Thursday, January 19, 2023

ደሞዝ እየተከፈላቸውና እየተቀለቡ አገር የሚያፈራርሱና ማንነትን ተኮር ያደረገ ጭፍጨፋ የሚፈጽሙ፣ እንዲሁም  ህዝብን የሚያፈናቅሉ አዲሶቹ የአገራችን ገዢዎች!

ደሞዝ እየተከፈላቸውና እየተቀለቡ አገር የሚያፈራርሱና ማንነትን ተኮር ያደረገ ጭፍጨፋ የሚፈጽሙ፣ እንዲሁም  ህዝብን የሚያፈናቅሉ አዲሶቹ የአገራችን ገዢዎች!
ፈቃዱ በቀለ(/)

                                                                  ጥር 19 2023

መግቢያ

እንደሚታወቀው ማንኛውም ግለሰብ አንድ መስሪያ ቤት ወይም ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ በሚሰራበት ጊዜ በስራ ቦታው ብቃትነትን ማሳየትና ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን በሚሰራበት መስሪያ ቤት ወይም ኩባንያ ውስጥ ታማኝነት የሚጣልበትና ከመሰል የስራ ባልደረቦቹ ጋር በፀባይ የሚግባባ መሆን አለበት። የአንድ መስሪያ ቤት ብቃትነትና ለህዝብ የሚሰጠው አገልግሎት የሚመዘነው  ወይም የአንድ ኩባንያ ምርታማነትና ምርቱ በገበያ ላይ ተቀባይነት ማግኘት በመስሪያ ቤቱ ወይም በኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው በሚሰሩት ሰራተኞች ብቃትነትና ኃላፊነትን መወጣት ነው። በተለይም ደግሞ አንድ አምራች ኩባንያ፣ ለምሳሌ መኪናን እያመረተ ለገበያ የሚያቀርብ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጣለው በማኔጅሜንቱና ማኔጅሜንቱን በሚመራው ኃላፊ ሰው ነው። ስለሆነም ማኔጅሜንቱም ሆነ፣ ሌሎች ኢንጀነሮችና እስከተራ ሰራተኛ ድረስ በተመደቡበት ኃላፊነት ብቃትነታቸውን የሚያሳዩ ከሆነ ኩባንያው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ በመሆን በየጊዜው አዳዲስና የተሻሻሉ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ቀስ በቀስም ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ የመያዝ ዕድል ያጋጥመዋል። በተለይም በማኔጅሜንት ውስጥ ጊዜውን የጠበቀ መሻሻል ካልተደረገ ወይም ኃላፊነት የተሰጠው ሰው በሙስና ውስጥ ከዘፈቀ፣ ወይም ደግሞ መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች ከዋጋ አንፃር በማየት ርካሽ የመለዋወጫ ዕቃ ካስገባ ወይም ደግሞ ሶፍትዌሩን ማኑፕሌት ካደረገና ከተነቃበት ኩባንያው በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ቅጣት ሲከፍል፣ የማኔጅሜንቱ ኃላፊ ደግሞ ከስራው ቦታ ይነሳል። እንደገና የመቀጠር ዕድልም አያገኝም።

ወደሌሎች ነገሮችም፣ ለምሳሌ ከፍተኛ ኃላፊነትን ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ጽናትን የሚጠይቁ ለምሳሌ እንደፓይለት የመሳሰሉ ሙያዎች፣ ማንኛውም ዐይነት የምህንድስና ስራና ዕውቀት፣ አውሮፕላንና መኪናን መስራት የመሳሰሉት በቀጥታ የሚያያዙት ከሰው ህይወት ጋር ስለሆነ ፓይለቶችም ሆነ መሀንዲሶች ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጣልባቸው ናቸው። ተሳፋሪውም ሆነ አዲስ መኪና ገዝቶ ለመንዳት የሚፈልግ ሰው ዕምነቱን የሚጥለው በፓይለቶችና መኪናን በሚሰሩት በመሀንዲሶች ላይ ነው። ይህ ዐይነቱ የአሰራር ልምድና ዕምነትን በሰራተኞች ላይ መጣል በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የተስፋፋና ሙሉ በሙሉ ተቀባይነትን ያገኘ ነው። የምንበላቸው ምግቦችና የምንጠቀምባቸው ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በሙሉ በሰው ህይወት ላይ ጉዳትን እንዳያደርሱ ወይም ጤንነትን እንዳያቃውሱ ሆነው መሰራት አለባቸው። ማንኛውም ነገር፣ በተለይም መኪናም ሆነ ሌሎች የኤሊክትሮኒክስ ዕቃዎችና ማቴሪያሎች ፈተናንና ሙከራን ካለፉ በኋላ ነው ገበያ ላይ የሚቀርቡት። ወዲያውኑ ተመርተው ወዲያውኑ የሚሸጡ አይደሉም ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ኩባንያ በተከታታይ በሰው ህይወት ላይ አደጋን የሚያስከትል ምርት በሚሸጥበት ጊዜ ፈቃዱን ይነጠቃል።

ወደ መንግስት መስሪያቤትም ስንመጣ፣ ምርጫን አሸንፎ ስልጣን ላይ የሚወጣ ፓርቲ ስልጣኑን ከመረከቡ በፊት ከጠቅላይ ምኒስተሩ ጀምሮ ሌሎች ምኒስተሮችም ፓርሊያሜንት ውስጥ የፓርሊያሜንት ፕሬዚደንቱ ፊት በመቆም ህገ-መንግስቱን አስመልክተው ቃለ-መሃላ የመፈጸም ግዴታ አለባቸው። ሲምሉም በህገ-መንግስቱ መሰረት በህዝብ ላይ ሊክሰት የሚችለውን አደጋ በሙሉ እከላከላለሁ፤ የህዝቤንም ጥቅም አስጠብቃለሁ በማለት የጠቅላላው ህዝብ ጠበቃ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ ማለት ነው።  ስለሆነም አንድ ጠቅላይ ምኒስተር ጠቅላይ ምኒስተር ስለሆነ እንደፈለገው ሁሉን ነገር የማድረግ ልዩ መብት የለውም። ማንኛውም አገርንና ህዝብን የሚመለከት ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት መመርመርና መጠናት አለበት። ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜም ሊያስከትል የሚችለውን ጥቅምም ሆነ ጉዳት በፓርሊያሜንት ውስጥም ሆነ በሲቪል ሶሳይቲው ዘንድ ሰፊና የጠለቀ ውይይትና ክርክር መካሄድ አለበት። በተጨማሪም  የተለያየ ሙያ ባላቸው ኤክስፐርቶች መገምገም አለበት። ይህም ማለት አንድ ጠቅላይ ምኒስተር ምኒስተሮችን የመጠባበቅ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጠቅላይ ምኒስተሩም ሆነ እያንዳንዱ ምኒስተር ስራቸውን ለፓርሊያሜንቱ ማቅረብና መገምገም አለባቸው። እያንዳንዱም ፓርሊሜንቴሪያን በሚሰጠው የሰዓት ገደብ ውስጥ በአገዛዙ የሚቀርበውን ሪፓርት የመተቸትም ሆነ በምክንያታዊ መንገድ የመደገፍ መብት አለው። ከዚህ ውጭ እያንዳንዱ ምኒስተርም ሆነ ራሱ ጠቅላይ ምኒስተሩ ከህገ-መንግስቱ ውጭ ኃላፊነት የጎደለው ስራ ሲሰሩ በፓርሊያሜንት አጣሪ ኮሚቴ የመመርመርና የመገምገም ግዲታ አለባቸው። ድርጊታቸው አደገኛ ከሆነና አገርንና ህዝብን አደጋ ውስጥ የሚጥል ከሆነ በዕምነት ድምጽ ማጣት ከገዢነታቸው እንዲወገዱ ይደረጋሉ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ድርጊትና ወንጀል እየፈጸሙና እየተሳሳቁ ስልጣን ላይ የመቆየት መብት የላቸውም ማለት ነው። በመጥፎ ድርጊታቸውም በህግ ፊት እንደማንኛውም ወንጀለኛ መከሰስ አለባቸው። ስልጣንን ስለያዝን የፈለግነውን ነገር ማድረግ ስለምንችል በህግ የመጠየቅ ግዴታ የለብንም ሊሉ አይችሉም። በተለይም በተደራጀ መልክና በዕውቅ በዓለም አቀፍ የአገዛዝ ሰንሰለት ውስጥ በመግባትና የተሰጣቸውን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ አገዛዞች የአገርን ጥቅም፣ ታሪክንና ብሄራዊ ነፃነትን ያጎደፉ ድርጊቶችን ከፈጸሙ በህግ ፊት መቅረብና መጠየቅ፣ እንዲሁም ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው። ወንጀል እየሰሩ፣ ህዝብን እያሰገደሉ፣ ወይም አንድ ብሄረሰብ በማንነቱ ሲጨፈጨፍና ሲፈናቀል የማይመለከታቸው ከሆነና ዝም ብለውም የሚታለፉ ከሆነ እነሱን የሚተካው ሌላ ኃይል ተመሳሳይ ወንጀል እየሰራ የሚታለፍ ይሆናል። እንደልምድም ስለሚወሰድ በዚህ መልክ አንድ ህዝብና አገር ይበደላሉ። ስለሆነም ማንም ይፈጽመው ወንጀል ስለሆነ ወንጀለኛው የግዴታ መጠየቅና መቀጣት አለበት።

ወደ አገራችን ስንመጣ ግን  የገዢው መደብ ኃላፊነት፣ ከጠቅላይ ምኒስተሩ ጀምሮ እስከሌሎች ምኒስተሮች ድረስ ያለው ተግባርና ኃላፊነት በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም አገርንና ህዝብን የሚጎዳ፣ ብሄራዊ ነፃነትን የሚያስደፍር እርምጃ ሲወስዱ፣ ማህበራዊ መዝረክረክ ሲፈጠር ዝም ሲሉ፣ በተለይም በተሳሳተ ወይም በኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሲፈጠር ... ወዘተ. ወዘተ. ማንም የሚጠይቃቸው የለም። ችግሮቹ እየተወሳሰቡና በቀላሉ መቀረፍ የማይችሉ ስለሚሆኑ ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረጅም ጊዜ አንፃር ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚያናጋ ሁኔታ በመፈጠር በቀላሉ ሊገታ የማይችል የፖለቲካ ቀውስ ሊከስት ይችላል። በተለይም አሁን በግልጽ እንደሚታየው የአገራችን ጠቅላይ ምኒስተር ፍጹም አምባገነን በመሆንና ልጠየቅም አልችልም በማለት ከፖለቲካ እስከ ኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ እስከ ባህላዊ፣ ከሚሊታሪ ቀውስና  እስከ ብሄራዊ ነፃነት መደፈር ድረስ የሚያስከትል ወንጀል እየሰራ ማንም ሊነካኝና ሊሟግተኝ አይችልም በማለት ሰፊው ህዝባችን ግራ ተጋብቶ እንዲኖር ለማድረግ በቅቷል። ከዚህም በላይ በመሄድ በተጨባጭ አገርን የማፈራረስ ተግባር የሚፈጽምና፣ በተለይም ማንነትን ተኮር ያደረገ ጭፍጨፋና ማፈናቀል እንዲካሄድ የሚተባበርና ዝም ብሎ የሚያይ ጠቅላይ ምኒስተር ነው በዛሬው ወቅት አገራችንን አስተዳድራለሁ የሚለው።  ጠቅላይ ምኒስተሩ ፍጹም አምባገነን ከመሆኑ የተነሳ ሊጠይቁት ወይም ሊሟግቱት የሚፈልጉትን ሁሉ በዚህም በዚያም ብሎ አይ ያስራቸዋል፣ ካሊያም ደግሞ በአንዳች መንገድ ደብዛቸው እንዲጠፋ ያደርጋል። በመንግስት ተቋማትም ሆነ በአገዛዙ ላይ ትችትን ማቅረብ እንደወንጀል በመቆጠር ተቺዎች ትችታቸው ተገቢና የሚያሳምን ቢሆንም ካለበቂ ምክንያት በወታደሩ ላይ የመተቸት መብት የለባችሁም በማለት ይታሰራሉ።  እንግዲህ  ይህ ዐይነት የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነትና ህገ-መንግስቱን የሚፃረር ስራ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ነው የሚፈጸመው። የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታም ስንመለከት ሁሉ ነገር የተመሰቃቀለና፣ ልክ የማዕክለኛው ክፍለ-ዘመን ውስጥ የምንገኝ ይመስል አንድ ግለሰብ እንደፈለገው የሚጋልብባት አገር ለመሆን በቅታለች። ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የመንግስትና የአንድ አገዛዝስ ዋናው ሚና ምንድነው? አንድ አገዛዝስ እንደፈለገው አንድን አገር የማመሰቃቀል፣ ሀብቷን የመዝረፍ፣ በህዝብ ላይ ማንነትን ተኮር ያደረገ ጭፍጨፋ ሲካሄድ ዝም ብሎ የመመልከት፣ ወይም አያገባኝም የማለት መብት አለው ወይ? እንደዚህ ዐይነት ገደቡን የሳተ አገዛዝስ ስልጣን ላይ የመቆየት መብት አለው ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች  አጠር መጠን ባለ መልክ እንመርምር;

የመንግስትን ምንነትና አወቃቀር የመረዳት ችግር!

በአብዛኛዎቻችን በተለይም በፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍ በዚህም በዚያም ድምጻችንን በምናሰማው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ውስጥ ያለው  ትልቁ ችግር መንግስት ማለት ምን ማለት  እንደሆነና፣ ተግባሩስ ምን እንደሆነ በቅጡ አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ በህዝብ ተመረጠም አልተመረጠም መንግስት የሚባለው አንድ የገዢ መደብ የሚቆጣጠረው መኪና የታሪክ ግዴታ የሆነውን ያህል፣ የግዴታ በጊዜው መታደስና መሻሻል፣ እንዲሁም  ከሁኔታዎች ጋር እንዲስማማ ሆኖ መዋቀር እንዳለበት አለመረዳት ነው።  ያለፉትን ከሃምሳ ዓመታት  በላይ የበለጠ የፖለቲካ ትግል በጥብቅ ለተከታተለ መንግስትን አስታኮ የተደረገ ሳይንሳዊ ጥናትና ትንተና ለመደረግ ባለመቻሉ መንግስትንና የገዢ መደቦችን አስመልክቶ በመሀከላችን ግልጽ የሆነ አስተያየት በፍጹም የለም። ስለሆነም መንግስትን ፍጹማዊ እንደሆነና፣ እንደፈለገው ሁሉን ነገር ሊያደርግ እንደሚችል በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ አስተሳሰብ ሆኗል። ከዚህም በመነሳት የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠር ሁሉ የሚፈራ፣ ካለአግባብ የሚከበርና ከህግና ከህዝብ በላይ እንደሆነ ተቀባይነትን ያገኘ ግንዛቤ ለመሆን በቅቷል።፡ ስለሆነም ማንኛውም እየተነሳ ካለብዙ መጨነቅ፣ ማውጣትና ማውረድ በድፍኑ መንግስት መንግስት  ይድረስልን እያለ ይጮሀል። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ይድረስልን የሚባለው መንግስት ለምን ራሱ ጨፍጫፊና አስጨፍጫፊ እንደሆነ፣ ወይም ደግሞ ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ማፈናቀል ሲካሄድ ለምንድነው ዝም ብሎ የሚመለከተው? ተብሎ ጥያቄ አይቀርብም።

የመንግስትንና የአገዛዞችን ተግባር ውስጣዊ ይዘት በሚመለከት ከፕሌቶ ጀምሮ እስከ ሊበራሎችና የማርክሲስት ቲዎሬቲሺያን ድረስ ግልጽ የሆነ አቋምና የቲዎሪ ጥናት አለ። ፕሌቶና የፕሌቶንን ፈለግ የሚከተሉ ምሁራን በአንድ አገር ውስጥ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠር አገዛዝ የግዴታ ህዝቡን ፍትሃዊ በሆነ መልክ ማስተዳደር እንዳለበት ያስተምራሉ። በተጨማሪም መንግስትን የሚቆጣጠር የገዢ መደብ ከፍተኛ የሆነ የሞራል ብቃትና የፍልስፍና ዕውቀት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በፍልስፍና መነፅር ብቻ ነው የተወሳሰቡና የተሳሰሩ ነገሮችን መመልከትና ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱ ሳይንሳዊ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ከሰማይ ዱብ የሚሉ ሳይሆኑ ስልጣንን የሚይዙ ኃይሎች በቂ ዕቅወትና ሳይንሳዊ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በጭፍንና በራሳቸው ስሜት በመገፋት ህብረተሰቡን የሚጎዱ ፖሊሲዎች ተግባራዊ በሚያደርጉበት ጊዜ ነው።  በእነሱ ዕምነትም በመንግስትና በአገዛዙ በሚሰሩ ስህተቶች ወይም ኢ-ፍትሃዊነት የተሞላበት አገዛዝ  የተነሳ አንድ አገርና ህዝብ አንድ ላይ በመተሳሰርና በመተጋገዝ እንደሰውና እንደህዝብ ተግባራዊ ማድረግ የሚገባቸውን ነገሮች እንዳያደርጉ ይገደዳሉ። ስለሆነም ኢ-ፍትሃዊነት በሰፈነበት አገር ውስጥ ህዝባዊ ስምምነት ሊኖር አይችልም። የተሟላ ዕድገትንና ነፃነትም ሊኖር አይችልም ይላሉ። በሶክራተስ ተመስሎ አያሌ ጽሁፎችን በጻፈው በፕሌቶ ዕምነት  የአንድ አገር መሪና በሱ ዙሩያ የሚሰበሰቡ ግለሰቦች አይ ፈላስፋዎች መሆን አለባቸው፤ አሊያም ደግሞ በፈላስፋዎችች የሚመከሩና የሚመሩ መሆን አለባቸው ይላል።

ይሁንና እነፕሌቶን ይህንን አስተሳሰብ ያፈለቁት እንደዛሬው ዘመን መንግስት የሚባለው ነገር በተለያዩ ተቁማት ባልተዋቀረበትና፣ የካፒታሊዝም ስርዓት ባልሰፈነበት ዘመን ነበር። በጊዜው በእነሱ ዘመን ብዙ ነገሮች ያልተወሳሰቡ ስለነበሩ፣ መንግስት የሚባለው ነገር በወታደር፣ በፀጥታ ኃይል፣ በስለላ ድርጅት፣ በፖሊስ፣ በፍርድቤትና በልዩ ልዩ ተቋማት የሚገለጽ አልነበረም። ስለሆነም ጭቆናውና በግለሰቦች ላይ ያለው ተፅዕኖ ዛሬ እንደምናየውና፣ በተለይም በአገራችን ምድር ጎልቶ እንደሚታየው መጠኑን የሳተ ጭፍጨፋና ማፈናቀል አይካሄድም ነበር ማለት ይቻላል። ወደ ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመንና ከዚያም በኋላ እስከ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ድረስ በአብዛኛዎች የአውሮፓው አገሮች  ግለሰብአዊ ነፃነትን ያፈኑ አስቸጋሪ ወም ዲስፖታዊ አገዛዞች ስለነበሩ በጊዜው የነበሩት ፈላስፋዎች፣  ሊበራል በመባል የሚታወቁ የተገለጸላቸው  ምሁራን ሁኔታው ስላስገደዳቸው የግዴታ አንድ አገዛዝ ገደብ እንዲኖረው ራሱ በህግ የሚገዛና የህግ የበላይነትን የሚያከብር መሆን እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ። በተለይም በጊዜው ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው የከበርቴው መደብና እየዳበረ የመጣው የስራ ክፍፍል ዲስፖታዊ አገዛዞች በሰፈነቡት አገር ውስጥ ሊስፋፋና ሊዳብር አልቻለም፤ ስለሆነም የግዴታ የሪፑብሊካን አስተሳሰብ ተግባራዊ መሆንና የግለሰብአዊ ነፃነት መከበር  እንዳለበት የተረዱ ከፍተኛና የተወሳሰበ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን ለከበርቴው መድብና ለአገዛዞች የቲዎሪ መሰረት በመዘርጋት የግዴታ ጥገናዊ ለውጥ እንዲካሄድ ተፅዕኖ ማሳደር ተቻለ። ከተማዎችና መንደሮች ሲገነቡና የስራ-ክፍፍል ሲዳብርና የንግድ ልውውጥ ሲካሄድ ዲስፖታዊ አገዛዞች በዚህ ዐይነቱ እያደገና እየተስፋፋ በመጣ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ቀስ በቀስ ሊዳከሙ ቻሉ። ይሁንና ግን በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የፈለቀው የሊበራሊዝም ቲዎሪና የህግ የበላይነት አስተሳሰብ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ካፒታሊዝም እያደገና እየተወሳሰበ ከመጣ በኋላ ነው ማለት ይቻላል። ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጊዜ ጀምሮ በተለይም በካፒታሊዝም ዕድገትና ውስብስብነት የተነሳ በወዝአደሩ ላይ የሚደረገው ብዝበዛና ጭነት በማየሉ በጊዜው የነበሩት የማርክሲስት ቲዎሬቲሽያን ይህ ዐይነቱ የመንግስት አወቃቀር የመጨረሻው ሳይሆን፣ የግዴታ የገዢው መደብ መሳሪያ በመሆን ጭቆናን በተወሳሰበ መልክ የሚያስፋፋ እንደመሆኑ መጠን ይበልጥ ዲሞክራሲያዊና ሶሻሊስታዊ የሆነ መንግስታዊ አወቃቀር መመስረት እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ። በካፒታሊዝም ስርዓት ላይ የተመሰረተው የመንግስት አወቃቀር የግዴታ የኢኮኖሚው መሰረት ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ ይህ ዐይነቱ መንግስት ህዝባዊ ባህርይ የሌለውና በተለያዩ የኢኮኖሚ መሳሪያዎች ሀብት ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ካፒታሊስቱ መደብ የሚያስተላልፍ ስለሆነ በተለይም የሰራተኛው መደብ እንደልፋቱ ማግኘት የሚገባውን ለዩ ልዩ አገልግሎቶች ማግኘት አይችልም ነበር። በሚያገኘውም ተጨባጭ ደሞዝ ብቻ ከተወሰኑ ነገሮች ባሻገር ለጤንነቱ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ሊሸፍንለት አይችልም ነበር። በካፒታሊዝም ዕድገት የተነሳ የመንግስት ጥያቄ ያለቀለቀት ጉዳይ ስለሆነ የመሻሻል ጥያቄዎች መነሳት የለባቸውም በሚል እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አልተቻለም።

ይህ የሚያሳየን ምንድነው? መንግስት የሚባለው መኪናና የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠሩት ገዢዎች የመደብ ባህርይ እንዳላቸውና ሳይወዱ በግድ ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል እንደሚያደሉ ነው። ይሁንና በጊዜው እያየለ የመጣው የሰራተኛው መደብ እንቅስቃሴና የሱን ጥቅም የሚያስጠብቁ ፓርቲዎች መፈጠራቸው የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው እንደፈለገው በጭፍን ወደፊት የሚገፋ ሳይሆን የግዴታ የጥገና ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ተረዳ። ካለበለዚያ ተከታታይነት ያለው ህብረተሰብአዊ ግጭት ስለሚፈጠር የወዝአደሩ መደብ በሙያ በመደራጀትና ተጠሪዎችን በመምረጥ ከአሰሪዎች ወይም ከካፒታሊስቶች ጋር የሚደራደርበት አመቺ ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። ስለሆነም በፋብሪካ ውስጥ ተቀጠሮ የሚሰራው ሰራተኛ የስራ ሰዓት ገደብ፣ ከዚያም በማለፍ ከስራው ቦታ በሚባረርበት ጊዜ ሊኖረው የሚችለው መብት በህግ መደንገግ ቻለ። ከዚህም በላይ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሰራተኛው ከስራ-መስኩ በሚባረርበት ጊዜ  ሌላ ስራ እስኪያገኝ ድረስ የስራ-አጥ አበል ማግኘት እንዳለበት በማመንና፣ ማህበራዊ የጥገና ለውጦች መደረግ እንዳለባቸው በመረዳት ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ጭቆናዊ ከሆነው አሰራሩ በመጠኑም ቢሆን በመላቀቅ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ አነሰም በዛም ግለሰብአዊ ነፃነት የሚጠበቅበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ።

በዚህ መልክ አጠር መጠን ብሎ የቀረበው የመንግስት አወቃቀርና የገዢ መደቦች ባህርይና የአገዛዝ ስልት የሚያረጋግጠው የመንግስት መኪናና የገዢ መደቦች አገርን በህግ የማስተዳደር ኃላፊነትን መረዳት ግዴታ የትግል ውጤት እንደሆነ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩት የዲሞክራሲን ጥያቄ፣ ግለሰብአዊ ነፃነትንና የህግ የበላይነትን ማመንና በዲሞክራሲያዊ መርሆች መገዛት ፈቅደው የተቀበሉት ሳይሆን በትግል የተገኘና በከፍተኛ ደረጃ የተገለጸላቸው ምሁራን የማያቋርጥ ትግል ስላደረጉና ህብረተሰብአዊ አስተላለፉም ግልጽ እየሆነ በመምጣቱ ነው።  የተገለጸላቸው ምሁራንና የወዝአደሩ ተጠሪዎች ሳይፈሩ ሳይቸሩ የመንግስትን መኪና ከጨበጠው የገዢ መደብና ከከበርቴው መደብ ጋር በመጋፈጣቸው ገዢዎችንና የከበርቴውን መደብ ጭንቅላት መግራት ቻሉ። የገዢውና የከበርቴው መደብ እንደፈለጋቸው ሊፈነጩ እንደማይችሉና አንድን ህብረተሰብ በአቦሰጡኝና በማንአለኝበት ማስተዳደር እንደማይችሉ  በመገንዝባቸው ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኘነት የህግ የበላይነትና ግለሰብአዊ ነፃነት የሚጠበቁበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። በተለይም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕምርታን ማግኘትና፣ የማኑፋክቸሪንግ መስፋፋት የመንግስቱ መኪና ከዚህ ዐይነቱ ውስጣዊ-ኃይል ካለው የካፒታሊስት የአመራረት ስልት ጋር የግዴታ እንዲጓዝ አደረገው። በተለያዩም የመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች የካፒታሊዝምን ዕድገት የሚያደናቅፉና በሙስና የተተበተቡ ሳይሆን የግዴታ በቂ ስልጠና የሚሰጣቸው በመሆን ለአጠቃላዩ የህብረተሰብ ዕድገት አመቺ ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ።

እንደ ኢትዮጵያ ባለው፣ በብዙ ሁኔታዎች ወደ ኋላ በቀረ አገር ውስጥ ያለው  ትልቁ ችግር የመንግስት መኪና አወቃቀር የካፒታሊስት አገሮች የተጓዙበትን ሂደት ለመጓዝ ባለመቻሉና በየጊዜው በምሁራን እየተገመገመ እንዲሻሻል አለመደረጉ ነው። ቢያንስ ከአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ የተዋቀረውን ቢሮክራሲያዊ የመንግስት መኪና በምንመረምርበት ጊዜ ከውስጥ ቀስ በቀስ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ እየተኮተኮተና እየዳበረ ለመምጣት ባለመቻሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና ግለሰብአዊ ነፃነትን የማፈን ኃይሉ ከፍተኛ ነበር ማለት ይችላል፤ አሁንም ነው። በንጉሳዊ አገዛዝ ዙሪያ የተሰባሰቡት በገዢው መደብ ውስጥ የተካተቱት፣ በተለይም የምኒስተርነትን ማዕረግ የተከናነቡት ዘመናዊ የሚባለውን ትምህርት የቀሰሙ ቢሆንም ለአንድ አገር የተሟላ ዕድገት የሚያመች ዕውቀት የሌላቸውና፣  የነፃነትንና የዲሞክራሲን ትርጉም የተረዱ ባለመሆናቸው ከውስጥ መደረግ ያለበትን መንግስታዊ የጥገና ለውጥ ማድረግ ተሳናቸው። በተለይም ውስን በሆነው ምሁራዊ ሁኔታ የተነሳ ከካፒታሊዝም ዕድገት አንፃር፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂዎች መዳበርና እየተወሳሰበ የመጣውን የህብረተስብ ችግር ለመፍታት ሲባል የመንግስቱ መኪና መሻሻልና መስፋፋት እንዳለበት የሚያስተምርና ግፊት የሚያደርግ የተገለጸለት ኃይል ባለመኖሩ የመንግስቱ መኪና ከጭቆናዊ ባህርይው ሊላቀቅ አልቻለም። ይሁንና የአፄ ኃይለስላሴን አገዛዝና የመንግስትን መኪና በምንመለከትበት ጊዜ ከዚያ በኋላ ብቅ እንዳሉት አገዛዞች፣ ከደርግ ጀምሮ እስከወያኔና እስከዛሬው አገዛዝ ድረስ ይህን ያህልም ጨቋኝ እንዳልነበር መገንዘብ ይቻላል። የአፄው አገዛዝና የመንግስቱ መኪና እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ፣ በተጨማሪም የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠረው የገዢ መደብ  በካፒታሊስት የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ የተካተተ ቢሆንም የራሱ የሆነ ነፃነት(Relative Autonomy) የነበረውና በዓለም አቀፍ ደረጃም ከሞላ ጎደል የሚከበር ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። እስከተወሰነ ድረስ ፊዩዳላዊ ሞራልም ስለነበር እንደወያኔውና እንደ አቢይ አሀመድ አገዛዝ አረመኔያዊ አልነበረም። በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ የነበሩት ወታደሮችና ፖሊሶች የራሳቸውን ገደብ የሚያውቁ ነበሩ። እንደዛሬው በአንድ ግለሰብ የማይጠመዝዙ በመሆናቸውና ጎሳዊ ስሜትም ስላልነበራቸው የአገራዊና ብሄራዊ ስሜት የነበራቸው ናቸው ማለት ይቻላል። እንደፈለገው አንድ ፖሊስ አንድን ግለሰብ ሆነ ወይም ብዙ ሰዎችን የሚያሰቃይበት ሁኔታ አልነበረም።

የደርግን አገዛዝ ልዩ የሚያደርገው በአብዮቱ ዘመን የተፈጠረው የተመሰቃቀለ ሁኔታና ከአገዛዙ ውጭ የነበረው በአብዛኛው መልኩ ኢ-ዲሞክራሲያዊና አገር አፍራሽ  የሆነ ኃይልና ሁኔታዎችን ማንበብ ያልቻለው በግራና በነፃነት  ስም የሚካሄደው እንቅስቃሴና ግፊት  ጨቋኝ እንዲሆን እንደገፋፋው መገንዝብ ይችላል። እንደሚታወቀው ደርግ ስልጣንን ሲረከብ የመንግስቱን መኪና እንዳለ የተረከበ ወይም የነጠቀ በመሆኑና፣ ራሱም ደርግ የሚባለው ኃይል ሰፋ ባለ ጭንቅላትን በሚቀርጽና በሚያዳብር ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላለፈ በመሆኑ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ዘመናዊ ከሚባለው ጋር በሚጋጭበት ጊዜ በስድሳኛውና በሰባኛው ዓመተ-ምህረት በአብዛኛዎቹ የደቡብና የማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች የሚታየው የፈላጭ ቆራጭነት ወይንም የአምባገነን አገዛዝ ሁኔታ በአገራችንም ሊፈጠር ችሏል። በሌላ ወገን ግን በአብዛኛዎቹ የላቲን አሜሪካ አገሮች ብቅ ብቅ ያሉት የወታደር አገዛዞች ኩሙኒዝምን አጥብቀው የሚጠሉና ዲሞክራሲያዊ ኖርሞችን እንዲዋጉ ተብለው በአሜሪካ የሚሊታሪ ሳይንስ በሚሉትና በስለላ ድርጅቱ የሰለጠኑ በመሆናቸው፣ በመሰረቱ በጭቆና መንፈስ የተኮተኮቱ በመሆናቸው እንደዚያ ዐይነት ዕልቂት ለማድረስ በቅተዋል። ተግባራዊ ያደርጉ የነበረው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲም ከውስጥ ለተስተካከለ ዕድገት፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መዳበር የማያመች በመሆኑ የየመንግስታቱ መኪና የበለጠ ፋሺሽታዊ በመሆን ዲሞክራሲያዊ ኖርሞችን የሚያፍን ሆነ።  እንደሚታወቀው  ግሎባል ካፒታሊዝም ከሶስተኛው ዓለም ተብለው ከሚጠሩ አገሮች ሀብት ወደ ካፒታሊስት አገሮች ሊያስተላልፍ የሚችለው በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጨቋኝና ፋሺሽታዊ አገዛዞች ሲኖሩ ብቻ ነው። በዚህም አማካይነት የተወሰነው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት በዚህ ዐይነቱ የጭቆና ሎጂክ ውስጥ በመካተትና ራሱን ከአገሩና ከህዝቡ በመነጠል በቀላሉ በአሜሪካን ካፒታሊዝም በሚመራው ግሎባል ካፒታሊዝም የሚጠመዘዝ በመሆኑ  የጭቆናውና የፀረ-ዕድገቱ አንድ አካል  ነው። ስለሆነም ከራሱ ጥቅምና ኑሮ ባሻገር የማያይ በመሆኑ ህብረተስብአዊ ኃላፊነት የማይሰማው ሆነ። በዚህ መልክ በግሎባል ካፒታሊዝምና በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የአመጽ ሎጂክ ውስጥ የተኮተኮተውና የተካተተው የመንግስት መኪናና አገዛዙ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኤሊቱ ድህነትንና የስራ-አጥነትን የሚፈለፍል፣ በዕዳ አማካይነት ሀብት ከላቲን አሜሪካ አገሮች ወደ አሜሪካን ትላልቅ ባንኮች የሚያስተላልፍ  በመሆን አገራዊና ብሄራዊ ባህርይ የሌለው ኤሊት ለመሆን በቃ።

ወደ ደርጉ አምባገነናዊ አገዛዝ ስንመጣ ከአብዮቱ ጋር መያያዙና፣ በተለይም ደግሞ እንደመሬት ለአራሹ የመሳሰሉት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተግባራዊ መሆናቸውና፣ በተጨማሪም ገበሬው የመሰባሰብ ወይም የመደራጀት  መብት ማግኘቱ የደርግን አገዛዝ ለየት ያደርገዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በመንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉት ትላልቅ ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች አብዮታዊና ሶሻሊስታዊ የሚባሉትን መጠሪያዎች እንዲከናነብ ሊያደርጉት ችለዋል። ከዚህ ዐይነቱ በተግባር ከሚታይ ድርጊት ውጭ የደርግ አገዛዝ ከማርክሲስት ቲዎሪና ከሶሻሊስታዊ ርዕዮተ-ዓለም አንፃር ሲታይ አብዮታዊ ሊያሰኘው የሚያስችል አንዳችም ነገር አልነበረም። የማርክሲዝምን ወይም ሶሻሊስታዊ ቲዎሪን ለመረዳት ደግሞ የብዙ ዓመታት ጥናት የሚያስፈልግና ከሌሎችም ትችታዊ አስተሳሰብ ጋር መያያዝ ያለበት በመሆኑ አጠቃላይ በሆኑና በቀኖናዊ መልክ የቀረቡ ጽሁፎችን ብቻ በማንበብ መንፈስን ማነጽ አይቻልም። ስለዚህም ደርግ አምባገነናዊና አልፎ አልፎም አረመኔያዊ ዕርምጃዎችን መውሰዱ የሚያስደንቅ መስሎ ባይታይም፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት ራሱን ለመቆጣጠር አልቻለም።  በዚህ ዐይነቱ አረመኒያዊ ተግባርስ አገርን ማዳን ይቻላል ወይ? ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ አልቻሉም። ይሁንና ሁኔታውን በጥብቅ ለተከታተለና እስከዛሬ ድረስ ዘልቆ የሚያነታርከንንና የሚያጫርሰንን ሁኔታ ቀረብ ብሎ ላጠና ሰው ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ፖለቲካዊ ድርጊቶች በጭንቅላታችን ውስጥ ሰርገው ለመግባት አለመቻላቸውን ነው የህብረተሰብአችን አወቃቀር የሚያረጋግጠው። በሌላ አነጋገር፣ አንድን አገርና ህዝብ በፈላጭ ቆራጭነት አስተሳሰብና አልበገርም በማለት መግዛት እንደማይቻል ነው። ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑና ጥበባዊ ባህርይም ያለው በመሆኑ አንድን ህብረተሰብ በጥበብ ብቻና ሁኔታዎችን በሚገባ በማጥናት ነው ማስተዳደር የሚቻለው። ከላይ እንዳልኩት በተፈጠረው ከአገዛዝ ውጭ በሆነ ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴና፣ ይህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ እንደ አሜሪካን በመሳሰሉት ማንኛውንም ዐይነት ለውጥ በሚጠሉት ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይሎች በመታገዙ ሳይወድ በግድ የደርግ አገዛዝ ጨቋኝና አምባገነን ወደመሆን ለማምራት ቻለ። ይሁንና ግን የደርግ አገዛዝ ከወያኔና ከዛሬው በአቢይ አህመድ ከሚዘወረው የብልጽግና አገዛዝና የመንግስቱ መኪና ጋር ሲወዳደር የራሱ የሆነ ነፃነት ነበረው። በአብዮታዊ እርምጃዎች የተነሳ አነሰም በዛም ከግሎባል ካፒታሊዝም ቁጥጥር ውጭ የሚንሳቀስና በብድር ያልተበተበ፣ በነበረውም ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ከሚባሉት፣ እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ከመሳሰሉት ብድር የማግኘት ዕድል አልነበረውም። ከዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ስንነሳ የራሱ የሆነ ነፃነት የነበረውና ብሄራዊ ነፃነትን የማያስደፍር ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

ወደ ወያኔ አገዛዝ ስንመጣ በመሰረቱ ስልጣን ላይ የተቀመጠው የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊስቶችን አገርን የማዳከምና የመበታተን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ ነው። ስለሆነም በአፄ ኃይለስላሴና በደርግ ዘመን የተዋቀረውን የመንግስት መኪና ለራሱ በሚስማማ መንገድ በማዋቀርና በራሱ ካድሬዎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ በማድረግ ወደ ዘራፊነት የተሸጋገረ አገዛዝ ነው። ዘራፊነቱንም ሊያጧጥፈው የቻለው በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው በሚጠሩት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ሲሆን፣ ይህ ፖሊሲ በአንድ በኩል የወያኔ ካድሬዎችን ሲያደልብ፣ በሌላ ወገን ባልተስተካከለ ንግድና ዕዳ አማካይነት ሀብት ከኢትዮጵያ ምድር ወደ ካፒታሊስት አገሮች ሊሸሽ የቻለበትን ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረጉ ነው። በተለይም ወያኔን አጥብቀው የሚጠሉትና የጎሳ ፌዴራልዝም ተግባራዊ በማድረጉ የሚከሱት ታጋዮችና ፖለቲከኛ ነን ባዮች ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ሊረዱና ሊገባቸው የማይፈልጉት ወያኔ የአሜሪካኖችና የእንግሊዝ ኦሊጋርኪ መደብ ቅምጥ መንግስት የሆነና ከዋሽንግተን ረቆ በመጣው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የዘራፊትንና የአዘራፊነትን ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው። በሌላ አነጋር፣ ወያኔ በአገራችን ምድር ተግባራዊ ያደረጋቸው አገርን የሚያፈራርስና ድህነትን የሚያስፋፋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍልን በማደለብና ብልግናን የሚያስፋፋ ፖሊሲ ከአሜሪካና ከተቀረው የውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ ነው በአብዛኛዎቹ ታጋይ ነን ባዮች የሚታመነው። ይህም ማለት ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ረግጦ ሲገዛ፣ ህዝባችንን ሲገድል፣ በጎሳና በቋንቋ ከልሎ በህዝብ ዘንድ አለመተማመን ሲፈጠር ይህ ሁሉ የተጠነሰሰውና ተግባራዊ ለመሆን የበቃው በራሱ በወያኔ ብቻ ነው፤ ስለሆነም አሜሪካንና የተቀሩትን የካፒታሊስት አገሮች መወንጀሉ ትክክል አይደለም እያሉን የሚታዩ ነገሮችንና በሳይንስ ሊረጋገጡ የሚችሉ ነገሮችን አምነን እንዳንቀበል ያላደረጉት ጥረት የለም። የግሪክ ፈላስፎች እንደሚሉት አዕምሮ ማየት ካልቻለ ዐይንም ማየት አይችልም ብለው እንደሚያስተምሩን ለአብዛኛዎቻችን በግልጽ የሚታዩ ነገሮች እንዳይታዩንና ጥያቄም እንዳናቀርብ ለመገደድ ችለናል። ሰለሆነም በህዝባችን ላይ የደረሱት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮሎጂያዊ ቀውሶች በሙሉ ሊታዩን  በፍጹም አልቻሉም ። ይህም የሚያረጋግጠው ከዕውነተኛ የነፃነት ትግል አንፃር የእነዚህ ታጋዮች  ትግል ያልተሟላ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የወያኔን አገዛዝ እንቃወማለን፣ እንታገላለንም የሚሉት በሙሉ ፖለቲካቸውን ለመረዳትና መንፈሳቸው በዲሞክራሲያዊ መርሆዎች መታነጹን ለማወቅ እንቸገራለን። ከዚህም በሻገር ትግላቸው ብሄራዊ የሆነና የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ህዝባችንንም ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል ሁለ-ገብ ፖሊሲ ያላቸው ለመሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ ነው። ስለሆነም  ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሎጂክ ውጭ ለአገራችን የተሟላ ዕድገት፣ ለብሄራዊ ነፃነትና ለዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መታገላቸውን እንድንጠራጠር አድርጎኛል። ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ህዝባችንና አገራችንን ረግጦ ሲገዛ ግልጽና ሰፊው ህዝብ እንዲረዳው የሚያደርግ ደረጃ በደረጃ፣ ከመንግስት መኪና አወቃቀር አንስቶ እስከ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ድረስ ትንተና መስጠት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ትግሉ የተሟላና በቲዎሪና በሳይንስ ያልተደገፈ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።  ወያኔ ከስልጣን ላይ ከተነሳ በኋላ እሱን የሚተካው አገዛዝ ደግሞ ምን ምን ነገሮችን በቅደም ተከተል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የነደፈው አስተሳሰብና በጽሁፍ ያስቀመጠው አንዳችም ነገር አልነበረም። ይጠብቅ የነበረው አዲሱ አገዛዝ ምን ያደርግ እንደነበር ነው። ተስፋ የሚጣልበትና ሊበራል የሆነ አገዛዝ ስልጣንን የተረከበ እንደሆነ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ለመታመን በቅቷል።

ወደ አቢይ የብልጽግናው አገዛዝ ስንመጣ ወደ ውጭ ሊበራል መስሎ ስልጣንን ሊጨብጥ የቻለ ኃይል ሲሆን፣ እዚያው በዚያው ግን እያሳሳቀና እያታለለ ወደ ገዳይነት፣ ወደ ማፈናቅል፣ ማንነትን ተኮር ወዳደረገ ጭፍጨፋና በቀጥታና በግልጽ ወደ ዝርፊያ የተዘዋወረ አገዛዝ ነው ማለት ይቻላል። የአቢይን አገዛዝ ከወያኔው የሚለየው በግልጽ ሁለንታዊ የሆነ የባህል ጦርነት መክፈቱና፣ በተለይም በጴንጤ ቆንጠ ሃይማኖት ተከታዮች በመታቀፍ  በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ግልጽ የሆነ ጦርነት ማወጁ ነው። ሌላው በመሀከላቸው ያለው ልዩነት ወያኔ ከ17 ዓመታት የበረሃ የጦር ትግል በኋላ በአሜሪካን የስለላ ድርጀት አማካይነት የኢትዮጵያን የፀጥታ ኃይል በማንኮታኮትና በወታደሩ ውስጥ ያለውን ግኑኝነት በመበጣጠስ ስልጣን ላይ እንዲወጣ አመቺ ሁኔታ ማግኘቱ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ግን አቢይና አጋሮቹ የወያኔን ጡት እየጠቡ ያደጉና በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላታቸው የተኮተኮተ ስለሆነ ስልጣንን ሲጨብጡ የተሳሳተ ትረካቸውን መሰረት በማድረግ ነው ለእነሱ በሚስማማ መንገድ አገራችንን መበወዝ የጀመሩት። ይህም ማለት፣ እነአቢይና አሁን በአጠቃላይ ሲታይ የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች በጭንቅላታቸው ውስጥ ሲያብሰለስሉ የነበሩት ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ከአማራው ብሄረሰብ በተውጣጣ የገዢ መደብ ስትገዛ የነበረችና፣ ይህም መደብ የአማራውን ብሄረሰብ ጥቅም ብቻ በማስጠበቅ ሌሎችን ይጨቁን የነበረ ነው የሚል ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከአማራው ብሄረሰብ የተውጣጣው የገዢ መደብ ሌሎችን አካባቢዎች የቅኝ ግዛት በማድረግና በመበዝበዝ ዕድገታቸውን እንዳሰናከለባቸው ነው። ይህ ዐይነቱ የተሳሳተ ትረካ ደግሞ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ አወቃቀር ጋር የማይጣጣም ብቻ ሳይሆን ኢ-ሳይንሳዊም ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የገዢ መደቡን ስብጥር ስንመለከት ከአማራው ብሄረሰብ የተውጣጣ ብቻ አልነበረም። በጊዜው በነበሩት አገዛዞች፣ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለስላሴ ድረስ ያሉትን አገዛዞች ስንመለከት አማራውን ብቻ እንጠቅማለን፤ በኢኮኖሚና በባህልም እንዲያድግ እናደርገዋለን፤ በአንፃሩ ደግሞ ሌላውን አቀጭጨን እናስቀረዋለን በማለት የተነሱ አልነበሩም።  የሁለቱም አገዛዞች አካሄድ አንድን አገርና ህብረተሰብ ለመመስረትና በአንድ ባንዲራ ስር በማምጣት ቀስ በቀስ ዕድገትን ለማምጣት የተወሰደ እርምጃ ነበር። በተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል እጦትና በነበራቸው በጣም ደካማ የሆነ የምሁራዊ መሰረት ከታች ወደ ላይ መደረግ የነበረባቸውን የህብረተሰብ ግንባታ በቅደም ተከተል ማካሄድ አልቻሉም። በዘመናዊነት ስም የገቡት የጥገና ለውጦች በህዝቡ ዘንድ መቀራረብንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ አንዳንድ ለአገር ወዳድነትና ለብሄራዊ አንድነት የሚሆኑ ነገሮች ተግባራዊ ቢሆኑም ጠንካራና አገር አቀፍ፣ እንዲሁም ፈጣሪ የሆነ የህብረተስብ ክፍል ሊፈልቅ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአፄ ምኒልክና የአፄ ኃይለስላሴ የጥገና ለውጦች ለስር ነቀል ለወጥ ወይም ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለሚደገፍ የካፒታሊስት ስልተ-ምርት የሚያመች አልነበረም። ሰፋ ያለና አገር አቀፍ የሆነ የኢኮኖሚ ግንባታ በሌለብት፣ ከተማዎችና መንደሮች በተስተካከለ መልክ ባልተገነቡበት አገርና፣ እነዚህም በተለያዩ የመመላለሻና የመገናኛ ዘዴዎች ባልተያያዙበት አገር ስለኔሽን ቢልዲንግ(Nation
https://amharic-zehabesha.com/archives/178937

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...