Thursday, February 23, 2023

"ከህወሓት ተኮርጆና ከሻዕብያ አምባገነናዊ የሆነ የአስተዳደር ዘይቤ ጋ ተዳቅሎ፤ እንዲሁም በማኬያቬሊያዊ ፍልስፍና ታሽቶ የቀረበው እጅግ አደገኛው ስልት!!!"


 መሰረት ተስፉ (Meseret.tesfu@yahoo.com)

በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው የህወሓት ሰዎች ትግል ሲጀምሩ እንደ ዋነኛ አላማ አድርገው የተነሱት ቁጥር አንድ ጠላቶቻችን ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን አማራንና ኦርቶዶክስን በማዳከም ታላቋን ትግራይን መመስረት ነበር። ይህንንም በማኒፌስቷቸው አስፍረው ረዘም ላለ ጊዜ ሲሰሩበት ቆይተዋል። ትግሉ እየገፋ ሲሄድ ግን ደርግ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ታላቋን ትግራይን መስርተን በሰላም መኖር አንችልም የሚል እምነት ላይ ስለደረሱ በመጀመሪያው አላማቸው አልገፉበትም። እናም ከተቻለ ደርግን ጥለው ራሳቸው ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የሚቀጥሉባትን ኢትዮጵያ መፍጠር ካልሆነ ደግሞ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋ ተባብረው ደርግን በማስወገድ መጀመሪያ ይዘውት የነበረውን ትግራይን አገር የማድረግ አላማ ማሳካትን በቅደም ተከተል አስቀምጠው ተንቀሳቅሰዋል። ያም ሆኖ ግን ይህ እቅድ በምስጢር ተይዞ የቆየው በከፍተኛ አመራሮቹ እንጅ ከመካከለኛ አመራሮች ጀምሮ እስከተራ አባላት ያሉት ታጋዮች የሚያውቁት ነገር እንዳልነበር ከትጥቅ ትግሉ ራሳቸውን ካገለሉ የቀድሞ ታጋዮች ጋ ከነበረኝ ውይይት ለመረዳት ችያለሁ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው የህወሓት ሰዎች በዋግ እንዲሁም በበለሳ አከባቢ ይንቀሳቀስ ከነበረው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) ጋ ተነጋግረው ወደ መላው ኢትዮጵያ ለመጓጓዝ የሚያስችላቸውን ኢህአዴግ የሚባል ግንባር በይፋ ያቋቋሙት።

ህወሓቶች በዚህ መንገድ (በዋነኛነት ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ተደግፈው) አዲስ አበባን ጨምሮ ዋና ዋና የሚባሉ የኢትዮጵያን ክፍሎች ከተቆጣጠሩ በኋላ ከራሳቸው አመራሮች ውስጥ ምስለኔዎችን መልምለው በሁሉም ክልሎች ያሉ ፈረሶቻቸውን እንዲመሩ ላኳቸው። ወደተለያዩ ክልሎች ከተላኩት ውስጥም ሰሎሞን ፂሞ በኦሮሚያ እና ቢተው በላይ ደግሞ በደቡብ ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው። ታዳጊ የሚባሉት አራቱ ክልሎችም ቢሆኑ እንዲሁ ምስለኔዎች ተመድበውላቸው የሚተዳደሩት በነዚሁ ምስለኔዎች እንደነበር የሚታወቅ ነው። ፡ አማራ ክልልም በክልል ደረጃ ባይሆንም ክፍላተ ሃገራትና ዞኖች ላይ በልምድ ማካፈል ስም ምስለኔዎች ተመድበው ለአማራ ህዝብ መብት ይታገሉ የነበሩ ግንባር ቀደም ሃይሎችን ቢሮክራት እያሉ ሲያሳድዷቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ከሃያ ሰባት አመታት በዃል ግን በፌዴራሊዝም ስም የከፋፍለህ ግዛ መርህን በመከተል ሁሉም በእጃቸው ሁሉም በደጃቸው እንዲሆን ማድረጋቸው ያንገሸገሸው  ህዝብ እንዲሁም ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የብአዴንና የኦህዴድ አባል  ባካሄደው መራር ተጋድሎ ከትከሻው ላይ አሽቀንጥሮ ጥሏቸዋል። በእርግጥ በህዝብ ትግል ይንኮታኮቱ እንጅ አስተሳሰባቸው ግን አሁንም በሃገር ደረጃ ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲያውም አስተሳሰቡ በደንብ ተከሽኖና ከሻብዕያ ፍፁም አምባገነናዊ የአስተዳደር ስርዓት ጋ ተዳቅሎ እንዲሁም በማኪያቬሊያዊ (Machiavellian) ፍልስፍና ተለውሶ  በዶክተር አብይ መሪነት እየቀጠለ እንደሆነ ለመረዳት የግድ የተለየ ስጦታ ያለው ሰው ሆኖ መፈጠርን አይጠይቅም።

ሁላችንም እንደምናውቀው የህወሓት ሰዎች የአስተሳሰብ ስሪት የተመሰረተው በአማራ ህዝብ እና በኦርቶዶክስ እምነት ጠልነት ላይ ነበር። የኦሮሞ ብልፅግናዎችም ቢሆኑ ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንዳላቸው በሚያሳይ መልኩ አማራ ህዝብ ላይ እንዲለጠፉ የተደረጉ “ነፍጠኛና የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚሉ ቃላቶችን በመጠቀም ስለጉዳዩ ምንም የማያውቀውን ሰፊውን የአማራ ህዝብ ለማሸማቀቅና አንገት ለማስደፋት ሲሞክሩ እየሰማንና እያየን ነው። አማራ ቅኝ ገዝቶናል ብለው ስለሚያስቡም በተራችን እኛ መግዛት አለብን የሚል አስተሳሰብ አንግበው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም በተደጋጋሚ ታዝበናል። እንዲያውም ለሶስት ሽህ አመታት ስለተገዛን እኛም ለሚቀጥሉት ሶስት ሽህ አመታት መግዛት ይኖርብናል እያሉ በየመድረኩ የሚደሰኩሩ በጠቅላይ ሚ/ር አማካሪነት ደረጃ ሳይቀር ተቀምጠው እንደነበር ሊካድ የሚችል ሃቅ አይደለም።

ይህን በተመለከተ እነአቶ ለማ፣ እነጃዋር፣ ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና መሰል ልሂቃን ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም። ልዩነት አላቸው ከተባለም ማን ስልጣን ይዞ ያልተገደቡ ፍላጎቶቹን በምን ፍጥነት ይፈፅም በሚሉት ጉዳዮች ላይ ብቻ ይመስለኛል። በዚህ ረገድ እነአቶ ለማ የኦሮሞ ህዝብ ቆጥሮ የሰጠንን ጥያቄዎች በአስቸኳይና አሁኑኑ በአዋጅ መመለስ አለብን የሚል የፀና አቋም እንዳላቸው ስልጣን ላይ እያሉ ሲያወጧቸው ከነበሩ መግለጫዎቻቸው መገንዘብ ይቻላል። ይህንን አቋማቸውን ለመረዳት የዴሞግራፊውን ጉዳይና “የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ እየሰራንበት ነው” የሚለውን መግለጫቸውን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው።

ዶ/ር አብይ ግን የነአቶ ለማን መንገድ ቢመርጥ አደጋ እንዳለው በመረዳቱ ከነሱ ጋ የተስማማ አይመስልም። ምክንያቱም ዶ/ር አብይ በነአቶ ለማ መንገድ ቢጓዝ “ሆ” ብሎ እየደገፈው ያለውን የአንድነት ሃይል ነኝ የሚል የህብረተሰብ ክፍል ሙሉ በሙሉ ሊያጣው እንደሚችል በደንብ ተረድቷል። አይደለም የነአቶ ለማን መንገድ በግልፅ መርጦ በድብቅ እየፈፀመ ባለው የሴራ ፖለቲካ ምክንያት እንኳ አያሌ ደጋፊዎችን እንዳጣ በሚገባ ተረድቷል። ስለዚህ የዶ/ር አብይ መንገድ ለዘብ ያለ፣ በጣፋጭ አማርኛ የተለወሰ፣ ሰው መስማት የሚፈልገውን እንጅ ሳት ብሎት ካልሆነ በስተቀር እሱ እንዲሆን የሚመኘውን የማይገልፅ፣ ንግግሩና ተግባሩ አብዛኛውን ጊዜ የሚጣረስና የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚደንት ከነበረው Harry S. Truman የቀዳውን “Convince or Confuse” ዘዴ ተጠቅሞ ከቻለ ሌሎችን በማሳመን፣ ካልሆነ በማደናገር፣ ይህ ካልተቻለ ደግሞ በማስፈራራትና ሃይል በመጠቀም የራሱን ቡድን የበላይነት በሌሎች ላይ መጫን እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ይህን ለማወቅ “በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ጦርነት እንከፍታለን”፣ የአዲስ አበባን ህዝብ ከመጤፍ ባለመቁጠር “መርንግስታችን ተነካ ብሎ “የሰበታና የሱሉልታ ህዝብ ግልብጥ ብሎ ወደ ቤተመንግስት ሊመጣ ነበር፤ አዲስ አበባ ላይ እጅግ ከግተኛ የሆነ የኦሮሞ ጥላቻ አለ የሚሉና ሌሎች መሰል ንግግሮችን በደንብ ማጤን ጠቃሚ ነው።

ከላይ በተገለፀው የአካሄድ ልዩነት ምክንያት እነአቶ ለማ በያዙት የተቻኮለ አቋም የረጅም ጊዜ ድብቅና በሴራ የተሞላ ግብ ሊያደናቅፉ ነው የሚል ስጋት በመፈጠሩ ምክንያት እስከመቸ እንደሆነ ባይታወቅም ከፖለቲካ ገለል እንዲሉ መደረጋቸውን ታዝበናል። ምክንያቱም ዶ/ር አብይ በሚከተለው ማኪያቬሊያዊ አስተሳሰብ ስሌት መሰረት ውጤቱ የተሳካ እንዲሆን በሂደቱ የቱንም ያህል አሰቃቂ ቢሆንም ማንኛውንም አይነት እርምጃ መውሰድ ተቀባይነት ያለው አሰራር ነውና። ከነአቶ ለማ ፖለቲካዊ መገለል በኋላ እነዶ/ር አብይ የኦሮሞ ህዝብ ቆጥሮ ሰጠን ያሏቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ያስችለናል ያሉት ብልፅግና ፓርቲን ነው። ምክንያቱም ልክ ህወሓት ኢህአዴግን ፈረስ አድርጎ እንደተጠቀመበት ሁሉ ዶ/ር አብይም “ብልፅግና ፓርቲ”ን እንደፈረስ እየተጠቀመበት እንደሆነ በአቶ ሽመልስ በኩል በድብቅ ባስተጋባው መልዕክቱ እንድናውቀው አድርጎናል ብየ አምናለሁ።

እዚህ ላይ ብልፅግና ፓርቲ ተጠፍጥፎ የተሰራው በዶ/ር አብይ መሆኑን በሚገባ መረዳት ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ። ሰው አንድን ነገር ሲሰራ ደግሞ የሚያወጣው ስሙን ብቻ ሳይሆን ይዘቱንም ጭምር ነው። ስለዚህ አቶ ሽመልስ የተናገረው ሁሉ በዶ/ር አብይ የተጠነሰሰ እንደሆነ ለመረዳት የሚከብድ ነገር ያለው አይመስለኝም። በሌላ አነጋገር አቶ ሽመልስ የዶ/ር አብይ አፍ እንጅ የሃሳቡ አመንጭ አይደለም ማለት ነው። ለማንኛውም በአቶ ሽመልስ ሲገለፅ የሰማነው ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረው በዋነኛነት የኦሮሞን ጥቅም ለማስከበር እንደሆነ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቅኝ ገዝቶናል የሚሉትን አማራን ማዳከም እንዳለባቸው አቶ ሽመልስ ካደረገው ንግግር መረዳት ይቻላል።

አማራን ለማዳከም እየተጠቀሙባቸው ካሉት ስልቶች ውስጥ ደግሞ አንደኛው ትግርኛ፣ ሶማልኛና አፋርኛ የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ማድረግን ነው። ይህን ያደረጉት አማርኛ ቋንቋን በማዳከም አፋን ኦሮሞ ጎልቶ እንዲወጣ ለማድረግ እንጅ ለተጠቀሱት ብሄሮች መብት መከበር ብለው እንዳልሆነ አቶ ሽመልስ ባደረገው ንግግር በግልፅ ጎልቶ ተቀምጧል። በሌላ በኩል የተለያዩ የኢትዮጵያ ዋና ከተማዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ሃገራዊና አለማቀፋዊ ትኩረት ሳቢነቷን በመቀነስ አማራ ተቆጣጥሯታል የሚሏትን አዲስ አበባን የመዋጥ ሌላ እቅድ እንዳለም ዶ/ር አብይ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ በኩል አስነግሯል። በዶ/ር አብይ እምነት ኢትዮጵያ የተለያዩ ዋና ከተማዎች የሚኖሯት ከሆነ የሃገር ውስጡም ሆነ የአለም አቀፍ ማህብበረሰብ በአዲስ አበባ ላይ ያለው ትኩረት ስለሚቀንስ ያኔ ዴሞግራፊውን በመቀየር ህዝበ ውሳኔ አካሄዶ ከተማዋን ለመጠቅለል ያለመ መንገድ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም።

ዴሞግራፊውን መቀየር ባይችሉ እንኳ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ እንዲኖራቸው በሚሰሩበት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት (Veto Power) ተጠቅመው እንዲሁም ታዳጊ ክልሎችን አድናግረውም ሆነ አስፈራርተው በድምፅ ብልጫ አዲስ አበባን የሴራቸው ሰለባ ሊያደርጓት እንደሚሞክሩ ለመገመት ከባድ አይደለም። እዚህ ላይ አቶ ርስቱ ይርዳው አዲስ አበባን በተመለከተ ከኦሮሞ ብልፅግና ጋር ብንወግን ነው ጥቅማቸን ሊከበር የሚችለው ሲል የተናገረውን ማስታወስ ተገቢ ነው።  ዶ/ር አብይ ስለአዲስ አበባ ሲጠየቅ የሚመልሰው ልክ እንደ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ሃዋሳ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ነች የሚል እንጅ በተለየ መንገድ የኢትዮጵያውያንና የነዋሪዎቿ መሆኗን ገልፆ የማያውቅ መሆኑንም ማስታወስም ምን ያህል በሴራ የተሞላ ስራ እየፈፀመ እንደሆነ ለመረዳትም ጠቃሚ ይሆናል።

ሌላው ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው መሰረታዊ ነገር ደግሞ ዶ/ር አብይ በፈጠረው የብልፅግና ዘመን ኦሮሞ ወይም ኦሮሞ ያልፈቀደለት ማንም ሌላ ሃይል ሃገር ሊመራ እንደማይችል እንዲሁ አቶ ሽመልስ ባደረገው ንግግር የተካተተውን ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ የሆነ ምኞት ነው። ለዚህ እንዲያመች ደግሞ የኦሮሞ ብልፅግና ፈረሶች በአብዛኛዎቹ ክልሎች እንዲቀመጡ ተደርገዋል። ሁኔታዎችን ልብ ብሎ ለታዘበ ሰው ይህን እውነታ ለመረዳት ይከብደዋል ብየ አላስብም። ምክንያቱም የብዙዎቹ ክልሎች ፕሬዚደንቶች በዶ/ር አብይ ይሁንታ የተመደቡ ናቸው። በዚያ ላይ በተለይ ታዳጊ ክልሎችን የሚያስተዳድሩት አመራሮች ከሚመሩት የህዝብ ቁጥር ማነስና ባለባቸው የአስተዳደር ልምድ እጥረት ምክንያት የሃገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ይዟል ብለው ከሚያስቡት ቡድን ጋ እንደሚለጠፉ ከህወሓት ጋ የነበራቸውን የቀረበ ግንኙነት አይቶ መገመት አይከብድም።

ስለዚህ ዶ/ር አብይ የኦሮሚያ ብልፅግናን ሰዎችና በየክልሉ ያሉ ፈረሶቹን ድምፅ ተጠቅሞ የሚፈልገውን ሁሉ ለማስፈፀም ጥረት ማድረጉ የሚቀር አይሆንም። ምናልባት እንኳ የታዳጊ ክልሎቹ አመራሮች የሴራ ፖለቲካውን ተረድተው ለህሊናቸው መቆም ቢጀምሩ ዶ/ር አብይ ከአቶ ኤሳያስ የቀሰመውን አምባገነናዊ ባህሪና ማኬያቬሊአዊ አስግተሳሰቡ ምክንያት ፍላጎቱን በሃይል ሊጭንባቸው አይሞክርም ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል።

ለማጠቃለል ያህል ዶ/ር አብይና እሱ የሚመራቸው የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች ይህን ሁሉ የሴራ እና የሽንገላ ፖለቲካ የሚያራምዱት (አይሳካላቸውም እንጅ) ልክ የህወሓት ሰዎች እንድደረጉት አማራውን አዳክመውና አንገት አስደፍተው (ወይም በ’ነሱ ቋንቋ ሰብረው) የራሳቸውን ቡድን የበላይነት ለመጫን ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ለመገንዘብ ከባድ አይደለም። አንዳንዴም አቶ ሽመልስ በድብቅ ካደረገው ንግግር ሾልከው ከወጡት ውጭ ያሉ በአማራው ላይ የመቆመር እቅዶች እየተቦኩና የማጥቂያ ሰበቦች እየተሸረቡ እንደሆነ የሚያሳዩ ፍንጮችን እያየን ነው።  በተለይ ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጦርነት በኋላ መከፋፈል የተለመደ ነው ማለቱ፤ አሁን ከህወሃት ጋር በነበረው ጦርነት ሊያጀግነው የፈለገው ሃይል መኖሩና እንዲሁም በደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪርና በተቀናቃኙ ሪክ ማቻር፤ በኬኒያው ኡሁሩ ኬኒያታና በተፎካካሪው ራይላ ኦዲናጋ መካከል ስለሚስተዋሉት ልዩነቶች ሲጠቅስ ምን እያሰበ እንዳለ ለመረዳት የሚከብደው ካለ መፈተሽ ያለበት ራሱን ነው።

ታዲያ ምን ይሻላል ከተባለ  ዶ/ር አብይና እሱ የሚመራቸው የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች ይህን ሁሉ ያረጀ ያፈጀ ምናልባትም በህወሓት ሰዎች ተሞክሮ ያከሸፈ ሴራና ሸር ከማጠንጠን ይልቅ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል ሊያደርግ የሚችል ፍትሃዊ፣ ግልፅ፣ ተቋማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት ለመገንባት ጥረት ማድረግ ይሆናል መልሱ። ቀላሉ መንገድም ይሄው ነው።

በሌላ በኩል በዶ/ር አብይ ለጆሮ የሚጥሙና አማላይ የሆኑ ሽንገላዎች/ማታለያዎች እምነት አድሮባቸው ወይም ተደናግረው ካልሆነም በጥቅም ምክንያት እሱን ከኢትዮጵያዊም በላይ ኢትዮጵያዊ በማድረግ unconditional የሆነ ድጋፍ እየሰጡት ያሉት በተለይ የአንድነት ሃይል ነን የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቆም ብለው ሊያስቡ ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ላሰምርበት እፈልጋለሁ። ይህም ማለት ዶ/ር አብይ ጥሩ ሲሰራ መደገፋቸው አንድ ነገር ሆኖ አገር መቀመቅ ውስጥ የሚያስገባ ስራ ሲሰራ ጭምር ሽምጥ እየጋለቡ ግፋበት ከማለት ወጥተው ወደ ትክክለኛው ህዝባዊና ሃገራዊ መንገድ እንዲገባ ግፊት ቢያደርጉበት ይሻላል ባይ ነኝ። ካለበለዚያ አሁን የያዙት መንገድ “ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆመው ማውረድ” የማይችሉበት ደረጃ ሊያደርሳቸው እንደሚችል ቢገነዘቡ መልካም ነው እላለሁ። ያኔ መፀፀትም ሆነ ፀጉር መንጨት እንወዳታለን ለሚሏት አገርም ሆነ ለህዝቦቿ የሚፈይደው አንዳችም ነገር አይኖርም።

ለማንኛውም ላሁኑ በዚህ ላብቃና በቀጣይ ደግሞ ዶ/ር አብይና እሱ የሚመራቸው የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች ሌላውን የኢትዮጵያ ክፍል አሳምነው፣ አደናግረው ወይም አስገድደው ከጎናቸው  በማስለፍ (አይሳካላቸውም እንጅ) ያው የፈረደበትን አማራ አንገት አስደፍተው የራሳቸውን የበላይነት ለመጫን ያላቸውን ቀቢፀ ተስፋ እውን ለማድረግ ምን ምን አይነት የማጥቂያ ምክንያቶችን/ሰበቦችን እያማተሩ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልከታዎቸን ለማጋራት እሞክራለሁ።

ከነዚህ ውስጥ መጀመሪያ ለማጋራት የምፈልገው ይወልቃይትንና የራያን ጉዳይ እንደ ካርድ ሊጠቀሙ ይሞክሩ ይሆናል የሚለውን አንኳር ነጥብ ነው። በተለይ ወልቃይት (ምንም እንኳ ለጊዜው ወደትግራይ እንዲካልለል ላይፈልጉ ቢችሉም)  በፌደራል መንግስቱ ስር መሆን አለበት የሚል እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ግልፅ የሆነ ትንኮሳ እስከመፈፅም ሊደርሱ እንደሚችሉ ለማሳየት እሞክራለሁ።

እስከዚያው መልካም ጊዜ።

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/180107

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...