Thursday, February 16, 2023

የተቆለፈበት ቁልፍ ! ከዶ/ር ምህረት ደበበ፣ የአዕምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት፣ 438 ገጽ ትችት! -  በዶ/ር ፈቃዱ በቀለ
ከዶ/ር ምህረት ደበበ፣ የአዕምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት፣  438 ገጽ  ትችት!  በዶ/ር ፈቃዱ በቀለ፣ የስልጣኔ ተመራማሪና የኢኮኖሚ ዕድገት ባለሙያ !

የካቲት 17፣ 2023

ይህን መጽሀፍ አግኝቴ ለማንበብ እድል ያጋጠመኝ ባለቤቴ ወደ ኢትዮጵያ ሄዳ ስትመለስ ይዛልኝ ከመጣች በኋላ ነው። በዶ/ር ምህረት ደበበ የተጻፉ ሁለት ወፈፍራም መጽሀፎች ሲሆኑ፣ አንደኛው መጽሀፍና በቅርብ የወጣውን የሽፋኑ ሰዕል ደስ ስላለኝ እንደ አጋጣሚ አንስቼ ካገላበጥኩኝ በኋላ፣ እስቲ ብዬ ደግሞ ሌላውን ሳገላብጥ አቀራረቡ ደስ ስላለኝ  ሃሳቡን ይበልጥ ለመረዳትና ለመገምገም ሆነ ወይም ለመተቸት እንዲያመቸኝ በሚል በመጀመሪያ ያገላበጥኩትን በመተው ቀደም ብሎ የታተመውን ማንበብ ጀመርኩኝ። እንደ ዕውነቱ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ የሚመጡ በአማርኛ ቁንቋ የተጻፉ መጽሀፎችን ትንሽ ካገላበጥኩኝ በኋላ ምንም ስለማይጥሙኝና አብዛኛዎችም ዝም ብሎ ትረካና የህብረተሰባችንን ህሊናዊ አወቃቀርና፣ በዚያም አማካይነት በመሬት ላይ የሚታየውን ህያው በሆነ መልክ ለመተንተንና እንድንረዳው የሚያደርጉ ስላይደሉ በንባቤ አልገፋባቸውም። የስነ-ጽሁፍም ዋና ዓላማ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉትን አስቀያሚም ሆነ ቆንጆ ነገሮች ስዕላዊ በሆነ መልክ መግለጽ ሲችሉና አንባቢውን በልዩ ሃሳብ ውስጥ ተመስጦ እንዲዋኝ ማድረግ ሲችሉ ብቻ ነው። ከዚህ አኳያ የዶ/ር ምህረት ደበበ መጽሀፍ ልዩና አንባቢዉን በሃሳብ ባህር ውስጥ ገብቶ እንዲዋኝ የሚያደርግና፣ የአገራችንን ነባራዊም ሆነ የህዝባችንን ህሊናዊ አወቃቀር ግሩም በሆነ መልክ የሚያቀርብ በታሪካችን ውስጥ በመጀመሪያ ጊዜ በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀና የተጻፈ ትምህርታዊ መጽሀፍ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። የመጽሀፉ አርዕስትም ካለምክንያት የተመረጠ ሳይሆን፣ ለአንድ የተቆለፈበት ነገር መፍትሄው በአዕምሮ ውስጥ ያለ ቁልፍና፣ ለአንድ ህብረተሰብ መዘበራረቅና ስነ-ምግባር መበላሸት ደግሞ የጭንቅላት መቆለፍ ወይንም የአዕምሮን የማሰብና የመፍጠር ኃይል ለመገንዘብ ካለመረዳት ጋር የተያያዘ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ጸሀፊው የኖይሮ ባዮሎጂ ሊቅ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ሙያ ባልሰለጠነ ከማንኛውም ምሁር የሚበልጥ ግንዛቤ ስላለው፣ የአዕምሮን ልዩ ልዩ ባህሪዎች የበለጠ የተገነዘበና፣ በመጽሀፉ ውስጥ ደረጃ በደረጃ ቲያትራዊ በሆነ መልክ ያቀረበ ነው። በመጽሀፉ ውስጥ የተዘረዘሩት ልበ-ወለድ ስሞች ባህርይና ድርጊት በእርግጥም የማንኛውም ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆኑ፣ የጠቅላላው የዓለም ህዝብ ባህርይ ሲሆኑ፣ በሌላ ወገን ግን ባደገና በሰለጠነው የካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖረው ግለሰብም ሆነ ህዝብ ከማቴሪያላዊ ዕድገት ጋር በተያያዘ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ለየት ያለ መሆኑን መረዳት ይቻላል።  ደራሲው በሁለት በተለያዩ አገሮች የኖረና፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር በመሆኑ በሙያው እዚያው በመሰማራት፣ በሁለት አገሮች ያለውን የዕድገት ልዩነት በንጽጽራዊ መልክ በማወዳደር ማቅረቡ አጠቃላይ የሆነ ማቴርያላዊ ዕድገትም ሆነ ዕድገት በቀጨጨበት ዓለም ውስጥ የሚኖር ህዝብ ስለሰው ልጅም ሆነ ስለተፈጥሮ  የተለያየ አስተሳሰብና ግንዛቤ እንዳላቸው ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።  ወደ መጽሀፉ መሰረታዊ ሃሳብና የአሰራር ስልት ላይ ደረጃ በደረጃ ልምጣበት።

የትዕይንቱ ዋና ተዋንያን መላኩና ሰሎሜ ሲሆኑ፣ ሁለቱም ለየት ያለ የማህበረሰብ መሰረት(Social Background)  ያላቸውና፣ በአስተሳሰብም የሚራራቁ አይደሉም። ከሁለቱ ተዋንያን ባሻጋር፣ በመጽሀፉ ውስጥ ልዩ ልዩ ባህርያት ያላቸው ስዎች ተካተውበታል። ጥሩ አመለካካት ያላትና መላኩን እንደታናሽ ወንድሟ አድርጋ ያሳደገችውና ለቁም ነገር እንዲደርስ የረዳችው፣ የህሊና ስፔሻሊስት የሆነችው ዶ/ር ሳራ፣ የስሜቱ ተገዥና የሚያደርገውን በትክክል የማያውቀው ምንተስኖት የሚባለው የዶ/ር ሳራ ባል፣ ቀና አመለካከት ያለው፣ ራሱን ከተንኮል ያፀዳውና በራሱ ጥረት ከታች በመነሳት ከፍተኛ ቦታ የደረሰው ማርቆስ የሚባለው የመላኩ የቅርብ ጓደኛ፣  የስሜቷ ተገዢ የሆነችና፣ የራሷን ጥቅም ለማግኘት ስትል ምንም ነገር ከማድረግ የማትመለሰውና በተንኮል የተካነችው ስንክሳር የምትባል ሴት፣ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸውና ብዙ ነገሮችን ማገናዘብ የሚችሉት የሰሎሜን አባትና እናት፣ አቶ ኦላናና ባለቤታቸው፣ መንፈሱ ቆንጆ የሆነውና በልጅነቱ የበሰለ አስተሳሰብን ያዳበረው የሶሎሜ ወንድም፣ ሶለን የሚባለው፣ በልጅነቷ ብዙ ስቃይን ያሳለፈችውና በእናቷ ግሪክ፣ በአባቷ ደግሞ ጥቁር አሜሪካዊ የሆነችው መንፈሷ ቆንጆ የሆነና የሰዕል ስጦታ ያላት ሶፊያ፣ የኩላሊት በሽታ ስፔሺያሊስት የሆነውና፣ የኩላሊትን በሽታ ከማከም በስተቀር በጭንቅላቱ ውስጥ ሌላም ብዙ ዕውቀት የሌለውና፣ ለመኖር ብቻ የሚኖረው፣ ክብሮም የሚባለው፣ እነዚህ ሁሉ እንደየባህርያቸው በመጽሀፉ ውስጥ በመካተት ለመጽሀፉ የንባብ ጣዕም  የሰጡት ናቸው ማለት ይቻላል።  ደራሲው እንደዚህ ዐይነት የተለያየና የተዘበራረቀ አመለካከት ያላቸውን ስዎች በልበ-ወለዱ ውስጥ ማካተቱና መቃኘቱ የሚያመለክተው የቱን ያህል  የህብረተሰብአችንን የተበላሸ ማቴሪያላዊ መሰረትና የህዝባችን የተዘበራረቀ የህሊና አወቃቀር እንደገባው ነው። ወደ ዋናው ተዋንያን ወደ መላኩና ሰሎሜ ጋ፣ እንዲሁም የሰሎሜ ቤተሰቦች ጋ በመምጣት የደራሲውን አመለካከትና፣ ስለሰው ልጅ ያለውን ግንዛቤና፣ እንዲሁም ይህ ጉዳይ ስለ አንድ ህብረተሰብ ዕድገትም ሆነ ፀረ-ዕድገት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖና አስተዋጽዖ ጠጋ ብለን እንመልከት።

መላኩ በአባቱ የአፋር ሰው ሲሆን፣ አባቱን ፈጽሞ አያውቀውም። ስለሆነም መላኩ አባቱ በሌለበት መቂ ከተማ አክስቱ ቤት የተወለደ ሲሆን፣ በእናቱና በአክስቱ አለመግባባት የተነሳ እናቱ አዲስ አበባ መጥታ አስር ዐመት እስኪሞላው ድረስ አሳድጋው በድንገት በመኪና አደጋ ሞተች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኑሮው ስቃይና ትምህርቱን በስርዓት ይከታተል አይከታተል የሚቆጣጠረው ዘመድ አልነበረውም። አጠገቡ ያለውም አጎቱ ሊረዳው የሚችል አልነበረም። መላኩም በኑሮው የተጎሳቆለ ስለነበር የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ይስቁበት፣ ይሳለቁበት ነበር።  እናቱ ተቀጥራ ትሰራ የነበረበት መስሪያቤት አለቃ የነበሩት ወይዘሮ የትናየት የሚባሉት እንዳጋጣሚ በመንገድ ላይ ሲሄዱ፣  መላኩ አንድ ቀን ውሃ በባልዲ ተሸክሞ ሲሄድ አሳዝኗቸው እያዩት ጠጋ ብለው በመጠየቅ የማን ልጅ እንደሆነ ለማረጋጋጥ ይችላሉ።  የሚኖርበትን ሁኔታም እስከቤቱ ድረስ ሄደው በማየት ወስደው እሳቸው ጋር እየኖረ ያስተምሩት ዘንድ አጎቱን ይጠይቁታል። በስነ-ስርዓት መላኩን መከታተልና ማሳደግ ያልቻሉት የመላኩ አጎትና ባለቤቱ፣ እንዲያውም ጎርምሶ እስቸግሮናል በማለት በመሄዱ መስማማታቸውን ለወይዘሮ የትናየት ይነግሯቸዋል።   መላኩም ወይዘሮ የትናየት ቤት በሳቸው የመጨረሻ ልጅ ሳራ በምትባለው  እየታገዘ ትምህርቱን በመከታተል ጎበዝ እየሆነ መጣ። ማትሪክንም አልፎ የህክምና ትምህርት በመከታተል ላይ ሳለ ደስ ስላላው ለሳራ ሌላ ዐይነት ትምህርት ለመማር እንደሚፈልግ ይነግራታል። እንደ ወንድም የረዳቸውና ያሳደግችው ሳራም እንግሊዝ አገር የመማር ዕድል አገኘችለት። እንግዝሊም የኢኮኖሚከስ ትምህርቱን በመከታተል ላይ እንዳለ ይበልጥ ያደላ የነበረው ፍልስፍና፣ ታሪክና የስነ-ልቦና  መጽሀፎችን በማንበብ ነበር። የኢኮኖሚክስ ትምህርቱን እንደዋና አይመለከተውም ነበር። ይህ በዚህ እንዳለ አንድ ካናዳዊ ዝንባሌውን በማየት ረድቶት፣ ካናዳ፣ ቶረንቶ ሄዶ እዚያ ትምህርቱን የመከታተል ዕድል አገኝለት። መላኩም የማስተር ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋለ ዶክትሬቱን ለመስራት ዕድል ቢያገኝም አገሬ ውስጥ ብዙ ያልተሰራ ነገር አለ በማለት በመመለስ አገሩን ለመርዳት ቆርጦ ተነሳ። እንደተመለሰ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ያገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መስሪያቤት ውስጥ ነው። እዚያም አንድ አራት ዐመት ያህል ከሰራ በኋላ መስሪያቤቱ የሰውና የገንዘብ ጠር ነው፣ ጥቂቶችን የሚያደልብና ድህነትን የሚያጠናክር ነው በማለት በግልጽ የሚታይ አነስ ያለ መስሪያቤት ውስጥ ተቀጥሬ ብሰራ ይሻላል በማለት ብዙ ገንዝብ የሚያገኝበትን መስሪያቤት ጥሎ በመውጣት ሌላ ቦታ ተቀጥሮ መስራት ይጀምራል።  እንዳጋጣሚ ወይዘሮ  የትናየት ቤት ማደጉና፣ እንደ እህትም እየተከታተለች ታስረዳውና ታስተምረው የነበረችው ሳራና፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለፍልስፍና፡ ለታሪክና ለህሊና ሳይንስ የነበረው ዝንባሌና፣ የተፈጥሮን ምንነት ጠጋ ብሎ ለመገንዝብ የነበረው ጉጉት ባህርይውንና ስለሰው ልጅ ያለውን አስተሳሰብና፣ ስለ አጠቃላይም ህብረተስብአዊ ዕድገት ያለውን አመለካከት መቅረጻቸው የማይካድ ለመሆኑ የልበ-ወለዱን አቀራረብ ለተመለከተ ሊገነዘበው ይችላል።

ሁለተኛዋና እንደሱው ዋናው ተዋናይ የሆነችው ሰሎሜ ደግሞ የተሻለ የህብረተሰብ መሰረት ካላቸው ቤተሰብ ውስጥ የተወለደች ስትሆን፣ ከአስራአንድ ዐመቷ ጀምሮ ከቤተሰቦቿ ጋር አሜሪካን አገር በመሄድ ትምህርቷን እዚያ  የተከታተለችና፣ በጥሩ ቤተሰብአዊ  አስተዳደግ በፍቅር ያደገችና፣ ስለሰውም ልጅ ያላት ዝንባሌ ከመላኩ ጋር የሚመሳሰል ነው። ሰሎሜ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ እንደዚሁ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትንና ሴተኛ አዳሪዎችን መልሶ የማቋቋም፣ በውጭ ሰዎች የሚደጎም የገብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ  መስራት ጀመረች። እዚያ ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ወዲህ፣ ይህ ዐይነቱ በህፃናት ላይ የሚደርሰው ግፍና፣ ካለ አሳዳጊ ጎዳና ላይ ተጥሎ ለማኝ መሆንና፣ በትንሹ በትልቁ እንደ ቆሻሻ ዕቃ መታየትና፣ በሴተኛ አዳሪዎችም ላይ የሚደርስባቸው ግፍ እየከነከናት በፍጹም ልትቀበለው የማትችለውና፣  እንደ ህብረተሰብአዊና እንደ ተፈጥሮ ህግ ሆኖ መታየት እንደሌለበት መገንዘብና፣ ይህንንም መዋጋት እንዳለባት ቆርጣ ተነሳች። ደራሲው ቁልጭ አድርጎ እንደሚተነትነው፣ ሶሎሜ እየደጋገመች የምታነሳው ጥያቄና መልስም ለማግኘት የሚያስጨንቃት፣ የሰው ልጅ ለምን ደሃ እንደሚሆን ነው። ለድህነት መንስዔ  የሚሆነው ምክንያት ምንድነው ? ድህነት ከህብረተሰቡ የአኗኗር አወቃቀርና አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ወይስ ዋናው ምክንያት ሌላ ነገር ነው? የሚለው ጥያቄ ያብሰለስላታል። እንደደራሲው አተናተን፣ “ .... አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃን ወይም ሴተኛ አዳሪ ችግራቸውም ሆነ ማንነታቸው ከህብረተሰቡ ሁኔታ ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን፣ የተሳሰረና የተጠላላፈ ነው፣“ የሚለው መደምደሚያ ላይ እንደደረሰች ደራሲው በግሩም ብዕሩ ያረጋግጣል።  ሰሎሜ ጥያቄን በመጠየቅና መልስም ለማግኘት የምትጨነቅ ብቻ አይደለቸም። ለሰው ልጅ ሁሉ ፍቅር አላት። ደሃ፣ ሀብታም፣ ቆሻሻ ልብስ የለበሰ፣ ወይም የዘነጠ፣ ለአንዳንዶች አስቀያሚ የሆነ ወይም የአካል ጉድለት የደረሰበት፣ ለሷ የሰው ልጅ ሁሉ አንድ ነው። አንዱ ከሌላው እንደማይበልጥ ነው የምትገምተው። አንዳንዶች፣  አንዱን ሰው ቆንጆ ነው፣ ሌላውን ሰው ደግሞ አስቀያሚ ነው ሲሉ ግራ ይገባታል። የሰውንም ልጅ የምትለካው በለበሰው ልብስ ወይም „መልኩ በማማሩ“ ሳይሆን፣ በመንፈሱ ቁንጅናነትና፣ ስለሰው ልጅ ባለው አመለካከት ብቻ ነው። ለሷ የሰው ልጅ ሁሉ ሰው ነው። አንዱ ከሌላው የሚበልጥበት ወይም የሚያንስበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ዕምነቷ ነው። አንድ ቀን ከመላኩ ጋር ተቀጣጠረው እሱን ለመጠበቅ ስትል አንድ ቡና ቤት ውጭው ላይ ትቀመጣላች። አንድ በፍጥነት የሚበር ታክሲ በአካባቢው ቆመው የሚለምኑ ሽማግሌ ገጭቶ ከወደቁበት ሳያነሳቸው ዝም ብሎ እየነዳ በፍጥነት ያመልጣል። የሽማግሌውን መውደቅና የደረሰባቸውን መጠነኛ ጉዳት የተመለከተችው ሰሎሜ በፍጥነት በመሄድ ከወደቁበት አንስታና ደግፋ በመውሰድ ቡና ቤቱ በራፍ ላይ ያለው የቡና ቤት መቀመጫ ላይ እንዲቀመጡ ታደርጋለች። ይህንን የተመለከተችው የቡና ቤቱ አሳላፊ ወደ ሰሎሜ ጋ በመምጣት ቡና ቤቱ እንደዚህ ዐይነት ቆሻሻ ልብስ የለበሱና የተጨራመቱ ስዎችን ማስተናገድ እንደማይችልና፣ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችም ደንበኞቿን እንደሚያባርሩባት ቦታውን ለቀው እንዲሄዱ ታመናጭቃቸዋልች። ሶሎሜም በአሳላፊዋ አነጋገር በመገረምና በመናደድ፣ ለምን እንደዚህ እንደምታስብና፣ ይህም ሊሆን እንደማይችል፣ የቡና ቤቱ ባለቤት መጥቶ እንዲያነጋግራት ለአሳላፊዋ ትነግራታለች። ይህ ሊሆን እንደማይችልና፣ እሷ ራሷ እንደምትወስን በመጨቃጨቅ ላይ እንዳሉ የቡና ቤቱ ባለቤት ውስጥ ሆኖ ይመለከታቸው ስለነበር ውጭ ወጥቶ ጉዳዩን ለማጣራት ከሰሎሜ ጋር ይነጋገራል። ሰሎሜም ነገሩን ካስረዳችው በኋላ ሁለቱም ብዙም ሰው የሌለበት ቦታ  ቡና ቤቱ ውስጥ ገብተው እንዲቀመጡ ቦታ ይሰጣቸዋል። ሰሎሜም በመኪና አደጋ የተጎዱትንና በድህነት የተጎሳቆሉትን ሽማግሌ ምግብ አዛላቸው ከተመገቡ በኋላ በህይወት ዘመናቸው አግኝተው የማያውቁትን ብዙ ገንዘብ አሽክማ ትሸኛቸዋለች። ደራሲው እዚህ ላይ ለማመልከት የሞከረውና በትክክልም እንዳስቀመጠው አብዛኛው ህዝብና፣ በተለይም ደግሞ በትንሽ ዕውቀት ጭንቅላቱ ለብ ለብ ያለው  ስለደሃና ቆሻሻ ልብስ የለበሰ ሰው ላይ ያለውን  የተዛባ አመለካከት ነው። የደራሲው አገላለጽ በአገራችን ውስጥ በተለይም ኤሊት ነኝ የሚለው ጭንቅላቱ ውስጥ የተንሰራፋውን የተወላገደና፣ ለህብረተሰብ ዕድገት ጠንቅና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ  ስለሰው ልጅ ያለንን የተዛባ አመለካከት ለማሳየት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ቀን መላኩና ሰሎሜ በመኪና ወደ ቦሌ አቅጣጫ እየነዱ ሲሄዱ የትራፊክ መብዛት በፍጹም አላንቀሳቅስም ይላቸዋል። ሰሎሜም በመገረም መላኩን ትጠይቀው የነበረው፣ ለመሆኑ አዲስ አበባ ማለት ቦሌ ብቻ ናት ወይ ? ለመሆኑ ለምን እዚህ አካባቢ ብቻ መኪናና ሰው በአንድ ላይ እየተጋፉ ይሄዳሉ ? እያለች ትጠይቀው ነበር። በተለይም ትላልቅ የቤት መኪና ይዞ የሚነዳውን ጎልማሳ ስትመለክት ስለሰው ልጅ ደንታ የሌለው ብቻ ሳይሆን መንገዱ ሁሉ ለሱ ብቻ የተሰራ ይመስል መንገዱን ሲያስጨንቅና በሰው ላይ ለመጋለብ ስታይ በጣም ያበሳጫታል። በተለይም የመንገድ አሰራሩ በደንብ ታቅዶና ለሰው ልጅ ታስቦ ባለተሰራበትና፣ የእግረኛ መሄጃ፣ መኪና ነጂዎች ልጆች ላይ አደጋ እንዳያደርሱ ተብሎ ልዩ መሄጃ መንገድ ባልተሰረባትና፣ የቢስኪሌትና የአውቶብሶች መሄጃ ልዩ መስመርና መንገድ በሌለበት ከተማ ውስጥ በሰው ላይ የሚደርሰው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ደራሲው በደንብ በመገንዘብ በጥሩ ብዕሩ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።

ሰሎሜ በስራዋ ላይ እያለችና ከመላኩ ጋር ያላቸውን ግን ደግሞ በግልጽ ወጥቶ ያልተመነዘረውን ፍቅርና ግኑኝነታቸውን  በማውጣትና በማውረድ ላይ እያሉ፣ አባቱና እናቷ፣ እንዲሁም የሰሎሜ ሁለት ወንድሞች የሚኖሩበት ከቺካጎ ከተማ ከሷ በሁለት ዐመት ከፍ የሚለው ታላቅ ወንድሟ ሶለን ላይ ሽጉጥ ተተኩሶበት ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበትና ሆስፒታልም ገብቶ በመታከም ላይ እንደሚገኝ፣ በፍጥነት ወደ ቺካጎ መምጣት እንዳለባት በስልክ ይነገራታል። ጉዞዋን ወደ አሜሪካ ከማቀናቷ በፊት ግን ከመላኩ ጋር በመገናኘት፣ እሷ የምታሳድጋቸውን የሷ አክስት ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት፣ ገና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆችን  መላኩ እንዲከታተላቸውና  በማንኛውም ነገር እንዲረዳቸው አደራ ብላ  ጉዞዋን ወደ አሜሪካ ታቃናለች። የሷ ወደ አሜሪካን መሄድና በመላኩና በሰሎሜ መሀከል ያለው መፈላለግና ውስጣዊ ፍቅር ሳይወጣ ሁለቱም እንደሚዋደዱና እንደሚፋቀሩ ስሜታቸውን ሳይገልጹ መሄዱ ልበ-ወለዱን በጉጉት እንድናነበው ይጋብዘናል። በሌላ ወገን ግን የልበ-ወለዱ ዋና መልዕክት፣ ይህ በሁለት ሰዎች ያለውን በጾታ ላይ የተመሰረተ ፍቅር ለማሳየት ሳይሆን፣ ዋና ዓላማው ሁለት በአስተሳሰብ የሚገጣጠሙ ፍቅረኞች ስለህበረተሰብአቸው ኋላ-መቅረትና አገራዊ መዝረክረክና የሰው ልጅም ኑሮ በዚህ መልክ መሄድና መታየት እንደሌለበት የግዴታ በአዲስ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሁለገብና አጠቃላይ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ለማመልከት ብቻ ነው።

ሶሎሜ ሁለት ታላላቅ ወንድሞች ሲኖራት፣ በተለይም  የሁለት ዐመት ዕድሜ ከሚበልጣት ሶለን ከሚባለው ታላቅ ወንድሟ ጋር በጣም ይዋደዳሉ።  ቤተሰቦቿ የዲቪ ዕድል አግኝተው አሜሪካን በመሄድ ኑሮአቸውን እዚያ የመሰረቱ ናቸው። የሰሎሜ አባትና እናት የሚከባበሩና ልጆቻቸውንም በስነስራዓት ያሳደጉ ሲሆኑ፣ የስሎሜ አባት የጊዜንና የገንዘብን አጠቃቀምን በደንብ የተገነዘቡና፣ ካለምክንያት የሚባክን ገንዘብና ጊዜን በስርዓት አለመጠቀም ያበሳጫቸዋል።   „ገንዘብ የጊዜ ምንዛሬ ነው፤ ጊዜም ያልተመነዘረ ገንዘብ ነው“ የሚል ፍልስፍና አላቸው በማለት ደራሲው የኑሮ ፍልስፍናቸውን ያስረዳናል። ፍልስፍናቸው ከዚህ ርቆ በመሄድ በአጠቃላይ ስለ አንድ ህበረተሰብ ዕድገት ያላቸውን አመለካከት፣ ልጃቸው ለአደጋ ከመጋለጡ በፊት፣ ከልጃቸው ከሶለን ጋር ክርክር ወይም ውይይት በሚያደርጉበት ጊዜ ጣል ጣል የሚያደርጉትን አስተሳሰብ ለተመለከተ የአገራቸው ኋላ-ቀርነት የሚያስጨንቃቸው እንደሆነ ከልበ-ወለዱ መገንዘብ ይቻላል።  እንደዚሁም ሶለን የአባቱን ፈለግ በመከተል ስለሰው ልጅ ያለው አመለካከት በወጣትነት ጊዜው የዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከያዙትና በዕድሜም ወደ ስድሳና ወደ ሰባ ዐመት ከሚጠጉት ጋር ሲወዳደር  ልቆ የሄደ መሆኑን ደራሲው በግሩም መልክ ያሰቀምጣል። በተጨማሪም የጥቁር አሜሪካንን የጭቆናና የስቃይ ትግል ታሪክ ያነበበና  የእነ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን ስራና የትግል እንቅስቃሴ ጠንቅቆ ያወቀ ስለነበር፣  አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከጥቁሮች ጋር ነው። ጥሩና ትችታዊ አመለካከት ያዳበረው ሶለን በተለይም አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች ራሳቸው ጥቁር ሆነው ጥቁር እንዳይደሉ፣ ጥቁር አሜሪካውያንን እነዚያ ጥቁሮች እያሏቸው ሲጠሩቸው በጣም ይገርመው ነበር፤ ይበሳጭም ነበር።  ይህም የሚያረጋግጠው የሶለንን የስባዊነት ባህርይና በዕውቀት የዳበረ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ተማርን፣ ረቀቅን ብለው ሌላውን ወንድማቸውን የሚንቁትን፣ የዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የያዙትን ስንትና ስንት እርምጃ እንደሚበልጣቸው ነው። በተጨማሪም ህብረተሰብአዊ ባህርይንና ሰብአዊነትን ያላካተተ፣ እንዲሁም ደግሞ ትችታዊ አመለካከት የሌለውና ስልጣኔ አጋዥ ያልሆነ የዶክትሬትነትና የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚበልጥ ከስነ-ጽሁፉ መረዳት እንችላለን።

ሰሎሜም ወንድሟን ለመጠየቅ ወደ ሆስፒታሉ ከሄደችና ወንድሟን ማጽናናት ስትጀምር፣ በመሀከሉ ብልጭ ያለባት ወንድሟ የተኛበትን ሆስፒታል እኛ አገር ካለው ጋር ስታወዳድር በጣም ነው የገረማትም፤ ያዘነችውም። ሁለም በሃሳብ ላይ እያሉ መጠየቅ የጀመረችው እንደዚህ በማለት ነበር:  „አንድ እንኳ እንደዚህ ዐይነት ሆስፒታል አገራችን ቢኖር ስንት ሰው ከሞት ይተርፍ ነበር ?“  እያለች ነው የህዝባችን መበደልና የአገራችንን ኋላ-ቀርነት የሚያብከነክናት። ሰለሆነም፣ ጥሩ ነገር ስታይ ይህም ነገር እኛም አገር ቢኖር ኑሮ በማለት ነው ምሬቷንና ብስጭቷን እንዲሁም ምኞቷን የምትገልጸው።  ስለ ዕድገት ያላትን የልጃቸውን አገላለጽና አስተያየት ጠጋ ብለው የሚያዳምጡት አባቷ አቶ ኦላና፣ ይህ ዐይነቱ በጥሩ መልክና ቆንጆ አካባቢ የተሰራ ሆስፒታል ከሌሎች ነገሮች ጋር ተነጥለው መታየት እንደሌለባቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ።  በሳቸውም ዕምነት፣ ይህ ዐይነቱ ሆስፒታል በአጠቃላይ ሲታይ ህዝቡ ወይም መንግስት ስለሰው ልጅ ያላቸው አመለካከት ለየት ያለና፣ ባህሉም የላቀ ስለሆነ የሰው ልጅ እንደ ዕቃ የሚጣል ሳይሆን የሚከበርም መሆኑን የሚያመለክት ነው በማለት ለልጃቸው ቀስ ብለው ያስረዷታል። እሷም የሳቸውን ነገር ሙሉ በሙሉ ሳትቀበል ይህ የግዴታ ከባህል ጋር ብቻ የሚያያዝ አለመሆኑን፣ ዱባይና ሪያድ ያሉትን በንጽህናና በአያያዝም የማይተናነሱትን ሆስፒታሎች እየተጠቀሰች ከኛው ጋር በማወዳደር „ደሃ ሁልጊዜም ደሃ ነው፤ አያልፍለትም“ እያለች ትነግራቸዋለች። ድህነት ተፈጥሮአዊ አለመሆኑ ስትናገር የነበረችው ሰሎሜ እዚህ ላይ ደግሞ ብዙም ሳታስብ ድህነትን እንደ ተፈጥሮአዊ እንደሆነና፣ ከባህል ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ለማስረዳት ትሞክራለች።  አቶ ኦላና ንግግሯን በደንብ ካዳመጡ በኋላ፣ የአረቦቹ ዕደገት ከጭንቅላት ተሃድሶና ከዕውነተኛ ስልጣኔ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከዘይት ሽያጭ የተገኘና፣ አንድ ቀን ዘይቱም ሲያልቅ የዶላርም እጥረት እንደሚኖርና፣ በድሮ ሁኔታቸውና የአኗኗር ስልታቸው ሊገፉበት እንደማይችሉ በሰከነና በጠለቀ መንፈሳቸው ረጋ ባለ መልክ ልጃቸውን ያስረዷታል። በሌላ አነጋገር፣ ዋናው የስልጣኔ ምንጭ በገንዘብ መደለብና መትረፍፈፍ ሳይሆን በጭንቅላት መዳበርና፣ ዕውቀትና ስልጣኔም ከጭንቅላት የሚፈልቁ መሆናቸውን ደራሲው በሚገርም ነገር ፕላቶናዊና ሶክራትሲያዊ በሆነ መንገድ ያስተምረናል። አቶ ኦላናም በመቀጠል፣ የጃፓኑንና የኮሪያውን ስልጣኔ ከአረቦቹ ጋር በማወዳደር ንጹህ በንጽሁ በአስተሳሰብና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣  ብዙ የአፍሪካ አገሮች የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብትና፣ ጥሩ አካባቢና አየር እያላቸው ባለማወቃቸውና መሪዎችም ስግብግቦችና የደነቆሩ ስለሆኑ ህዝቡ ደህ እንዲሆን አድርገውታል በማለት ያስረዷታል።

ሰሎሜም የአባቷን ግሩም አገላለጽ ከአዳመጠችና በመደነቅ፣ እንደኛ ያለው ህዝብ ታዲያ ድህነትን ለማስወገድ ከየት መጀመር አለበት ብላ? አባቷን በጥያቄ ታፋጥጣቸዋለች። በመቀጥልም፣ በልመና መኖር ስልችቶኛል፣ እስከመቼ ነው በልመና የምንኖረው?  እያለች የምሬቷን ትናግራለች።  በመሀከሉ ስልክ በመወደሉ የሰሎሜ እናት፣ እንደመሰላቸት በማለት እስቲ ወደ ስልኩ ጋ ልሂድ፣ የአንድ ሺህ ዐመት ችግር በአንድ ቀን ክርክር አይፈታም በማለት ለባለቤታቸውና ለልጃቸው ይነግሯቸዋል። አቶ አላናም ፣ „ የአንድ ሺህ ማይል ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል“  በማለት ቀልዳቸውን ጣል ያደርጋሉ። አቶ ኦላናም አፋቸውን ከጠራርጉ በኋላ ከየት እንጀምር ብለው ጥያቄ በማቅረብ፣ እዚያው  ካለንበት ነው መነሳት ያለብን በማለት ለልጃቸው ያስረዷታል። በመቀጠልም ችግራችንን ለመቅረፍና ስልጣኔንም ለማምጣት የግዴታ ያለንበትን ሁኔታ በሚገባ ማወቅ እንደሚያስፈልግና፣ ያለፈውን ትውልድም እንደተጠያቂ ማድረግ እንደማይቻል ደራሲው እንደ አቶ ኦላና በመመስል ልቆ በሄደው አስተሳሰቡ እጅግ በሚያሰደንቅ አገላለጹ ዕድገት ከየት መጀመር እንዳለበትና፣ ምንስ መመስልና ወዴትስ መጓዝ እንዳለበት ያስተምረናል። ስለዚህም ይላል ደራሲው፣ በአቶ ኦላና በመመሰልና ኋላ-ቀርነትና የጎታች ባህልን የዕድገት ጠንቅነት እያመለከተ፣ „ በየትኛውም ሥልጣኔ ውስጥ ፈር ቀዳጅና ፋና ወጊ ተብለው ለውጥ ያመጡ ሰዎች መጀመሪያ ወንጀለኛ፣ ከዚያም አሳሳች ተብለው መፈረጃቸው የተለመደ ነው። በእርግጥም እነዚህ ጥቂት ብርቅዬ ከዋክብት ከህብረተሰቡ በሰላሳና በአርባ ዐመት ቀድመው ወደፊት የሄዱ ስለሆነ ከሰው አይገጥሙም፤ ሰው አንድም ባለበት ስለሚረግጥ አንድም የኋልዮሽ እንጽርት ጨዋታ ላይ ስለሚባትል እነሱን ይፈራቸዋል፤ ስለዚህም ይጠላቸዋል። ምንም እንኳ እንደ ዕውነት ፀርና አሳች መሲህ ቢታዩም በሚቀጥለው ትውልድ ግን ሁሌም ብሩህ ከዋክብት ተብለው ይሞገሳሉ፤ የመታሰቢያ ሐውልትም ይሰራላቸዋል።“  በማለት አቶ ኦላና ከልጃቸው ጋር ያደረጉትን የሃሳብ መለዋወጥ ይነግረናል። ይህ አገላለጹ በሶፊስቶች በውሸት ተወንጅሎ  መርዝ እንዲጠጣና እንዲሞት የተፈረደበት ሶክራትስን፣ ወደ እስር ቤት የተወረወረውን ጋሊሌዮንና፣ እንዲቃጠል የተደረገውን ታላቁን የሬናሳንስ ምሁር ጊዮርዳኖ ብሮኖን ሁኔታ ያመለክተናል። ሁልጊዜም ለዕውነት የሚታገል በመጀመሪያ አሳሳቸ በመባል የውሸት ወሬ እንደሚነዛበትና እንዲጠላ የሚደረገውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ደራሲው ያስረዳናል። ስለዚህም ይላል ደራሲው፣ የስልጣኔ ፈር ወዳጆች ጥቂቶች ሲሆኑ የሚቀጥለው ትውልድ ተግባር ያንን በመመርኮዝ፣ በማስፋፋትና በማዳበር ዕምርታ በመሰጠት ህብረተሰብአዊ ለውጥ መምጣት እንደሚችል ነው። ለዕውነተኛ ስልጣኔ የሚታገል በምንም ዐይነት በስም አጥፊዎችና ሰውን በሀሰት በሚከሱ መደናገጥና የስልጣኔውን መንገድ ለቆ መውጣት እንደሌለበት ደራሲው ያመለክታል። ዕውነት ለጊዜው ብትዳፈንም አንድ ቀን ግን ባሸናፊነት በመውጣት ውሽት ነዢዎችን እርቃናቸውን እንዲቀሩ ማድረጓ በታሪክ የተረጋገረጠ ነው። ዛሬ በቴክኖሎጂ የተራቀቁና ዓለምን የሚቆጣጠሩ አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና የአደገ ሁኔታ ላይ ሊደርሱ የቻሉት የአሰተሳሰብ ለውጥ በማድረጋቸው ሲሆን፣ የጭንቅላት ተሃድሶ ለማግኘትና የተፈጥሮን ህግ ለመረዳትና የነበሩበትን የጨለማ ሁኔታ ለመለወጥ ሶስት መንፈስን የሚያድስ መንገድ እንደተጓዙ ደራሲው ቁልጭ ባለ መልክ ያስተምረናል። በእሱም አገላለጽ፣ ሬናሳንስ ወይም የግሪኮችን ዕውቀት መልሶ ማግኘትና በሱ ላይ በመመርኮዝ የስልጣኔውን ፈር መቅደድ፣ ሬፎርሜሽን ወይም በሃይማኖት አካባቢ የተደረገው የአስተሳሰብ ለውጥና ይህም ለካፒታሊዝም መነሳትና ማደግ አንደኛው መንገድ መሆኑና፣ ከዚህም ባሻገር ኢንላየትሜንንት በመባል የሚታወቀው ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ፣ እነዚህ ሶስቱ ደረጃ በደረጃ ለአውሮፓ ህዝብ ዕድገት መንገዱን ያሳዩት እንደሆኑ ደራሲው በደንብ ያስቀምጣል። ከዚህ ስንነሳ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች የገበያ ኢኮኖሚ አማራጭ የሌለው የዕድገት ትክክለኛው መሳሪያ ነው የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን ዶ/ር ምሀረት በግሩም ብዕሩ ሳይንሳዊ  በሆነ አቀራረብ ያስተምረናል።

ሰሎሜ ወንድሟን ለማስታመምና የጤንነቱን ሁኔታ ለመከታተል ወደ አሜሪካ ተመልሳ ከሄደች በኋላ እዚያው ለረጅም ጊዜ ትቆያለች። በመጀመሪዎች ሳምንታትና ወር በየጊዜው ኢ-ሜይልም ሆነ ስልክ ከመላኩ ጋር ይጻጻፉና ይደዋወሉ ነበር። መላኩም ስንክሳር ልምትባለው የሰሎሜ ጓደኛ ወደ አሜሪካ ስትሄድ ለሰሎሜ ቆሎና ደብዳቤም ይልክላታል። ይሁንና ግን ስንክሳር የደብዳቤውን ምስጢር ለማወቅ ስትል ቺካጎ ከደረሰች በኋላ ለራሷ በማስቀረት እንደጠፋባት ለመላኩ ትነግረዋለች።  በአንድ በኩል  ሰሎሜ አንድም በወንድሟ በሞትና በሽረት ላይ መገኝትና በደረሰበትም ከፍተኛ አደጋ በሀዘን ላይ በመውደቋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ቤተሰብ እዚያው ቤታቸው ውስጥ ጉድ ጉድ ከሚለው ክብሮም የሚባለው የኩላሊት ሀኪሙ ጋር ግልጽ የሌለው ግኑኝነት ይጀምራሉ። አልፎ አልፎም ለብቻቸው እየተገናኙ ይገባበዛሉ። እንደገና ቺካጎ ከተማ ውስጥ ለረጅም ወራት እንድትኖር የተገደደችው ሰሎሜ በመላኩና በክብሮም መሀከል መዋለል ትጀምራለች። በአንድ በኩል መላኩን ከልቧ ትወደዋለች፤ በሌላ ወገን ደግሞ በጠባዩ ቀለስለስ የሚለውን ክብሮምንም ላለማስቀየም ትሞክራለች። መላኩ ሰሎሜ ወደ ቺካጎ ከሄደችና እዚያም ለረጅም ጊዜያት እንድትኖር ከተገደደች ወዲህ በአስተሳሰቡ ብዙም ተለውጧል። በሃሳብ ከመዳበሩና ከመደንደኑ የተነሳ የመጀመሪያ ፍቅረኛው ልባዊ ፍቅር ማሳየት ስላልቻለ ወደ ካናዳ ጥላው ከሄደች በኋላ ግራ የተጋባው መላኩ ራሱን መልሶ መላልሶ የሚጠይቀው የመጀመሪያው ጓደኛው ለምን ጥላው እንደሄደች ነው። እሷንም በክርክክርና በሙጉት ለማሳመን ያደረገው ሙከራ ሁሉ የባሰውን እንዳራቃትና፣ ሌላ ሰው እንድትወድ እንደተገደደች ደራሲው ይነግረናል። ይህ በእንደዚህ እያለና በመላኩና በሰሎሜ መሀከል የነበረው የጠበቀ ግኑኝነት ወደ መላላቱ በማምራቱ፣ የቤተሰቦቹና በተለይም የአባቱ ሁኔታ የሚከነክነው መላኩ ከስራ ፈቃድ በመውሰድ ለመፈለግ ሲል ወደ መቂ ከተማ ያመራል። ወደ መቂ ከሄደ በኋላ አንድ ሆቴል ቤት ውስጥ ካረፈ በኋላ  አንደ ሆቴል ቤቱ ውስጥ በሚሰሩ ሴት አማካይነት ሁኔታውን ካጣራ በኋላ አብረው ያፈላልጉታል። የመጨረሻ መጨረሻም አክስቱንና የእህቱን ልጆች ሁሉ ያገኛቸዋል። የሚኖሩበትንም ሁኔታ ሲያይ በጣም ያዝናል። እንደ አጋጣሚ ከቤተሰቦቹ ጋር የተገናኘው የበዓል ዕለት ስለነበር አንዱን ልጅ ወደ ገበያ ይዞ በመሄድ በግ ገዝቶ  አምጥቶና አሳርዶ ያሽመነምናቸዋል። በረሃብና በችግር ሲሰቃዩ የኖሩትን ቤተሰቦቹን ደስታ በደስታ ያደርጋቸዋል። መላኩም ቀኑ ከመሸ በኋላ እዚያው ቤት ሲያድር ቁንጫና ትኋን በሰውነቱ ላይ እየደነሱበትና ደሙን እየመጠጡበት እንቅልፍ ያሳጡታል። አስተዋዩና አርቆ አሳቢው መላኩ በዘመዶቹ ላይ የሚደረሰውን፣ ከሃሳብ ድህነት የመነጨ ድህነትና ጉስቁልና እንዲሁም እጅግ አስቀያሚ ኑሮ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ይከነክነዋል። ጥቂት ቀናት እዚያ ከቆየ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ይወስናል። በመጀመሪያ ግን መኪናውን ወዳቆመበት ወደ ሆቴል ቤቱ ጋ ከአክስቱ ትልቋ ልጃቸው ከመዐዛ ጋር ተያይዘው ይሄዳሉ። ከመሄዱ በፊት እዚያ ተቀምጠው አንዳንድ ነገር አዘው በመጠጣት ላይ እያሉ መዐዛ አንድም በደስታ በመዋጧ፣ በሌላ ወገን ደግሞ መላኩ እስኪመጣ ድረስ እሷና ልጆቿ እንዲሁም እናቷ በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀው እንደነበርና፣ ልጆቿንም መመገብ ባለመቻሉ የመጨረሻ መጨረሻ የአይጥ መርዝ ጠጥታ ለመሞት መርዙን ገዝታ በመወሰንና ባለመወሰን ላይ እንዳለች መላኩ እንደደረሰላቸው ስቅቅ ብላ ታለቅሳለች። ቀደም ብሎ ግን መላኩ ለአክስቱም ሆነ ለመዐዛ ልጆች ገንዘብ ይሰጣቸዋል። ታሪኳን ከመናገሯም በፊት አምስት ሺህ ብር ያህል ይሰጣታል። እሱን ከሸኘች በኋላ ወደ ቤት በመመለስ ከእንግዲህ ወዲያ መላኩን በማስጨነቅ መኖር እንደሌለባቸው በመረዳት ገንዘቡን ሁሉ በመሰብስብ ንግድ ለመጀመር ቆርጣ ትነሳለች፤ በዕቅዷም በመግፋት ስኬታማ ትሆናልች። በየጊዜው በዕርዳታ መኖር እንደሌለባትና በትንሽም ገንዘብ ራሷን መለወጥ እንዳለባት በመረዳት የማሰብ ኃይል እንዳላት ታረጋግጣለች። መላኩም በአንድ በኩል ዘመዶቹን ለመርዳት በመቻሉና ከድህነት የሚወጡበትንም ሁኔታ በማመቻቱ ደስ ሲለው፣ በሌላ ወገን ደግሞ  እናቱ እሱን  አክስቱ ጋ ጥላ ብትሄድ ኖሮ ሊደርስበት የሚችለውን ሁኔታ ማውጣትና ማውረድን ተያያዘው። ብዙ አሰበ። ምናልባትም የኤይድስ ሰለባ ሆኖ ዕድሜው በለጋ ወጣትነቱ ይቀጭ እንደነበር ቁልጭ ብሎ ታያው። ካሊያም ሹፌር በመሆንና ትልቅ መኪና በመንዳትና ቤተሰብ በመመስረት ብዙ ልጆች ወልዶ አስቸጋሪ ኑሮም እንደሚኖር ታየው። እንድ አጋጣሚ የዶ/ር ሳራ እናት ባያገኙትና ባያስተምሩት ኖሮ ይህንን ያህል ደረጃ ላይ መድረስ እንደማይችል መገንዘብ ቻለ። ይህም በመሆኑና ጥሩ መንፈስም ስላለውና ጭንቅላቱም በፍልስፍና የተገነባ ስለሆነ ቤተሰቦችን ሳይረሳና ሳይንቅ ለመፈለግ መሄዱና እነሱንም መርዳት መቻሉ እያንዳንዱ የተማረ እንደሱ ማሰብ ቢችል የቱን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ታየው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የደራሲውን የላቀ የጭንቅላት መዳበርና ለአገርና ለህዝብ ማሰብ የሚያመለክት ነው። በዚህ መልክ እያንዳንዱ ዕውቀቱን ቢያገናኝና የማሰብ ኃይሉንም ካዳበረና ለወገኑ የሚያስብ ከሆነ ለውጥ በውጭ ዕርዳታ ሳይሆን ከውስጥ በራስ የማሰብ ኃይል ብቻ ሊመጣ እንደሚችል የኖይሮ-ባዮሎጂው ምሁርና ሃኪም፣ እንዲሁም በታሪክና በፍልስፍና ጭንቅላቱ የዳበረው ታላቅ ምሁር ድ/ር ምሀረት ከበደ ስለድህነት ዋናው ምክንያትና እንዴትም መፈታትና በአራት እግር መቆም እንደሚቻል በሚገባ ያስተምረናል።

የመላኩና የሰሎሜ ግኑኝነት ያልተቋጨ ፍቅር በነበረበት ሁኔታ ውስጥና፣ በመሀከላቸው የነበረውን መፈላለግ ለማፍረስ ተንኮል የምትሸርበው ስንክሳር አመቺ ጊዜን በምትጠባበቅበት ወቅት የስሎሜን ወንድምም ሶለን ከአደጋው ለመትረፍ ባለመቻሉ ከዚህ ዓለም በሞት ይለያል። ይህ በእንደዚህ እንዳለ እንደ እናት ሆነው ያሳደጓት ልጅ ዶ/ር ሳራ ከባሏና ከሶስት ልጆቿ ጋር የባሏን ቤተሰቦች ለመጠየቅ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። ዶ/ር ሳራም በጣም ስለደከማት ያንኑ ዕለት የባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር መሄድና ማረፍ ባለመፈለጓ ለጊዜው ሆቴል ቤት ውስጥ አረፉ።  የዶ/ር ሳራ ባል በራሱ ስሜት የሚነዳ ስለነበር ለባለቤቱና ለልጆቹ ደንታ ሳይሰጥ አብዛኛውን ጊዜውን ከድሮ ጓደኞቹ ጋር ነው የሚያሳልፈው። በሁለቱም መሀከል የነበረው ፍቅር የሻከረ ስለነበር ደራሲው እንደሚለን የመባለጊያ የወረቀት ፈቃድ የሰጠቺው ይመስል የትም እያደረ ነው የሚመጣው። ስለሆነም የህሊና ሳይንስ ሃኪም የሆነችው ዶ/ር ሳራ አብዛኛውን ጊዜዋን ከልጆቿና ከመላኩ ጋር ነው የምታስልፈው። አንደኛው ልጃቸውም ኦቲዝም(Autism) በሚባል የአዕምሮ መሰናክል የሚሰቃይ ስለሆነና፣ ከፍተኛ ክትትልም ስለሚያስፈልገው ዶ/ር ሳራ ከልጇ በፍጹም አትለይም። ጊዜዋን በተለይም ከአንድ ልጇ ጋር የምታሳልፈው ዶ/ር ሳራ ከመላኩም ሆነ ከመላኩ ጓደኛ ማርቆስ ጋር እየተዘዋወሩ በከተማ ውስጥም የተሰሩትን አዳዲስ ህንፃዎችና የአማኑኤልንም ሆስፒታል መጎብኘት ደስ ይላታል። በተለይም የአማኑኤልን ሆስፒታል ስትጎበኝ የምታነፃፅረው አሜሪካን ካሉ ካማሩና በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ከመቶዎች በላይ የሚገኙበት ሃኪሞችና ነርሶች እንዲሁም ድሬሰሮች ጋር ነው። በተለይም የአማኑኤል ሆስፒታል መርካቶ ውስጥ መሆኑ ነገሩ ይከነክናታል። እንደዚህ ዐይነት ሆስፒታል እንደዚህ ዐይነት ቦታ መሰራት ያለበት ሳይሆን ወጣ ያለና፣ አካባቢውም ሆነ ግቢው በአማሩ ዛፎችና አበባዎች፣ እንዲሁም የሰውን ጭንቅላት በሚያድሱ መናፈሻዎችና መቀመጫዎች ማማርና መሰራት የነበረበት እንደነበር ለማስረዳት ትሞክራለች። ስለሆነም ሃሳቧ ስለዚህ ሁኔታና ስለጭንቅላት ህመምና በተለይም ደግሞ ስለ ኦቲዝም ምንነት በዩኒቨርስቲው የነርብ ህክምናና የህፃናት ክፍልና ሆስፒታል ውስጥ ሰሚናር ለመስጠት አቀደች። በቴሌቪዝንም ተጠይቃ ስለኦቲዝም ሰፊ ማብራሪያ ሰጠች። ቃለ-መጠይቁንና ገለጻዋን በተሌቪዝን የተመለከተው ባላቤቷ ይዘዙኝ ልቀቁኝ ማለት ጀመረ። ባለቤቷ ወያኔን የሚጣላ በመሆኑና እሷም በአባቷ ትግሬ ስለሆነች የባሰውኑ ወያኔን ሆንሽ አይደለም ብሎ ጮኸባት። ምንተስኖት አሜሪካን አገር በኢንተርናሽናል ዴቬሎፕሜንት የሰለጠነ ቢሆንም ይህንን ያህልም የዳበረ ጭንቅላት የለውም። በራሱ ስሜት የሚመራና አርቆ የማሰብ ኃይሉ ውስን ነው። ስለሆነም የነገሮችን ሄደት ሳያጤን ቶሎ ብሎ ወደ ጠብ ያመራል። ከሱ ዕምነት ውጭ ያለውን እንደ ጴንጤ ቆንጤ የመሰለውን ሃይማኖት ፈረንጆች ሆን ብለው የሰውን ጭንቅላት ለማደንዘዝና የጥቁርንም ህዝብ ተገዢ ለማደረግ የፈጠሩት ሃይማኖት ነው ብሎ ስለሚያምን ከመላኩ ጋር፣ መላኩ የጴንጤ ቆንጤን መዝሙር ሲያዳምጥ ሲሰማ በመብገን ግጭት ውስጥ ሊገባ ቻለ። መላኩም ረጋ ባለ መልክ መዝሙሩ የጴንጤ ቆንጤ በመሆኑ ወይስ ጠቡ ከሃይማኖት ጋር  ነው? ብሎ በመጠየቅ፣ የኦርቶዶክስም ሃይማኖት እንደዚሁ የራሱ መዝሙር እንዳለውና በአጠቃላይ ሲታይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት በታሪክ ሂደት ውስጥ ብቅ ያለና የጥንት አባቶቻችንም ተገደው የተቀበሉትና እንደ ዕምነትም የወሰዱት እንደሆነ በጥሞና ያስረዳዋል። የመላኩን የበሰለና ረጋ ያለ ክርክር ያዳመጠው ምንተስኖትም በመገረም  ወደ ጠብ ሳያመራ በውይይት ብቻ በመሀከላቸው ያለውን ልዩነት ለማብረድ እንደቻሉ ደራሲው ግሩም በሆነ መልክ ያስረዳዋል።

ይህ በእንደዚህ እንዳለ መላኩ ወደ ዱባይ ለስብሰባ ከመሄዱ በፊት ከሳራና ከቤተሰቦቿ ጋር በየጊዜው እየተገናኙ ከተማውን ያሳያታል።  በተለይም በአገራችን ውስጥ ያለውን ጭንቅላት ላይ የሚከሰት በሽታ ሁኔታ ለማከም አንድ ማዕከል ለማቋቋም እንዳሰበች ለመላኩ ታስረዳዋለች። እንደ ኦቲዝም የመሳሰሉት የጭንቅላት መዛባቶች ቢኖሩም ችግሩ በደንብ የታወቀና በዚህም መስክ ስፔሽያላይዝ ያደረገ እንደሌለና፣ ህክምናም እንደማይሰጥ ደርሳበታለች። በመሆኑም ዕቅዷን በዝርዝር ለመላኩ ትነግረዋለች። መላኩም የሷን ቀና አስተሳሰብ በደንብ ካዳመጠ በኋላ ስለ ኦቲዝም ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንድታስረዳው ይጠይቃታል። ዶ/ር ሳራም የመላኩን ጥያቄ ካዳመጠች በኋላ በጥሞና ጥያቄውን በሚከተለው መልክ ታስረዳዋለች። „ ኦቲዝም አንድ በሽታ ነው ማለት አይቻልም። በአጠቃላይ ተመሳሳይ መግለጫ ያላቸው ከአዕምሮ ዕድገት መዛባት ጋር የተያያዙ ችግሮች የጋራ ስም ነው። ኦቲዝም የሚለው ስም `አውቶ´ ማለትም የአንድ ሰው እኔነት (ራስ ) ከሚለው ቃል የወጣ ሲሆን፣ ኦቲዝም የተባለበት ምክንያት ይህ ችግር ያጋጠማቸው ሕፃናት አብዛኛው ዓለማቸው በራሳቸው ውስጥ ስለሚሽከረከር ነው። አሁን አየህ አዕምሮው በትክክል የሚሠራ ሰው ውስጣዊውንና ውጫዊውን ዓለም አመጣጥኖ ነው የሚኖረው። ኦቲዝም ያለባቸው ሕፃናት ግን ልክ ሳጥን ውስጥ እንዳለ ሰው ብዙውን ጊዜ የሚያሳልፉት በራሳቸው ጭንቅላት ውስጥ ነው። ከዚህም የተነሳ ለሰው ግራ የሚያጋባና ለመረዳት አስቸጋሪ የባህርይ፣ የቋንቋና የማህበራዊ ግኑኝነት ጉድለቶች ይታዩባቸዋል። ደግሞም በአብዛኞቹ ላይ የአዕምሮ ዝግመት ይከሰታል። እንደባቢዬ(ልጇ)
https://amharic-zehabesha.com/archives/179841

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...