Friday, March 24, 2023

ጆከሩን መዘው ፖለቲካዊ የፖከር ካርታ ጫዎታውን ጠቅላዩ አሥጀምረዋል - ሲና ዘ ሙሴ
ጠ/ሚ አብይ አህመድ ፣ ከረመዳን ፆም ቀድመው ፣ አዲስ ካርታ መዘዋል ። ጆከርን ። በአዲስ የፖለቲካ ቁማር ጫዎታ ብቅ ብለዋል ። ፆሙ በመግባቱ ዛሬ አላህ ልብ እንዲሰጣቸው እንለምንላቸዋለሁ ። መካሪ የሌለው ንጉሥ ሆነዋልና !

" የካርታ ፖለቲካ ወይም ፖለቲካዊ ፖከር "  በሚባል የማዘናጋት ፣ የማሳሳት ፣ ግልፅ ሐሳብን ያለማሳወቅ ፣ ዕድልና ብልጠትን አዋህዶ ቁማሩን የመጠቅለል ወይም የመብላት   ጫዎታ ጠቅላያችን  ብቅ እንዳሉ ፣ በትግራይ እና በአማራ ክልል ለመተግበር የፈለጉት ፖለቲካ በግልፅ የሚያሳብቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ   ። የዛሬው ፖለቲካዊ ቁማር ጫዎታ በየጊዜው ከተሰጡን አጀንዳዎች ሁሉ ረቀቅ ያላለ እንደሆነም ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም ። ካርታ ጫዎታ ገንዘብን አንድ ሰው ጠቅልሎ የሚወስድበት ፣ የአቋማሪና የቆማሪ ጫዎታ እንደሆነም ከህዝብ የተሰወረ አይደለም ። በዚህ የወገነ የፖለቲካ ቁማር ፣ ቆማሪዎቹና አቋማሪው የሚከብሩበት እንደሆነ ህዝቡ ያውቃል ። ( አሁን በዚች ሰዓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ሥንት ፐርሰንቱ እንደሚወዳቸው የመረጃ ሹማቸውን እሥቲ ይጠይቁ ። እውነቱን ከነገራቸው ካልደነገጡ ራሳቸው ሌሎችን የተሳደቡበት ሥድብ  ለራሳቸው እንደሚሆን ከወዲሁ ይገነዘቡት ። )

የእኛው ፣ የዛሬው ፖለቲካዊው ፖከር “ ስፔድስ “  ከተሰኘ የካርታ ጫውታም ፍፁም የተለየ  ነው ። ይኽ ጫዎታ  በ1930ዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተፈለሰፈ የካርታ ጫውታ ነው ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በወታደሮች የሚዘወተር ጫወታ እንደነበር ይታወቃል  ።

ዛሬ እና አሁን ዓለም እየተጫወተ ያለው ጫዎታ ግን ፖከር ነው ። ይኽ ጫዎታ በመጀመሪያ የተፈለሰፈው በቻይና ነው ። በ9ኛው ክ/ዘ ።

ዘመናዊ የፖከር ጫዎታ ፣ የመጀመሪያው ዙር ቁማር የሚጀምረው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ተጫዋቾች ካርታ ታድለው ነው ። ጫወታው የሚጀምረው  ። ከዛም ካርታ በመሳብ ና ከአቋማሪው በመቀበል  የቁማር ውርርዱ   ይጧጧፋል ። በመደበኛ ፖከር እያንዳንዱ ተጫዋች እጁ ከሌሎቹ ተጫዋቾች ጋር ሲወዳደር ዋጋ አለው ባለው ባመነበት ካርታ   ጫዎታውን ይጀምራል ። እያንዳንዱ ተጫዋች በተራው ከፍተኛውን የቀደመውን የቁማር ውርርድ በጫዎታው ሰዓት ተወራርዶ እንደ ጫዎታው ፍሰት   ውርርዱን  ከፍ በማጦዝ ፣  ደጎስ ያለ ገንዘብ ሊያገኝ ይችላል ። ሁሉም ተጫዋቾች ወደ መጨረሻው  እየተንጠባጠቡ ይደርሳሉ ። ዙሩን አንድ ሰው ጠቅልሎት ቁማሩ  ያበቃል። ከአንድ ተጫዋች በስተቀር ሁሉም በየትኛውም ዙር ላይ ሊታጠፉ ወይም ከጫወታው ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ ። ከመጨረሻው የውርርድ ዙር በኋላ ከአንድ በላይ ተጫዋቾች በፉክክር ውስጥ ካሉ የካርታ ውድድር  ተካሂዶ ከፍተኛ ነጥብ ያመጣ ገንዘቡን ጠራርጎ ይወስዳል ።

ከዚህ ጋራ በተመሳሰለ በህብረት እስከ አምሥት ሰው  የሚጫወተው   የካርታ ጫዎታ አይነት አለ ። ያው ፖከር ነው ። 13  ካርታ ሰጪው ያድላል ። ካርታ አዳዩ ከአምስቱ ከፍተኛ ካርድ የደረሰው ሰው ነው ። 13 ካርድ ለአራቱ ተጫዎቾች ከማደሉ በፊት በደንብ ያሰባጥረዋል ( Paw ያደርገዋል )

ከዛም ለእርሱ አ14 ካርድ ይወስድና በየመልካቸው አሥተካክሎ አነሥተኛ ዋጋ ያለውን እና የማይጠቅመውን ካርታ ይጥላል ። በሥተቀኙ ያለው ተጫዎችም ካርታው ከጠቀመው አንስቶ ይወርዳል ። ወይም ሊዘጋ ይችላል ። በአጋጣሚ የተሰራ ካርታ ሊደርሰው ይችላልና ! ….

በዚህ ጫዎታ ብዙ ሴራዎች ፣ አሻጥሮች ፣ ከቁማሩ ጠረጴዛ ጀርባ ድርድሮች ሊኖሩ ይችላሉ ። ያላወቀ የገንዘብ እንጂ የህሊና ቱጃር ያልሆነ በወጥመዱ ይገባል ። አንድ ሁለቴ ያስበሉታል ። ( ይዘጋል ) ከዛ በኋላ ያልቡታል ። የነቃ ሲመስላቸው አንድ ሁለቴ እየሰጡ ያዘጉታል ። ኮድ አላቸው ። በአይን ይጠቃቀሳሉ ። አውቀው ይጣላሉ ። ደጋግሞ የሚዘጋውን ይሳደባሉ ። ያሽሟጥጣሉ ። ታላቢው በዚህም ይሸወዳል ። ይኽ ጫዎታ ከእኛ ፖለቲካዊ ሴራ ጋር ይመሳሰላል ። ካርታ ተጫዎቾቹን እንደ ፖለቲካ ፖርቲ ዓባላት ተጠሪዎች ውሰዷቸው ። የማዕከላዊ ኮሚቴ ዓባላት አድርጓቸው ። ወዘተ ። ሊሆኑም ይችላሉ ።

ፖከር የካርታ ጫዎታ ከ 20 ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ተወዳጅነት ያገኘ እልህ የሚያሲዝ   ቁማር ነው ።  ዛሬ በትንሽ የአድናቂዎች ቡድን ብቻ ​​ተወስኖ ከመቅረት ወደ መላው ዓለም ተሰራፍቶ ከመዝናኛነትም ከፍ ብሎ ለተሳታፊዎች በኢንተርኔት አማካኝነት በቀጥታ አሳታፊ ህኖ ተመልካቾችንም  ጭምር የሚያዝናና የካርታ ጫዎታ ሆኗል ። አቋማሪው  ብዙ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች በማሳተፍም  በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያንቀሳቀስበታል ።

በእኛ አገር  እየተካሄደ ያለውን በመንግሥት ደረጃ እየተከናወነ ያለውን ቁማር የጋሃዱ ዓለም "ፖለቲካዊ ፖከር " ብዬዋለሁ ። ይኽ ፖለቲካዊ ቁማር ጫዎታ አጫዎቹና መጨረሻ ጠቅላዩም አንድ ሰው ነው ። የፈለገውን ካርታ በተገቢው ጊዜ በሁነኛ ሰዓት ፣ በተመቸ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ይመዛል ። ጆከር ፣  ጦር ፤ ልብ፣ ዳይመንድ ፣ ፍላዎር ፣ ...ኬሻ፣ሸሌ፣ወለድ ...23456789... ። እንደ አሥፈላጊነታቸው በወቅቱ መዘዝ አርጎ ያሰልፋቸዋል ። ለምሳሌ ዛሬ  ከሁለት እስከ አሥር  የቲዲኤፍ ጀነራሎችን ከአብይ ጎን ናቸው ። አንድ ጦር ፣   ጀነራል ታደሰ ወረደ ነው ።  ወለድ  ልብ ፣ (   ጄ ) ፃድቃን ገብረተንሣይ ነው ። ሞጆሪኖ ኪው ጦር ናት ። ኬሻ ዳይመንድ  ወይም ኬ ፣ ደብረፅዮን ገ/መድህን ነው ። ጆከር ደግሞ ጌታቸው ረዳ ነው ። የትም ብታሥገባው የመሆን ችሎታ አለውና !

እናም በዚህ የፖለቲካ ፖከር መሠረት አቋማሪው   የኢትዮጵያ  ጠ/ሚ አብይ ጌታቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት ማድረጋቸው ተገቢ ይመሥለኛል ። በፖለቲካዊ ፖከር ሊበሉት ያሰቡት ቁማር አለና !

ይህንን " ራያ  የተወለደ  ጆከር ሰውዬ  ፕሬዝዳንት በማድረግ የቁማሩን ካርታ መዘው ጠረጴዛው ላይ ሲያሥቀምጡ ግባቸው የታወቀ ነው ።  የካርታ ጫዎታ እንደ ቼዝ ማሰብን ቢጠይቅም ብልጠትና ዘዴ ፣ የሌሎች ቁማርተኞችንም ቀልብ መሥረቅ ይጠይቃል ። እንግዲህ የእኛም ፕለቲካዊ ፖከር ተመሳስሎቱ እዚህ ላይ ነው ።

መና ከሰማይ የሚወርድልን ይመሥል " አይዞን ይህንን ዘመን ከተሻገርን ቅቤ በአፍንጫችሁ ይንቆረቆራል ። " ያሉን እነ ዳይቆን ዳንኤል ክብረትም ይህንኑ የሸፍጥ ፖለቲካ አይተው ነው ። ሰውያችን ጥሩ እያጎ ከጎኑ አሥቀምጧል ። በበኩሌ ጌታቸውና ዲያቆኑ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው ። ሁለቱም መተርተር ሆቢያቸው ነው  ። እንዴ ምን ማለት ነው ፣ አጠቃላይ ኑሯችን ሲዖል ሆኖ ሣለ “ ወደፊት  ዓለም በጎናችሂ ታልፋለች ። ላይፋችሁን ትቀጫላችሁ ። “ ማለት ። ...

እርግጥ ዲያቆን ዳንኤልና መሠሎቻቸው ፣ ኑሯቸው ቤተመንግሥት በመሆኑ የተርታውን ህዝብ ሥቃይ እና መከራ ላይገነዘቡ ይችላሉ ። ዛሬ ወላጅ ልጆቹን ለማኖር ፆሙን እያደረ እንደሆነ ማን በነገራቸው ! ...

በሁሉም ዜጋ ላይ ፣ የምግብና የትራንሥፖርት ዋጋ  በ2014 እና 2015 ዓ/ም  ውስጥ ብቻ በእጥፍ መጨመሩን እና ኖሮን ለመቋቋም እንዳልቻለ  እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ ። ጊዜያቸውን ያሳለፉት የጠቅላዩን መፅሐፍ እያረቱ በመሆኑ አጠቃላይ ኑሮቸው ቤተመንግሥት በመሆኑ  ። ሃቁ ግን ፣ በዓሉ ግርማ እንዳለው መኖርም መሞትም ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል ።

ሥቃያችን በዝቷል ። እውነታውን ላይቀይሩ፣በታሪክ ጥቁር መዝገብ መፃፋቸው ላይቀር ፣ ከህዝብ ልብ ውሥጥ መውጣታቸውን እያወቁ ፣ ዛሬም በኃይል መግዛት እንችላለን በማለት በቀቢፀ ተሥፋ ፣ ሃቀኛ ምሁራንን ማሰቃየታቸውን እና ማሰራቸውን ግን “ ጊዜው የእኛ ነው !” የሚሉ ደናቁርታት ቀጥለዋል ።

የመቀነሥ ትውልድ አፍርተው የመደመር ትውልድ ይሉናል ። ጥላቻን እየዘሩ ፍቅርን አጨድን ብለው ለማታለል ይቃጣቸዋል ። እያሠቃዩ፣ እያሰሩ ፣ እያሥራቡ ና እየገደሉ “ እንደ ኢየሱስ የፅድቅ ሥራ እየሰራን ነው ። “ ማለት የለየለት የፖከር ፖለቲካ ሤራ ነው ።

ነገ አፈር የሚሆነው ደንቆሮ አሽከራቸው ከጥበብ በመራቁ የተነሰ ፣ እንደ ድሮ የፊውዳል  እና የአምባገነኖች ገራፊ ፣  በትዕዛዛቸው መሠረት  ያለርህራሄ ዜጎችን እያሰቃየ ነው ። እነሱም ከቁማሩ ዛሬ የሚያገኙትን የገንዘብ ትርፍ እንጂ ነገ ለልጅቻቸው የሚያተርፉትን ሥድብ፣ ውርደትና መሸማቀቅ ዛሬ ላይ ሆነው አይረዱትም ።

በፖለቲካዊ ቁማራቸው ሳቢያ ሃቀኛ የኢትዮጵያ ልጆች በራሳቸው ቅኝ ገዢዎች ፣ በራሳቸው መንግሥት አሣር መከራ ቢያዩም ( ጎምቱ ጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱን ጨምሮ አያሌ የፖለቲካ እሥረኞች በቅኝ ገዢዎቻችን በየእሥር ቤቱ  እየተሰቃዩ ነው ።  )

በራሳቸው አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው እየተሸማቀቁ የሚኖሩ በ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች  ናቸው ። አለአግባብ እየታሰሩ በጉቦ የሚፈቱም በኦሮሚያ ክልል እንደበዙመ የአገሪቱ ደህንነት አያውቀውም ማለት አይቻልም ።   በተቀናጀ መንግሥታዊ በሚመሥል አፈና እየታፈኑ በሚሊዮን እና በመቶሺ እየከፈሉ ከእገታ የሚፈቱ ጥቂቶች አይደሉም ።

በየተቋማቱ ጉቦ እየሰጡ መብታቸውን የሚያስከብሩም ጥቂት ዜጎች እንዳልሆኑ ይታወቃል ። እንግዲህ ይኽን የመሣሠለ ግፍና የዳቦ ችግር በሰፈነበት ህዝብ ላይ ነው ጠቅላዩ ጆከር መዘው “ ጌቾ ምላሡን “ የትግራይ ጊዚያዊ መንግሥት ፕሬዘዳንት አድርጌዋለሁ ያሉት ። ከታላቅ ህቡ ድርድር በኋላ የተመዘዘች የፖለቲካዊ ፖከር ካርታ ናት ። ጆከሯ ። …

ግና ፣ “ ይኽም ያልፋልና “  ጊዜ አልፎ  ነፍሰ ገዳዮች፣ ዘራፊውች ፣ ጨካኞች ፣ አይጠረቄ ሥግብግብች ። ወዘተ ። ሁሉ በሰፈሩት ቁና እንደሚሰፈርላቸው ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም ። እሥከዛው ግን ግፉ ና ፖለቲካዊ ቁማሩ ይቀጥላል ። የኢትዮጵያ ህዝብም አሥቀድሞ ባወቀው ቁማር እንደማይበላ ቢያውቅም በብሥለት እና በብልሃት ከህዝብ ባነሰው መንግሥት እያዘነ የመንግሥትን ፖለቲካዊ የካራታ ቁማር በአንክሮ ይከታተላል ።
https://amharic-zehabesha.com/archives/180972

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...