እለቱ ህዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡ በኢ.ፌ.ደ.ሪ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በ6ኛው ዙር 2ኛው የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ ተሰይሟል፡፡
ዋንኛው የእለቱ የመወያያ አጀንዳ ደግሞ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለዎርቅ ዘውዴ ከበርካታ ሳምንታት በፊት ለኢ.ፌ.ደ.ሪ የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች አባላት የጋራ ስብሰባ አድርገዉት የነበረውን አመታዊ የመክፈቻና የመንግሥታዊ ስራ እቅድና ፕሮግራም ማስተዋወቂያ ንግግር በተመለከተ በእንደራሴዎቹ አማካኝነት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ተፈላጊውን መልስና ማብራሪያ ለመስጠት ሲሆን ይህንኑ ተግባር ከበቂ በላይ የሆነ ጊዜ ወስደው አከናውነዋል፡፡
ከዚያ ባሻገር በት.ህ.ነ.ግና በፌደራሉ መንግሥት መካከል ሲካሄድ የቆየውን ድርድርና በአፍሪካ ሕብረት ሸምጋይነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ፕሪቶርያ ላይ የተፈረመውን የተኩስ ማቆም ውልም ሆነ የዘላቂ ሠላም ስምምነት ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅና ተዛማጅ ያልሆኑ ጉዳዮችን አክለው ሰፊ ሀተታ አቅርበዉባቸዋል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ መድረክ ከተነሱባቸው አያሌ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን በሚገባ የመለሱ ሲሆን ሌሎቹን ደግሞ ከአንደኛው ጠርዝ ወደሌላው እያንገዋለሉ ያለጥልቅ ምርመራ ሲዘሏቸው ተመልክተናል፣ አዳምጠናልም፡፡ ጨርሶ ያልዳሰሷቸው ጥያቄዎችም እኮ ነበሩ፡፡
ሆኖም በዚህ አጭር መጣጥፍ ትኩረት ለማድረግ የምሻው ተዥጎርጉረው በታለፉ ወይም ሀቀኛ ምላሽ ባልተሰጠባቸውና ከናካቴው ባልነካኳቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሆናል፡፡
ፈርዶብኝ ቀዳሚ ትኩረቴን የሳበው ታዲያ የዎልቃሂት ጠገዴና የራያ እጣ ፈንታን የሚመለከተው ጉዳይ መሆኑ አልቀረም፡፡
ቀድሞ ነገር ወደደቡብ አፍሪካ የተጓዝነው በሠላም ድርድሩ ስም በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁትን እነዚህን አካባቢዎች ለተደራዳሪው ቡድን አሳልፎ ለመስጠት ወይም ለማስረከብ አልነበረም በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተንደረደሩበት የማስተባበያ ምላሽና ማብራሪያ ገና ከጅምሩ እንደተወሰደ አቋም ተደርጎ ተተርጉሞባቸዋል፡፡ ይልቁንም የፌደራሉ መንግሥት ይህንን የማድረግ መብት ጨርሶ እንደሌለው በአጽንኦት ካስታወሱ በኋላ በተለይ ዎልቃሂቴ ዎትሮውንም ቢሆን የተወላገደ አማርኛ ወይም ትግርኛ ሲናገር የኖረና የራሴ የሚለው ማንነት ያለው ማሕበረ-ሰብ እንጂ የግድ ትግሬ ወይም አማራ ካልሆንክ ተብሎ ሊቀነቀንለት የሚገባ እንዳልሆነ የራሳቸው ድምዳሜ ላይ የደረሱበትን ሃሳብ እንዳዲስ አስተጋብተዋል፡፡
በርግጥ የምክር ቤቱ አሰራር ስለማይፈቅድ መሰለኝ፣ የክትትል ጥያቄ በማቅረብ መልሶ የሞገታቸው ሰው ባለመኖሩ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከልባቸው ይሁን ከኩላሊታቸው በውል ለመረዳት ያዳግታል፡፡
አንድ ጥሬ ሀቅ ግን ተፈናጥሮ እንደወጣባቸው የሚያከራክር ሆኖ አልተገኘም፡፡
ያ ንግግራቸው የዎልቃሂት-ጠገዴና የሰቲት ሁመራ ነዋሪ ህዝብ ለማንነት-ነክ ውዝግብ እንደተዳረገ መቀጠሉ ቀርቶ ተጠሪነቱ ለአማራም ሆነ ለትግራይ ክልል ሳይሆን ለፌደራሉ መንግሥት ሆኖ እንዲተዳደር በህቡእ መታቀዱን አመላካች ተደርጎ ተወስዶባቸዋል፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ በህ.ወ.ሀ.ትና በፌደራል መንግሥቱ መልእክተኞች መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ፕሪቶርያ ላይ በተፈረመው የሠላም ስምምነት ውስጥ በየትኛውም ስፍራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተካቶ አናገኘውም፡፡ ከዚያ ይልቅ የስምምነት ማእቀፉ በአንቀጽ 10 ንኡስ አንቀጽ (4) ስር የደነገገው የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውና ሁለቱን አጎራባች ክልሎች የሚያነታርኩት የትኛዎቹም ግዛቶች በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥትና ሕገ-መንግሥታዊ ስርአት መሰረት ታይተው አስተዳደራዊ መፍትሄ የሚሰጥባቸው ስለመሆኑ ብቻ ነው፡፡
ይህ በራሱ ምን ማለት እንደሆነ በሰፊው ሊያወያይና ሊያከራክር ቢችልም ቢያንስ ግን በምክር ቤቱ ፊት እየተቅለሰለሱ እርሳቸው እንዳቀረቡት ዎልቃሂት ራሱን ችሎ እንደሚደራጅና ለፌደራሉ መንግሥት እንደሚጠራ ከወዲሁ የሚጠቁም አንድምታ የለውም፡፡ ያንን በማድረግም ለችግሩ ፍትሃዊ መፍትሄ ላይ መድረስ የሚቻል መስሎ ከወዲሁ አይታይም፡፡
በመሰረቱ የፌደራሉ መንግሥት አካባቢውን ለትግራይ ክልል የመመለስ መብት እንደሌለው ሁሉ ለኔ ይጠራና ራሴ በማእከላዊነት ላስተዳድረው እስከማለት የሚዘልቅ መብትም አይኖረውም፡፡
የዎልቃሂት ጠገዴ ህዝብ አሁን በስራ ላይ ያለው የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ከመውጣቱ በፊት በህ.ወ.ሀ.ት የአገዛዝ ቀንበር ስር ወድቆ በማንነቱ ያለአግባብ ሲገፋ፣ ሲታሰር፣ ሲሳደድ፣ ሲገደልና ከቀየው ሲፈናቀል የኖረ ህዝብ መሆኑን ለመካድ ያልደፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መሬቱ ቅድመ-ሕገ-መንግሥት በሀይልና በግፍ እንደተወሰደበት ቢያምኑም በጊዜው ስህተት ነበር ያሉት ይህ አይነቱ የጉልበተኞች እርምጃ ግን በሌላው ወገን ጊዜ ተጠብቆ ይደገም ዘንድ ፈጽሞ እንደማይፈልጉ በአደባባይ ነግረዉናል፡፡
እንደርሳቸው የስጋት አስተያየት ከሆነ እንዲህ ያለው የተረኝነት እርምጃ ማለቂያ ለሌለውና ለማያባራ የርስበርስ ግጭትና ደም መፋሰስ ይዳርገን እንደሆነ ነው እንጂ በአካባቢው ዘላቂ ሠላምን ሊያረጋግጥ ስለማይችል የተሻለ አማራጭ የሚሆነው በዳይና ተበዳይን አቀራርቦ በማደራደር ለተራዘመው ውዝግብ አይነተኛ መቋጫ ማበጀት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ሰለባዎቹ በማያምኑበትና ለጉዳዩ አግባብነት በሌለው ሕገ-መንግሥት መሰረት ውዝግቡ እንዴት ሊዳኝ እንደሚችል በውል አላስረዱንም፣ ሊያስረዱን የሚችሉም አይመስለኝም፡፡
ከሠላም ድርድሩ ጋር በተያያዘ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባደረጉት ገለጻ በጨረፍታም ቢሆን ያነሱት ሌላው ነጥብ በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር የመወያየቱን ተገቢነት ወይም ኢ-ተገቢነት የሚመለከተው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ተደጋግሞ የሚሰነዘርባቸውን ትችትና ወቀሳ ያጣጣሉት ዶ/ር አቢይ አህመድ ሕጉን የራሳቸው ካቢኔ እንዳላመነጨው ሁሉ ያወጣችሁት ሕግ ከአሸባሪ ጋር አትተባበሩ ነው እንጂ አትደራደሩ አይልም ሲሉ በመሸርደድ የህግ አውጪ አካሉን አባላት መክረው ላወጡት አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም ሳይቀር የሩቅ ባይታዋሮች አስመስለዋቸዋል፡፡
የተከበሩት እንደራሴዎች ግን በምላሹ የተስማሙ በሚመስል ሁኔታ ሳቅና ጭብጨባውን ሲያቀልጡት አስተውለናል፡፡ ሕግ በዋነኝነት ከሞራል ፍልስፍና የሚቀዳ እንደመሆኑ መጠን አስቀድሞ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ቡድን ለምክር ቤቱ አቅርቦ ቅድመ-ድርድር ፍረጃውን ማስነሳት እንደሚገባ እንኳ ከወዲሁ አምኖ ለመቀበል አላስፈለጋቸውም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአርበኛ ዘመነ ካሴ ጉዳይ በተለይ ተጠቅሶ ራሱ መንግሥት አስቀድሞ በሚያውቀውና በፈቀደው አግባብ በአካባቢው ተቀባይነት ያለውን የሽምግልና እሴት ተጠቅመን ሰውየውን ብናቀራርበውም ይህ በጎ ጥረታችን ወደጎን ተትቶ ባልተጠበቀ ሁኔታ ላልተገባ እስር መዳረጉ እንደምን ለሠላም መስፈን ያግዛል? እንዲህ ያለው እርምጃስ የተከበሩትን የአገር ሽምግልና እሴቶች መናድና መሸርሸር አይሆንምን? የሚል ሌላ ፈታኝ ጥያቄ በምእራብ ጎጃም ዞን የጅጋ ምርጫ ክልልን ከሚወክሉ አንድ እንደራሴ በኩል ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ሆኖም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደፊትም ቢሆን ለሠላም የምታደርጉትን ይህንን አይነቱን ጥረት ብትቀጥሉበት የሚታሰር ዜጋ አይኖርምና ግፉበት ሲሉ ጥያቄውን ያቀረቡትን ንቁ የህዝብ እንደራሴ በመሸንገል ብቻ ያለአንዳች ውል ያለው ምላሽና ማብራሪያ ማለፋቸው ይበልጡኑ አስገርሞኛል፡፡
ለመሆኑ ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ እስኪመስል ድረስ እንዳሻው ለሚፈነጨውና ንጹሃን አማሮችንና ለዘብተኛ ኦሮሞዎችን ያለከልካይ በግፍ ለሚጨፈጭፈው ለኦ.ነ.ግ ሸኔ ትጥቅና ስንቅ የሚያቀርብለት ማነው? ለሚለው የሌላዋ ሴት እንደራሴ ቁልፍ ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አንዳች ረብ ያለው ምላሽ አልነበረም፡፡
የሸኔ ነገር እንኳን ለኛ ለጋላቢዎቹም የበረታ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል በማለት ነበር ጥያቄውን እንደዋዛ ከአግራሞት ጋር የዘለሉት፡፡
በመሰረቱ ከሰዎች ተፈጥሯዊ እኩልነት ባሻገር የሀገሪቱ ዜጎች ሁሉ በየትኛውም አካባቢ ከአንድ ስፍራ ወደሌላው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ እኩልና ያልተሸራረፈ ሕጋዊ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ በየትኛውም እርከን የተደራጀ መንግሥታዊ መዋቅር ቀዳሚና ተኪ የለሽ ኀላፊነቱ ነው፡፡
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራቸው ኮርተውና መንግሥታዊ ጥበቃን ተማምነው በህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች እየተሳፈሩ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ወደአዲስ አበባ ከተማ ለመግባት የሞከሩ በርካታ መንገደኞች በብሔራዊ ማንነታቸውና በሚናገሩት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ እየተመረጡና የነዋሪነት መታወቂያቸው እየታየ ጉዟቸውን አቋርጠው ወደኋላ እንዲመለሱ በኦሮምያ ክልል ጸጥታ ሀይሎች አማካኝነት ስለሚገደዱበትና ያለአግባብ ስለሚንገላቱበት ሕገ-ወጥና አይን ያወጣ እርምጃ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት የአገም-ጠቀም ማብራሪያ የምር እንዳሳዘነኝና ተስፋ እንዳስቆረጠኝ ፈጽሞ ለመደበቅ አልፈልግም፡፡
ከዚሁ ስሞታ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ሠላምና ደህንነት ይጠበቅ ዘንድ ንጹሃን ወገኖች በፍተሻ ስም ከሁለትና ከሶስት ቀናት ላልበለጠ ጊዜ ወደመዲናይቱ ድርሽ እንዳይሉ በአቅራቢያ ኬላዎች ላይ በጅምላ መታገዳቸውና ጉዟቸው እንዲስተጓጎል እየተደረገ አውላላ ሜዳ ላይ የሚፈሱበትንና ከፍተኛ ዋይታ የሚያሰሙበትን አደገኛ እርምጃ ለሀገር ደህንነት እንደተከፈለ ዋጋ ሊቆጥሩት ይገባል ብለዉናል፡፡
እኔ በበኩሌ ይህንን አይነቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ እንደለየለት ሹፈት ነው የምቆጥረው፡፡ ምናልባትም ይህ አይነቱ ኀላፊነት የጎደለው አመላለስ ነው እንግዲህ በሕግ ማስከበር ስም እንንቀሳቀሳለን የሚሉትን ሕግ ተላላፊዎች የልብ ልብ የሚሰጣቸውና ባፈነገጠው እርምጃቸው እንዲገፉበት የሚያበረታታቸው፡፡
እስካሁን በለሆሳስ ስለሚወሳለት የጫካ ፕሮጀክትም ቢሆን በመጠኑ ዘርዘር አድርገው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነገሩን በዚህኛው የፓርላማ ቆይታቸው ነበር፡፡ ይህንኑ በተመለከተ ለህዝብ እንደራሴዎቹ ሲያብራሩላቸው እንደተከታተልነው ከሆነ 49 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ሲባልለት የሰማነው ይህ አስደማሚ ፕሮጀክት አምስት መቶ ቢሊዮን ብር እንኳ ቅም እንደማይለው እቅጩን ተናግረው የሞቀውን የጓዳ ሹክሹክታ አቀዝቅዘዉታል፡፡
በርካታ ዜጎችን ከየመኖሪያ ቤቶቻቸው ያፈናቅላል ተብሎ ክፉኛ የተሰጋለት የሳተላይት ከተማ በርሳቸው አገላለጽ መሰረት ለብዙ ወገኖች የስራ እድል የመፍጠርና ዳጎስ ያለ ብሔራዊ ገቢ የማመንጨት አቅም ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡
ያም ቢሆን ታዲያ የሩቅ ህልመኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ገና ግልጽ ያላደረጉልን ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም አብዝተው የሚረገረጉለትን ግዙፍ ፕሮጀክት በመሬት ላይ እውን ለማድረግ ወረቱን ያገኙት ከማንና ከየትኛው ምንጭ እንደሆነ በትክክል አለመታወቁ ነው፡፡
አሁን ለያዙት ከፍተኛ ኀላፊነት ገና እንደተሾሙ ስራቸውን በብቃትና በታማኝነት ለማከናወን በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ-መሃላ የፈጸሙበትና ህዝባዊ አደራ የተቀበሉበት የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ደግሞ በአንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ (1) ስር የመንግሥታቸውን አሰራር ግልጽነትና እርሳቸውን ጨምሮ የባለሥልጣኖቻቸውን ተጠያቂነት አጽንኦት ሰጥቶ ይደነግጋል፡፡
በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ ጊዜ ወስደው የሚያስጎመጅ ማብራሪያ በመስጠት ሲደክሙ ያረፈዱት ምክር ቤቱ ጨርሶ ስለማያውቀውና ዝርዝር እቅዱንም ሆነ የማስፈጸሚያ በጀቱን አስቀድሞ ስላላጸደቀለት ወደር-የለሽ ፕሮጀክታቸው ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
ከፍ ብሎ ለተጠቀሰው ለዚሁ አነጋጋሪ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ከውጭ በጎ አድራጊ ወገኖች የተቀበሉት አንዳች ድጋፍ ቢኖር እንኳ በመንግሥት ስም ታውቆና በሚገባ ተመዝግቦ በጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል እንጂ እርዳታ ወይም ስጦታ ነው ስለተባለ ብቻ የሀገሪቱ ሕግ ከሚፈቅደው አሰራር ውጭ ገቢ ሆኖ በስራ ላይ እንደማይውል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የተደራጀ ሌብነትንና ከቀን ወደቀን ለከት እያጣ የመጣውን መንግሥታዊ ዝርፊያ አስመልክቶ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን አሁን ከመቸውም ጊዜ በላይ ያመረሩ መስለው ታይተዋል፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ ለጊዜው እሳት የሚያጠፋ ኮሚቴ ማቋቋምም ሆነ ግብረ-ሀይል መሰየም በሀገራችን ያን ያህል እንግዳና ያልተለመደ ነገር እንዳይደለ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ በውሱን ቁመናና በተዳከመ አቅም የሚንከላወሰውን የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮምሽን እንደተቋም የሚያጠናክር ብሔራዊ ኮሚቴ እስከመሰየም መድረሳቸውንና በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ከላይ እስከታች በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚታየውን ሙስናና ብልሹ አሰራር አምርረው ለመዋጋት መወሰናቸውን ለሕግ አውጪ አካላቱ በይፋ ማሳወቃቸውና የዜጎችን ያላሰለሰ ድጋፍ መጠየቃቸው በበኩሌ የሚበረታታ ሆኖ ተመልክቸዋለሁ፡፡
በግብር ላይ ካላዋሉት ደግሞ በቃላቸው መሰረት ነገ ከነገ ወዲያ ጠብቀን እንይዛቸዋለንና ይህንን ውሳኔያቸውንና አለቅጥ እየገነገነ ከመጣው ዘርፈ-ብዙ ችግር ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ገለጻ ከወዲሁ ባናጣጥለው መልካም ነው፡፡
እዚህ ላይ የዶ/ር ትእግስትንና የአፈ-ጉባኤውን እሰጥ አገባ ሳላነሳ መጣጥፌን ልቋጨው አልወደድኩም፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወከሉት እኝህ የህዝብ እንደራሴ የመዲናዋን ፖለቲካዊ አቋም በተመለከተና አቀራረቡ የሴቲዮዋን ግላዊ ነጻነት በሚያጋልጥ ብርቱ ጥያቄ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያፋጥጧቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ጠቅላዩ ግን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዙሪያ መለስ መሽከርከሩን የመረጡ መስለው ታይተዋል፡፡
በዚህ ምክር ቤት አሰራር የተዛነፈ አካሄድ አለ ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ የተመለከትናቸው እኒያ የህዝብ እንደራሴ የስብሰባውን አውድ በመጠኑም ቢሆን ቀይረዉታል ለማለት ያስደፍራል፡፡
ሴቲዮዋ ከተከበሩ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ከአቶ ታገሰ ጫፎ ጋር ያደረጉት ምልልስ ፍሬ አስገኝቶ ይናገሩ ዘንድ ከተፈቀደላቸው በኋላም ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣ ያሉና ተደራራቢ ጥያቄዎችን አቅርበዉላቸው ነበር፡፡
እንደሴቲዮዋ አቀራረብ ለገጣፎና አዲስ አበባ በቆዳ ስፋትና በህዝብ ብዛት ዝሆንና ትንኝ ናቸው በሚል ድምጸት ፓርላማውን ትንሽ ፈገግ ያሰኙት ንቁ የህዝብ እንደራሴ ሁለቱም በአንድ አይነት አጠራር የከተማ አስተዳደሮች መባላቸው ያመናልና ለመሆኑ አዲስ አበባ የማን ናት? እኔስ የማን ነኝ? በሚሉት ጥያቄዎች ሳይወሰኑ የመዲናዋን መጻኢ እጣ ፈንታ በተመለከተ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንደሚያሻቸው አመልክተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይቀር ፖለቲካዊ ውክልና የሚያገኙበት እድል አለመኖሩን ሲያስቡ አብዝቶ እንደሚያስጨንቃቸው ሞግተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ግን የእንደራሴዋን ማንነት በእጩነት ከመለመላቸውና ለምክር ቤቱ ወንበር ካወዳደራቸው የፖለቲካ ድርጅት ጋር አቆራኝቶ ከመተቸት የዘለለ ባለመሆኑ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ሆኖ ነበር እስከመጨረሻው ድረስ የተከታተልነው፡፡
በመሰረቱ ፓርቲዎን እንጂ እርስዎን በግል ማን ያውቅዎታል? ተብለው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳሳተ አመላለስ በአደባባይ የተወረፉ ጊዜ የተሸማቀቅንባቸው እንደራሴ ያለጥርጥር ላወዳደራቸው ፓርቲና እርሱ ለቀረጸው ፖሊሲም ሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም ምንጊዜም ቢሆን ታምኖ መገኘት ይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ አንድ ጊዜ በህዝብ ተመርጠው የምክር ቤቱን መቀመጫ ከተረከቡ በኋላ ግን ተጠሪነታቸው ለመራጩ ህዝብ፣, ለሕገ-መንግሥቱና ለራሳቸው ህሊና እንደሆነ መዘንጋት ባልተገባው ነበር እላለሁ፡፡
በመጨረሻም ይህ ጸሃፊ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የግል ጠብ የለውም፡፡ ይልቁንም አሁን ወደያዙት ከፍተኛ የኀላፊነት ማማ ከመውጣታቸው በፊት አቢይን በአካል ከማወቅ አልፎ ለፈጣን አእምሯቸውም ሆነ ለተባው አንደበታቸው ላቅ ያለ ክብርና አድናቆት አለው፡፡ ይህንንም አቋሙን በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ከመግለጽ ቦዝኖ አያውቅም፡፡
መሪያችን በሀገርና ህዝብ ባለአደራነታቸው እስከቀጠሉ ድረስ አልፏልፎ መመከርና መስተካከል አለባቸው ብሎ ሲያስብ ግን እስከዛሬ ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ በአመክንዮ የተደገፈ ሂስ ከመሰንዘር ወደኋላ አይልም፡፡
ለዛሬው እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡
https://amharic-zehabesha.com/archives/177881
Saturday, November 26, 2022
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment