Tuesday, December 13, 2022

 

- እንደመንደርደሪያ

‘‘ወያኔ/ትግሬ ከሚገዛኝ ሳጥናኤል ቢገዛኝ ይሻለኛል?!’’

(አቡነ ጴጥሮስ/የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ)

ዋልድባ የማን ነው… እዚህ ቁጭ ብላችሁ ጣላችሁን ከምትጠጡ ግንባር ዘምታችሁ አንድ እፍኝ የማይሞሉ ሰዎችን መደምሰስ አቅቷችሁ ነው …?!

(አቡነ መቃርዮስ/ሊቀ ጳጳስ)

‘‘በዚህ ጦርነት ላይ የሰማይ ሰራዊት ጭምር ሊሳተፉና ከጎናችን ሊቆሙ ይገባቸዋል፤’’

(አቶ አበባው አያሌው፤ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር)

‘‘… ወያኔ/ሕወሓት ከምድር-ገጽ ብቻ ሳይሆን ከትውልድ አእምሮም ሊሰረዙ ይገባል …’’

(የተከበሩ የፓርላማ አባል፣ ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት)

‘‘የወያኔ ባንዳነት፣ ክህደት የታሪክ መሠረት ያለው ነው… ለአብነትም የትግራዩ ዐፄ ዮሐንስ ዐፄ ቴዎድሮስን አሳልፎ በመስጠት …፤’’

(ዶ/ር መንግሥቴ ሲሳይ/የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል)

‘‘… የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው… ርግጠኛ ነኝ አሁን የትግራይ ሕዝብ ‘እገነጠላለኹ’ ቢል እዚህ ምክር ቤት ውስጥ ያላችሁ ሁላችሁም መጮኻችሁ አይቀርም፤ ስለዚህ ለሕዝቡ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ሰብአዊ ዕርዳታ እንዲደርሰው መንገዶች መከፈት ይኖርባቸዋል …፤’’

(ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ በጦርነቱ ወቅት ለፓርላማ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)

- አነጋጋሪውየአንዳንድ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት ሰዎች አቋም       

ዶ/ር ደረጄ ዘለቀ ባለፈው ሰሞን ከቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ ‘‘ርዕዮት ሚዲያ’’ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ አንድ ነገር ተናግሮ ነበር፡፡ ይኸውም የሰማዕቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የግፍ አሟሟት የተመለከተ ነበር፡፡ ደረጄ በዚሁ ቃለ-መጠይቁ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ መንግሥት የመገደላቸው ምክንያት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ ጋር ደብዳቤ ሲጻጻፉ ተይዘው እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡

በወቅቱም ይህን ቃለ-መጠይቅ የሰሙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ካህን የኾኑ ሰው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በተመለከተ የተናገረው ነገር ፍጹም ስሕትት መሆኑን እንደነገሩት ከሰለሞን ሱምዬ/ገበያኑ ጋር በነበረው ቆይታ አንስቷል፡፡ ስለሆነም ደረጄ ቅዱስነታቸውን በተመለከተ ላስተላላፈው የተሳሳተ መረጃ ይቅርታ ለመጠየቅ እንደወሰነ ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ለማለት ይህንን ዕድል በጉጉት ሲጠባበቅ እንደነበር ገልጾልናል፡፡

ዶ/ር ደረጄ አክሎም፤ ‘‘ይቅርታ ማለት ካለብኝ ግን ይቅርታ ለማለት የምፈልገው የቅዱስነታቸው የሥጋ ዘመዶች እንጂ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያንን ይቅርታ ለመጠየቅ ፍላጎቱም ሐሳቡም እንደሌለው፤’’ ከሰለሞን ሹምዬ/ገበያኑ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ በግልጽና በድፍረት ነግሮናል፡፡

ዶ/ር ደረጄ ለዚህ አቋሙ ምክንያቱን ሲገልጽም፤ ‘‘… ትግሬ ከሚገዛኝ ሳጥናኤል ቢገዛኝ ይሻለኛል …!!’’ የሚል ጳጳስን ተሸክማ የምትኖር ቤተክርስቲያን ከእኔ ይቅርታን የምትሻበት የሞራል መሠረትም ሆነ የሞራል ተጠየቅ ሊኖራት አይችልም፡’’ ሲል በአጽንኦት ተናግሯል፡፡

ዶ/ር ደረጄ በቃለ-ምልልሱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አባቶች ላይ የሰነዘረውን ወቀሳ መሠረት አድርግንና የሐሳቡን ፈር እንደያዝን ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት- የአንዳንድ አባቶችና የመንግሥት ሰዎችን አቋም ምን ይመስል እንደነበር መፈተሽና መነጋገር ግድ ይለናል፡፡

በዚህ የጦርነት ወቅት ዘንባባ ይዘው፣ አሊያም እንደ ጋሞ አባቶች ለምለም ሳር ወይም የወይራ ዝንጣፊ ይዘው ስለዕርቀ-ሰላም መናገር የነበረባቸው የሃይማኖት አባቶች ጦርነቱን በመደገፍ መልእክት ሲያስተላልፉ በመገርምና በኀዘን ውስጥ ሆነን ሰምተናቸዋል፡፡ ለአብነትም ያህል፤ የግንቦት 7 የአርበኞች ሰራዊትን በረሃ ድረስ ወርደው ሲያበረታቱ አብረው ፎቶ ተነስተው የነበሩት አቡነ መቃርዮስ፣ በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ባደረጉት ንግግራቸውም፤

‘‘… እነዚህን እፍኝ የማይሞሉ ሰዎች ተዋግታችሁ ጠላቶቻችሁን መደምሰስ ነው እንጂ እዚህ ቁጭ ብላችሁ ጠላችሁን እየጠጣችሁ ምን ታደርግላችሁ…?!’’ የሚል ዝምት፣ ተዋጋ… የሚል ንግግራቸው በመገናኛ ብዙኃን ተመዝግቦ አለና እናስታውሰዋለን፡፡

በተመሳሳይም የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊና በትምህርት ረገድም እስከ ፒ.ኤች.ዲ. ድረስ ዘልቀው የተማሩት ሌላው አባት አቡነ ጴጥሮስ በጦርነቱ ወቅት፤ ‘‘… እነርሱ/ወያኔ ከሚገዛን ሳጥናኤል ቢገዛን ይሻላል!’’ የሚል አባታዊ መልእክትን/ምክርን አስተላልፈዋል፡፡

ከሃይማኖት አባቶች ባሻገርም፤ ከመንግሥት ሹመኞች መካከልም፤ የቅርስ ጠበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር የኾኑት አቶ አበባው አያሌው በብሔራዊ ቴያትር- ለመከላከያ ድጋፍ በተጠራ መድረክ ላይ እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር፤

‘‘… በዚህ ጦርነት የሰማይ መላእክትም ሊሳተፉና ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል!’’ ሲሉ… የጦርነቱን ፍትሐዊነትና ቅዱስ ጦርነት መሆኑን ጭምር፤’’ በአጽንኦት ሊያረጋግጡልን ሞክረዋል፡፡

የዕርቀ-ሰላም ሰባኪና መምህር ሊሆኑ የተገባቸው አባቶች ስለሰላም ለመስበክ ባይቻላቸው እንኳን እንኳን አደባባይ ወጥተው ጠርነትን የሚያበረታታ መልእክት ማስተላለፋቸው ብዙዎችን አስገርሟል፣ አስደንግጧልም፡፡ ሌላኛውና ‘‘የጠቅላይ ሚ/ሩ አማካሪ’’ ናቸው የሚባሉት ሰው ዲ/ን ዳንኤልም፤ በመረረ ጥላቻና ምሬት ውስጥ ኾነው፤

‘‘… ወያኔ/ሕወሓት ከኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ መደምሰስ ብቻ ሳይህን ለወደፊቱም እንደ እነርሱ ዓይነት ሰው በምድሪቱ እንዳይፈጠር ማድረግና በትውልድ አእምሮ ውስጥ ምንም ዓይነት መታሰቢያ እንዳኖራቸው አድርጎ ማጥፋት፣ መደምሰስ ይገባል …፡፡ የሚል መልእክትን አስተላልፈዋል፡፡

የሚገርመው ነገር ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ከአንጀታቸውም ይሁን ከአንገታቸው ጦርነቱ የእርስ በርስ ጦርነትና የወንድማማቾች እልቂት መሆኑን በፓርላም ጭምር ተናግረው፣ ለሰላማዊ መፍትሔ መንገዶችን፣ አማራጮችን ማፈላላግ ይኖርብናል እያሉ በሚወተውቱበት ጊዜ እንኳን ጠቅላይ ሚ/ሩ አብራዋቸው ያሉ የቅርብ ሰዎቻቸው ጭምር ከእርሳቸው ሐሳባቸው ተቃራኒ የኾነ አቋም ነበር ሲያራምዱት የነበረው፡፡ እንደውም እነዚህ ሰዎች ሕወሓት/ወያኔ ጠላት፣ የሕዝብና የሀገር ዋና አደጋ በመሆኑ ያለን የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው መፍትሔ እነርሱን ከኢትዮጵያ ምድር መደምሰስ፣ ማጥፋት ነው፤’’ በሚል አቋማቸው ጸንተው- ‘‘ጦርነቱ ለምን ሲባል ይቆማል?!’’ በማለት በየሚዲያውና በየዩ ቲዩብ ይህን አቋማቸወን ሲያራምዱ በአግራሞት ታዘበናቸዋል፡፡

 

የመንግሥት ሰዎች ሆነ ምሁራኑ ሕወሓትን ከኢትዮጵያ/ከትግራይ ምድር ስለማጥፋት ሲናገሩ አንድ የሳቱት ሐቅ አለ፡፡ ይኸውም፤ ሕወሓት/ወያኔ የትግራይ ሕዝብ አካል ብቻ ሳይሆን በተለየ ደግሞ በዚህ ጦርነት ከትግራይ ሕዝብ ጋር መቼም ላይለያይ የመንፈስ ውሕደትን ጭምር ዕውን ያደረገ ድርጅት ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ ይህ የታሪክ ሐቅ፤ ‘‘ሽብርተኛ፣ የሀገር፣ የሕዝብ ጠላት ነው’’ ተብሎ ለተፈረጀው ለኦነግና ለኦነጋውያንም የሚሠራ ነው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በኦሮሞ ሕዝብ የትግል ታሪክ ውስጥ ኦነግ ትልቅና የከበረ ስፍራ እንዳለው መዘነጋት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ይህን የታሪክ ሐቅ የአሁኖቹ የኦሕዴድ ብልጽግና ሰዎች አሳምረው ያውቃሉ፤ ያምናሉም፡፡ አብዛኞቹ የኦሮሞ ባለሥልጣናትም ለኦሮሞ ሕዝብ ትግል ታሪክ ውስጥ ከነክፍተቱም ቢሆን ደማቅ አሻራ ያለውን ኦነግን መቼውንም ቢሆን ከልባቸው ሊፍቁት እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ የሕዝብን ትግል መቼውንም ቢሆን ማዳፍን እንደማይቻል ማወቅ ይበጃል፡፡ እናም መፍትሔው በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር፣ ወመያየት ብቻ ነው፡፡

- እንደመውጫ

የሃይማኖት አባት፣ መምህራንና ምሁራን ሚናቸውና ምክራቸው ሊሆን የሚገባው ሰላማዊ መፍትሔ እንጂ በወንድማማቾች ጦርነት መካከል የጦርነት ነጋሪ መጎሰም ሊሆን አይገባም፡፡  ‘ለይቅርታ፣ ለፍቅርና ለሰላም ሐዋርያ፣ አምባሳደር ናቸው’ ተብለው የተጠሩ የሃይማኖት አባቶችና መምህራን ትልቁ ሥራቸው ሊሆን የሚገባው ሰላምን በቃልም በተግባርም ማስፈን ነው፡፡ እነዚህ አባቶቻችን መመሪያ አድርገው የተቀበሏቸው የሃይማኖት መሠረት የኾኑት መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርአን ትልቁ መልእክታቸውም ሰላምና ሰላም ነውና፡፡

ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍላ ያስተማረቻቸው ምሁራኖቻችንም ከጦርነት ይልቅ ለሕዝቦች አንድነት፣ ሰላምና ኅብረት የሚበጁ የታሪክ ሰበዞችን እየመዘዙ ወደፊት እጅ ለእጅ ተያየዘን የምናድግበትን የሰላም ጎዳና ሊያሳዩን ነው የሚገባቸው፡፡ እንዴት ታሪክን እያወላገዱ አንድን ሕዝብ በባዳነት ፍርጆ በወንድማማች ሕዝብ መካከል ጠላትነትንና የመለያየትን ግምብ ለመገንባት ይደፍራሉ፡፡

ምሁራኖቻችን ሀገር በጭንቅና በመከራ ውስጥ በገባች ጊዜ የመውጫ መንገድ የሚያሳዩ ብልሆች፣ ሩቅ አሳቢና አላሚ ሆነው በድቅድቅ ጨላማ ውስጥ የብርሃን ወጋገን የሚያሳዩን መሆን አለባቸው እንጂ- በመከራችንና በሰቆቃችን ጊዜ አብረውን የሚያለቅሱና የሚያላቅሱ ሊሆኑ ባልተገባቸው፡፡ ስለሆነም አንዳንድ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራኖች ራሳቸውን፣ አቋማቸውን በቅጡ ሊፈትሹ ይገባቸዋል፤ እናም ከመቼውም ጊዜ በላይ በሕዝብ መከካል መቀራብ፣ አንድነት፣ ሰላም፣ ልማት… እንዲሰፍን በቃልም በተግባርም ሊሠሩ ይገባቸዋል፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/178235

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...