Friday, February 17, 2023

አንዱ ዓለም ተፈራ

ሐሙስ፣ የካቲት ፱ ቀን ፪ ፻፲ ፭ ዓ. ም.

 

በቅድሚያ በአገራችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተፈጠረው የውስጥ ችግር ተፈትቶ ዕርቅ መደረጉና ውጥረቱ መርገቡ ደስ የሚያሰኝ ነው። ይኼ የጉዳዩ መጨረሻ ነው ወይ? የሚለውን ውለን አድረን የምናየው ይሆናል። ለጊዜው ግን ቢያንስ በቤተክርስትያኗ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል። ይህ በፖለቲካው ዙሪያ ባሉት መካከል ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል? ሌላው ጥያቄ ነው። ይህ በዚህ እንዳለ፤ የአገራችንና የቤተክርስትያኗ ትልቁ ችግር ይህ የቤተክርስትያኗ የውስጥ አሰራር ብቻ እንዳልነበረ መረዳት አለብን። አሁን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ኃላፊነቱን ከተረከበ በኋላ፤ አንድ ጊዜ አንድ ጉዳይ፣ ሌላ ጊዜ ሌላ ጉዳይ እየተነሳ፤ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸው አልፏል። ለምን? ነገ የሚከተለውስ ጉዳይ ምን ይሆን? በዚህ ጽሑፍ ያሰፈርኩት፤ መንግሥት የሠራዉን ወይንም ያልሠራውን መመርመርና ማውገዝ ሳይሆን፤ ጠቅለል ባለ መልኩ ለሌሎቻችን መልዕክት ማስተላለፍ ነው።

እስካሁን የተከሰቱት ጉዳዮች ምንድኖች ናቸው? ለምን ተነሱ? እኔ የምጽፋቸውን ለሚከታተሉ መልዕክቴን መገመት አይከብዳቸውም። ከኔ ክልል ውጣ! ወደ አዲስ አበባ አትገባም! የኔ ክልል ደንበር ትክክል አልተሰመረም! እኛም የራሳችን ክልል ይኑረን! ኡእራሳችን የሃይማኖት ክፍል ይኑረን! በቋንቋችን ይሄ ይደረግልን! ያ ይደረግልን! የኛ የበላይነት ጥግ የለውም! የሥራ ፈላጊው ቁጥር እየበዛ ሥራ ግን አልተፈጠረም! የተነሳንበትን ጉዳይ ሕገ-መንግሥቱ ይፈቅድልናል! የመሳሰሉት ናቸው። እኒህን ሁሉን የሚያያይዛቸው ምንድን ነው? ይህ ነው መታየት ያለበት። እንዲያው እያንዳንዱን እየለዩ ቢያባጥሉት፤ መልሶ መልሶ! ይሆናል። ይህ ሁሉ ባንድ ላይ ሲሰበሰብ፤ የአገርን እንደ አገር መቀጠል ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ጉዳይ ነው። እናም የአገርን ጉዳይ መመልከቱ ዋና የአሁን ጥያቄ ነው። አንዳንዶች በአንዱ ጉዳይ ተጠምጥመው መፍትሔ ለማግኘት ይሯሯጣሉ። ለማንኛውም ጉዳይ መፍትሔ መሻቱና ማግኘቱ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን፤ ከላይ የደፈረሰን ፈሳሽ ከታች እናጥራው ቢሉ፤ ለድካም ከመዳረግ ሌላ ትርፉ ባዶ ነው። እናም ከመንግሥት ሥልጣን ውጪ ያለን፣ በአገራችን ያለውን የፖለቲካ ሀቅ የተረዳን፣ አደጋውን ተረድተን የመፍትሔው አካል መሆን የምንፈልግ፣ ኢትዮጵያ ነገ ቀጥላ ለወደፊቶቻን እንድናተርፋት ከፈለግን፤ መምከር አለብን። በኢትዮጵያ ያለው አንገብጋቢ ጥያቄ፤ የአንድ ጎሳ፣ የአንድ ሃይማኖት፣ የአንድ አካባቢ፣ የአንድ ተበዳይ፣ የአዲስ አበባ፣ የወልቃይት፣ የራያ፣ የጉራጌ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የጉጂ፣ የሲዳማ፣ የተነጣጠለ ጉዳይ አይደለም። የአገር እንደ አገር መቀጠል ወይንም አለመቀጠል ነው።

ይሄ ግራ የሚያጋባ ነው። ኢትዮጵያ አለች! ለወደፊቱም ትኖራለች! በሚል ግትር የተፈጥሮን ሕግ በውል የማይመለከት ጭፍን እምነት የተሰለፉ አሉ። ይሄን በቀላሉ የታሪክ መዝገብን በማገላበጥ መረዳት ይቻላል። ከኢትዮያ የገዘፉ ታላላቅ አገሮችና መንግሥታት ፈርሰው ዛሬ የሉም። ገናናዎቹ የግሪክ፣ የሮማ፣ የሞንጎሊያ፣ ፀሐይ አይጠልቅበትም የተባለው የእንግሊዞች አገር(ከደሴቷ በስተቀር)ና መንግሥታት፤ በታሪክ መዝገብ ብቻ ነው ያሉት። ትናንት ዩጎዝላቪያ ነበረች። ዛሬ ስሟን ከመጽሐፍ በማገላበጥ እንጅ፤ በዓለም ካርታ ላይ አያገኙትም። ኢትዮጵያ የተለየች አገር አይደለችም! እኛ ካልጠበቅናት ሌላ ጠበቃ የላትም። በሃይማኖት ለሚተማመኑት፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት በሙሉ የፈጣሪ አገራት ናቸው። ያዳላል ካላልን በስተቀር ሁሉም አገራት አንድ ናቸው። ኢትዮጵያዊያንንም ከሌሎች አብልጦ ወይንም አሳንሶ አይመለከትም። እናም ኢትዮጵያ ከሌሎች አገር የተለየ ምንም ነገር የላትም። ያሏት እኛ ብቻ ነን። እኔ አንድ እግሬን ወደ መቃብር በመስደድ ላይ ያለሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኢትዮጵያን ግን በታትኜ ለማለፍ ዝግጁ አይደለሁም። ሌሎች ሲያፈርሷት ደግሞ፤ እነሱ ናቸው ብዬ እጄን በሌሎች ላይ ልጠቁም አልፈልግም። የራሴ ኃላፊነት አለብኝ። የኢትዮጵያዊነትና የትውልድ ኃላፊነት አለብኝ። ይሄን ከመወጣት አኳያ፤ ኃላፊነቱ ከሚሰማቸው ጋር በኢትዮጵያ እንድ አገር መቀጠል ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ።

ከላይ የዘረዘርኳቸውና ሁላችን የምናውቃቸው ጉዳዮች መሠረታቸው፤ ወንበሩን ለሌሎች እንዲለቅ ተገዶ የተባረረው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጥሎት የሄደው ሕገ-መንግሥትና፤ በቦታው አስቀምጦ እንዲወርስ ያደረገው መንግሥታዊ መዋቅር ነው። ይህ አገራችንን ወደ መፈራረስ እየወሰዳት ነው። በምን መንገድ ይሄ እንዳይሆን መከላከል ይቻላል? ምናልባት በሥልጣን ላይ ያሉት፤ እኛ በትክክል እየመራናት ነው! ብለው ሊምኑ ይችላሉ። አልፈርድባቸውም፤ በሚያውቁት የሚያውቁትን እያደረጉ ነው። ጥያቄው፤ ከነሱ ውጪ ያለነው፤ ያለውን ተጨባጭ ሀቅ ተረድተን፤ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ወይ? ነው። የፖለቲካ ፓርቲ፣ የዝመናና ሥልጠና ጉዳይ፣ የልማትና የማደግ ጉዳይ፤ ቦታ ቦታ አለው። አሁን አገር የማዳን ጉዳይ ሁሉን ጨፍልቆ ስለመጣ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ መምከሩ ግድ ነው እላለሁ። በተለያዩ ድርጅቶች የተሰባሰባችሁ ሁሉ፤ ይሄ ዋና ጉዳይ ነው ብላችሁ ካመናችሁ፤ ይሄ ጥሪ ከየትም ይምጣ ከየት፤ የራሳችሁ ጥሪ ነው። እናም እናንተም ጥሩት ሌላው፤ መሰባሰቡ አጣዳፊ ነው። ይህ ለነባር ታጋዮች ወይንም ለነገ ተረካቢዎች የተደረገ ጥሪ አይደለም። ለማንኛውም ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን ለማዳን ለሚሻ ሁሉ ነው። ይህን ማድረግ፤ የገንዘብም ሆነ የጉልበት አቅም አይጠይቅምና እኔ እገፋበታለሁ። አለን የምትሉ ጥሩኝ፤ እገኛለሁ። ነገ ለመቆርቆር ጊዜ አይኖረንም። ዛሬ ኢትዮጵያ በንጥልጥልም ብትሆን ባለችበት ደረጃ እንድረስላት።

eske.meche@yahoo.com

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/179860

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...