Friday, December 9, 2022

በወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ጉዳይ የቀረበ ምክረ-ሀሳብ
መግቢያ

1. የታሪክ መነሻ

ከቅድመ-አክሱም ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ከበጌምድር ስሜን ግዛት ተነጥለው አያውቁም፡፡ በአስተዳደራዊ ታሪክ ደረጃ የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት ታሪክ ከበጌምድር ስሜን ታሪክ የማይነጠል የተጋመደ ታሪክ አለው። ይህን የአስተዳደራዊ ታሪክ በማስረጃ ህግ መመዘኛ መስፈርቶች ማለትም ገለልተኝነት፣ ተዓማኝነት፣ የእውነታ ይዞታ እና አግባብነትን መሰረት በማድረግ የተለያዩ የአገር ውስጥ እና የውጭ ጸሐፊዎች፣ አሳሾች፣ የመንግስታት ቆንስሎች ዲፕሎማቶች፣ የሀይማኖት ሰባኪዎች ሚስዮናዊያን እና የነገሥታት ዜና መዋዕል ጸሐፊዎች ከቅድመ-አክሱም ዘመነ መንግሥት እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ያሉትን ታሪካዊ ማስረጃዎችን መሰረት አድርገን ስንመለከተው አካባቢዎቹ የበጌምድር-ጎንደር አካል ዐማራ ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡

ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት በውል በሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ በበጌምድርና ጎንደር ክፍለ ሀገር፣ ስሜን እና ወገራ አውራጃ ሲተዳደር ቆይቷል። የትግራይ እና የበጌምድር (ጎንደር) ወሰን ተከዜ ስለመሆኑ አያሌ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ፡፡

በዚህ መነሻ፣ የግዛት ተስፋፊው ህወሓት/ወያኔ ድኀረ-1983 ያለሕዝብ ይሁንታ በኃይል የነጠቃቸውን እነዚህ አካባቢዎች በተመለከተ የትግራይ ክፍል ስላለመሆናቸው በአጭሩ በሚከተሉት ስድስት መከራከሪዎች ማጠቃለል ይቻላል፡፡

1ኛ. ከታሪክ አንጻር ሲመረመር የተነጠቁት መሬቶች የትግራይ አካል ሆነው አያውቁም ታሪካዊ ባለቤትነታቸው የበጌምድር ጎንደር ነው።

2ኛ. ከመሬት ይዞታ አንጻር ሲታይ፤ የተነጠቁት መሬቶች በሕግ የሚታወቁበት ‹ስሜን በጌምድር› ክፍለ-ሃገር የሚል መጠሪያ አላቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ አካባቢያዊ መጠሪያዎቹ ‹ጎንደሬ› ሲባል፤ የብሔር ማንነቱ ደግሞ ‹ዐማራ› ይባላል። ይህ ሲባል በአካባቢው ሌሎች ብሄረሰቦች የሉም ማለት ሳይሆን ክፍለ-ሃገራቱ ከተፈጥሯዊ ይገባኛልነት አኳያ የጎንደር ዐማራ ናቸው።

3ኛ. ከአስተዳደር አንጻር ሲታይ፤ ቅድመ 1983 በነበሩ አስተዳደራዊ አከላለሎች ይህ ክፍለ ሃገር (በጌምድር) በትግራይ ተወላጆች የበላይ ባለሥልጣናት (ጠቅላይ ገዢዎች ወይም አስተዳዳሪዎች) አንድም ጊዜ አልተዳደረም ወይም አልተገዛም። ለትግራይ አስተዳደር ግብር ከፍሎ አያውቅም።

4ኛ. ከሕዝብ ስርጭት አንጻር ሲመረመር፤ የህወሓት/ወያኔ ተስፋፊነት የነዋሪውን የብሔር ስርጭት በኃይል ከመቀየሩ በፊት ያለው ሁኔታ የሚያሳየው፤በተነጠቁት አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ፤ ከ90 በመቶ በላይ ዐማራ ነው። በዚህ ክፍለ-ሃገር የሚኖረው ጎንደሬ ከአያት፤ከቅድመ አያት ነዋሪነትና ተከታታይነት አኳያ ዐማራ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

 

5ኛ. ከባህል፤ ከሥነ-ልቦና፤ ከሥነ-ጥበብ፤ ከሕዝብ ግንኙነት፤ ከጋብቻ፤ ከመደጋገፍና ከተመሳሳይ እሴቶች አንጻር ሲታይ፣ በጎንደር የሚኖረው ሕዝብ በጎንደሬ ዐማራነቱ እንጅ “ትግሬ ነኝ” ብሎ አያምንም፡፡ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ “ጎንደሬ፤ ዐማራነኝ፤ ማንነቴ ይከበር” እያለ፣ በግድ “ትግሬነትን ተቀበል” በሚል ለሠላሳ ዓመታት መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የማንነት ጭፍለቃ ሲካሄድብት መቆየቱ ግን ደግሞ “የዐማራ ማንነቴ ይታወቅልኝ” በሚል የመብት ትግል ለማድረግ ተደራጅቶ መታገሉ ለማንነቱ የሰጠውን ቦታ ያመላክታል፡፡

6ኛ. ከመልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥና ከኢኮኖሚ ትስስር አንጻር ሲታይ ጎንደሬው በግልጽ የሚታወቅ ወሰን ነበረው፤ ወሰኑም ተከዜ ወንዝ ድረስ ነው፡፡ የኢኮኖሚውና የማኀበረሰብ ግንኙነቱም የሚያንጸባርቀው ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ድንበርና በመሬት ላይ የሚታይ የኑሮ ግንኙነቶች ሁኔታ ነው።

በአጠቃላይ ከታሪክ፤ ከመሬት ይዞታ፤ ከአስተዳደርና ከግብር ክፍያ፤ ከመልክዓ-ምድራዊ፤ ከሕዝብ ስርጭት፤ ከሥነ-ልቦና ባህል፣… ወዘተ ማመሳከሪያዎች አንጻር ሲታይ ህወሓት/ወያኔ የመሳሪያ ኃይልን ተጠቅሞ ድኀረ-1983 የፈጠረው አዲስ የመሬት ነጠቃ፤ ተስፋፊነት፤ የሕዝብ ሰፈራና አዲስ ካርታ ሕገ-ወጥ ነው።

 

የህወሓት/ወያኔ አገዛዝ የኢትዮጵያን ታሪክና የሕዝቡን ትስስር አፈራርሶ፤ አገሪቱን ምርኮኛ አድርጎ የቀደመውን የአገሪቱን ካርታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። በኢህአዴግ ግንባር ውስጥ የበላይነት ሚና የነበረው ህወሓት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ “የኢትዮጵያን የፖለቲካና የአስተዳደር ካርታ” ለእራሱ አላማ ሰኬትና የበላይነት በሚጠቅም መልኩ ለውጦታል።

የዚህ መነሻው በፖለቲካ አቋሙ “በዐማራ ቁልቁለት የሚጸና የትግራይ ታላቅነትን መፍጠር” የሚል በመሆኑ ነው፡፡ ድርጅቱ በባህሪው በኢትዮጵያ አቅም ሀገረ-ትግራይን ለመፍጠር ሲያሴር የኖረ፤ እኩልነትን የማይፈልግ፤ በቀዳሚነት እና የበላይነት “የእኔነት” (Igo) ስሜት የታወረ ኃይል በመሆኑ የሌሎችን በመንጠቅ ራሱን ማግዘፍ ይፈልጋል፡፡ ዐማራ ጠልነቱም ሆነ የግዛት ተስፋፊነት ባህሪው ከዚሁ ይመነጫል፡፡

በዚህ መነሻ ድኀረ-1983 የተገበረው ካርታ 1968 ላይ በረሃ ላይ ያዘጋጀው የማኒፌስቶው አካል የነበረውን ነው፡፡ መንግሥት ከሆነ በኋላ በተገበረው በዚሁ ካርታው የነባር ሕዝቡን ታሪክ፤ መልክዓ-ምድር፤ ድንበር፤ ግንኙነት፣ ትስስርና ጥቅም ሳይሆን የድርጅቱን ጥቅምና የታገለለትን የተስፋፊነት ዓላማ በመተግበር ሠላሳ ዓመታት አካባቢውን ከቅኝ ግዛት በከፋ ሁኔታ ገዝቶታል። የጎንደርን ለም መሬት ወሰንና ይዞታ፤ ነዋሪውን ሕዝብ በዘር ማጽዳት ተግባር በሚያመነምንና በሚያደኸይ ደረጃ ነባራዊውን ሁኔታ ለመቀየር በሰፊው ተንቀሳቅሷል። የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ማንነት ጥያቄ ትግል የተነሳው በዚህ ምክንያት ነው።

 

2. ሕዝቡን ስለመረዳት

ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ዓለም ጆሮ የነፈገው የዘር ማጥፋት ወንጀል በወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ሕዝብ ላይ ተፈጽሟል፡፡ ምናልባትም በብዙሃኑ ኢትዮጵያውያንና በተወሰኑ የዓለማቀፉ ማኀበረሰብ አባላት ዘንድ የተሰማው በህወሓት/ወያኔ ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም. በማይካድራ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ብቻ ነው፡፡ በርግጥ በማይካድራ ጭፍጨፋ 1,644 ዐማራዎች የጉዳት ሰለባ ሆነዋል።በጭፍጨፋው የተገደሉት 1,563 ሲሆኑ፤ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ 81 ናቸው፡፡ በዚህ ጭፍጨፋ የተነሳ በርካታ ሕጻናት ያለወላጅ ቀርተዋል። ይህ ዓለም ያወቀው እውነት ቢሆንም ሕዝቡ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በርካታ ማይካድራዎችን አሳልፏል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለአስራ ስምንት ወራት ባደረጉት ጥናት በወልቃይት ከስድስት በላይ የታወቁ የጅምላ መቃብሮችን አግኝተዋል፡፡ በጥናቱ ላይ እንደተመለከተው በሁመራ አውሮፕላን ማረፊያ ግቢ፣ እንዲሁም በየዋሻውና በምድር ውስጥ እስር ቤቶች የጅምላ ጭፍጨፋዎች ስለመካሄዳቸው ከሰለባው የተረፉ ሰዎች አንደኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ናቸው፡፡ የጅምላ መቃብሮቹ በራሳቸው ማስረጃዎች ሆነው ለተጨማሪ ተመራማሪዎች ክፍት ናቸው፡፡

በየትኛውም የዓለም ክፍል የተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች አንዴ ተጀምረው በተወሰነ የጊዜ ገደብ የተጠናቀቁ ቢሆንም፣ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ግን በአይነትም ሆነ በድርጊት የተለየ ነው፡፡ ለሠላሳ ዓመታት ያለ ማቋራጥ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ዐማራን ለይቶ የማጥፋት ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የዐማራ ተወላጆች በማንነታቸው ተገድለዋል፡፡

ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወገኖች ወደ መቀሌና ወዳልታወቁ ስፍራዎች ታፍነው ተወስደው በእስር ሲማቅቁ ኖረዋል፤ ብዙዎችም ባሉበት አልፈዋል፡፡ በጥቅሉ በሠላሳ ዓመቱ የህወሓት አፓርታይዳዊ ዘመን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ዐማራ ከርስቱ ተፈናቅሏል፡፡ መፈናቀሉ በሀገር ውስጥ ወደ ጎንደር ከተማና አልፎም ወደ መሀል ሀገር እንዲሁም፤ በአቅራቢያ ወደሚገኘው ሱዳንን በመሰሉ ጎረቤት ሀገራት በጅምላ እንዲሰደድ ተደርጓል፡፡ ይህ አገር ጥሎ በግዴታ የመሰደድ ሁኔታ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውስትራሊያና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን የሚያካልል ነበር፡፡ ዛሬ በመላው ዓለም ተበትኖ የሚገኘው የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ የስደቱ መነሻ የሕወሓት/ወያኔ አገዛዝ ነው፡፡ ሕዝቡ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ላሳለፈው መከራ ምንጩ የህወሓት የዐማራ ጠል ትርክት እና የግዛት ተስፋፊነት ነው፡፡

ህወሓት/ወያኔ የሀገር ክህደት ወንጀል ከፈጸመበት ከጥቅምት 24/2013 ምሽት ጀምሮ እንደሀገር በተጀመረው ሕግ የማስከበር እና የህልውና ዘመቻ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ ሕዝብ ከፌዴራልና ከዐማራ የጸጥታ ኃይል ጋር ተሰልፎ ራሱን ከወራሪ፤ ሀገሩን ደግሞ ከከዳተኛና ባንዳ ነጻ ለማውጣት ተፋልሟል፡፡ በዚህም ነጻነቱን መጎናጸፍ ችሏል፡፡ ሕዝቡ ትርጉም የሚሰጥ መስዋዕትነት ከፍሎ ያገኘውን ነፃነት፣ ዛሬ ማንም ኃይል ጣልቃ ገብቶ “በማንነታችሁ እኔ ልወስን” እንዲል አይፈቅድም፡፡

ነገር ግን ሕዝቡ ነጻነቱን ባገኘ ማግስት ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ የተጣራ መረጃ የሌላቸውና የአካባቢውን ሕዝብ የዘመናት መከራና በደል በውል ያልተረዱ ኃይሎች በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የተዛቡ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ቆይተዋል፤ አሁንም ከቀደመ ጥፋታቸው ያልታረሙ እንዳሉ ይስተዋላል፡፡

ሕዝቡ በህወሓት ከደረሰበት ግፍና በደል አኳያ ዛሬም ድረስ የዘለቁ ጠባሳዎችና የታሪክ ቁስሎች አሉበት፡፡ ጥቂቶች ቢሆኑም አሁን ላይ እነዚህ ቁስሎቹ እንዲያመረቅዙ የሚያደርጉ የፖለቲካ ሸፍጦች ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ኃይሎች መሰማቱ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ይህ ፍትህን የማዛባት፣ በመረጃና ማስረጃ ያልተመሰረተ ፍርደ ገምድልነትና የክህደት ተግባር ነው፡፡ ለዘመናት ግፍና በደል ከደረሰበት የወልቃይት፣ ጠገዴናጠለምት ዐማራ ፍላጎት በተቃራኒ መቆም በትንሹ የሞራል ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ማንነት ጥያቄ የታሪክ፣ የሕግ፣ የፍትሕና የሞራል መሰረት ያለው መሆኑን በመረዳት ለሚከተሉት አካላት ምክረ-ሀሳባችን እንዲህ እናቀርባለን፡-

3. ለሚመለከታቸው አካላት የቀረቡ ምክረ-ሀሳቦች

3.1 ለዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ

ከፍ ሲል እንደተመለከትነው የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ጉዳይ ከታሪክ፤ ከመሬት ይዞታ፤ ከአስተዳደርና ከግብር ክፍያ፤ከመልክዓ-ምድራዊ፤ ከሕዝብ ስርጭት፤ ከሥነ-ልቦና ባህል፣…ወዘተ ማመሳከሪያዎች አንጻር ሲታይ የዐማራ እንጅ የትግራይ ሁነው አያውቁም፡፡ በህወሓት የበላይነት ድኀረ-1983 በተፈጠረው አዲስ ሥርዓት እነዚህ ቦታዎች፣ ያለሕዝቡ ይሁንታ በኃይል ወደ ትግራይ የተጠቃለሉ ናቸው፡፡ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በተለይም በአለፉት ሠላሳ ዓመታት ህወሓት በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረውን ነባሩ የዐማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሞበታል፡፡ ስለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የትኛውም ገለልተኛና ነጻ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ወደአካባቢው መጥቶ ማጥናት ቢፈልግ ሕዝቡ የተፈጸመበትን ግፍና በደል ለማሳወቅ ፍቃደኛ ነው፡፡

ስለሆነም፦

1ኛ. በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ስንመለከተው በወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ሕዝብ ላይ ዓለም ያልሰማው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል፡፡ ለዚህም ወንጀል ፈጻሚ የህወሓት አመራሮች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርበው ሊጠየቁ ይገባል!!

2ኛ. የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ እና ተቋማት በእነዚህ አካባቢዎች ቅድመ እና ድኀረ ነጻነት ያለውን ሁኔታ የሚያዩበትን መንገድ በተለይም የመረጃ ምንጮቻቸውን እንዲፈትሹ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

3ኛ. ዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ሊረዳው የሚገባ እውነት የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ ያስመለሰው ማንነት እንጂ የነጠቅነው መሬት አለመኖሩን ነው፡፡ ምዕራብ ትግራይ የሚባለው ሽሬ፤ እንጅ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አይደሉም፡፡

4ኛ. ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የጎንደር ክፍለ-ሃገር ታሪካዊ አካል ናቸው፡፡ የዐማራ ሕዝብ የማይገባውን አልፎ አልጠየቅም፤ የራሱንም አሳልፎ ሊሰጥ ፍቃደኛ አይደለም!!

5ኛ. የዐማራ ሕዝብ ከመላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ጋር እኩልነትን መርሁ አድርጎ በወንድማማችነት ስሜት፣ በሠላምና በፍቅር ከመኖር ውጭ የተለየ ፍላጎት የለውም፡፡

3.2 ለኢፌዴሪ መንግሥት

 

በሕዝብ ግፊት እና በመሪ ድርጅቱ ሳቢነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመጋቢት/2010 ጀምሮ የአመራር ለውጥ መጥቷል፡፡ በዚህም የኢፌዴሪ መንግሥት ለማንነትና የወሰን አስተዳደር ጥያቄዎች የሰጠው ትኩረት እጅግ የሚያስመሰግነው ነበር፡፡ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰል ጥያቄዎችን የሚያጠናና የውሳኔ ሀሳቦችን የሚያቀርብ ኮሚሽን በማቋቋም፤ እንዲሁም የተነሱ ጥያቄዎች ጉዳዩ በሚመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲታዩ ለማድረግ ያደረጋቸው የአሰራርና ተቋማዊ ማሻሻያዎች ለዜጎቹ ከሚጨነቅና ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቁ ተግባራት ቢሆኑም ኮሚሽኑ አሁን ላይ ህልውናው መክሰሙ መሰል ጥያቄዎች የሚፈቱበት አግባብ ከታሪክና ሕግ ጥናት ውጭ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

በሌላ በኩል ህወሓት/ወያኔ በየትኛውም የሕግ፣ የሞራል፣ የፖለቲካ መርሆ የማይመራ ፍላጎቱንም በጠመንጃ የማስፈጸም ልምድ ያለው አሸባሪ ድርጅት በመሆኑ የማንነትና አስተዳደር ጥያቄው ምላሽ እንዳያገኝ እንቅፋት ሆኖ ከመቆየቱም በላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ሳትወድ በግድ ወደ ጦርነት በማስገባት ለኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ህልውና አደጋ ደቅኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ በተደረሰው የጋራ ሰላም ስምምነት አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡

የሰላም ስምምነቱን ከማፅናት ጎን ለጎን የፌዴራሉ መንግሥት የሚከተሉትን መነሻዎች ልብ በማለት ተገቢ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይገባል፡፡

ይኼውም፡-

- ሕወሓት/ወያኔ ወልቃይት-ጠገዴ ጠለምትን ወደ የሚመሠርታትየትግራይ ሪፐብሊክ ለማካለል የወሰነው በረሀ እያለ ባወጣው የ1968ቱ ማኒፌስቶ ነበር፡፡

- ሕወሓት/ወያኔ በደርግ መውደቅ ማግስት እነዚህን አካባቢዎች ወደ ትግራይ ክልል (በወቅቱ ክልል 1) ያጠቃለላቸው በጉልበት ነበር፡፡

- ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ወደ ትግራይ የተካከለለው የብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 7/1984 በሚጥስ መልኩ ነበር፡፡

(ድኀረ-1983 አዲስ የአስተዳደር መዋቅር በሚፈፅምበት ወቅት መዋቅሩን ለማስፈፅም ተደንግገው የወጡት የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ ቻርተር በአንቀፅ ቁጥር 13 “የክልሎች አስተዳደር በብሔሮች አሰፋፈር ላይ ተመርኩዞ ይቋቋማል” ፣ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 7/1984 በአንቀፅ ቁጥር 4 “የብሔር፣ብሄረሰብ እና ሕዝብ ኩታ ገጠም አሰፋፈር ለብሄራዊ መስተዳደር ወሰን አከላለል መሰረት ይሆናል” የሚለው ሕግ ተጥሶ ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት በጉልበት ወደትግራይ እንዲካለሉ ተደርጓል)

- ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምትወደ ትግራይ የተካለለበት መንገድ ሕገ-መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት ሲሆን፤ አከላለሉም ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው ነው፡፡

(የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከመዋቀሩ ከሦስት ዓመት በፊት ወልቃይት ጠገዴ ያለሕዝብ ይሁንታ በጠመንጃ የበላይነት በኃይል ወደትግራይ ክልል እንዲካለለ የተደረገ መሆኑና ይህ አከላለል፣ በወቅቱ ለአስተዳራዊ መዋቅር የወጡ አዋጆችን በመጣስ የተካሄደ ከመሆኑም በላይ በ1987 በፀደቀው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ቁጥር 46 “ክልሎች የሚዋቀሩበትን የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፍቃድ ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ይሆናል” በማለት በግልፅ የተደነገውን ሕግ በተቃረነ ሁኔታ የወልቃይት-ጠገዴሕዝብ በብሔር፣ በኩታ ገጠም አሰፈፈር፣ በማንነትና በቋንቋ ከሚመስለው የቀድሞው በጌምድርእና ጎንደር ክፍለ ሀገር የተካለሉበት የዐማራ ክልል ወጥቶ ወደትግራይ የአስተዳደራዊ ወሰን በጉልበት እንዲካለል ተደርጓል።)

- ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ወደ ትግራይ ክልል የተካለለበትንሕገ-ወጥ መንገድ ለማጽናት፣ ሕወሓት በነባሩ ሕዝብ (Indigenous People) ላይ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች ፈፅሟል፡፡

በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት እነዚህን እውነታዎች በመመርመር የሚከተሉትን አምስት ቁልፍ ተግባራት ማከናወን ይጠበቁበታል፡-

1ኛ) የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ማኀበረሰብ የጠየቀው “የዐማራ ማንነቴ ይታወቅልኝ” ይፋዊ ጥያቄ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እውቅና እንዲሰጠው፣

2ኛ) ሕወሓት/ወያኔ በወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ ሕዝብ ላይ የፈፀማቸውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት ወንጀሎችን የሚመረምርና ወንጀለኞችን ለፍርድ የሚያቀርብ ልዩ አቃቢ ህግ ተቋቁሞ ፍትህ እንዲበየን ማስቻል፣

3ኛ) የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ማንነት ጉዳይ ታውቆ ያደረ አጀንዳ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡ ለዘመናት ሲያቀርበው የኖረው ወደዐማራ ክልል የመጠቃለል አስተዳደራዊ ጥያቄ በፌዴሬሽን ምክርቤት በሕግእ ንዲፀናለት፣

ይህም ሲባል፡- የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 (1) እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1261/2013 አንቀጽ 37 እና 38(1) መሠረት የሕዝብ አሰፋፈርን መሠረት አድርጎ የመወሰን ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክርቤት በመሆኑ በሕግም የሚደገፍ ነው።

4ኛ) በግዛት ተስፋፊው ህወሓት አገዛዝ ስር በነበሩት በእነዚህ አካባቢዎች ዐማራ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ከባድ የሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግዷል፡፡ አያሌ ወገኖቹ በጅምላ ተገድለውበታል፡፡ በማንነቱ ሞትን የማስተናገድ መራር ዕጣ ፈንታ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ገብቷል፡፡ እንዲሳደድና እንዲፈናቀል ተደርጓል፡፡ ሀብትና ንብረቱንም ተዘርፏል፡፡ ለዚህም በዓለማቀፍ ተሞክሮዎች መሰረት ሕዝቡ ለደረሰበት ግፍና በደል ካሣ ያስፈልገዋል፡፡ የሚጠየቀው ካሣ ለሰላሳ ዓመታት በዘለቀው የህወሓት የአፓርታይድ የአፈና አገዛዝ ያጣናቸውን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሕይወት ባይመልስም፣ ለደረሰው ግፍና በደል እውቅና መሰጠቱ የሕዝቡን ቁስል ያሽረዋልና፣ የፍትሕና የካሳ ጥያቄው በፌዴራሉ መንግሥት በኩል ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡

5ኛ) በሕወሓት/ወያኔ የግፍ አገዛዝ ተሰቃይተውና በእርሱ አስገዳጅነት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ተወላጆች ወደቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ መደረግ አለበት። የመልሶ ማቋቋሙን ተግባር የፌዴራሉ መንግሥት ኃላፊነት ሲሆን፤ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጋር በመተባበር ሊሰራው የሚገባ ቁልፍ ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡

3.3 ለኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች

ከጅምሩ የኢትዮጵያን የጋራ ማንነት ክዶ ለ “ታላቋ ትግራይ” የአገር ምስረታ የተነሳው ህወሓት፣ በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የሚጠላውን ሀገርና ሕዝብ የመራ ብቸኛው ድርጅት ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የተሰወረ አይደለም፡፡ በህወሓት/ወያኔ የጥፋት ሴራ ደም ያልፈሰሰበት የኢትዮጵያ ግዛት የለም፡፡ “ለብሔር ብሄረሰቦች መብት ታገልኩ” ቢልም በተግባር ግን የኢትዮጵያን ልጆች ለሥልጣኑ የበላይነት ሲል እርስ በርስ ሲያጋጭና በመካከላችን በሚፈጠረው ቅራኔ የፖለቲካ ትርፍ ሲሰራ የኖረ የጥፋት ቡድን ነው፡፡

ከ “ትግራይ ሪፐብሊክ” ወደ ትግራይ የበላይነት የተሸጋገረው ህወሓት/ወያኔ፣ በአገዛዛ ዘመኑ ዐማራውን ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያዊያን ለመነጠል፣ ባይተዋር አድርጎ ለመግዛት ሰፊና አፍራሽ የሐሰት ትርክትና የፕሮፖጋንዳ ስልት ተከትሏል፡፡ ዐማራው በማንነቱ የደረሰበት ግፍና መከራ እንዲሁም ያጣቸው ብሔራዊ ጥቅሞች መነሻ መሰረቱ በዐማራ ጥላቻ የተዋቀረው የደደቢት ትርክት ነው፡፡ የህወሓት የፖለቲካ ግብ ሕብረትና አንድነቷን ባጣች የተዳከመች ኢትዮጵያ ስር የትግራይ የበላይነትን ማረጋገጥ በሂደትም ኢትዮጵያን አፍርሶ ‹‹ታላቋ ትግራይ››ን መገንባት ስለመሆኑ ከፈጠራቸው ሐሳዊ ትርክቶች፣ ከጥላቻ ፖለቲካው እና ከግዛት ተስፋፊነቱ መረዳት ይቻላል፡፡

የወልቃት-ጠገዴና ጠለምት ጉዳይም የሚታየው ከዚሁ አውዳሚ የፖለቲካ ባህሪው በመነሳት ነው፡፡ በታሪክ፣ በሕግና በሞራል አግባብ ከታየ እነዚህ አካባቢዎች የበጌምድር ጎንደር (ዐማራ) ናቸው፡፡ ይሁንና በግዛት ተስፋፊው ህወሓት ለሠላሳ ዓመታት በጉልበት ተነጥቀው ያለማንነታቸው የትግሬ ማንነት ለመጫን በአፓርታይድ የሚመሰል አገዛዝ ስር አይነተ ብዙ የሆነ ግፍና መከራ ሲደርስባቸው ቆይቷል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች እንዲያውቁት የሚፈለገው እውነት ህወሓት ለሠላሳ ዓመታት በጉልበት ይዟቸው በነበሩ በእነዚህ አካባቢዎች በዐማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን ነው፡፡ ለዚህም የሰውና የጅምላ መቃብር ምስክሮችን አስረጅ ምሳሌ አድርገን እናቀርባለን፡፡ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በወልቃይት ዐማራነት የጥቃት ምንጭ ነበር፡፡ ሰዎች ዐማራ በመሆናቸው ብቻ ማይካድራን በመሰሉ ቦታዎች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፡፡

አሁን ላይ ያ ሁሉ መከራ አልፎ፣ እነዚህ አካባቢዎች ነጻ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ በአማራ ክልል፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ስር እራሱን እየተስተዳደረ ይገኛል፡፡ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ዐማራ እየጠየቀ ያለው፣ “ማንነቴ ዐማራ ነው፤ ማንነቴና አስተዳደራዊ ፍላጎቴ ተከብሮልኝ በዐማራ ክልል ስር ልተዳደር” የሚል ነው፡፡ ስለሆነም ፍትሕና ነጻነት ወዳድ የሆኑ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለጥያቄው ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ህወሓት በዐማራ ሕዝብ ላይ ከፍቶት በኖረው የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ የተነሳ የዐማራ ጥያቄ የሌሎችን መብት የሚጋፋና የሚጨፈልቅ እንዲመስል ለማድረግ ሞክሯል፡፡ እውነታው ግን ዐማራየሚፈልጋትኢትዮጵያ ከማንም በላይ አልያም ከማንም በታች መሆን ሳይሆን፡- ነጻነት፣እኩልነት፣ ፍትሕ እና በሕግ-ገዥነት የተመሠረተ ዴሞክራሲ የሰፈነባት ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላት አገር ተገንብታ ማየት ነው፡፡

በዚህ መሻቱ ውስጥ በመሰረታዊነት የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ከታሪክ፣ ከሕግ፣ ከሞራል የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ጉዳይም በዚሁ አግባብ የሚታይ ነው፡፡

ወልቃይት ኢትዮጵያ ካሏት ወሳኝ ስትራቴጂያዊ ስፍራዎች አንዱ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ፣ ሕወሓት “ታላቋ ትግራይ” ን ከሱዳን ጋር ለማገናኘት በግዛት ተስፋፊነት አካባቢውን በኃይል ይዞ ለሠላሳ ዓመታት ቆይቷል፡፡ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያ ደመኛ ጠላቶች ድጋፍ እየተደረገለት ከጎረቤት ሀገራት ተነስቶ ኢትዮጵያን ለመውጋት ተደጋጋሚ ጥረቶችን የሚያደርገበት አካባቢ እንደሆነ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተጨባጭ ታይቷል፡፡

ህወሓት/ወያኔ ሁኔታዎች ፈቅደው አካባቢውን ዳግም የመቆጣጠር ዕድል ቢያገኝ ግብጽን ለመሰሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ወታደራዊ ቤዝ ከመስጠት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ህልውና ከእስካሁኑ የከፋ አደጋ ሊያደርስ የሚችልበት የጂኦ-ፖለቲካ ዕድል ያገኛል፡፡

በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች በቀደመ አስተዋይነታቸው ከወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የአማራ ማንነት ፍትሐዊ ጥያቄ ጎን እንደሚቆሙ እምነታችን የጸና ነው፡፡

 

3.4 ለትግራይ ሕዝብ (በይበልጥ ለልሂቃኑ)

ስለ ዐማራ እና የትግራይ ሕዝብ የሺህ ዓመታት ትስስር አለም የሚያቀው እውነት ነው፡፡ ሁለቱም ብሔሮች የማህበረ-ባህል ተቃርኖ የሌለባቸው ስለመሆኑና “ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ፤አንድ ቤተሰብ” ሆነው ለሺህ ዓመታት በጋራ ስለመኖራቸው ነጋሪ አያሻቸውም፡፡ ስለ እውነት ነጋሪ የሚያሻው፣ አኗኗሪ ምክረ-ሀሳብ የሚያስፈልገው፣ ደደቢት በረሃ ላይ ስለተጸነሰው ጸረ-ዐማራ የጥላቻ ትርክትና ድኀረ-1983 ጀምሮ በመዋቅር ገቢር ስለተደረገው የጥላቻ ፖለቲካ ባለቤትነት፣ የግዛት ተስፋፊነት እና ውጤቱ ነው፡፡

 

ህወሓት በትርክትና በተግባር በዐማራ ሕዝብ ላይ ለሠላሳ ዓመታት የፈጠረው የወል ሰቆቃ እና የታሪክ ቁስል እንዴት ይታከም? በሚለው ላይ መምከር፣ በጥፋቱ ልክ ለበደሉ እውቅና መስጠት እና በደባባይ ይቅርታ መጠየቅ የዘመኑ አሰገዳጅ እውነት ሆኖ ከፊት ለፊት ቀርቧል፡፡

 

ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ በተለይም ልሂቃኑ

- ከምስረታውጀምሮ የዐማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ፣ በትርክት፣ በተቋምና በሥርዓት ዐማራን ሲያጠቃ እና በሌሎች እንዲጠቃ ሲያደርግ፣

 

- በግዛት ተስፋፊነቱ ተከዜን ተሻግሮ የበጌምድር ስሜን አካል የሆኑትን ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም የወሎ ክፍለ-ሀገር አካል የሆነውን ራያን በወረራ ወደ ትግራይ ሲያጠቃልል፣

 

- በእነዚህ አካባቢዎች ባለርስት ሆነው ይኖሩ በነበሩ የዐማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም፣ በጅምላ ወደ እስራት ሲያግዛቸው፣ ከቀያቸው በገፍ ሲያፈናቀላቸው፣… ነበር፡፡

 

ህወሓት እነዚህን ወንጀሎች የፈጸመው በ “ትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭነት” ስም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይሁንና ልሂቃኑ ለሠላሳና ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት “በስሜ ይህ አይደረግም/Not in My Name/” አለማለታቸው፣ ወደጋራጥፋተኝነት ያስጠጋቸዋል። የጋራ ጥፋተኝነት ጽንሰ ሃሳብ ከግል ጥፋተኝነት በተቃርኖ ምንም ማለት አይደለም፤ይልቁኑም ዕውነቱን በመደበቅ ከበስተጀርባ ለጥፋተኛ ግለሰቦች/ቡድኖች ለብቻ በመሸሸጊያነት የሚያገለግል ነው። የጋራ ጥፋተኝነት የአንድ ቡድን አባላት የሚጋሩት አስነዋሪ ሆነው የሚታዩ ድርጊት ወይም ድርጊቶች ናቸው።ያልተነገረ ነገር ግን በድርጊት የሚገለጥ እንደማለት ነው።

 

የትግራይ ልሂቃን ህወሓት በዐማራ ሕዝብ ላይ በተለይም ደግሞ በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ያደረሰውን ግፍና በደል እያዩ እየሰሙ “በስሜ ይህ አይደረግም” በማለት ፈንታ፤ አንዳንዶች የዘር ማጥፋቱን በሀሳብና በድርጊት ሲደግፉ ታይቷል፡፡ “Your silence gives consent” እንደሚባለው አብዛኛው የትግራይ ልሂቃን ደግሞ ህወሓት/ወያኔ በወልቃይት ሕዝብ ላይ የፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በዝምታ ማለፋቸው ጥፋቱን መደገፋቸውን ያሳብቃል።

 

በርግጥ የትግሬ መስፍን የሆኑት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም እና የህወሓት የቀድሞ ታጋይ የነበሩት አቶ ገብረመድኀን አርዓያን የመሰሉ የታሪክ እውነታዎችን የተናገሩ የትግሬ ልሂቃን ቢኖሩም ከተፈጸመው በደልና ግፍ አኳያ እነዚህ ምስክርነቶች የህወሓትን የጥፋት ድርጊቶች ሊያስቆሙ አቅም አልነበራቸውም፡፡ ስለሆነም በዐማራና በትግራይ ሕዝብ መካከል በቀላሉ የማይሽር የታሪክ ጠባሳ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡

 

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሁለቱ ሕዝቦች ቅራኔ እንዲለዘብ በትንሹ የሚከተሉት ኃላፊነቶች ከትግራይ ሕዝብ በተለይም ከልሂቃኑ ይጠበቃሉ፡-

 

1ኛ) ህወሓት በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ተወላጆች ላይ ለፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እውቅና መስጠትና የፋዊ ይቅርታ (Public Apoloygy) መጠየቅ፣

 

2ኛ) ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በእነዚህ አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ ልዩ ልዩ ግፍና በደሎች ለተፈጸመበት የዐማራ ሕዝብ የፍትሕና የካሳ ጥያቄው እንዲመለስለት አጋርነትን ማሳየት፣

 

3ኛ) ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በሃሳብ የደገፉ፣ በተግባር ያስፈጸሙ የህወሓት አመራሮች፣ ታጣቂዎች፣ አባላትና አጋሮቹ በስም ዝርዝር ተለይተው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት ተባባሪ ሆኖ መገኘት፣

 

4ኛ) ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት በታሪክ የበጌምድር ጎንደር (ዐማራ) አካል መሆናቸውን፣ ድኀረ-1983 በጉልበት ተነጥቀው ተወስደው እንደነበሩ አምኖ መቀበል፤

በትንሹ ከትግራይ ሕዝብ በተለይም ከልሂቃኑ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡

በግልጽ እንደሚታወቀው የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ አስተዳደራዊ ፍላጎቱን በተመለከተ ትላንትም ሆነ ዛሬ ቃሉ አንድ ነው፡፡ “ማንነታችን ዐማራ ነው፤ አስተዳደራዊ ፍላጎታችን በዐማራ ክልል ስር መተዳደር ነው” የሚለው ሕዝባዊ መሰረት ያለው ጥያቄ ሊከበርለት ይገባል፡፡ “ከትግራይ የሚመጣ ጥሩ ጎረቤት እንጅ፤ አስተዳደር ፈጽሞ አንቀበልም!” እያለ ያለው ሕዝቡ “ዛሬ ወደኋላ ላንመለስ ነጻ ወጥተናል” የሚል አቋሙን በአደባባይ ደጋግሞ አሰምቷል፡፡

 

ስለሕዝቡ ማንነት ከራሱ በላይ ምስክር ሊሰጥ የሚችል አንዳች አካል የለም፡፡ ከእንግዲህ ከትግራይ ሊመጣ የሚያስብ የትኛውም አስተዳደራዊ ኃይል በማንነቱ ብቻ ሲጨፈጭፈው ከኖረውህወሓት ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡

ስለሆነም ተፈጥሯዊ ድንበር የሆነውን ተከዜ ወንዝን በጋራ የምንጋራው የትግራይ ወንድም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ምድር በሠላምና በነጻነት መኖር ይችላሉ፡፡ ሕግና ሥርዓትን አክብረው ለሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ክፍት ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ከታሪክ፣ ከሕግና ሞራል ሁኔታዎች በሚቃረን መልኩ ወልቃይትን እንደ 1983ቱ በጉልበት ልጠቅልል ብሎ ለሚመጣ ኃይል ተከዜን የጎላን ኮረብታዎች አምሳያ ከማድረግ ውጭ ፋይዳ የለውም፡፡

የዐማራ ሕዝብ ከተከዜ ወዲህ ያስመለሰው ማንነት እንጂ የነጠቀው መሬት የለም!

ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ህዝቡ ጎንደሬ-ዐማራ፣ ወሰኔ ተከዜ!

- ••

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/178157

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...