Tuesday, December 6, 2022

 አዲስ አበባ ወይስ አዲስ አባባ? - ኤፍሬም ማዴቦ
አዲስ አበባ ወይስ አዲስ አባባ?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)   ክፍል አንድ

አባት የእጅ ስልኩን ረስቶ ወደ ቤት ሲመለስ፣ ትምህርት ቤት ያደረሰው ልጁ ሶፋው ላይ ተጋድሞ ያገኘዋል። ምነው ዱዱሻ ትምህርት የለም እንዴ? . . . . . አባቢ እኔ ትምህርት በቃኝ። አባት ይደነግጥና እንደሱ አይባልም ዱዱሻ ትምህርት የህይወት መሰረት ነውኮ! እሱን መች አጣሁት አባዬ፣ ግን ገና ከጅምሩ ማንነቱ የተፋቀ መሰረት ምን ያደርግልኛል? ትምህርት ቤት ስሄድ ስቀል የምባለው ባንዲራ ያ ባንዲራ አይደለም (ግድግዳው ላይ የተሰቀለውን ባንዲራ እያሳየው)፣ የምዘምረው መዝሙር የዜግነት መገለጫዬ አይደለም. . . . . ታዲያ ለምን ት/ቤት ልሂድ አባቢ?

አይዞህ ዱዱሻ ትዕግስት ባህላችን ነው፣ ግድ የለም መዝሙሩንም ዘምር፣ ባንዲራውንም ስቀል፣ ሙያ በልብ ነው። ምን ማለትህ ነው አባቢ! ልቤን እያፈረሱት የምን ሙያ በልብ ነውሱ? . . . . . ሁሉንም ችለህ በትዕግስት ትምህርትህን ተማር እያልኩህ ነው ልጄ! አባቢ ትዕግስት መሆን የማልፈልገውን የሚያደርገኝ ከሆነ ይቅርብኝ፣ትምህርትም ማንነቴን የሚቀይረው ከሆነ ባፍንጫዬ ይውጣ! ዱዱሻ እኔና እናትህኮ ታግሰን ነው እዚህ የደረስነው። . . . . አባቢ ታግሰህ የደረስከው የምትፈልገው ቦታ ነው?. . . . አዎ! ታድያ ሌላ ነገር በለኝ እንጂ ለምንድነው እኔ የማልፈልገው ቦታ እንድደርስ ታገስ የምትለኝ? እኔኮ አጉል ትዕግስት የሚሰጠኝን ማንነት ነው እንጂ መታገሱን አይደለም የጠላሁት፣ ደሞስ ስንቱን ልታገስ?

አባቢ . . . አቤት . . . . . አንድ ነገር ልጠይቅህ?  ጠይቀኝ። እባክህ እንጦጦ ውሰደኝ።

አባትና ልጅ እጅ ለእጅ ተያይዘው እንጦጦ ጫፍ ደርሰው መቀመጫ ቦታ ሲፈልጉ አራስ ዉሻ ታስደነግጣቸዋለች። አባት ትልቅ ድንጋይ አንስቶ ሊመታት ሲል፣ ልጅ አባዬ ተዋት እኛ ነን የሄድንባት እንጂ እሷ አልመጣችብንም፣ ደሞም ቤቱ ድረስ ሲመጡበት እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ እሱም ቤቱም ይፈርሳሉ አለው። ከዉሻዋ ትንሽ እልፍ እንዳሉ ዱዱሻ አባቱን የተጣመመ ዛፍ ያሳየውና፣ አባቢ እስኪ ይህንን ዛፍ እንደዛኛው ዛፍ ቀጥ እንዲል አድርገው ይለዋል። አባት ልጁ ለምን እንጦጦ ውሰደኝ እንዳለው ገባውና አለቀሰ።

ስማኝ አንተ አዲስ አበቤ፣ስሚኝ አንቺ አዲስ አበቤ የዱዱሻ ወላጆች ብትሆኑ ምን ታደርጉ ነበር? አልቅሳችሁ ትተዋላችሁ? የዱዱሻን ትምህርት ቤት ትቀይራላችሁ? ወይስ እንዲህ አይነቱን ዕብደት በቃ ትላላችሁ? አዲስ አበባን የሁላችንም ከተማ ታደርጋላችሁ ወይስ መስገድ አይሰለቻችሁ ነገር ለ”አዲስ አባባዎች” እየሰገዳችሁ ትኖራላችሁ? ይህ ጥያቄ ትክክለኛ አዎንታዊ ምላሽ ካላገኘ፣ሦስተኛዋ አልማዝ ከሁለቱ አልማዞች ካልተማረችና “አዲሶቹ አባባዎች” አደብ ካልገዙ አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤዎች፣ ለ”አዲስ አባባዎች” እና ባጠቃላይ ለኢትዮጵያችንም የመጨረሻው መጀመሪያ የመሆን ዕድልዋ ትልቅ ነው። እሳትን አለመነካካት ነው እንጂ ከነካካነው ሰው አይመርጥም፣ ሁላችንንም ነው የሚያቃጥለው። ስለዚህ እኔን እራሴን ጨምሮ እያንዳንድሽ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሆይ፣ አዲሶቹ አባባዎች አድርጉ የሚሉንን ፍጹም ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ድርጊት አንገታችንን ደፍተን የምናደርግ ከሆነና እነሱ ከህግ በላይ ሆነው እኛን ከነሱ በታች ሁኑ ሲሉን አሁንስ በቃ የማንል ከሆነ ዕዳው እንደ ዱዱሻ አባት እንጦጦ ላይ ወጥቶ የአዞ እምባ ማንባት ይሆልና እናስብበት።

በቅርቡ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴና ወ/ሮ አዳነች አበቤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተለዋወጡት ጥያቄና መልስ፣ "ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል" የሚለውን የአበው አባባል እንዳስብበት አድርጎኛል። ወ/ሮ አዳነች ዶ/ር ሲሳይ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚዘመረውንና የሚሰቀለውን የኦሮሚያ ክልል መዝሙርና ባንዲራ አስመልክቶ  የጠየቋቸውን ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት - “አዲስ አበባ የኦሮሚኛ ማስተማሪያ ካሪኩለም ስለሌላት፣ የአዲስ አበባ  ትምህርት ቢሮ የኦሮሚኛ ማስተማሪያ ካሪኩለም ከኦሮሚያ ወሰደ። ካሪኩለሙ ላይ ኦሮሚኛ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የኦሮሚያ ህዝብ መዝሙር ይዘመራል፣ የኦሮሚያ ባንዲራ ይሰቀላል የሚል አስገዳጅ ቃል አለ። ካሪኩለሙን እንዳለ ነው የወሰድነው፣ ካሪኩለሙን ለአዲስ አበባ እንደሚሆን አስተካክሎ መተግበር የአዲስ አበባ ድርሻ ነው” ። ይህንን አባባል አንዳንዶች ፌዝ፣አንዳንዶች ዕብሪት፣ አንዳንዶች ማንአለብኝነት፣ አንዳንዶች ደግሞ “ምን ታመጣላችሁ” አይነት እብጠት ብለውታል፣ለኔ ሁሉም ነው። የኦሮሚያን ክልል የትምህርት ካሪኩለም እንዳለ ነው የወሰድነው ያሉት ወ/ሮ አዳነች ካሪኩለሙ እንዳለ መወሰዱ ስህተት መሆኑ የገባቸው ይመስላል፣ ግን አዲስ አበባን መስሎና ተስተካክሎ መምጣት የነበረበት የሌላ ክልል የትምህርት ካሪኩለም እንዳለ መጥቶ አሳቸው በሚያስተዳድሩት ከተማ ውስጥ ተግባራዊ ሲሆን አፉቸውን ዘግተው በመቀመጣቸው ለተፈጠረው ስህተት ሃላፊነት መውሰድ አልፈለጉም። እሳቸውማ ጭራሽ በጥያቄና መልሱ ወቅት ያደረጉት በእልህ የታጀበ ንግግር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሳይሆን የኦሮሚያ ክልል እምባ ጠባቂ ነው ያስመሰላቸው።

የከንቲባ አዳነች አቤቤን አባባል ባሰብኩ ቁጥር የሚከነክነኝ አንድ ጉዳይ አለ፣ እስኪ ይታያችሁ እያንዳንዱ ክልል ህገ መንግስቱን እያሻሻለ የክልሉ ልጆች በሚማሩበት ቦታ ሁሉ የክልሉ ህዝብ መዝሙር መዘመር አለበት፣ ባንዲራውም መሰቀል አለበት ቢል፣ የየከተማው ከንቲባዎች ስራ መዝሙር ማዘመርና ባንዲራ ማሰቀል ሊሆን ነው እንዴ? ወይስ ሁሉም ክልሎች እኩል ናቸው፣ አንዳንድ ክልሎች ግን . . . . ነው ነገሩ?

በነገራችን ላይ ወ/ሮ አዳነች ሆን ብለው አይናቸውን ስለጨፈኑ ማየት ተሳናቸው እንጂ ጥያቄው አስፈላጊ፣ ትክክለኛና አግባብ ያለው ጥያቄ ቢሆንም፣ የዶር ሲሳይ ጥይቄ የአዲስ አበባ ተማሪዎች ለምን የኦሮሚያን ክልል መዝሙር ይዘምራሉ የሚል አይደለም። መሰረታዊው ጥያቄ የአዲስ አበባ ተማሪዎች የኦሮሚያን ክልል መዝሙር እንዲዘምሩ ሲደረግ ግቡ ምንድነው የሚል ነው። ግቡ ቋንቋ እንዲማሩ ከሆነ፣ መዝሙር በማዘመርና ባንዲራ በመስቀል ቋንቋ ማስተማር አይቻልምና፣ የአንድን ክልል ድብቅ አላማ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ከማስፈጸም ለምን አንዱኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሶ ለተማሪዎቻችን ትምህርት ቤት ውስጥ መሰጠት ያለባቸው ቋንቋዎች ዝርዝር ወጥቶ ተግባራዊ አይሆንም? ዶር ሲሳይንና ሌሎች ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ያሳሰበው ውይይት ሳይደረግና መግባባትና ስምምነት ላይ ሳይደረስ አንድ ክልል በራሱ የሚያደርገው መዳረሻው የጋራ ያልሆነ በዕብሪት የታጀበ ሩጫና፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የዚህ ሩጫ የክብር ስፖንሰር መሆናቸው ነው እንጂ መዝሙር መዘመሩ ብቻ አይደለም። አጉል ሩጫና ትልቅ ነኝ ብሎ መንገደኞች ላይ መውጣት ለሲኖ ትራክም “ቀይ ሽብር” የሚል ስም አሰጠው እንጂ የመኪናዎች ንጉስ አላሰኘውም!

ወ/ሮ አዳነች አበቤ የሚኖሩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፣ ውስጡን ለቄስ እንተውና የተመረጡትም በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ነው፣ በታማኝነት አገለግላለሁ ብለው ቃለ መኃላ የፈጸሙትም ለአዲስ አበባ ህዝብ ነው። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በግልፅ እንደሚያስቀምጠው አዲስ አበባ እራሷን በራሷ የምታስተዳድር ከተማ ናት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መተዳደሪያ የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግስት አይደለም። ህወሓቶች አፈናቅለው መሬቱን የቀሙት በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበረው ህዝብ ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ ያለው ህዝብ እንደነበረ ወ/ሮ አዳነች በእልህ ተናግረዋል። በእርግጥም ነበረው አሁንም አለው። ታድያ ምነው እሳቸው የሚያስተዳድሩት የአዲስ አበባ ህዝብም ማንነት፣ባህልና ቋንቋ እንዳለው ረሱ? ወይስ ማንነት፣ቋንቋና ባህል እራሳቸውን ብሔር ብለው ለሚጠሩ ስብስቦች ብቻ የተሰጠ ስጦታ ነው?  ለምንድነው ወ/ሮ አዳነች የዚህ የራሱ ማንነት ያለውና እራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ከተማ ህዝብ ልጆች ምን እንደሚል እንኳን በውል የማይረዱትንና በፍጹም ማንነታቸውን የማይገልጽ መዝሙር እየዘመሩ የአንድ ክልል ባንዲራ ሲሰቅሉ ዝም ብለው የተመለከቱት? ይህንን እንዲያደርጉለት ነው አንዴ የመረጣቸው? ለምንድነው ክብርት ከንቲባችን ለማይኖሩበትና ላልመረጣቸው ክልል ያሳዩትን ክብርና የውክልና መንፈስ እጁን አውጥቶ ለመረጣቸው ህዝብ የነፈጉት? ደሞስ ለምንድነው ይህንን ከአዲስ አበባ ውጭ ታስቦበትና ተሸርቦ የመጣ የፖለቲካ ሸፍጥ ማውገዝም ማስቆምም ሲገባቸው፣ጭራሽ “ለምን ተለጥጦ የፖለቲካ አጀንዳ ይሆናል” በሚል የከተማውን ምክር ቤት አባላት የሚከሱት?  “ጩኸቴን ቀሙኝ” ካልሆነና በግልጽ እንነጋገር ከተባለ፣ ነገሩኮ ከቅርብም ከሩቅም የሚታይ የፖለቲካ አጀንዳ ነው፣ የተሰጣቸውን የፖለቲካ አጀንዳ እያሰፈጸሙ ያሉትም እራሳቸው ወ/ሮ አዳነች ናቸው።

አዲስ አበባ በአስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ውጭ የሆነችና የኦሮሚያ ህገ መንግስትም የኦሮሚያ መንግስትም በፍጹም የማይመለከታቸው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት። ይህንን እውነት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣የኦሮሞ ልህቃን፣ የኦሮሞ ሶሻል አክቲቪስቶችና የኦሮሚያ ክልል መንግስት በውል ሊረዱት ብቻ ሳይሆን የተረዱትን በተግባር የመተርጎም ህገ መንግስታዊ ግዴታም አለባቸው። የጡንቻው መንገድ ከአሸናፊና ተሸናፊ ውጭ ሌላ ምንም የሚሰጠን አዲስ ነገር የለም። ሁሌ እንዳሸነፈ የሚኖር እንደሌለ ሁሉ ሁሌ ተሸንፎ የሚኖርም የለም፣ ዝንተ አለም  እየተሸናነፍንና አንዳችን ሌላችንን እያጠፋን መኖርም አንችልም። ስለዚህ የሚበጀን ኦሮሞው ከአማራ፣ አማራው ከጉራጌው፣ ጉራጌው ከትግሬው፣ ትግሬው ከሱማሌው፣ ሱማሌው ከከምባታው፣ ከምባታው ከሲዳማው ወዘተ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን የኛንም፣ የከተማችንንም፣ የአገራችን የኢትዮጵያንም የህይወት ውጣ ውረድ እያሸነፍን በሰላም መኖር ነው።

አዲስ አበባ ላለፈው 30 አመት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች፣ ይህ ህገ መንግስታችን ላይ ያለ ጉዳይ ነው ብለው ነበር ወ/ሮ አዳነች። እንደዚህ የሚል አንቀጽ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ላይ እንደሌለ ግልጽ ነው። ለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ “ህገ መንግስታችን” ያሉት የትኛውን ህገ መንግስት ነው? ወይስ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ በየትኛውም የሃላፊነት ቦታ ሲቀመጥ (የአገር መሪም ቢሆን) “ህገ መንግስታችን’ የሚለው የኦሮሚያን ክልል ህግመንግስት ነው? መልሱን ለሳቸው እተዋለሁ። ወ/ሮ አዳነች የማን ቋንቋ ማንን ጎዳ? ሰዎች ተጨማሪ ቋንቋ በማወቃቸው ይጠቃማሉ እንጂ ማንን ጎዳ? አብረው የሚያድጉ ጨቅላ ህጻናት አዕምሮ ውስጥ ምንድነው እየጻፍን ያለነው ሲሉ ተከታታይ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል። መልሱ ቀላል ነው። ቋንቋ ይጠቅማል እንጂ ማንንም አይጎዳም፣ ጎድቶም አያውቅም። ቋንቋ የሚጠቅመን ግን የአገራችን የስራ ቋንቋዎች የትኛዎቹ ይሁኑ፣ በየትኞቹ ቋንቋዎች እንግባባ፣ ልጆቻችንን በየትኞቹ ቋንቋዎች እናስተምር ብለን ስንስማማና ስምምነታችንን በህግ ስናስረው ነው እንጂ፣ ማንም እየተነሳ የራሱን ቋንቋ ሲጭንብን አይደለም። የጎዳን በማንነት ስም የሚጫንብን ጭነት ነው እንጂ ቋንቋው አይደለም! ደሞስ ባንድራችን የተለያየ ነው፣ ባንዲራችንን የምንሰቅልበት መዝሙርም የተለያየ ነው፣ የኛ ባንዲራ እናንተጋ ይሰቀላል የናንተ ባንዲራ ግን እኛጋ አይሰቀልም እየተባባሉ የሚያድጉ ልጆችን አብረው የሚያድጉ ልጆች ናቸው ማለት እንችላለን? ልጆቻችን አብረው አደጉ የምንለው አንድ ግቢ ውስጥ ስለተማሩ ነው እንዴ ለዛዉም እነሱን የማይወክል ባንዲራ ስቀሉ እያልን እያስገደድናቸው?

ወ/ሮ አዳነች አብሮነት በቦታ ቅርበት ብቻ የሚገለጽ ከመሰሎት ተሳስተዋል፣ አገራዊ አብሮነት ከቦታው ቅርበት ይልቅ የጋሪ ትርክት፣የጋራ ማንነት፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ግብና ስነልቦናዊ ቅርበት የሚገዛው እሴት ነው። እንዲህ አይነት የጋራ እሴቶች ሲኖሩን ነው ውቅሮ፣ደብረታቦር፣ይርጋለም፣ያቤሎ፣ጬንቻ፣ጎዴና አሶሳ ውስጥ ተወልደው ያደጉና አንድም ቀን ተያይተው የማያውቁ ወጣቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ውስጥ ሲገናኙ ሁሉም በአንድ ቃል ኢትዮጵያዊያን ነን ለማለት የማይቸገሩት። በግልጽ እንነጋገር ከተባለም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሰላሳ አመታት ከራሴ ውጭ ሌላ ቋንቋ አልማርም ያለው ነው የተጎዳዉ እንጂ ቋንቋ በማወቁ የተጎዳ ህዝብ የለም። እደግማለሁ የአዲስ አበባ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህጻናት አፋን ኦሮሞ እየተማሩ ቢያድጉ ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ግን እዚያው ክልሉ ውስጥ ይሰቀል እንጂ አዲስ አበባ ውስጥ ምን ይሰራል? አለቦታው ወርቅም አያምርምኮ!

የአዲስ አበባ ልጆች ኦሮሚኛ እንዲማሩ ከተፈለገ የት፣እንዴት፣መቼ የሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎችን በጋራ መመለስ ነው ያለብን እንጂ፣ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ ቢያውቀው የሚጠቅምውንና አገራችን ውስጥ የፌዴራል የስራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛን አየገፋን መሆን የለበትም፣ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋ መኖር አለበት ካልን ሌሎቹን ቋንቋዎች የምናሳድገው አማርኛን እያሳነስን መሆን የለበትም። አማርኛምኮ ማደግና መጎልበት ያለበት ቋንቋ ነው!

ወ/ሮ አዳነች እስኪ እኔንም ይስሙኝና አንድ ጥያቄ ልጠይቆት - ህፃናትን በጠመንጃ እያስገደድን፣ ወላጆችን ኡኡ እያሰኘንና የከተማ ነዋሪውን ህዝብ ጸጥታ እየነሳን አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሁለት የተለያየ መዝሙር በሁለት ተለያየ ቋንቋ እንዲዘመር ስናደርግና ሁለት የተለያየ ባንዲራ ስናሰቀል፣ ህጻናቱን መቀራረብ ነው መራራቅ እያስተማርናቸው ያለነው? ወይም በእርሶ በራስዎ ቋንቋ፣ ይህንን ስናደርግ በህፃናቱ አዕምሮ ውስጥ ምንድነው እየጻፍን ያለነው? ጥላቻ፣ፍቅር፣አንድነት ወይስ ልዩነት? ወ/ሮ አዳነች፣ ከድፍረት ዕውቀት፣ የጋራ መዳረሻ ከሌለው ሩጫ ማስተዋል የተሞላበት ዝግታ፣ከቁጣ ምክር፣ ከመጨፍለቅ ማቀፍ ይሻላልና እባክዎትን አጠግብዎ ብዙ አዋቂዎች አሉና ቁጭ ብለው ይማሩ።

የአዲስ አበባ ከንቲባ ከሶስት ወራት በፊት “መዝሙሩ ይዘመራል፣ባንዲራውም ይሰቀላል” ብለው በአደባባይ የዘሩት ፍጹም ሃላፊነት የጎደለው ፀረ-አንድነት ዘር ይሄውና ዛሬ ፍሬ አፍርቶ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል አፉን እንዲዘጋ የተደረገው ጠመንጃ አዲስ አበባ ውስጥ እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት (ሽሮ ሜዳ)፣ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኅኔዓለም ት/ቤትና ብሔራዊ የህጻናት መዋያና አንደኛ ደረጃ ት/ቤት (ቂርቆስ)  ገብቶ ተማሪዎችን፣ ወላጆቻቸውን፣አዲስ አበባንና ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላም እየነሳ ነው። ሐሙስ ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በቀድሞው አምሃ ደስታ በዛሬው እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት ውስጥ የኦሮሚያ ክልልን መዝሙር እየዘመራችሁ የኦሮሚያን ባንዲራ መስቀል አለባችሁ ተብሎ በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመው ወንጀል በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ወይም እንዲህ አይነት ብልግና በፍጥነት የማይቆም ከሆነ፣ ይህንን ተክትሎ የሚነሳውን አገራዊ ቀውስና የርስ በርስ ግጭት ጀማሪዎቹም የችግሩ ሰለባዎችም ማቆም እንደማይችሉና ከሁሉም በላይ ደሞ ይህ የጀብደኝነት ጉዞ አገራዊ ኪሳራ እንጂ ሌላ ምንም ነገር እንደማያስገኝ የዚህ ችግር ባለቤቶች ሁሉ ሊገነዘቡ ይገባል።

የአዲስ አበባ ከተማ በጆግራፊ አቀመመጧ በቀኃስና በደርግ ዘመን በሸዋ ጠቅላይ ግዛት/ ክፍለ ሐገር ውስጥ ነበር የምትገኘው፣በሽግግሩ ግዜ አዲስ አበባ “ክልል 14” በመባል ትታወቅ እንደነበር የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው። ማን ያውቃል አዲስ አበባ ለወደፊት ሌላ ቅርጽና አድራሻ ሊኖራት ይችላል፣ ዛሬ ግን አዲስ አበባ በአስተዳደር ሳይሆን በጆግራፊ አቀመመጧ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ ከተማ ናት። ይህ ማለት ግን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አዲስ አበባን ያስተዳድራል ማለት አይደለም፣ አስተዳደራዊ አቀማመጥና ጆግራፊያዊ አቀማመጥ እጅግ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፣አንዳንዴ ይህ ልዩነት የሰማይና የምድርን ያክል ነው። አፍሪካ ውስጥ ሌሴቶ ሙሉ ለሙሉ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የምትገኝ አገር ናት፣ ጋምቢያም በሴኔጋል የተከበበች አገር ናት፣ ግን ደቡብ አፍሪካ ሌሴቶን፣ሴኔጋሎች ጋምቢያን የኛ ነው አይሉም፣ መዝሙራችንን ዘምሩ ባንዲራችንን ስቀሉም አይሉም።

አዲስ አበባ ሁሉም ኢትዮጵያዊ “የኛ” የሚላት፣ የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን፣አፍሪካውያንና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የሚኖርባት እራሷን በራሷ የምታስተዳድር ከተማ ስለሆነች አዲስ አበባን የኔ ናት የሚል የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል ሊኖር አይገባም። ደሞስ እንዴት አይነት ዕብደትና ምን አይነት እብሪት ነው ከ80% በላይ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባትንና በቋንቋ፣ በባህልና በስነልቦናዊ ዘይቤ የማትመስለንን ከተማ የኛ ናት የሚያሰኘን? 120 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ዋና ከተማችን የሚሏትንና የኢትዮጵያን 2/3ኛ አገራዊ ምርት (GDP) የምታመርት ከተማ የኛ ናት ብለን በየትምህርት ቤቱ እየሄድን ባንዲራችንን ስንሰቅል በከተማዋ ውስጥ ለአስር ተከታታይ ትውልድ የኖረውንና ከተለያዩ የአገራችን አላባቢዎች መጥቶ አዲስ አበባን “አደስ አበባ” ያደረጋትን ህዝብ ምንድነህ እያልነው ነው? ደሞስ ያልገነባነውን፣ አንጻራዊ በሆነ መንገድ የማንኖርበትንና ቋንቋችን የማይነገርበትን ከተማ የኛ ነው ስንል፣ የኛ ነው የምንለው መሬቱን ነው፣ህዝቡን ነው ወይስ መሬቱንና ህዝቡን ነው? በአዲስ አበባ ከተማ የማንነትና የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ህዝበ-ውሳኔ ይሰጥ ቢባል የትኛው ህዝብ ነው ህዝበ-ውሳኔውን የሚሰጠው? የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ? የኢትዮጵያ ህዝብ? ወይስ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖረው የኦሮሞ ህዝብ? ድምጽ ለመስጠትስ መስፈርቱ ምንድነው የሚሆነው? ብሔር፣ ቋንቋ ወይስ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መሆን?

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተፈጥሮ ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠችው መብት ነው እንጂ ማንም የሚሰጠንም የሚከለክለንም መብት አይደለም ብለው ጫካ ገብተው ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ የታገሉ ልህቃን የአዲስ አበባ ህዝብ የ“ራሴን ዕድል በራሴ ልወስን” ብሎ ቢጠይቃቸው እሱ መብት ያንተ አይደለም የመሬቱ ነው ሊሉት ነው? አንተ “ህዝብ” አይደለህም ሊሉት ነው? ወይስ ሰዎቹ ጭራሽ ከጫካ ሲመለሱ ህዝብ፣መሬትና መብት ተደባለቀባቸው?

ቤልጂግ እንደ ኢትዮጵያ ፌዴራል የመንግስት ሥርዓትን የምትከተልና የፈረንሳይ፣የዳችና የጀርመን ቋንቋ የሚነገርባት አገር ናት። ቤልጂግ ውስጥ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ዋሎኖችና ዳች ተናጋሪ ፍላሚሾች በብራስል ከተማ የባለቤትነት ጥያቄ ለረጂም አመታት ተወዛግበዋል። ቤልጂጎች ዛሬ በሰላም የሚኖሩት ለዘመናት ያጋጨቻቸውን ከተማ ብራስልስን እራሷን የቻለች ክልል ካደረጓት በኋላ ነው።

የአውሮፓ ህብረት መዲና የሆነችው ብራስልስ በጆግራፊ አቀማመጧ ሙሉ ለሙሉ የምትገኘው ፍላሚሽ ተብሎ በሚጠራው የዳች ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚገኙበት ክልል ውስጥ ነው፣  በከተማዋ ውስጥ በብዛት የሚኖሩት ግን ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ዛሬ ብራስልስ የራሷ ክልላዊ አስተዳደር፣ የራሷ ፓርላማና የራሷ ባንዲራ አላት። የብራስል አካባቢ ክልል ፓርላማ 89 አባላት ያሉት ሲሆን፣ 72ቱ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች 17ቱ ደሞ ዳች ተናጋሪዎች ናቸው። ብራስልስ በጆግራፊ አቀማመጧ ሙሉ ለሙሉ የምትገኘው ፍላሚሽ በሚባለው ክልል ውስጥ ቢሆንም አብዛኛው የከተማዋ ኗሪ ግን ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ዋሎኖች ስለሆኑ፣ በብራስል አካባቢ ክልል ፓርላማ ውስጥ አብዛኛውን መቀመጫ የያዙት ዋሎኖች ናቸው። ይህ የሚያሳየን ሰዎች ሲሰለጥኑንና ለሰው ልጅ መብትና ነጻነት ያላቸው ክብር ከፍተኛ ሲሆን ቅድሚያ የሚሰጡት ለመሬት ጆግራፊያዊ አቀማመጥ ሳይሆን በመሬቱ ላይ ለሚኖረው ህዝብ መሆኑን ነው። እኛስ መቼ ነው እንደነሱ የምንሆነው? ወይስ የኛ ምርጫ በሰለጠነ አለም ውስጥ እየኖርና ከሥልጣኔ ጋር የማይገናኝ ስራ እየሰራን መኖር ነው? መቼ ይሆን ከጉልበት ለሃሳብ፣ ከጠመንጃ ለውይይት፣ ከሁሉም በላይ ደሞ ከመሬት ይልቅ መሬቱ ላይ ለሚኖረው ህዝብ ቅድሚያ ሰጥተን ሰው መሆናችንን የምናረጋግጠው? መቼ ነው አዲስ አበባ የኦሮሚያን ባንዲራ እየሰቀለች በስም ብቻ እራሷን በራሷ የምታስተዳድር ከተማ መሆኗ ቀርቶ የኢትዮጵያንና የራሷን ባንዲራ እየሰቀለች እራሷን በራሷ የምታስተዳድር ክልል የምናደርጋት?

ክፍል ሁለትን በሚቀጥለው ሳምንት ጠብቁ

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/178061

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...