Wednesday, February 22, 2023

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የካቲት 13/ 2015 ያወጣው መግለጫ አሁናዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ በትክክል  የዳሰሰ እና ትክክለኛ የትግል አቅጣጫዎችን ያመላከተ ነዉ
ነአምን ዘለቀ

በመግለጫው በጉልህ እንደተቀመጠዉ  በ2018 የመጣው ለውጥ እንዲመጣ የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩ ልዩ ትግሎችን ለ 27 አመታት አድርጎአል፣ በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን የተጫነባቸዉን በአንድ ዘር የፖለቲካ ሊሂቃን የበላይነት ሚዘወር የጭቆና ቀንበር ለማስወገድ ትግል አድርገዋል። ለህግ የበላይነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህ፣ ሁሉም የቋንቋና የባህል ማንነቶች/ብዝሃነት የሚከበርበት አካታች ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርአት እውን እንዲሆን  የህይወትና አካላዊ መስዋእትነትን ከፍለዋል፡፡ ለከባድና ቀላል አካላዊ እና አእምሯዊ ጉዳት ተዳርገዋል ።

ነገር ግን  ይሄ ሁሉ መስዋእትነት የተከፈለለት ለዉጥ ትላንት አምርረን የታገልነውን የአንድ ብሄር ልሂቃን ግፈኛና ዘራፊ ስርአት ዛሬ በእኩልነት ሽፋን ያንኑ የከሸፈና  ስርአቱን  ለውድቀት  የዳረገ  ጭቆናን ፣  አድሎዊነትን፣ አፈናን ፣ ቅጥ ያጣ ዘረፋን መሳሪያው ያደረገ በአንድ ሰፊ የተከበረ ህዝብ ስም የሚነግዱ ጥቂት የብሄር ልሂቃን የበላይነትን የሚዘወር  የበላይነትን   በማስፈንና በሌሌች ብሄሮች ክልሎች   በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ ተጭኖ እንዲደገም፣  በዛም ሳቢያ ለሌላ ዙር ሀገራዊ ቀውስና ለለውጥ ወደ ሚደረግ የትግል አዙሪት እንድንመለስ አልነበረም።

በ21ኛ ክፍለ ዘመን የማይመጥን ፣ “የታሪክ ምርኮኞች” ብቻ ሳይሆን ታሪክንም በትክክሉ ከማይተርኩ፤ በ19ኛ ክፍለ ዘመን ተቸክለው በቀሩ ቆሞ ቀሮች በእኩልነት ሽፋን የሚዘወረው ቅጥ ያጣና ሁሉ ለኔ አልጠግብ ባይ ስሜት እና ስግብግብነት ዕሳቤ የተጠለፈው የአድራጊ ፈጣሪነት የፖለቲካ አቅጣጫ አገራችንና ዜጌቿን ለከፋ ውድቀት ከመዳረጉ በፊት ቆም ብለው  ማሰብ የሚያስፈልግበት መስቀልያ መንገድ ላይ መደረሱን ሁላችንም መገንዘብ ያስፈልገናል።

በዚህ ሁሉ የኔና ለኔ በሚል የስግብግብነትና የአድራጊና ፈጣሪነት ስሜት የተጠናወተው እሳቤ የተፈጸሙት ተግባራት ለምሳሌ በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ  በመግባት  የኢትዮጵያ  እስልምናን  እንዲሁም የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በመከፋፈልና ለመቆጣጠርና  የፓለቲካ መሳሪያ ለማድረግ፣ በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ላብ፣ ጥሪት፣ ደምም  ጭምር  የተገነባችውን ፣ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም መዲና የሆነችውን አዲስ አባባን ወደ አንድ ክልል ለመጠቅለል እየተፈጸመ ያለው አደገኛ ሂደት ፤  በተመሳሳይ በሁሉም  ክልሎች በሚባል ደረጃ በይገባኛል ሰበብ፤ በቁማር እና በሀይል ማንነትን በመጫን አካባቢዎችን በመዉረር፤ ግጭት በመቀስቀስ ህዝብን መጨፍጨፍ እና ማፈናቀልና፤ ሌሎችም እየተሞከሩ ያሉ የቀቢጸ ተስፋ ፕሮጄክት አካል የሆኑ ውጥኖች እየተባባሱና እጅግ አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

እነዚህን አገር አፍራሽ የቀቢጸ ተስፋ ፕሮጄክቶች እርግፍ አድርጎ በመተው  ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን  እኩል የሆነች ኢትዮጵያ፣  በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ክልሎች  ዜጎች እኩል የሚታዩበትና መብቶቻቸው የሚከበሩባት፣ የሚረጋገጡባት  ኢትዮጵያ፣ በሁሉም ክልሎች ኢትዮጵያን ዜጎች በማንነታቸው ሳቢያ ደህንነታቸው አደጋ ላይ የማይወድቅበት ኢትዮጵያ፣ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው እንደ ባይተዋር የማይታዩበት ኢትዮጵያ፣ ሁለንተናዊ  መብቶቻቸው የተከበሩባት፣ የሚረጋገጡባት ኢትዮጵያ ፣የሁሉም ማህበበረሰቦች  ባህልና ቁንቋዎች የሚከበሩባት ኢትዮጵያን በታሪክ አጋጣሚ የተረከቡትን ታላቅ ሃላፊነት እነዚህ ልሂቃን በጥልቀት በመረዳት  እዉን ማድረግ ይበጃቸዋል። ፣ ወደ ልማት በማተኮር   በድህነትና  በስራ አጥነት፣ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት የሚሰቃየውን ህዝብ ክድህነት ለማላቀቅና ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር ። ፍትሃዊና ፣ ዴሞክራሲያዊ ፣ ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የበኩላቸዉን ቢወጡ  ለሁላችንም  ይበጀናል። እነዚህም ልሂቃን  በጎ ታሪክ ሰርተው ያልፋሉ፡፡

ስለሆነም  የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የካቲት 13/ 2015 ያወጣው መግለጫ በቅነነት መንፈስ በመመልከት  በማንአለብኝነት በሴራ እና በብሽሽቅ በአድራጊ ፈጣሪነት ስሜት ከመጠመድ ይልቅ፤  የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሰፊ ህዝቦች (ሰፊ የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የአማራ፣ የደቡብ ፣ የትግራይና፣ ወዘተ ህዝቦች ) ትክክለኛና አንገብጋቢ  ጥያቄ የሆኑትን፤  ዳቦ፣ ስራ፣ ሰላም፣ የተረጋጋ ህይወት፣ ደህንነት፣ ፍትህ፣ የህግ የበላይነት፣ የመንግስት ተጠያቂነትና ግልጽነቶችንና መሠል ጥያቄዎችን በውል ተገንዝቦና ቅድሚያ ሰጥቶ ተገቢውን  ጀሮና ልብ  በመስጠት፤ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉን አካታች የሆነ መፍትሄዎችን በማስቀመጥ   ከጫፍ ጫፍ፣ ሰላም፣ ተስፋና  እፎይታን ለዜጎች የሚያጎናጽፍ አካሄድ መከተልና አገርንና ዜጎችን ከጥፋት መታደግ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው፤ ለነገ የማያድር ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡

 

Hiber Radio Daily Ethiopia News Feb 19, 2023 | thiopia
https://amharic-zehabesha.com/archives/180027

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...