Tuesday, January 17, 2023

Saturday, 30 July 2016 11:29 

 አሰፋ ጫቦ

 

ከአዘጋጁ፡- ለአቶ አሰፋ ጫቦ በቃለ-መጠይቅ መልክ በኢሜይል ከላክንላቸው በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ ለአራቱ የሰጡትን ምላሽ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ፡- “ሦስቱን መንግስታት በንጽጽር እንዴት ይገልጹዋቸዋል?” በሚል ለላክንላቸው ጥያቄ፣ አስፋፍተውና በመጣጥፍ መልክ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ብዙ በመሆኑ በሁለት ክፍል እናቀርበዋለን፡፡ የመጀመርያው የመልሱን ክፍል እነሆ፡-

“ያለፍክባቸውን ሶስቱን መንግስታት በንጽጽር እንዴት ትገልፃለህ?”

የሚለው በጣም ከባድ ጥያቄ ይመስለኛል። ዘርዘር ባደርገው ጋዜጣው በቂ ቦታ አይኖረው ይሆናል ብዬ ፈራሁ። ሰብሰብ ያደርኩ እንደሁ ደግሞ ከመልስ ይልቅ ተጨማሪ ጥያቄዎች የሚጋብዝ ይሆናል ብዬ ፈራሁ።  እስኪ መጠነኛ፤ መሀል መንገድ ፈልጌ ለማትኮር እሞክራለሁ።

ለዚህም ሁለት አብይትና ገላጭም ናቸው ብዬ የምገምታቸው ነጥቦች ላይ አተኩራለሁ። የመጀመሪያው እነዚህን 3 መንግስታት፤ ማለትም የንጉሰ ነገስቱን፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊት ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ (ኢሕድሪ (ደርግ) እና አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት እንደ ሥርዓተ-መንግሥት (System of Government) ምን ይመስላሉ የሚለውን ቀንጭቦ ማየት ይሆናል። ሁለተኛው እነዚህን መንግሥታት በቁልፍነት ሲያሽከረክሩና  አድራጊ ፈጣሪ የነበሩትን  ግለሰቦች፣ ማለትም፣ ኃይለሥላሴን፤ መንግስቱ ኃይለ ማርያምንና መለሰ ዜናዊን ለማየትና ለማሳየት መሞከር ይሆናል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሶስቱንም በቅርብ የማወቅ፤ አብሮ የመስራት፤ ከዚያም ፈግጠው-ፈግጠው ተባብለን ተለያይተናል። በቅርብ ርቀት (የቅርበት-ርቀቱ መጠን ቢለያይም) ሰብእናቸውንም የማየትና የመታዘብ እድል ነበረኝ። ይህ የዐይን ምስክርነቴ ለምለው ተጨማሪ ምንጭም ሆኖ ያገለግላል የሚል እምነት አለኝ። በፈግጠው ፈግጠው ጉዳይ፣ እኔ ውድ ዋጋ ከፍያለሁ። እየከፍልኩም ነው። ”… ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው” የሚሉት ሆኖ እንጅ እነሱም ከፍለዋል። እርግጥ የእጁን ያላገኘው መንግስቱም አለ።

 

ሕገመንግሥት

የማንኛውም አገር ሥርዓተ-መንግስቱ መግለጫ ሕገመንግስቱ ነው። ሕገመንግሥት ማለት አንድ አገር የሚገነባበት ጽኑ መሠረቱ፤ ጣራውን ተሸካሚ አስተማማኝ ግርግዳውና፤ ደመና ዞር ባለው ቁጥር፣ ብርድ፤ ፀሐይ ብቅ ባለች ቁጥር፣ ሙቀት የማያስገባ፣ የረጋና የተረጋጋ ጣሪያ ያለው ጽኑ አዳራሽ እንደ ማለት ነው። እዚያ ታላቅ አዳራሽ ውስጥ ነው ክፍሎቹ እንደ ቤተሰቡ ዕውነት የሚከፋፈሉትና የሚደላደሉት:: ሕገመንግስትን መሠረታዊ ህግ፤ የሕጎች ሁሉ ምንጭ (እናት) (Basic Law,Fundamental Law) ይሉታል። ነውም! ስለሆነም፤ በሕገመንግስቱ ብንጀምር የሚሻል ይመስለኛል።

በንጉሱ ሕገ መንግስት (1948 ዓ.ም) እንጀምር። ይህም “የተሻሻለው የ1948 ዓ.ም ሕገ መንግስት” ተብሎ የሚጠራው ነው። ይህ ሕገመንግስት አብዛኛው ህዝብ ከማያውቀው ታሪክ፣ ሌላም ታሪክ ከኋላው አለ። ንጉሱ፤ “ለምንወደዉና ለሚወደን ሕዝባችን በራሳችን ፈቃድ ተነሳስተን ሰጠነው” እንደሚሉት አይደለም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔ የፈደራል አክት (The Federal Act 1952) የሚባል አለ። ይህም ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ለማገናኘት የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ነበር። በአለም አቀፍ የሕግና የፖለቲካ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ሕገ መንግስት አለ። ፌዴሬሽኑን ለመቀበል ይህንን የፌዴራል አከት መቀበል እንጅ አማራጭ አልነበረውም። ኢትዮጵያ ያኔ የነበራት የ1923 ዓ.ምቱ፤እጅግ ኋላቀር ሕገ-መንግስት ነበር። የፌዴሬሽኑ ርእሰ ብሔር ደግሞ ንጉሱ ሊሆኑ ነው። ስለዚህም ኤርትራን 25 ዓመት (1948-1923) ወደ ኋላ ከመውሰድ፣ ኢትዮጵያን 25 አመት ወደፊት መጎተት ይሻላል የሚል እርቅ ሃሳብ (Compromise) መሆኑ ይመስለኛል። ሌላው ቢቀር በወረቀት ላይ እንኳን ቢሆን ጎተት እናድርጋት እንደ ማለት ነው።

ቁልፉና ተፈላጊው ነገር ኤርትራን በዚህም ይሁን በዚያ ወደ እናት አገሯ መመለሱ ነበር፡፡ ብዙም ሳይሰነብት ኤርትራን ለዚህ ያበቃው ዘር መዘራት ተጀመረ። ይህ ያልተጣጣመም፤ ፈላጭ ቆራጭ ንጉስ ነገስትና ዘመናይ የሆነው የኤርትራ ሕግ አብሮ አለመሄድ፤ የፌዴሬሽኑ ማፍረስና መፍረስ መነሻ ምክንያቶች ሆኑ። እርግጥ አባባሽ የሆኑ ሌሎችም ምክንያቶች፣ ሰበቦች ሞልተዋል። ከመጀመሪያውም ቢሆን፣ ይሁን-ይሁን ተብሎ እንጅ ሁለንተናው ሲታይ የፌደራል መለኪያዎች አያሟላም ነበር የሚሉ የሕግም የፖለቲካም ምሁራን አሉ።

ከዚህ፤ 131 አንቀጽ ከነበረው ከ1948 ዓም ሕገመንግስት ውስጥ 35ቱ የንጉሰ ነገስቱን ዝርያና ውርስ፣ ስልጣን የሚናገር ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ አንቀጽ የያዘው፣ ዘውድ በሳባ በኩል ከአይሁዱ ነገሥታት ከዳዊትና ከሰለሞን ሳይቋረጥ የመጣ፣ ኃይለስላሴም የዚያ ዝርያ ስለሆኑ ከእርሳቸው ዝርያ ለዘለዓለም አይወጣም የሚል ነው። እንዲህ ሲያዩት የሚገርም ነው። እኔን ይገርመኛል። መጀመሪያ ለስላሴ ኦሮሞ ናቸውና እዚህ ስለ ንግስት ሳባ ከሚወራው ትንግርት ውስጥ (እውነትነት ቢኖረው እንኳን) የሚያገባቸው ነገር ያለ አይመስለኝም። ከሁሉም በላይ ግን ኃይለስላሴ፤ ይህንን እስከ ወዲያኛው ሊያደርስ የሚችል፤ የሚመኙትን ዘውድ የሚያጓጉዝ አልጋ ወራሽ አልነበራቸውም። አልጋ ወራሽ የተባሉት አንደበታቸው ተይዞ አውሮጳ ለሕክምና ከሔዱ አመታት አልፏል። ንጉሱ መጃጀታቸው ደግሞ የአደባባይ ሚስጥር ነበር። ለሁሉም ለሁሉም በ1966-67 የኃይለ ሥላሴም ሆነ የዝርያቸውም መጨረሻ እስከ ወዲያኛው ሳይሆን ከርቸሌ እንደነበረ ያየነው ወይም የሰማነው ነው።

ያም ሆኖ የዚህ ህገመንግስት ገላጫ ባህርዩ አንዱና ቁልፉ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያስቀምጥ ነው። “ኢትዮጵያ ማለት ምድሪቱ፤ ባህሩ፤ ደሴቶቹና ከላይ የከበበው ሰማይ ጭምር ነው” ይልና ይህ የማይደፈርና የማይቆራረስ ነው ይላል። ስለዚህም  ኢትዮጵያ  ማን እንደሆነች፤ የት እንደምትገኝ፣ ምኑና ምኑ ተሰባስቦ፣ ወጥና አንድ ኢትዮጵያ እንደሚያሰኛት በማያጠራጥር፤ በማያሻማ ቋንቋ ተጽፎ ተቀመጧል። ይህም አይደፈርም አይገሰስም ይላል።

የደርግ ሕገመንግሥት፤ኢትዮጵያ የሶሺያሊስት አገር መሆኗን በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጧል። ዛሬ ነፋሱን ተከትለንም ሶሺያሊስት፤ ካህኑ፤ አጥማቂው ጭምር የነበርነው ሁሉ “እኔኮ! ነገር ግን…!” ማለት ጀምረናል። እዚያ ውስጥ አልገባም። ከሐዲዎቹ ያላስተዋልነው ነገር ቢኖር አብዛኛው የምዕራብ አውሮጳ አገሮች በተለይም እስካንዲኔቪያ (Scandinevia) የሚባሉት ወይ ሶሺያሊስት ወይም የዚያ ጥምር መሆናቸውን ነው። ለምሳሌ የአሁኑ፤ የዛሬው፤ የፈረንሳይ መንግስት ሶሺያሊስት ነው። ይህ ደግሞ ወደ መቶ ዓመታት የሚጠጋ ታሪክ አለው።

የደርግ መንግስት፤ የኢትዮጵያ ማንነት ልክ የንጉሱ መንግስት ሕገመንግሥት ያለውን በተጠናከረ መልኩ ይደግመዋል። ኢትዮጵያ ነጻ የማትደፈርና የማትከፋፈል ነች ይላል። ሌላው የደርግን ሕገ መንግሥት ለየት የሚያደርገው፣ ይህ መንግስት የተመሠረተው ለነማን፤ በነማን እንደሆነ ይዘረዝራል። ይህም ዝርዝር “የሠርቶ አደሩ፤ የገበሬው፤ የምሁራን፤ የአብዮታዊው ሠራዊት፤ የእጅ ሠራተኞችና የተቀሩት የዲሞክራቲክ ኃይሎች መንግስት ነው !” ይላል። እዚህ ዝርዘር ውስጥ ያልገባ ቢኖር፤ “ሳይሰራ የሚባለው!” ነበር። ማለትም፤ ደርግ በዝባዥና አቆርቋዥ የሚላቸው መሆናቸው ነው። ደርግ ዛሬ ከመቃብሩ ቀና ብሎ ቢያይ “ምነው!?  ስምንተኛው ሽህ ገባ እንዴ!?” ሳይል የሚቀር አይመስለኝም፡፡

አሁን ደግሞ በሥራ ላይ ያለውን የኢህአዴግን ሕገመንግሥት ለማየት እንሞክር። ለመንደርደያ ያክል ይህንን ሕገመንግሥት ያረቀቀው፤ “ዶክተር” ፋሲል ናሆም መሆኑን መግለጹ ጥሩና አስፈላጊም ይመስለኛል። CONSTITUTION FOR A NATION OF NATIONS ,The Ethiopian Prospect የሚል መጽሐፍ ጽፏል። መጀመሪያ ነገር ይህ መጽሐፉ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አይደለም። ለመንግሥቶች መንግሥት የወጣ ሕገመንግሥት ይለዋል። ትርጉሙ ግልጽ አይደለም። ለኔ ግልጽ አይደለም! ብቻ በዚህ ሕግ መንግስት፤ እንደ ፋሲል ናሆም አባባል፤ አቀራረብ ኢትዮጵያ የመጽሐፉም፤ የሕገመንግሥቱም ዋና ተዋናይና እምብርት አይደለችም እንደ ማለት ነው። ተለጣፊ መሆንዋ ነው። PROSPECTS  የሚለው ቃል ትርጉም ይኸውና፤ prospect,noun ,the possibility or likelihood of some future event occurring.” ምናልባት ሊሳካ ይችላል ማለት ነው። ምናልባት ሊሳካ የሚችለው ምኑ ይሆን? አልነገረንም! የሚጽፈው ስለ ኢትዮጵያ ስለሆነ ኢትዮጵያ፤ እንደ ኢትዮጵያነትዋ ላትሳካ ትችላለች ማለት ይሆን? ይህም የሚያስኬድ ትርጉም ይመስለኛል። ሌላው፤ወያኔ ይህንን የማ

ይመስል ነገር ተግባራዊ ማድረጉ አይሳካለት ይሆናል ለማለት ይሆን? አሁን ምድሪቱ ላይ የምታየውን ዕውነት ልብ ያልን እንደሆነ፣ ይህኛውም ትርጉም የበለጠ የሚመስል ነው።ፕሮፌሰር ቲዎዶር ቨስታል፤ TheodoreM.Vestal “ETHIOPIA:A Post-Cold War African State” በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ፋሲል ኖሆም በሰፊው ጽፈዋል። በገጽ 95-96 ይገልጹታል። በገጽ 102 የግርጌ ማስታወሻም ላይ፣ ፋሲል በ1966 የኃይለ ሥላሴን ሕገመንግሥት፤ በኋላም ትንሽ ቆየት ብሎ የደርግን ህገ መንግስት አርቃቂ መሆኑና አሁን ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ የዚህኛው አርቃቂ መሆኑንም ያመለክታሉ። ሌሎች ምሁራን መፈልፈል እንዲቻል የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅንም ያቋቋመው ፋሲል ናሆም ነው።

የፋሲልን መጽሐፍ አንድ ቀን አበራየዋለሁ፤ ወይም “ገላልጦ ለማየት” እሞክራለሁ የሚል ሐሳብ ስለአለኝ እመለስበታለሁ። የፋሲል መጽሐፉ ሽፋን ሁለት የአኩሱም ሐውልቶችና በመካከሉ አሮጌ የብራና ጽሁፍ የሚመስል ተሸንቅሯል። ወደ ጥንታዊቱ ዘመነ አኩሱም እንመልሳችኋለን ነው መልእክቱ? መቼም ትርጉም አለው! ከሌሎች ነጥቦች ጋር ሲገናዘብ፣ ለዚህም ትርጉም ቦታ አለው።

የዛሬን የኢትዮጵያን ማንነትና ምንነት ለመረዳት፣ የኢህአዴግን  ሕገመንግሥት አንቀጽ 2 ማንበብ ይበጃል። ኢትዮጵያ ማለት የፌዴሬሽኖቹ አባላት ጥርቅም ነው ይልና ዳር ድንበሯ ግን በስምምነት ይወሰናል ይላል። ስለ ምድሩ ስለ ሰማዩ፤ ስለ አየሩ፣ ስለ ባሕሩ የሚያወሳው ነገር የለውም። እርግጥ ስለ ባህሩ የሚያነሳው ነገር የለዉም። ቀይ ባህርን ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥነት ያገኘችው ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም፣ አልነበረችምም ብሎ መለስ ዜናዊ ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ ጽፏልና፣ ስለ ባህር ንብረት ሊነሳ አይችልም። ዳር ድንበሯ የተከበረ፤ የማይደፈር፤ የማይቆራረስ ነው አይልም። አንዴ ኤርትራ ተቆርሶ ሔዷልና፣ ከአሁን በኋላ አይቆራረስም ማለቱ ትርጉም የለውም ብለውም ሊሆን ይችላል። በህግ Precedent ይሉታል። አስቀድሞ የተወሰነውን፣ ይህኛውም ይከተላል እንደ ማለት ነው።

በዚህ ላይ አሁን ሲነገር እንደምሰማው፤ (ተጠናቆ እንደሁ አላውቅምና) ለሱዳንም መሬት ይሰጥና ከዚያ በኋላ ይመስለኛል የምዕራቡ ድንበራችን የሚወሰነው። በምስራቅ በኩል ያለው ድንበራችን ጉዳይ በእጃችን ያለ አይመስለኝም። ሶማሌ መፈረካከሷ ብቻ ሳይሆን ሞቃዲሾን ያማከለው የሱማሌ መንግስት የሚሉት፣ እንኳንስ ድንበር ሊካለል፣ ለራሱም ቢሆን ከመንግስት ይልቅ የመንግስት ቅዠት ነው የሚመስለው። ብቻ ብዙ ማለት ሲቻል ላሳጥረው። በኢህአዴግ ሕገመንግሥት አንቀጽ ሁለት መሠረት፤ ኢትዮጵያ የታወቀ፣ የጸና፣ የማይሸራረፍ፣ የማይቦጨቅ ዳር ድንበር የላትም፡፡

መሪዎቹ

አሁን ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለ መንግስት፣ አድራጊ ፈጣሪ የነበሩ መሪዎች፤ ማለትም ኃይለ ሥላሴን፤ መንግስቱ ኃይለማርያምንና መለስ ዜናዊን በጨረፍታ ለማየት እንሞክር።

በኔ አስተያየት፤ አስተያየት ብቻ ሳሆን ከተግባራቸው በመነሳት እነዚህ ሶስት ግለስቦች ከጠበቅነውና ከምንጠብቀው በላይ የሚጋሩት የጋራ ባሕርይ ያላቸው ይመስለኛል። ከእነዚህ የጋራ ባሕርያት ውስጥ  ሰውን የመረዳትና የመመዘን ብቻ ሳይሆን ሰንጥቆ ውስጡን የማየት፤ሰውን ፈጽሞ አለማመን፤ የሰውን ጠንካራና ደካማ ጎኑን ማወቅ፤ ጠንካራ ጎን አለው ብለው የገመቱትን ቢቻል ማራቅ፣ ካልሆነም ማጥፋት፤ በጣም የከረረ ራስ ወዳድነት፤ ርህራሔ (Empathy,Smpathy) የሚባለውን ነገር ጨርሶ አለማወቅ፤ ከዚህም የተነሳ ከወዳጅ ዘመድ፣ ጓደኛ ጀምሮ ይበልጠኛል ብሎ ያመኑትን ሰው ለማጥፋት ወደ ኋላ አለማለት፤ ለድርጊታቸው ተቀባይነት ያለው በአገር ፍቅር የተቀባባ ምክንያት መስጠትና ከራሳቸው በስተቀር ምንንም ማንንም አለመውደድና ያቀረቡ መምሰል እንጅ ሰው አለማቅረብ —– ገላጮቹ ናቸው። ዋና መመሪያቸው፤ “ጠርጥር ገንፎም ውስጥ አለ ስንጥር!” የሚል አይነት ይመስላል።

የሰውን ልጅ ስነአዕምሮ አጥኝዎች (Psychologists) ይህንን ከአዕምሮ ህመም እንደ አንዱና ለማከምና ለማዳን የማይቻል መሆኑን ይገልጻሉ። ለማከምና ለማዳን የማይቻለው፣ የዚህ አይነት ህመም ያለባቸው ሰዎች በጣም ጠልቀው የሚያዩ ስለሆነ፣ ሐኪሙ ለሚጠይቀው ጥያቄ “የሚፈልገው መልስ ይህ ነው!” ብለው አውቀው፣ ወስነው ስለሚመልሱ፤ በሩን መዝጋት ስለሚችሉ፣ ውስጥ ገብቶ አይቶ መድኅኒትም ሆነ ምክር መስጠት አይቻልም ነው የሚሉት።

ይህን የአዕምሮ ህመም አይነት Sociopath  ይሉታል። በአማርኛ ለመተርጎም ይከብደኛል። ምናልባትም ዕቡይ ማለት ይቻል ይሆናል። ይህንን ለመረዳት M.E Thomas  የምትባል የሕግ ፕሮፌሰር Confessions of a Sociopath: A Life Spent Hiding in Plain Sight: በሚል የጻፈችው ዝነኛ መጽሐፍ አለ። የመጽሐፉ ተጨማሪ ርዕስ፡- A Life Spent Hiding in Plain Sight የሚል መሆኑን ልብ ይሏል! አብረውን ናቸው ግን አንለያቸውም፤ አናውቃቸውምም ለማለት ነው። እንደሌላው በሽታ በአደባባይ የሚገለጥበት መንገድ የለውም ለማለት ነው። ራስዋ የዚህ ሕመምተኛ መሆንዋን አምና፣ በምርጥ የአዕምሮ ሕመም ሐኪሞች (Psychiatrists) ተመርምራ የጻፈችው ነበር።  እኔም ይሕንን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ አንድ በዚህ ሙያ  25 አመት የሰራና ልምድ ያለው፣በሚያስተምርበት ተመዝግቤ አንድ የሳይኮሎጂ ትምህርት ወሰድኩ። ከዚያ በፊት ዩኒቨርስቲ እንደ መግቢያ የወሰድኩት የሳይኮሎጅይ ትምህርትና በንባብም ያዳበርኩት ተጨምሮ ነው እዚህ ከሙያዬ ውጭ ይህን አስተያየት እንድሰነዝር የገፋፋኝ። አንድ ቀን ክፍል ውስጥ ይህንኑ ፕሮፌሰር፤ “ታዲያ ስለ Sociopath ምን ይሻላል?” አልኩት። “መሆኑን ከለየህ፣ ከቻልክ ከአጠገቡ ሮጠህም ቢሆን አምልጥ!” ያለኝን አስታወስኩና ሳቅሁኝ። ሩጬ አላመለጥኩምና!

ባለሙያዎቹ ይህ የአዕምሮ ሕመም፤ ሁለት ምንጭ አለው ይላሉ። አንዱ በተፈጥሮ (Genetic) ሲሆን ሁለተኛው ከአስተዳደግ ነው ይሉናል። Nature and Narture ይህንን አሁን ባለው ማስረጃ ኃይለ ሥላሴን እንመለከት። የ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰው ነበሩ። ይህም ማለት ወጣቱ ምንሊክ ነበሩ ማለት ነው። የገዙት፤ የነዱት ደግሞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ነበር። ይህም ማለት ዘመኑ የርሳቸው ዘመን አልነበረም (anamoly) ለማለት ነው። ቢሆንም ፊደልም ቢሆን ከፈረንጅ ጋር ቆጥረዋል። ሰዉ ማመስገን የማይሆንላቸው ተፈሪ መኮንን፤ “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ“ በሚለው መጽሐፋቸው፤ የሚያመሰግኑት ይህንኑ ፈረንጅና አንድ ከኦርቶዶክስ የኮተለክ አስተማሪያቸውን ብቻ ነበር። ተፈሪ መኮንን፤ እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህት የሌላቸው፣ በመጥፎ ሞግዚት ያደጉ ነበሩ። የዘውዴ ረታን፤ “ተፈሪ መኮንን” እና የፈታውራሪ ተክለሐዋሪያትን፤ “ሜሟር” ማንበብ ነው። አባት የላቸውም ያልኩት በሕይወት ሳይሆን ከስራቸው የተነሳ፣ ራስ መኮንን የሚያሳድጉ አባት አልነበሩም ለማለት ነው። ይህ እንግዲህ የኃይለ ሥላሴን ድብቅና ሽምቅ ፍቅር አልባ ነፍስ የቋጠረ ይመስለኛል። ጸጋዬ ገብረመድኅን፤ “በክልስ አባ ልበ እግረኛ” ግጥሙ፤ “..ከራሱ በስተቀር ሌላ ያለው የማይመስለው..” የሚለው አይነት መሆኑ ነው።

ከሌላ እናት የሚወለዱ አንድ ወንድማቸው፤ ደጃዝማች ይልማ፤ ቢኖሩም እሳቸውንም ቢሆን በመጽሐፋቸው ውስጥ ይከሳሉ። ይቀናቀነኝ ነበር! ይላሉ።

(ይቀጥላል)

========

August 08, 2016 

ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ሳምንት አቶ አሰፋ ጫቦ በቃለ-መጠይቅ መልክ በኢሜይል ከላክንላቸው ጥያቄዎች ለአንዱ፡ – “ሦስቱን መንግስታት በንጽጽር እንዴት ይገልጹዋቸዋል?” ለሚለው ሰፊና ዝርዝር ምላሽ ልከውልን ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ባለመቻላችንም ቀሪውን ክፍል አሳድረነው ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ አቅርበነዋል፡፡ አቶ አሰፋ ለሌሎች ጥያቄዎች የሰጡንን ምላሾችም ወደፊት በተከታታይ የምናወጣው ይሆናል፡፡

— ኃይለስላሴ ምክር የማይቀበሉ ነበሩ። ምክሩ ብዙ መልክ ይዞም መጥቶ ነበር። የእነ ቢትወደድ ነጋሽ፤የእነ ጄነራል መንግስቱ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ፣ ምክር ብቻ ሳይሆን ግልጽ ማስጠንቀቂያም ነበር። መካሪዎችን ከመቅጣት በስተቀር “ወይ ፍንክች!” ከዚያም ከእነ መንግስቱ ንዋይ ሙከራ ማግስት፣ አቶ ሐዲስ አለማየሁ፤ ወዲያ ወዲህ በማይል፣ ቁልጭ ባለ ቋንቋ፣ ይህ የባሪያ አሳዳሪ ሥርዓት ሊዘልቅም ሊያዛልቅም አይችልም ብለው በደብዳቤ ጽፈው መክረው ነበረ። ግን ወይ ፍንክች! ለምን ነበር የማይሰሙት። ይህ ድብቅ ተፈጥሮ፤“ከእኔ ሌላ ለኔ የሚያስብልኝ የለም!” ከሚል የመጣ ይመስለኛል።

ወጣቱ ምንሊክ ወደሚለው ልመለስ። የምንሊክ መንግስት አስገባሪና የባሪያ አሳዳሪ መንግስት ነበር። የሚያስገብረው ይህን በጦር የተሸነፈውን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ነበር። ባሪያም የሚፈነገለው በአብዛኛው ከደቡብ ኢትዮጵያ ነበረ። በምንሊክና በኃይለሥላሴ የመጀመሪያ ዘመናት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ውስጥ 30% ባሪያ ነበር። ኃይለሥላሴ በዚሁ መቀጠል ብቻ ሳይሆን ባሪያ ይገዙም ነበር። የተክለሐዋርያትን መጽሐፍ ማንበብ ነው። ባሪያ ነጻ ይውጣ የሚል የእንግሊዝ ድርጅት፤ አዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ ስለዚህ ጉዳይ ቢጠይቃቸው፣ የኃይለሥላሴ መልስ፡-“ታዲያ ባሪያ አሳዳሪው እንዴት ሊኖር ነው!?” የሚል ነበር።

ጣሊያን ገባና የዚህ የመሬት ይዞታውንም የባሪያ ሥርዓቱንም አፈራረሰው። ኃይለስላሴ ፈርጥጠው ከሔዱበት ሲመለሱ፣የመሬቱን ከምንሊክ ከወረሱት ዕጥፍ ድርብ አሳደጉት። አርበኛ ለተባለ መሬት ተሰጠ። ስደተኛ ለተባለ ጋሻ መሬት ተሰጠ። የውስጥ አርበኛ የሚባልም ነበርና ለዚያም ጋሻ መሬት ታደለ። መሬት የሚታደለው ያው ከደቡብ ኢትዮጵያ ነበር። ወለጋ ሲቀር። ወለጋም ጥንትም በስምምነት የገባ፣ በኋላም አምቻና ጋብቻ  በመሆኑ ነበር። ”የመሬት ለአራሹ!” ለመውደቂያቸው ዋናው ምክንያት የሆነው ሥረ-መሠረቱ ይኸው ነበር።

ኃይለስላሴ ራስ ወዳድ ነበሩ። አገር ምድሩ፤ ትምህርት ቤቱ፤ ከተማው ሳይቀር “የኃይለስላሴ” ነበር። አልጋ ወራሽም ሆነው ይኸው ነበር። ሐረርጌ “ተፈሪ በር” እንዴት ተፈሪ በር እንደተባለ የፊታውራሪ ተክለሐዋርያትን መጽሐፍ ማንበብ ነው። በአንጻሩ ለምንሊክ የነበረው፣ በምንሊክ ጊዜ የነበረው ብቻ ነበር። ለጣይቱ፤ ለቴዎድሮስ፤ ለራስ አበበ፤ ለገረሱ ዱኪና ቁጥር ስፍር ለሌላቸው የኢትዮጵያ ጀግኖች የተሰየመ፣ የሚረባ የሚታይ ነገር አልነበረም። ደርግ ነው የቴዎድሮስ አደባባይ ያለው። ደርግ ነው የበላይ ዘለቀ መንገድ ያለው። ደርግ ነው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያለው።

የኃይለሥላሴ ራስ ወዳድነት ቁንጮ፣በ1966 የሆነው ነበር። በኋላ ደርግ የሆነው የወታደሮች አሰባሳቢ ኮሚቴ፣ እያንዳንዱን ሚኒስቴር አራተኛ ክፍለ ጦር ወስዶ ሲያጉር፣ ኃይለ ሥላሴን አስፈቅዶ፤ “ውሰዳቸው!” ተብሎ ተፈቅዶ ነበር። አድሮ ዉሎ ልጆቻቸውንም፣ የልጅ ልጆቻቸውንም አስፈቅደው ወህኒ አወረዷቸው። ይሄ የፈረንሳዩን ንጉስ ሊዊ 15ኛ ያስታውሰኛል። après moi le deluge ነበር ያለው። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” እንዳለችው አህያ መሆኑ ነው። ወይም ሊዊ 14ኛ፤ እንደ ኃይለ ሥላሴ “ፀሐዩ ንጉስ!” ይባል የነበረው l’état, c’est moi አለ እንደሚባለው ነው፡፡ ”ኢትዮጵያ እኔ ነኝ፤ከኔ በኋላ……!”

ትልቁ ነገር እንግሊዝን እግዜር ይይላት! ፈርጥጠው የተገላገልነውን ለራስዋ የቅኝ ግዛት መስፋፋት መልሳ ባታመጣ ኖሮ፣ ጣሊያን በጠረገው መንገድ ኢትዮጵያ፤ በ1930ዎች ውስጥ ሬፑብሊክ ትሆን ነበር። አንድ የኃይለስላሴን ራስ ወዳድነት የሚገልጽ ዩኒቨርስቲ እያለሁ መጸዳጃ ቤት ያየሁት ነው። “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽንት ቤት!” ብሎ ተማሪ በጉልህና በማይለቅ ቀለም ጽፎ ነበር። ብለው! ብለው! በስንት ቀንና መከራ ሲያስለቅቁት እንደገና ይጻፋል። እኔ ታዲያ ወድጀው ነበር! ጥሩ ባህርይ ገላጭ ይመስለኝ ነበር!

ከዚህ ሌላ ኃይለሥላሴ የሐገር ሀብት ዘራፊ ነበሩ። ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ የአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያን፤ “የሕይወቴ ታሪክ”ን ማንበብ ነው። የአዶላ ወርቅ ገቢን፣ ገንዘብ ሚኒስቴር አያውቀውም። አንድ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀሰ ነው። ደርግ ሲፈትሽ፤ የኃይለ ስላሴ ትራሳቸውና ፍራሻቸው ውስጥ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ተወሽቆ ተገኘ። የፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን መጽሕፍ ማንበብ ነው።

የኃይለሥላሴ ነገር ብዙ ነውና ትንሽ መዝጊያ ጨምሬ ላብቃው። መላውን ዓለም ዞረዋል። በኢትዮጵያ ስም ነበር! ሳይጠሩ፤ አንዳንዴም “አይምጡ!” ሲባሉ ጭምር የግድ አስጨንቀው ይሔዱ ነበር። ለዚህ ምሳሌ 8 ጊዜ ወደ ዩጎዝላቪያ የተመላለሱትንና ማንን አስከትለው እንደሚሔዱ እንደገናም ከተክለ ጻድቅ መጽሐፍ ማንበብ ነው።

አንዴ አሜሪካ አይምጡ ሲባሉ አስጨንቀው ሔዱ። በኒክሰን ዘመን መሆኑ ነው። በዚያ ላይ ለኒክሰን ያለ – የሌለ፤ አሁን የኢትዮጵያ ችግር ያልሆነ ይዘበዝባሉ። ሰውዬው ሰልችቶታል። አስተርጓሚ የሆኑት ዶክተር ምናሴ ኃይሌ፤ ንጉሱ ያልተናገሩትን ግን የኢትዮጵያ ችግር የሆነውን ለኒክሰን ያስተረጉማሉ። በኋላም ምናሴ ላይ ይጮሀሉ። ይህንን  ጆን ስፔንሰር (John Spencer) Ethiopia at Bay የሚለው መጽሐፍ ውስጥ ማንበብ ይቻላል።

ሌላው ከ1967 በፊት አዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያንን የምታውቁ የኃይለ ሥላሴ ፎቶግራፍ ከመላእከት፤ ጻድቃንና ቅዱሳን ምስል ጋር ተሰቅሎ አይታችኋል። ኦርቶዶክሱ ቤተክርስቲያን ሲገባም ሳይገባም ይሰግዳልና ለኃይለሥላሴም ሲሰግድ ኖሯል ማለት ነው። ይህ የ50 ዓመት የራዲዮ፤ የጋዜጣና የቤተ ክህነት፣ “ለንጉሱ ተገዙለት!” የኢትዮጵያን ህዝብ የተማረውን፤ ማወቅ የሚገባውን ጭምር የንጉሱ አምላኪ አደረገው። የአንጎል እጥበት Brain Washing የሚሉት ነው። ዛሬ የዚያ ሁሉ ውጤት ስለ ኃይለስላሴ ታሪካዊ እውነት ሲነገር፣ ማተብ እንደተበጠሰ አድርገው ያያሉ።

የመንግስቱ ኃ/ማርያም ዘመን

አሁን ደግሞ መንግስቱ ኃይለማርያምን ትንሽ እንየው። ስለ መንግስቱ ከማስታውሰው፤አንዴ ሻለቃ ደበላ ዲንሳ (ያኔ ሻለቃ ነበር) የነገረኝ ነው። “ህዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም 60ዎቹ የኃይለሥላሴ ባለስልጣናት የተረሸኑ ለት ማታ ሸዋ ይነሳብናል!፤ ጦሩም ሊነሳብን ነው! በሚል ፍርሐት ብዙዎቻችን ያደርነው እዚያው ታላቁ ቤተ-መንግሥት ግቢ ነበር” አለ። “እንቅልፍ በዐይናችን ዞር አላለም! ጥዋት የምንጠብቀው መሪያችን፤ መንግስቱ ኃይለማርያም፣መጥቶ ማታ ከሰበሰበው መረጃ በመነሳት ያረጋጋናል የሚል ነበር” አለ። “በኋላም እንደተጠበቀው ጥዋት መንግስቱ መጣና ቦታውን ይዞ ተቀመጠ። ከዚያ ከቦርሳው የሆኑ ወረቀቶች አውጥቶ አደለን። ወረቀቶቹ የሚያሳዩት የወታደሩን አለባበስ (ዩኒፎርም) ንድፍ ነበር። ከዚያም ሲናገር፤ ያለፈው ሥርአት በመለዮና በልብስ ከፋፍሎን…!” ብሎ ቀጠለ፤” ትላንትና ማታ ስለሆነው አንዳችም ነገር አላነሳም! እንኳንስ ሊኖርበት የሰማዉም አይመስልም ነበር! የሚያውቀው ነገር ቢኖር ነው፤ እንዲህ ከመጤፍ ያልቆጠረው ብለን እኛም ተረጋጋን!” አለ።

ከዚህ ሌላ በወቅቱ የነበርን በመንግሥቱ ላይ የመግደል ሙከራ በተደረገበት ማግስት በቴሌቪዥን ቀርቦ የተናገረውን የምናስታውስ ይመስለኛል። ”በዚች በኩል (እግሩን እያሳየ) አንዲት ጥይት አልፋለች!”  ብሎ እንደ ዋዛ አለፈው። የሆነው ነገር ደግሞ ሲታይ የነበረበት መኪና ብጥቅጥቁ ወጥቶ በተአምር ነበር የዳነው። ይህንን ሁለቱን ያነሳሁት እነዚህ ዋንኛ የዕቡይ ባሕርይ (Sociopath) መገለጫ ባህርይ መሆናቸውን ለማሳየት ነበር። ፍርሐት፤ ሐዘኔታ አልፈጠረባቸውም። ተፈጥሮ ያንን ነስቷቸው ከሆነ ደግሞ አስተዳደጋቸው ገድሎ ቀብሮታል ማለት ነው። ስለዚህ፤ በውሻ፤ ድመት፣ አይጥ፣የዱር አውሬና የሰው ልጅ ሞት መካከል ያለው ልዩነቱ አይታያቸውም! አይሰቀጥጣቸውም! የታወቀ የተረጋገጠ የሰው ልጅ የሐዘን ስሜት የምንለው የላቸውም። ስለዚህም ሁለንተናቸው ወደሚቀጥለው እቡይ ተግባር ይሸጋገራል።

እነዚህን የመንግስቱን ባህርያት እስቲ በድርጊት እንይ። ጥር 26 ቀን 1969 ጀኔራል ተፈሪ በንቲንና ሌሎች የደርግ ባለስልጣናት በረሸነ ማግስት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከአደረገው ንግግር እንጥቀስ፡- “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረኳቸው!” ነው ያለው። ልብ ማለት ነው! ምሳም ቁርስም ተፈጥሮ የሚያስገድደን፤ ለመኖር መሠረታዊና አስፈላጊዎች ናቸው። ምግብ ነው! መንግስቱ የሚለን እነዚህን ሰዎች  በላኋቸው ነው። ህመሙ ይህንን ይመስላል! ለማለት ነው።

ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ለቁርስነት የሚያበቃ በአገሪቱ ላይ የፈጸሙት ነገር ነበር? መልሱን ፍቅረሥላሴ ወግደረስም ሆነ ፍስሀ ደስታ በየመጽሐፍቶቻቸው ላይ ገልጸዉታል። “የደርግ ጠቅላላ ጉባዔ ተሰብስቦ የመንግስቱን ኃይለማርያምን ሥልጣን ቀንሶ አዲስ አዋጅ ስለ አወጣ ይህንኑ አዋጅ በስራ ላይ አዋሉ!” ነው።  መንግስቱ ከደርግ ውስጥ መርጦ የገደላቸውን ሰዎች እንይ። ሻለቃ ሲሳይ ሐብቴ፤ ሻለቃ ኪሮስ አለማየሁ፤ ሻለቃ ሞገስ ወልደሚካኤል፤ የመቶ አለቃ አለማየሁ ኃይሌ የዩኒቨርስቲ ምርቁና ብቻ ሳይሆን አብዮቱን አብዮቱ ያሰኙትን ዋና ዋና ተግባርትን ያመነጩና በስራም ለመተርጎም የሚሯሯጡ የደርግ ሞተር የነበሩ ናቸው። እንደ መንግስቱ ደግሞ አዲስ አዋጅ ወጣ አልወጣ ይበልጡታልና ቁርስ ማድረግ ነበረበት።ሌላው ሽምቅ ተዋጊ መሆኑን ከሚያሳየው አንዳንድ ለመጥቀስ በኮሎኔል ሽታዬ፤ ኮሎኔል ወልዴ፤የፖለቲካ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪና ዲሬክተር በነበሩትና በሻለቃ ጌታቸው አግዴ ላይ የፈጸመው ነው። ጌታቸው ሊገደል ከመሔዱ ጥቂት ደቂቃ በፊት ከመንግስቱ ጋር በለሆሳስ ሚስጥር ይነጋገሩ ነበር። ሲገደሉ ደግሞ በጥይት አልተረሸኑም! መንግስቱ ቆሞ ሲመለከት ተቀጥቅጠው ነበር የተገደሉት! በመንፈንቅለ መንግስት ተካፍላችኋል የተባሉ ጄነራሎች የታሰሩበት ቦታ ሌሊት ሔዶ እያንዳንዱን በስም እየጠራ ያንቧርቅና ያዋርድ ነበር። ይህ እንግዲህ ጄኔራሎቹና ምስክርነት በተባሉ መጽሐፍት ላይ የተገለጸ ይመስለኛል። የዕቡይ ባሕርይ መገለጫ ነው!

ያለበለዚያ በሕይወቴ እንደ መንግስቱ አይነት አንድን ነገር የሚረዳ ፤ከተረዳም በኋላ የተውሶ ሳይሆን ገንዘቡ አድርጎ መልሶ የሚገልጽ፣ የሚያብራራ፤ስብሰባ መምራት ብቻ ሳይሆን የተንዛዛ የስብሰባ ውይይት ማጠቃለል የሚችል፤ሰውን ከፍቶ ማየት የሚችል ሰው አላጋጠመኝም።መንግስቱ ደግሞም እንደ ድመት ለስላሳ፤እንደ ለማዳ ውሻ ተለማማጭ፤ እንደ ነብር ቁጡም መሆን ይችልበታል! ያውቅበታል! ታዲያ ፈቶ አይቶና ገምቶ ነው! የባሕርዩ አካል ነው። መንግስቱን “ከኔ በላይ ማወቅ ላሳር!” የሚያሰኝ ያክል የማውቀው ይመስለኛል። የማውቀው ግን አይመስለውም ነበር። ይህ የመንግስቱ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ጭምር ይመስለኛል። የማውቃቸው የማይመስላቸው አሁንም ብዙ አሉ። ክፋት የለውም! ያለበለዚያ መንግስቱን ቤቱን፤ ባለቤቱን፣ ልጆቹን ጭምር አውቃለሁ። ልቆጥረው ከምችለው በላይ አብሬ በልቻለሁ፤ ጠጥቻለሁ። ሊያደርሰኝ የፈለገው የትና የት ቦታ ነበረው። እምቢ አልኩኝ። አሁን ሳስበው፣ “እንኳንም እምቢ አልኩኝ!” ከዚያስ የቁርጡ ማእከላዊ ይሻለኛል። በሕይወት ታሪኬ የምመለስበት ስለሆነ ልለፈው። የዚህ የህመሙ ምንጭ ምን እንደሆነም ሌላ ምክንያት ፈልጌ እመለስበታለሁ። ለአሁኑ የእያንዳንዱ ሰው ግምት ይበቃል ብዬ አስባለሁ።

የመለስ ዜናዊ ዘመን

በመጨረሻም መለስ ዜናዊን እንዴት ታየዋለህ? የሚለው ይመጣል። ለመንግስቱ ኃይለማርያም ያልኩት ለመለስ ዜናዊም እንዳለ እንኳን ባይሆን 75% የሚሰራ ይመስለኛል። አንድ ጉልህ ልዩነት ቢኖር መንግስቱ ሊቀ መንበር ሲሆን የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሻለቃ ነበር። ያም ማለት ቢያንስ የ20 ዓመት የመንግስት የስራ ልምድ ነበረው ማለት ነው። መለስ የአንድ ቀንም የስራ ልምድ አልነበረውም። ያ ብቻ ሳይሆን የስራ ልምድ አላቸው የሚለውንና የሚጠረጥራቸውን ሲቪሉንም ወታደሩንም “ዐይንህ ለአፈር!” አለ።ይህንን፤የእድሜም ልዩነት፤ የስራ ልምድ አለመኖርም ምክንያት አድርጌ መለስን በብርቱ መክሬው ነበር። ከልቤ የመከርኩት አንድ ሰው ቢኖር መለስ ዜናዊን ነበር። ይህም የሆነው በሐምሌ 1983 ነበር።

ቤተ መንግሥት ከገቡ በኋላ፤ ቀጠሮ ይዤ፤ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኜ፤ የመለስም ሰዎች በነበሩበት አጋጣሚ ነበር። ምናልባትም ከሁለት ሰአት በላይ የወሰደ ይመስለኛል። ያዳመጠኝም፤የገባውም፤የተረዳኝም ነበር የመሰለኝ። ቀጣይ ድርጊቱን ሳየው በተቃራኒው የተረዳኝ ነው የሚመስለኝ። ተረዳኝ ያልኩት መምስልና ማስመሰል መሆኑ ነው።መለስና ኢትዮጵያ እንዴት ይተያያሉ? የሚለውን አጥኝዎች ቢያዩት ጥሩ ይመስለኛል።ወያኔ የተነሳው ለትግራይ ሬፑብሊክ ነው። አድሮ ዉሎ አሜሪካኖችና ሌሎቹም ደጋፊዎቻቸው ”ኸረ ትልቁ ዳቦም ይቻላል!” ሲሏቸው፣ በተማረከ ወታደር ካምፕም ተሯሩጠው ኢሕአዴግ የሚል ፍጥረት ፈጠሩ። ያ ማለት እንግዲህ የመለስ ልቡ፤ቢያንስ ሙሉ ልቡ ኢትዮጵያ አልነበረችም ወደ ማለት ይወስዳል። መንግስታችንና ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከሆነ በኋላ ብዙ ተናግሯል። ከተናገራቸው አንዳንዶቹ በኢትዮጵያዊነቱና አብረን የምንካፈለው ማዕድ ስለ መኖሩ ጥርጣሬ ላይ የሚከት ነው። ለምሳሌ ያክል “የአክሱም ሐውልት ለዎላይታ ምኑ ነው?” ያለውን እንውሰድ። ማለትም፣ አክሱም የትግሬ ስለሆነ ዎላይታን አያገባውም እንደ ማለት ነው። ዎላይታ ለምሳሌነት ተነሳ እንጅ የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም በአክሱም ነገር የሚያገባው ነገር የለውም እንደ ማለት ነው። ይህም ድንገት “የኛው የኛ! የኛ ብቻ! የእናንተም የኛ!” ነው ወደሚለው የሚወስድ ይመስለኛል። በተግባር ላለፈው 25 ዓመት የታዩት ይህንኑ የሚደግፉ ይመስለኛል።ሌላው አንዴ መቀሌ ለምን ይሆን ሔዶ የተናገረው ነው። ቃል በቃል አላስታውሰውም። የትግራይን ሕዝብ፤ “እንኳን ከእናንተ ከወርቅ ሕዝብ ተፈጠርኩ!” አለ። ይህን ሲል ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር። የኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ባያምንበት እንኳን እንዴት አንዱን ብሔረሰብ ወርቅ ሌላውን ጨርቅ ይለዋል። የአባትነት፣ የመሪነት፤ በሰፊ መነጽር የማየት ንግግር አይመስለኝም። ሌላው ስለ ሰንደቅ አላማው የሚናገረው ነው። ጨርቅ ይለዋል። ሰንደቅ አላማ’ኮ የትም አገር ከጨርቅ ነው የሚሰራው! አርማ ስለሆነ ክብር እንጎናጸፋለን! ሰንደቅ አላማ ሲወርድና ሲወጣ ትምህርት ቤት ጭምር መዝሙር ይዘመራል። መንገድ የሚሔደውም፣ ባርሜጣ ካለውም አውርዶ ይቆማል። እንዳልኩት ዓርማ ነው! አይዘረጠጥም! “ከሰው መርጦ ለሹመት! ከእንጨት መርጦ ለታቦት!” እንዲሉ። ይህና ከላይ ስለ ሕገ መንግስቱ የተናገርኩት ሲጨመር የመለስ ዜናዊን ለኢትዮጵያ ያለው ታማኝነት በራሱ አንደበት የተነገረው ሲታይ የሚያጠያይቅ ይመስለኛል። እኔም ይኸው ማጠያየቄ ነው።

ከኔ ጋር ከአፍሪቃ አዳራሽ “የሰላምና የዲሞክራሲ ስብስባ (ድንቄም!) ጀምሮ ብዙም አልተጣጣምንም። ወደ መጀመሪያው “አቶ አሰፋ ለመሆኑ ምንድነው የሚፈልጉት?” ይለኝ ነበር። ሹመት ሽልማት እፈልግ እንደሁ ለመሰለል ይመስለኛል። ባንድ ሁለት ወያኔ ወዳጆቼ በኩልም የጠየቀኝ ይመስለኛል። ያ ሳይሆን ሲቀር ወረደብኝ። “ነፍስ ገሏል!” ብሎ በሌለሁበት 16 አመት ፈረደብኝ። ነገሩ “ወደ ኢትዮጵያ ዝር እንዳትል!” የሚል መልእከት ነው። ይኸው ዝር አላልኩም! አንድ ቀን በጥር 1984 የወጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ለአሰፋ ጫቦ ብቻ አደረገው። ተስፋዬ ገብረ አብ በመጽሐፉ እንደሚለው፤ ያንን መለሰ ዜናዊ ጽፎት በረከት ስሞዖን አምጥቶ፣ ሌላው ሁሉ ይቅር ብሎ ጋዜጣው ላይ አስወጥቶታል፡፡

ለማጠቃለል

“ሦስቱን መንግስታት በንጽጽር እንዴት ትገልጻለህ?” ከባድ ጥያቄ ቢሆንም ሞክሪያለሁ። ዋናው ነገር ለኢትዮጵያ ለወደፊቱ የተሻለ መንግስት እንጅ ካለፈውም ካለውም ምኑንም ምኑንም አልፈልገውም። የግድ አማርጥ ከተባልኩ ደግሞ የንጉሱን አልፈልግም። አስገባሪ፤ ባሪያ አሳዳሪ ስለሆነ አልፈልገውም! ንጉስ በችሎታ ሳይሆን በዘር ማንዘር ተረታ-ተረት ስለሚመጣ እኔ የምመርጠው የዘር ሳይሆን የባለሙያተኞች መንግስት ነው፡፡ ደርግንም አልፈልገውም! በአንጻራዊ አመለካከት ከሶስቱ ምረጥ ብባል ደርግን እመርጣለሁ። ደርግ ንጉስ አስወግዷላ! ኢትዮጵያን ሬፑብሊክ አድርጓላ! የገጠር መሬት አዋጅ አውጇላ! ለምስኪኑ ቤት ሰጥቷላ! የብሔረሰቦችን ጥያቄ በጥናት ለመወሰን የጥናት ተቋም አቋቁሟላ! የደርግ ዋናው ችግሩ የወረሰው ነበር! አብዮቱ በአብዮትነቱ ያመጣው ነበር! እናውቃለን ባዮች ለስልጣን ሲባል የወታደሩን ቃታ የሳብንበት፣ የቀረነውንም በሌላው ተጽዕኖ ህዝብ የፈጀንበት፣ ያፋጀንበት ባይኖር ደርግ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቼም ሊያገኘው የማይችለው አይነት መንግስት ነበር! “ከመሔድሽ ሌላ ምንሽንም ምንሽንም አልፈልግም!” የሚባል የረሳሁት አባባል አለ። በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት መልካም ምኞቴ ይኸው ብቻ ነው!

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/178849

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...