢትዮጵያ በፍፁም ልትበታተን እና ሥሞ ሊጠፋ ከቶም እንደማይችል ትገነዘባላችሁ ። ) ሲደማመር  የአማራ ህዝብ ብዛት  በትንሹ  ከ 45  ሚሊዮን በላይ ይሆናል ። …. እናም  ይህ ትልቅ ህዝብ የኢትዮጵያ መመኪያ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ።

ከዚህ እውነት አንፃር ህዝብን ከህዝብ ጋር ከማጫረስ ፤ ወንድምና እህታማማቾችን ፈጣሪ በፈጠረውና ነገ በሚቀበሩበት መሬት የእኔነው እያሉ እንዲጫረሱ በማድረግ ፤ በህዝብ እልቂት አትራፊ እሆናለሁ  በማለት በቀቢፀ ተሥፋ ከመዳከር ይልቅ ፣ ቆም ብሎ በማሰብ ፣ ለእውነተኛ ፍትህ በመወገን ፣ በዛ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ከሸፍጥ ነፃ የሆነ ህዝበ ውሳኔ ቢደረግ መልካም ነው ። ከህዝቡ ውሳኔ በፊት ሸፍጡ ከቀደመ እና ፖለቲካዊው  ሤራ ከተጫጫሰ  ተመልሰን ወደማጡ መግባታችን እና እንደአገርም ክፉኛ እንደምንጎዳ ከወዲሁ መገንዘብ ይኖርብናል ።

ኧኩኩሉ !?

                      መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

" ፀረ ለውጥ ! "  ነህ ብትሉኝም_እኔ ግን አይደለሁም ፤

በትላንት አቋሜ ላይ ነኝ ትግሌን ፤   አላቋረጥኩም ።

በቀቢፀ ተሥፋ ከእናንተ ጋር አልቦዝንም

እያልኩ “ኩኩሉ  ! አልነጋም ! “

በከንቱ ጊዜዬን አልገድልም ።

“ በነጋ ! አልነጋም ! “ …

ዘላለሜን በጨለማ ውሥጥ  አልዳክርም ።

በነጋ አልነጋም የድበብቆሽ ጫዋታ

ሁሉም በየነገዱ ተደብቆ ሲያምታታ

እያየው ነው ዛሬም ከ27 ዓመት በኋላ

የሰው ልጅ እንደአውሬ እየዘረፈ ሲበላ ።

" ፀረ ለውጥ ! "  ነህ ብትሉኝም ፤

እኔ  ግን አይደለሁም ፤

በለውጥ አቋሜ ላይ ነኝ  ፤ ትግሌን አላቋረጥኩም ።

የምረካ አይደለሁም   በቁሥ ክምር በመሥከር

የአኩኩሉ ጫዎታችሁ ቢቆም ከምር እደግፋችሁ ነበር ።

ድብብቆሽ ጫዎታ ውሥጥ ሆናችሁ ፤ ኩኩሏችሁ ካላባራ

አልነጋም ወይ እያለ ህዝብ ብርሃን ለማየት ሲጣራ

አንደበቱ ሞት ጠራበት በቋንቋው ሥላወራ

የአኩኩሉ ጫወታው ለካ ደብቋል  ቢላዋና ካራ ።

" ፀረ ለውጥ ! "  ነህ ብትሉኝም_እኔ ግን አይደለሁም ፤

በለውጥ  አቋሜ ላይ ነኝ ፤ ትግሌን አላቋረጥኩም ።

የምረካ አይደለሁም እንደ ጎሰኞች  ቁሥ በመከመር

የአኩኩሉ ጫዎታችሁ ቢቆም ፤ አብሬ በቆምኩ ነበር ።

ለውጥነው አትበሉኝ ፤ ከቶም ባልተለወጠ ነገር

ፖለቲካውን እሥከ አንገት ተዘፍቃችሁበት በዘር

ለውጡ  ሁሉን አቃፊ  አሣታፊ ተራማጅ  ሥትሉን ነበር ።

ኧረ እንዲህ ነው እንዴ የመደመራችሁ  ነገር ?

" ፀረ ለውጥ ! "  ነህ ብትሉኝም_እኔ ግን አይደለሁም

በለውጥ አቋሜ ላይ ነኝ _ ትግሌን አላቋረጥኩም ።

የምረካ አይደለሁም እንደ ጎሰኞች  ቁሥ በመከመርየአኩኩሉ

ጫዎታችሁ ቢቆም ፤ አብሬያችሁ በቆምኩ  ነበር ።

ለጅብና ለአህያ ፤

ለነብርና ለሚዳቋ ፤

ለአይጥና ድመት ፣

ለእባብና ገበሎ ...

ለአራዊት እና እንሥሣ ሁላ

ፈፁም ምቹ የሆነ _ ለሰዎች በሟላ

በዘር እየከፋፈለ _ ሰውን ከሰው ጋር የማያጣላ ።

ቢሆን ኖሮ ለውጡ ያደረበት ፈርሃ እግዜር

የሚያኗኑረን በአንድነት _ ሰብዓዊ መብታችንን በማክበር

እኔም ከልቤ ለውጡን በደገፍኩት ነበር ።

" ፀረ ለውጥ ! "  ነህ ብትሉኝም_እኔ ግን አይደለሁም ፤

በለውጥ አቋሜ ላይ ነኝ _ ትግሌን አላቋረጥኩም ።

የምረካ አይደለሁም እንደ ጎሰኞች  ቁሥ በመከመር

የአኩኩሉ ጫዎታችሁ ቢቆም ፤ አብሬ በዘመርኩ ነበር ።

በቃል በወሬ ቀረ ፤ ትላንት የታቀደው  አሻጋሪ መርከብ

እርስ በእርስ ስንተላለቅ ፤ በጥይት ስንደባደብ ።

እኔም አዝኜ ማቅ ለበስኩ  ፤ እውነት በሐሰት ሥትቀበር

ወንድም ወንድሙን ገድሎ ሲያቅራራ ያለማፈር ።

" ፀረ ለውጥ ! "  ነህ ብትሉኝም_እኔ ግን አይደለሁም ፤

በለውጥ አቋሜ ላይ ነኝ _ ትግሌን አላቋረጥኩም ።

የምረካ አይደለሁም እንደ ጎሰኞች  ቁሥ በመከመር

የአኩኩሉ ጫዎታችሁ ቢቆም ፤ አብሬያችሁ  በታገልኩ ነበር ።

አብዮት ቢሆን ኖሮ አሉኩኝ አኩኩሉን የሚያሥቀር

እግዜር ያደረገው አይነት ከኖህ ጋር በትብብር ።

በሃቅ ፣ ሥለሃቅ በመቆም ፤ ኖህ እጅግ  ፀንቶ በእምነቱ

ያኔ ! ያኔ ! ድሮ !እግዜር ተቆጥቶ ፤ ዶፍ ሲያወርድ በፍጥረቱ

ዝናብን  ያለማቋረጥ  ሲያወርድ  በቀን እና  በለሊቱ

ኖህ ፣ አስቀድሞ አውቆ ነበር  ሥለ ሥር ነቀል አብዮቱ ።

ፍጥረታትም እንዳይጠፉ ሁሉን መርጦ በመርከቧ በማሳፈር

የራሱን ፃድቅ ወገኖችም በውስጦ በመደመር

በአብዮቱ እንዳይጠፉ በፈጣሪ መርከብ አስጠልሎ

ይኸው እሥከዛሬ አለን ህይወትን አሥቀጥሎ ።

ያኔ  በእግዜር አብዮት ፤   በሆነው እጅግ ሥር ነቀል

ፈጣሪ አቅዶ ነበርና አዲስ ትውልድ ለማብቀል

ፍጥረታቱ  እና  የኖህ ትውልድ በመርከቧ ተጠልሎ ተረፈ

የእግዚአብሔር አብዮትም በውሃ ፍጥረታትን ሁሉ ቀሰፈ ።

እናውቃለን  በዛ አብዮት ኖህ ዳቢሎስን በፀሎቱ ታግሎ እንደጣለ

ሰው ሁሉ ይጠፋል ያለው ሤጣን እራሱ  በኖህ መርከብ እንደተገደለ

እናውቃለን ፣ ኖህ ከፈጣሪ አብዮት ጋር ተባብሮ ህይወትን እንዳስቀጠለ ።

" ፀረ ለውጥ ! "  ነህ ብትሉኝም_እኔ ግን አይደለሁም ፤

በለውጥ አቋሜ ላይ ነኝ _ ትግሌን አላቋረጥኩም ።

የምረካ አይደለሁም   በቁሥ ክምር በመሥከር

የአኩኩሉ ጫዎታችሁ ቢቆም ፤  አብሬያችሁ በቆምኩ ነበር ።

 

 

የደራሲው ማስታወሻ

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Godmyc1955godmyc@gmail .com  አድራሻዬ ነው

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/181387

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...