Tuesday, December 20, 2022
በምስራቅ አፍሪካ የሚገኝ፣ ሰፊ የውቅያኖስ ዳረቻ ያለው፣ በባህርም ውስጥ ይሁን በመሬት ላይ ላቅ ያለ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነ ምድር ሱማሌ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ይህ ሃገር የተረፈ ቅኝ ግዛት ጣጣና የኢሪዴነቲስም ፖለተካ ሰለባ ሆኖ መኖር ከጀመረ ሲሶ ምዕተአመት አልፎታል፡፡
የአብዛኛው አፍሪካ ሃገሮች የፖለቲካ ነውጥ የቅርብ ግዚያዊ አዙሪት የሚጀምረው ሃገሮቹ ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ ጀምሮ ነው፡፡ በሩቁ ግዜ በየሃገሮቹ ውስጥ የነበሩ የጎሳ ግጭቶችን ቀኝ ገዢዎች ለአሰተዳደራቸው ስሙርነት ይጠቀሙበት ስለነበር፣ በገዢና ተገዢ መሃል በነበረው ፖለቲካዊ ትርክት ውስጥ ትልቅ አስተዋጾ እንዲኖረው አድርገው ሰርተውታል፡፡
ስለዚህም የምስራቅ አፍሪካን ምስቅልቅል ፖለቲካ ስናይ የቀኝ ግዛት ዘመንን መነሻ መድረግ ተገቢና ፍትሃዊ ነው፡፡ ሱማሌ የሚባለው ህዝብ በሶስት የውጭ ሃይሎች ቅኝ ተገዝቷል፡፡ ፈረንሳይ የጅቡቲ ሱማሌዎችን ገዝታለች፡፡ እንግሊዝ ሶማሌ ላንድን፣ መቋደሾንና አካባቢውን ደግሞ ጣሊያን በቀኝ ግዛት ገዝቷል፡፡ ይህ እንግዲህ የሆነው ከ1880ዎቹ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ባለው ግዜ ውስጥ ነበር፡፡
ሱማሌ የምትባለው ሃገር ሱማሌ ላንድ፣ ፑነት ላንድ፣ ጁባ ላንድ፣ ሶማሌ…ተብላ ተከፋፍላ ብዙ የደም ግብርን ስትከፍል የምናያት ቀኝ ገዢዎች በከፋፈሉት ሴራና ያን ተከትሎ በተሰመረው መስመር ላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ሱማሌዎች በኢትዮጵያና ኬንያም ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሱማሌዎች ከቀኝ ተገዥነት የተረፉት እነ ራስ መኮንንና የሱማሌ(የኢትዮጵያ) ጀግኖች ባደረጉት ትግል ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሱማልያ የአልሸባብ መፍንጪያ ሆናለች፡፡ በየለቱ በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ የሚጠፉት ሱማሌውያን ህይወት አፍሪካዊ ነኝ ለሚል ሁሉ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያዊ አንድ ጥያቄን፣ ከሃያ ሁለት አመት በፊት፣ እራሴን ጠይቄ ነበር፡፡ እውን ኢትዮጵያ ከነበረችው ሱማሌ ጋር ያላት ታሪክ መቶ አመት የማይሞለ ነውን? ከዚያም ከልጅነቴ ትዝታዎች ተነስቼ መልሱን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡
አስታውሳለሁ በልጅነቴ ማን እንደከፈተው ባላሰታውስም በአማርኛ የሚተላለፍ የሱማልያ የፐሮፓጋንዳ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ “ጡሩራው መንግስቱ ሐይለማሪያም…” የሚል ዜና ሃተታ ደጋግሜ ሰምቼአለሁ፡፡ ከዚያም አባቴ የጤና ባለሙያ ስለነበር በኢትዮጵያ ሱማልያ ጦርነት ግዜ ዘምቶ ነበር፡፡ በኋላም ሞተ ተብሎ ተረዳን፡፡
የዚያን ቀን አንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ ህጻናቶቹ ተቀምጠን ነበር፡፡ ያቺ ክፍል ግድግዳዋ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተለበጠ ነበር፡፡ ከአንዱ ጋዜጣ ላይ አንድ ዜና ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ “ኢትዮጵያ ከሶሻሊዝምና ከኤርትራ“ ትምረጥ የሚል ነበር ” ፡፡ እንግዲህ ይህን ያሉት አሜሪካኖቹ ነበሩ፡፡
በኋላ ላቅመ ንባብ ስደርስ አንድ ሊፋጋሮ በተባለ ጋዜጣ ላይ ጃንሆይ እ.ኤ.አ 1964 ዓ.ም. ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ስመለከት፣ ነገሩ ትንግርትን ፈጠረብኝ፡፡ እሳቸው ቃለ ምልልሱ ላይ፣ በሃገራቸው ላይ ተቃውሞ የሚያስነሳ ከመቋደሾ እስከ አስመራ የተሰራ ተረፈ ፋሺስት የጣሊያን መስመር እንዳለ ይገልጻሉ፡፡
ያው በዚያኑ ሰሞን፣ በጃንሆይ ዘመነ መንግስት፣ ሱማሊያ በራሺያ ድጋፍ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አደረገች፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት ደግሞ ሱማልያ በአሜሪካ ድጋፍ እስከ ድሬደዋ ድረስ በመውረር ጦርነት አደረገች፡፡ በሁለቱም ጦርነቶች ግዜ ሲያድ ባሬ በወታደራዊ አመራርና በኋላም በፕሬዝደንትነት ሱማሊያን አገልግሷል፡፡ እሱ ከስልጣን ከተባረረ በኋላ ሱማልያ የአሸባሪዎች መነሃሪያ ሆናለች፡፡
ከሃያ አመት በፊት አልቃይዳ አፍጋኒስታን ላይ ሲመታ መሸሺያ ያደረገው ሱማሊያን ነበር፡፡ ከዚያም ሆኖ ብዙ ሱማሌዎችንና ኦሮሞ ሞስሊሞችን በመመልመል የመን ከመበታተኗ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ሱማሌዎችንና ኦሮሞዎችን በዚያ ለጦርነት አሰልፏል፡፡ አንድ የጂማ ኦሮሞ የአልቃይዳ ታጣቂ ሆኖ የመን፣ ሰንአ አካባቢ ባለ ኮረብታ ላይ መሽጎ ብዙ የየመንን ወታደሮች እንደገደለ እ.ኤ.አ. ከ2012 በፊት መረጃውን ሰምቼለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም. በሱማሌ ኢስላሚክ ኮርት ህብረት የሚባል ኋይል ስልጣንን መቆጣጠር ጀመረ፡፡ ከአስራ ሁለት አመት በፊት ያገኘሁት አንድ ወታደራዊ ኮኖሬል፣ ይህ ኮኖሬል በፒስ ኤንድ ስኩሪቲ ከነ ጀ/ል ሳሞራ የኑስ ጋር በተልኮ እንግሊዚ ሃገር በሚገኝ ዩነቨርስቲ በዚያን ግዜ ይማር የነበረ ነው፡፡ ኢስላሚክ ኮርት መወገዱ ለኢትዮጵያ ብዙ ጥቅም እንዳለው ነግሮኝ፣ አልሸባብ ግን ትንሽ ሞድሬሽን እንዳለው አጫውቶኛል፡፡
በግዜው የነበረው የዋያኔ መንግስት በእስላሚክ ኮርት ህብረት ላይ ያን አቋም የያዘው፣ እስላሚክ ኮርት እንደሚለው፣ ማነኛውም ሱማሊኛ ቋንቋ የሚናገር ሰው ሁሉ በእንድ ሱማሌ ውስጥ መጠቃለል አለበት በማለቱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የታለቋ ሱማሌ የሲያድባሬ መፈክር በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር የግዛት ይገባኛል ጥያቄን ስለሚያነሳ ነበር፡፡
ዛሬም ይህን የእሪዴንቲዝም ፖለቲካ በቅጡ ያልተገነዘቡ የኦሮሞ መሪዎች ኦሮሚኛ ተናጋሪ ያለበት ስፍራ ሁሉ ኦሮሚያ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አስተሳሰባቸውም የኬንያን መንግስት ድጋፍ እንኳንነ ማግኘት ሲሳናቸው ተመልክተናል፡፡
ይገርማል፣ በጨቅላነቱ ዘመን በሱማሌ ፓስፖርት ሲንቀሳቀስ የነበረው ወያኔ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ 1998 ዓ.ም. ላይ ወደ ሱማሊያ ለመዝመት መለስ ፓርላማውን ሲያነጋግሩ በሕይወታቸው ዘመን አንድ ግዜ ብቻ ከአፋቸው የወጣውን ቃል “እናት ኢትዮጵያ እንዲህ ትጠይቃለናችን…” ብለው ተናገሩ፡፡ እኔ ድሮ የዩንቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ምናልባትም በአርባና ሃምሳ እድሜያቸው መካከል የማውቃቸው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለጠ/ሚ ጥያቄ እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ እኛ ይህን ነገር አንቃወምም…እንደው ዝም ብለን እናያለን አይነት ነገር ተናገሩ፡፡ በግዜው እሳቸው የአጥር ላይ ተንጠልጣይ ፖለቲከኛ ተደርገው በወያኔ ሚዲያዎች ተብጠለጠሉ፡፡
የወያኔ ጦር አሜሪካኖቹ ኮንተራክት አውት በደረጉለት ጦርነት ውስጥ ዘሎ ገባ፡፡ ኢሳያስ አፈወረቄ ግን፣ ዘለህ ሰው ሃገር ገብተህ አቧራ አቡነህ የት ትደርሳለህ ሲሉ ጠየቁ፡፡ እውነታቸውን ነው፣ አቧራው እስከአሁን እንደ ቦነነ ነው፡፡
ኤርትራ ሱማሊያ ውስጥ እጇ ረዘም ያለበት ነገር ምንድን ነው ብለን እራሳችንን ብንጠይቅ መልሱ ሌላ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በሃገር ደረጃ ቀኝ ገዢዎችን ያልተዋጋች ሃገር ኤርትራ ነች ብለው የሚጽፉ አሉ፡፡ ነገር ግን ቀናዊያን የኤርትራ ተወላጆች ሃገራችን ነች ብለው ባመኑባት ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው ተዋግተዋል፡፡ የአዶልፍ ፓርስላክ “የሃበሻ ጀብዱ” የሚለውን መጽሐፍ ብናነብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን የሰላሌው ጀግና የአቢቹን ጦር ደግፈው ትግራይ ውስጥ ይዋጉ እንደነበር ጥሩ መረጃ ይሰጠናል፡፡ ታላላቅ ኤርትራውያንን እነ ሞገስ አስጎዶም፣ አብርሃም ደቦጭ፣ ዘራይ ደረስ…ብንረሳ ታሪክም ይቅር አይለንም፡፡
ጣሊያን መጀመሪያ የባህረ ነጋሽ ሃገርን(ኤርትራ) ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የትግራይ ትግሬውና አማራው ተግተው ተዋጉት፡፡ ነገር ግን ቆንጆዋና እድለቢሷ ኤርትርያ በጣሊያን ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡ ጣሊያንም በብዙ አስር ሺህ የሚቆጠሩ ኤርትርያኖችን ወደ ትርምቡሌና(ትሪፖሊ) ሶማሊያ ለወታደርነት መልምሎ ላካቸው፡፡ ያ ኤርትራ ውስጥ መሽጎ ፋሺስስት ጣላያንን ሊዋጋ ይችል የነበረው ኋይል መከነ፡፡ ዛሬ በሱማልያ መቋደሾ ያሉ ሱማሊያውያን የኤርትራ ዘርም ያለባቸውና ወደ ኤርትራ ያልተመለሱ ወታደሮች ልጆችም ናቸው፡፡
ሱማሊያ ከሃበሻ ጋር ያገናኘው ታሪክ በመቶ አመት የሚቆጠር ብቻ አይሰደለም፣ ከፍረኦን ዘምን ጀምሮ የሚቆጠር እንጂ፡፡ የጥንት ግብጻውያን አሁን ያለው የሃበሻ መልክ የነበራቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ይህንንም በድንጋይ ከተቀረጹ ሃውልቶቻቸውና በግድግዳ ላይ ከተሳሉ ምስሎቻቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ማርቲን በርናል የጻፉትን “ብላክ አቴና” ሁለት ቅጽ መጽሐፍት ስለ ጠይም ግብጻውያን ጥሩ ግንዛቤ የሚሰጥ መጽሐፍ ነው፡፡
በ1372ዓ. ዓ. የተወለደው የፈርኦን አክናቶን ታሪክም ይህን ነው የሚያስረዳን፡፡ እናቱ ንግስት ቲዬ ስትባል ከምስራቅ አፍሪካ የሄደች ነግስት እንደሆነች ነው የሚተረክላት፡፡ ግማሾች ከዛሬዋ ወሎ ክ/ሃገር ነው ሄደችው ሲሉ ሌሎቹ ደግም ሱማሌ ነች ይላሉ፡፡ ንግስቲቱ የአይሁድ እምነት ተከታይ እንደነበረችም የሚናገሩም አሉ፡፡
አክህነአቶን ብዙ ጣኦታት ታመልክ የነበረችውን ግብጽ በአንድ አምልክ፣ ፍቃዱና ግብሩ በፀሐይ በሚገለጥ አቶን በሚባል አምላክ ቀየረ፡፡ ከዚያም የራሱን ከተማ “አማርና” የተባለ በከፍተኛ ፍልስፍና፣ ግልጽነትና ስነውበት ላይ ንድፍ በወጣበት ከተማ ላይ መሰረተ፡፡ ነገር ግን እሱ ከሞተ በኋላ ግብጻውያን ወደ ጥንት አምልኳቸው ተመለሱ፡፡ የሱንም ስራና እምነት ከየ ሃውልቱ፣ ግድግዳ ጽሑፍና ምስል ላይ ደመሰሱት፡፡
ዛሬ ዛሬ እክናቶን እራሱ ሙሴ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከእስራኤላውያኑ ጋር ያልውጡና በግብጽ የቀሩ ጥቁር አይሁዶች ናቸው የሚሉም አሉ፡፡ የሆኖ ሆነ አማራ ከሚል ቃል ጋር ተመሳሳይ የሆነ በአባይ ሸለቆ ውስጥ ለመጀመሪያ የተጠቀሰው የከተማ ስም አማርና ነው፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን አማራ የሚለውን ቃል በጥንት ግብጻውያን ሂሎግራፊክስ ጽሑፍ ሲፈቱ፤ አም-ሓ-ራ ማለት የሰማይ ሰራዊት ማለት ነው ብለው የአማርናን ተዛማች ትርጉም ያፀናሉ፡፡
ከአክናቶን ዘመን መቶ አመት በፊት በንግስት ሃትሼፕሱት ዘመነ መንግስት 1478 ዓ. ዓ. ላይ ንግስቲቱ የፑንት(አማልክት) ምድርን ለመፈለግ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ያደረገችው ጉዞ አለ፡፡ ፑንት ማለት ግብጻውያኑ የአማልክቶቻችን ምድር ነው ብለው የሚያምኑት ስፍራ ነበር፡፡ ይህ ምድር በኤርትራ፣ጂቡቲ ኢትዮጵያና ሱማሌ ባህር ዳርቻዎች ላይ የነበረ ነው የሚሉ የታሪክ ተመራማሪዎች አሉ፡፡
በደቡብ ግብጽ በ ሐማማት ሸለቆ በሂሮግላፊክስ የተፃፈ ማስረጃ እንደሚለው በ2278 ዓ.ዓ. ከግብጽ ወደ ፑነተ አማልክት ሃገር ሃኑን የተባለ ሰው፣ ቅመማቅመም፣ ኪሰሞቲኮቸ፣ የነብር ቆዳና ጭላዳ ዝነጀሮዎችን ወደ ግብጽ ወስዷል፡፡ እሱም ይህን ሁሉ ነገር ይዞ የሄደው በአማልክት ምድር ከኡግ እስከ ሩህ ተጉዞ እንደነበር ጽፏል፡፡ይህም ከዋግ እስከ ሮሃ ወሎ ውስጥ ያደረገውን ጉዞ ያመለክታል ሲሉ ታሪክ ጸሐፊዎች ይጠቅሳሉ፡፡ የጥንት ግብጻውያን ከፑንት የመጡት የነበረው እጣንና ኩል የመሳሰሉት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነገሩበት ቃላት ጋር አንድ ናቸው፡፡ እንግዲህ ቤተ አማራ(ወሎ) በዚህ መልክም በጥንት ግብጻውያን ዘንድም ይታወቅ ነበር፡፡ የጥንት ግብጻውያን እስከ አምልኮት የደረሱለት የጭላዳ ዝንጀሮ በላስታ ላሊበላ አማውሬ ተራራዎች ላይ እንደሚገኝም እናሰታውስ፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ከሱማሌ ጋር ምን አገናኘው ትሉ ይሆናል፡፡ ሱማሌ ውስጥ ያቢር(ሂብሩ) የሚባል የቤተእስራኤል ዘር አለ፡፡ እነዚህ ዘሮች እንደ ዝቅተኛ ጎሳ ነው የሚታዩት፡፡ ለተወለደ ህጻንም በእነሱ የሚደረግ ሪቱአል አለ፡፡ ከያቢሮች ውስጥ ጎነደሬዎች ነን ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ በሱማልያ ያሉ የቦታ ስሞችን እያነሱ፣ ለምሳሌ ቀብሪ ዳህር(ከቀብር በኋል)፣ መቋደሾ(መቅደስ) ቀብሪ በያን… የጥንት ሴማዊ የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች በሱማሌ ይኖሩ አንደነበር አስረግጠው የሚጽፉ አሉ፡፡
በልጅነቴ አንድ የአባቴ ዘመድ ወለዬ የነገረችኝን ነገር አልረሳም፡፡ ግዜው የኢትዮጵያና ሱማሌ ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ ጎዴ ይኖሩ የነበሩ ወለዬዎችን በሱማሌ ጦር ይያዛሉ፡፡ ከዚያም በነበረው ንቃተ ህሊና ደረጃ ”እናንት ማን ናችሁ?“ ብለው ሱማሌዎቹ ይጠይቋቸዋል፡፡ እነሱም ወለዬ ኢትዮጵያውያን ነን ብለው ይመልሳሉ፡፡ በዚያን ግዜ እናንተማ ዘመዶቻችን ናችሁ ብለው ይምሯቸዋል፡፡
ለነገሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘመዳቸው ነበር፣ አልተመረመረም እንጂ፡፡ እዚህ ውጭ ሃገር ከመጣው በኋላ የይስሃቅ ጎሳ አባላት የሆኑትን ሱማሌዎችን አግኘቻለው፣. እንዲሁም የፑንት ላንዶቹንና የመቋሾዎቹንም፡፡ ሁሉም በአንድነት እናታችን ሃበሻ ወለዬ ነች(ሃቡሽ አበዳር) ይላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በዘር ማንዘራቸው ሲንከባለል የወረደላቸው ጥንተ ነገራቸው መሆኑ ነው፡፡
በኦሮሞና ሱማሌ መካከል ያለ ግንኙነት ይገርማል፡፡ ኦሮሞዎችም ሆኑ ሌላው ብሔር በጽሑፍ ስለ ኦሮሞ ታሪክ ከመጻፉ በፊት ቅድመ እስልምና የሱማሌዎች አምላክ ዋቅ እንደነበር በአረቦቹ ተጽፉል፡፡ ይህ ዋቅ፣ አያንሌ የሚባሉ በሰዎችና ዋቅ መካከል የሚማልዱ መናፍስት እንደነበሩት እንዲሁም ሁር የተባለ የሞት መለአክት እንደነበረው ይተረካል፡፡ ልክ ዛሬ በዋቄፈና ኦሮሞ እንዳለው ዋቅና ና አያና ማለት ነው፡፡
የሱማሌዎቹ ሆር፣ እንግዲህ የጥንት ግብጻውያን የሚያመልኩት የነበረውን ሆረስን አመላካች ነው፡፡ ምናልባት ቢሸፍቱ ካለው ሆራ ሓይቅ ጋር ይገናኝም ይሆናል፡፡ ታዲያ እዚህ ባለሁበት ሃገር፣እንዲህ ያለውን ታሪክ የሚያውቁ ሱማሌዎች አግኝቼ ነበር፡፡
እነሱ እነደሚሉት ኦሮሞ ማለት የሱማሌና የደጋው አማራና ሌሎች ህዝቦች ቅልቅል ነው፡፡ እነሱ የሚሉት ታላቋ ሱማሌ ድንበሯ እስከ ደብረዘይት(ቢሸፍቱ) ድረስ ነው፡፡ ለዚህ ምክነያታቸው ደግሞ ግራኝ አህሃመድ ደገኞቹን ነገስታት 16ኛው ክ/ዘ ላይ በተደረገው ጦርነት ያሸነፈው ናዝሪት አካባቢ ሽንብራቁሬ የሚባል ቦታ ላይ መሆኑን የአረቦቹንና የደገኞቹን ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፉትን ታሪክ አጣቅሰው ይናገራሉ፡፡ በነገራችን ላይ ሱማሌዎች ግራኝ አህመድ ሱማሌ እንደሆነ ነው የሚያምኑት፡፡ ሰሜቲክ የሆኑት ሃረሪዎች ግን ግራኝ አህመድ የኛ ነው ይላሉ፡፡
አንዳንድ ሱማሌዎች ኦሮሞ እስልምና ከመነሳቱ በፊት የሱማሌ ህዝብ ነበር፡፡ ሱማሌዎች ከ7 ክ/ዘ በኋላ ሞስሊም ሲሆኑ ኦሮሞዎቹ እስልምናን አንቀበልም በማለታቸው ከአረብኛው ቃል ጋ(ቃ)-ላ ያው በአረብኛ ”ላ“ አይሆንም ማለት ነው፡፡ “እምቢ አለ” የሚለውን ትርጉም ይዞ በዛው ተጠራበት ይላሉ፡፡ ሱማሌ ውስጥ ከምትገኝ ጋላይኮ ከተማ እነዚህ በሱማሊኛ ”ጋ(ቃ)ለ“ ወይም እስልምናን ያለተቀበሉ(ኢአማኒያን) ተብለው የሚታወቁት ተገፍተው በመውጣት ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ሰፈሩ፡፡ በሂደትም ይናገሩት የነበረው ሱማሊኛ ወደ ኦሮሚኛ ተቀየረ ይላሉ፡፡
ይህ በሱማሌዎቹ ዘንድ እራስን የመጀመሪ አድርጎ መናገር ባህል ኢትዮጵያ ውስጥም ይንጸባረቃል፡፡ አማራውም፣ትግሬውም ኦሮሞውም ሁሉም እኔ ነበርኩ የመጀመሪው ይላል፡፡ የሰው ዘር አዳማዊ ነው ካልን ዘንዳ፣ አዳም ትግሬኛ፣አማርኛ፣ኦሮሚኛወይም ሱማሊኛ ተናጋሪ ነበር ማለት ግን ይከብዳል፡፡ ስለዚህም መጀመሪያም የሌለን መጨረሻችንም የማይታወቅ ድብልቅ ህዝቦች ነን፡፡ ዲ.ኤን.ኤችን እየመሰከረ የሚገኘውም ይህንኑ ነው፡፡
እዚህ ባለሁበት ሃገረ ካናዳ ኤሲያውም ሆነ ሌላው አውሮፕያን መሰረት ያለው ሰው፣ አፍሪካን የሚያያት እንደ አንድ ሃገር ነው፡፡ ብትጠቁርም ብተቀላም፣ አፍንጫህ ቀጥ ቢልም ቢጎመድም፣ ለውጥ የለውም ሁሉም ጥቁር ጠቁር ነው በቃ፡፡ ምዕራብ አፍሪካ፣ምስራቅ አፍሪካ ወይም ደቡብ አፍሪካ ብለው አይለዩህም፡፡ እንዲህ አይነት አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በእየሄድክበት ያጋጥሙሃል፡፡
ከአምስት አመት በፊት የጉልበት ሰራተኛ ነበርኩ፡፡ ድክም ብሎኝ እራቴንም መክሰሴንም ልበላ አንድ አነስተኛ ሬስቶራንት ውስጥ ገባሁ፡፡ ወንበር ፈልጌ ከአንዲት ነጭ ሴት ፈንጠር ብዬ ተቀመጥኩ፡፡ ከዚያም በመሃላችን እንግሊዘኛ እንደ ካናደውያኖቹ የምትነገር አንዲት ኤሲያውት መጥታ ተቀመጠች፡፡
ለካ ሁለቱ ይተዋወቁ ኖሯል፡፡ ትንሽ ካወሩ በኋላ ወደጭቅጭቅ አመሩ፡፡ ነጯ ይህን ግዜ ወደእኔ አስጋ በማየት፡ እዚህ የቀጠርሽኝ ለዚህ ሱማሌ አሳልፈሽ ልትሰጪኝ ነው አይደል? ተነቅቶብሻል አይነት ንግግር ተናገረች፡፡ ኢትዮጵያውያንና ሱማሌዎች ብዙ የመልክ መመሳሰል እንዳለን አውቃለሁ፡፡
አንዲሁ አንድ ግዜ አንድ የማውቀው ኤርትራዊ አንድ ቦታ ይዞኝ ሄዶ፤ አንድ ነጭ ጓደኛው ወደ እኛ ሲመጣ ተዋወቀው ሲል ወደእኔ ጠቆመው፡፡ ሰውየውም ሱማሌ እስካልሆነ ድረስ እተዋወቀዋለው አለ፡፡ መች በዚህ ብቻ አበቃና በቅርብ ግዜ ሪሜምበራንስ ደይ ላይ እመስሪያ ቤቴ አጠገብ ያለ ሬስቶራንት ውስጥ ቁጭ ብዬ ሰው እየጠበኩ እያለ(ኮርያኖች ሬስቶራነት ነው) አንድ ነጭ ሰው መጥቶ ከፈለገ በአራት ሰአት ውስጥ ወደ ሃገርህ ልመልስህ እችላለው አለኝ፡፡ ከዚህ ሰውዬ ጋር አብረው የሚሆኑ ኤርትራውያንን በሌላ ግዜ አግኝቼቸው፣ ለምን እንደዛ እንዳለ ስጠይቅ ሱማሌ መስለህው ነው አሉኝ፡፡
ሱማሌ ብሆንስ? ካናዳ ድረስ ሱማሌዎች የመጡት የካናዳ መንግስት ተቀብሎቸው ነው፡፡ የዚህች ሃገር ዜጋ ሆነው የራሳቸውን አስተዋጾ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እዚህ ሃገር ስራ ሰርተህ ታክስ ከከፈልክ፣ ካናዳን ከናዳ ከሚያደረጓት መካከል አንዱ ነህ፡፡ ይህንን ፍርደቤት ላይ ቆመህ ልትከራከርበት ትችላለህ፡፡ ተቀባይነትም አለው፡፡ እዚህ ሃገር ለመምጣት ተራው ሱማሊያዊው እንደማይችል ቢውቁ ኖሮ ምናልባት እንዲህ አይነቱን ጅምላ ፍረጃ የሚያደርጉ ሰዎች በጣም ይቀንሱ ነበር፡፡
እንድ ፊፍዝ ሰቴት የሚል መርማሪ ዘገባ ፊልም ላይ ከሲያድባሬ መውደቅ በኋላ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ዳኞችና የደህንነት ስራተኞች የነበሩ ሱማሊያዎች በሲ.አይ.ኤ. እርዳታ መጀመሪያ ወደ አሜሪካ መጥተው፣ መዳረሻቸውን ካናዳ እንደአደረጉ ፊለሙ በተጨባጭ ሁኔታ ይዘግባል፡፡ ታዲያ እነዚህ ወንጀለኞች ስልጣን ላይ እያሉ ዘመዶቻቸውን የገደሉባቸው ሱማሊያውያን እያደኗቸው ይገኛል፡፡
የሚገርመው ነገር ብዙ የወያኔ አገልጋይ የነበሩ ሰዎች እዚሁ ካናዳ ውስጥ ገብተው፣ ተቃዋሚ ነበርን ብለው በሰላም እየኖሩ ይገኛል፡፡ አይነተኛውና አንዱ ምሳሌ የሃረሪው ዶክተር በመባል የሚታወቀው የወያኔ የህዝብ ደህንነት ኋላፊ ነው፡፡ እነ አብዲ ኢሌ ላይ የዘመተው የአብይ መንግስት፣ በምስራቅ አፍሪካ ፖለተካ ላይ ደህንነቱን ሲያሾር የነበረውን ይህን ሰው አምልጦ ሲሄድ ዝም ብሎ አይቶ፣ ዛሬ ካናዳ ላይ ነጻነቱን ሲያሰጠው ማየት ወቼ ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡
እዚህ ያገኘኋቸው ሱማሌዎች፣ ሱማሊያ ውስጥ የባህር ላይ ዘራፊዎች የተነሱት እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. በተነሳው ሱናሜ ምክነያት፣ በሱማሌ የባህር ዳርቻዎች የተቀበሩ ገዳይ ራዲዮ አክቲቭ ኬሚካሎች ከባህር ዳርቻ ወጥተው መሬት ላይ በመታየታቸውና በዚህም ብዙ ሰው ለሞትና ለበሽታ በመዳረጉ ነው ይላሉ፡፡ ይህንን ከብዙ የተማሩ ሱማሌዎች ሰምቼለው፡፡
እውነት አላቸው፣ ግን ፈረንጆች ሃስቲ ጀነራላይዜሽን የሚሉትን ተጠቅመዋል ባይ ነኝ፡፡ የፈረንጆቹ የፖለቲካ መዋቅር ምነም አይነት ገዳይ ኬሚካል አምጥቶ አፍሪካ ላይ አይቀብርም፡፡ የኒውኩላር ዝቃጭንም ይሁን ገዳይ ከሚካሎችን አፍሪካ ውስጥ አምጥተው የሚቀብሩት እነዚህን ውጤቶች የሚጠቀሙ ኩባንያዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ኩባኒያዎች ያላጠፉት የምድር አካለ የለም፡፡ ሰላማዊ ውቅያኖስንና ሜደተራኒያን ባህርን ሁሉ በክለዋቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ አፍሪካ ሃገር ያሉ ፖለቲከኞች ስንት ትከፍለኛለህ እያሉ እነዚህ ኬሚካሎችን እያስቀበሩ ይገኛሉ፡፡ ምዕራብ አፍሪካም የዚሁ ጉዳይ ሰለባ ነች፡፡
እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ.ም. የጣልያን ኩባኒያዎች ሱማሌ ውስጥ ቶክሲክ ዌስት ይጥሉ እነደነበር የአውሮፓውያን መጽሔት አጋልጧል፡፡ አሁን ጦርነቱ የጎሳ፣የብሔር ወይም የሃገር አይደለም አለም አቀፋዊ ነው እንጂ፡፡
ሱማሌ ውስጥ የነበረውን ገዳይ ኬሚካልና ራዲዮ አክቲቨ ዝቃጭ፣ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም. የነበረው ሱናሜ ከባህሩ ውስጥ ገልብጦ ወደ ላይ አወጣው፡፡ ነገሩ ለአለም ይፋ ሲሆን፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊም፣ እንዴት ይህ ይደረጋል ብለው እምቧ ከረዩ አሉ፡፡ እውነት አላቸው፣ ያን ግዜ ከ1993 ዓ. ም. በፊት ከ60 በመቶ በላይ ወያኔ የስዮ አብርሃ ደጋፊ በነበረበት ግዜ አንድ ነገር ሆኖ ነበር፡፡
ስድስት ኮንቴይነር፣ እላዩ ላይ በግዜው ምስጢሩን ያወጣው ልጅ ግማሽ ግማሽ ክቦች የተመሳቀሉበት ምልክት ያየበት፣ የበርሜሎች ጭነት፣በኢትዮጵያ ጅምሩክ በኩል ይመጣል፡፡ በዚያን ግዜ የነበሩ የፋያይናንስ ፖሊሶች ነገሩን ለመፈተሸ ይሰማራሉ፡፡ አምሰቱ ላይ እርምጃ ሲወሰድባቸው አንዱ ተረፈ፡፡ ይህ ሰው ምስክርነቱን ለመአድ(መላው አማራ ድርጅት) ለነበሩ ሰዎች የምስክርነት ቃሉን ቢሰጥም፣ እስከ ኡጋንዳ ተከታትለውት አጥፍተውታል ነው የሚባለው፡፡
ዛሬ ስንለየው እኒያ ሁሉ ወደ ሃገራችን የገቡ ቶክሲክ ኬሚካሎች የት ተቀበሩ ካልን፣ የሃገራችን ተምቤንና የሃገራችን ሰቆጣ ዋሻዎችን እያሰብን እግዜር ይሁንላቸሁ ከማለት በቀር ምን ልንል እንችላለን፡፡ አራዳው ጠ/ሚ መለስ ግን አፈንጋጭ ጀነራሎቹን ለማሸማቀቅ ሱናሜና ሱማሊያ የሚል ጨዋታ ተጫወቱ፡፡ እነ ስዬ ከታሰሩ በኋላ ሁለት ሶስት አመታት ያክል ጠ/ሚ መለስ እንዳልተዋቸው ከምናይባቸው የሴራ ቅንብሮች አንዱ በአዲስ አበባ የትግራይ ሆቴል ፍንዳታን እናስታውስ፡፡
የኬሚካል ዝቃጮች በምእራብና ምስራቅ፣ ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ላይ ተቀብረዋል፣ እየተቀበሩም ይገኛል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ተጠያቆቹ ደግሞ የአፍሪካ ንቅዝ ወታደራዊና ፖለቲከኛ ሹሞኞች ናቸው፡፡ ከካምፓኒዎቹ ገንዘብ እየተቀበሉ ኬሚካል ዝቃጭዎችን ሃገራቸው ላይ ያሰቀብራሉ፡፡ ይህ ሱማሌ ውስጥ ሲያደባሬ በስልጣን ላይ በነበረበት ግዜ ተደርጓል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች በአውሮፓ፣ አሜሪካና ኤሲያ ይገኛሉ፡፡ የከሚካል ዝቃጭዎቻችውን ሃገራቸው ላይ መቅበር አይችሉም፡፡ ምክነያቱም ያን እንዳያደርጉ የሚግድ ህግና ተፈጻሚነቱን የሚከታተል ድረጅት አለ፡፡ ስለዚህም ወይ መሳሪያ ወይ ገንዘብ ለሚፈልግ አፍሪካዊ የጦርነት ከበረቴ ጀባ ይሉታል፡፡ ነገሩ እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡
ዶ/ር ሰለሞን ይርጋ የሚባሉ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የባሎጂ መምህር የነበሩ… አንድ ሰው “ህልውና” የሚል መጽሐፍ ከሃያ አመት በፊት ጽፈው ነበር፡፡ በሳቸውን መጽሐፍ ላይ በብሔራዊ ሙዚየም ከአስር አመት በፊት ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ በእለቱ እሳቸውም ታዳሚ ነበሩ፡፡
እሳቸውም ለአፍሪካ በታላቅ ተቆርቋሪነት ይህንኑ ኬሚካል ዝቃጭ ቀበራ ተቃውመው ጽፈዋል፡፡ ግን ኩባንያዎችንና መንግስትን አንድ ላይ ጨፍልቀው ነበር ያቀረቡት፡፡ እኔም በዚህ አቀራረባቸው ላይ ሂስ አቅረቤባቸው ነበር፡፡ ያ መጽሐፍ የሴራ ትንታኔ ቅባት ባይኖረው ኖሮ ወይም የቢሆንስ ትንታኔን መንገድን ዘዬ(Senario analysis)ቢከተል ኖሮ አለም አቀፋዊ ተቀባይነትን ያገኝ እንደነበር አሁን እዚህ ሆኜ(ውጭ ሃገር) ይሰማኛል፡፡
በአውሮፓና አሜሪካ መርማሪ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ ህይወትን በየገጽታዋ ይመረምሯታል፡፡ ወላ ሚሊተሪው፣ፖለቲከኛው፣ በሃሰት ማስረጃ ዶ/ር የሆኑ ባለስልጣናት አይቀሯቸውም፣ እምጥ ይግቡ ስምጥ ፈልፍለው ያወጧቸዋል፡፡ የዲሞክራሲ ከፍተኛው ጠቀሜታው እዚህ ላይ ነው፡፡
እኔም ጎሰኝነትና ብሔርተኝነት ለሰፈነባት፣ እራሷን ለተለያዩ አደጋዎች አጋልጣ ለሰጠቸው አፍሪካዬ በተለይም ምስራቅ አፍሪካዬ አያሌ መርማሪ ዘጋቢዎችን ተመኘሁላት፡፡ ዛሬ ኢተዮጵያ ውስጥ ኦሮሚኛ ተናጋሪው አማራ ወለጋ ውስጥ በኦሮምኛ ተናጋሪ ወንደሙ እየተገደለ ነው፡፡
ወለጋ ደግሞ ጥሩ የእረሻ መሬት ሃገር ስለሆነች ሳይሆን የተባረከ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት በመሆኗ ነው እዚያ ቤት ምን አለ ደላሎች አይን ማረፊያ የሆነችው፡፡ እኛ እንስማማ እንጂ የምስራቅ አፍሪካ ሃገሮች ሁሉ በመአድን የበለፀጉ ናቸው፡፡ መዋጊያ መሳሪያ ከፈለግክ ግን ብዙ ህሊና ቢስ ደላሎች ያለህን የመአድን ሃብት በታሳቢነትም ቢሆን አሲይዘህ መሳሪያ ያቀርቡልሃል፡፡
የአንተ የብሔር ንቃተ ህሊና እነሱ ካለቸው ልምድ ጋር ሲተያይ ምንም አይደለም፡፡ አትችላቸውም፣ አትጀምረው እንጂ ያጫርሱሃል፣ ይጨርሱሃል፡፡ በል እንግዲህ ካላመንከኝ Blood Dimond የሚለውን ፊልም እንድታይ ጋብዤሃለሁ፡፡ ህዝብን አጽድተህ መሬቱን ለልማታቸው በአጭር ግዜ ዝግጁ ካላደረክ ደግሞ ተለዋጭ ፕላን አላቸው፡፡ የኬሚካል ጥምባቸውን አምጥተው ይጥሉብሃል፡፡
ለምን ይመስልሃል የውጭ መአድን ኩባንያ የውጭ ዜጋ ሰራተኞች ወለጋ ውስጥ የሚገደሉት፡፡ አንዱ ድረጅት የጥቅም ግጭት ሲኖረው ሌላዎቹን ለማጥፋት በየ ብሔርና ጎሳ ውስጥ የሰገሰጋቸው ምልምሎቹን ስለሚያሰማራ ነዋ፡፡
ዛሬ ቫግነር የተባለ የሩሲያ ወታደራዊ አንደር ግራውንድ ድርጅት በመካከለኛው አፍሪካ ውስጥ ያሰማራቸው ወታደሮች ጥቅማቸውን በሚኒራል እየተቀበሉ የአፍሪካ መሪዎችን በነጭ ወታደሮች እያሰጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ያሳዝናል አፍሪካ ራስሽን የምስራቁም ይሁን የምዕራቡ የጦርነት ንግድ አትራፊዎች ኩባኒዎች ላይ ስትጥዪ ስናይ፡፡ አረ ምኑ ቅጡ የሩቅ ምስራቁስ ቢሆነ መች ቀረና፡፡
ነበዴ ሱማሌ፣ ሰላም ለዜጎች ሁሉ!!!
አስቻለው ከበደ አበበ
ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ
https://amharic-zehabesha.com/archives/178372
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment