Monday, February 27, 2023

የብልጽግና መንግስት ሆይ! 

የብልጽግና መንግስት ሆይ!


- የፌደራል መንግስትም የክልል አስተዳደር፣ የከተማ አስተዳደር ተጠያቂነት፣ ግልጽነት ጠፍተው፣ ሕዝብን ያማረሩ ጉዳዮች በየደረጃው ተበራክተው፣ በዲያስፓራ የሚገኘውን ኢትዮጵያውያን ለማማለል፣ ለመከፋፈል፣ ብሎም  የመንግስት ደጋፊ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ መመሪያ ለኤምባሲዎች ማስተላለፉ በሀገራችን ለሚፈጠሩና እየተፈጠሩ ለሚገኙ በርካታ ግዙፍ ችግሮች ፣ የመብቶች ጥሰቶች መፍትሄ አይሆንም። ለህወሃትም አልፈየደም ።


- በዓለም ዙሪያ የሚገኘው ዲያስፓራ አብዛኛው ምንም ጥቅም ሳይጠይቅ፣ከመንግሥት ዲፕሎማቶችበይበልጥ ሳይቀር ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ትንቅንቅ ያደረገው አደጋ ላይ የወደቀውን ሀገሩን ለመታደግ እንጂ ጥቅም ፈላጊ ቢሆን በህወሃት ዘመን ያደርገው ነበር:፡


- በውጭ አለም የሚገኘው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን መንግሥትን የደገፉት የለውጡ ጅማሮ ሀገርን ይታደግ ይሆናል በሚል ተስፋ: በጦርነቱም ሙሉ ድጋፍ የሰጠውም የሀገር ህልውና ከፍተኛ አደጋ ወድቆአል በሚል ጭንቀት፣ ካለፉ ስርአቶች የተወረሱና አዲስ የመጡም  የህገራችንን ውስብስብ ችግሮችና ችግሮቹን የደራረቡ ገፊ ምክነያቶች ስረ- ምክነያቶች  ብዙ ስራ ይጠይቃሉ ፣ መንግስት ግዜና ቦታ ያስፈልገዋል በሚል በመረዳት እንጂ ኢፍታሃዊ ህሊናን የሚያሳምሙ ደባወች ሕዝብ ላይ እየተፈጸሙ እንደሆነ ሳይታዘብ ቀርቶ አይደለም።


- ህገ ወጥነት፣ ኢ-ፍትሃዊነትን ኢ-ሰበአዊነት (ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከአስር ሺ ዜጎች በላይ  ማፈናቀል፥ በሺ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ፣ ህሙማንን ጨምሮ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከል፣ ዜጎች የአጼ ሚኒልክን ምስል የያዙ ቲ-ሸርቶች ሸጣችሁ፣ በሱቆች ሰቀላችሁ በሚል ማስፈራራት፣ ሱቆችን ማሸግ ፣ ወዘተ)፣ ቅጥ ያጣ ሌብነት፣ የስልጣን ብልግና ወዘተ እንዲሰፍን በሩን ከፍተህ ስድ ለቀቅህ።


- በሁሉም ብሄረሰቦች ፣ በነዋሪዎቿ ላብና ጥሪት የተገነባችው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንደዘረኛ ወራሪ በጉልበት ወደ አንድ ክልል ለመሰልቀጥ፣ ነዋሪዎች ድምጽ አልባ ተደረጉ  ፣ ማሸማቅቅ የእለት ተእለት ክስተት ሆነ ፣ መብትና ነጻነት መግፈፍ ፣ ቅጥ ያጣ ስግብግብነት ተስፋፋ።


- ይህን ሁሉ ግፍ እየተቀበለም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለመደው ትእግስቱና አስተዋይነቱ ከዛሬ ነገ የተሻለ ይመጣል መንግሥት ጩኸታችን ለቅሶአችንና ምሬታችን ይሰማል እያለ በጸሎትና በተስፋ እየተጠባበቀ ነበር። ግን መንግሥት ማዳመጥ አልፈለገም! አሁንም ፊቱን አዙሮ ልቡን ከፍቶ ግፉን ካላየና ሕዝቡን እያዳመጠ አቅጣጫውን ካላስተካከለ በእራሱም ሆነ በሀገራችን ላይ አደገኛ መዘዝ ያመጣል::


- መንግስት ሆይ! ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎች መልስ ስጥ፣ የመረጠህንም ሆነ ያልመረጠህን ሕዝብ በእኩል ዐይን እይ: የህግ የበላይነትን አክብርና አስከብር፣ ሕዝብን በፍትህና በእኩልነት አገልግል።


- ስለዚህ የብልጽግና መንግሥት ሕዝብን እንዲሰማ እንጠይቃለን! ከአድዋ ድል ቅድም አያቶቻችን አስተውሎ የምንማረው ብዙ አለ! ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

Neamin Zeleke
https://amharic-zehabesha.com/archives/180246

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...