Sunday, October 30, 2022
October 30, 2022
ጠገናው ጎሹ
ሸፍጠኛና ሴረኛ የፖለቲካ ነጋዴዎች (merchants of hypocritic and conspiratorial politics) የሚፈራረቁበት የአገራችን ፖለቲካ እጅግ ሥር ለሰደደው ሁለንተናዊ የህመም ስቃይ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ለመረዳት የሚቸገር ባለ ጤናማ አእምሮ (ህሊና) የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
ታዲያ ይህ እጅግ መሪር ሃቅ ፈጥቶና ገጥጦ በሚታይበት ሁኔታ ውስጥ እጅግ አብዛኛው ምሁርና ልሂቅ ነኝ ባይ የህብረተሰብ ክፍልና ፖለቲከኛ የሁለንተናዊ በሽታ ምንጭ (the root cause of serious disease) የሆነውን ሥርዓተ ፖለቲካ በቀጥታ መጋፈጥን እየሸሸ በሽታው ስላስከተለውና እያስከተለ ስላለው የህምም ስቃይ (deeply terrible and complicated pain) ጨርሶ ፋይዳ ቢስ የሆነ የእግዚኦታ ትንታኔ እየደረተ የመቀጠሉ ጉዳይ በእጅጉ አሳዛኝና አስፈሪ ነው።
አዎ! ስለ እውነት በእውነት ከተነጋገርን አስከፊውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ውድቀትና የሞራል ዝቅጠት ቫይረስ (በሽታ) ዋነኛ ምንጭ ወይም ምክንያት የሆኑትን እኩያን ገዥ ቡድኖች በግልፅና በቀጥታ በቃችሁ ለማለት ወኔው ሲከዳው “እባካችሁ ያቋቋማችሁልን ኮሚሽኖች ወይም ቦርዶች ወይም ኮሚቲዎች እና በመሪነት (በሻንጉሊትነት) የሾማችሁልን ሹሞች ከተቻለ የፈውስ፣ ቢያንስ ግን የህመም ስቃይ ማስታገሻ እንዲያፈላልጉልን አድርጉልን " በሚል አይነት እጅግ የወረደና አዋራጅ የተማፅኖ አቤቱታ ክፉ አዙሪት ውስጥ በሚርመጠመጥ ምሁርና ፖለቲከኛ ነኝ ባይ የምን አይነት የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ናፋቂ እንደሆነ ለመረዳት ይከብዳል።
እራሱ የመማር እድል ሳያገኝ ለነፍስ አድንነት እንኳ የማትበቃውን ገቢውን እየከፈለ ሳይማር ላስተማረው መከረኛ ህዝብ የነፃነትና የፍትህ አቅጣጫውንና መንገዱን በቅጡ በማሳየት አኩሪ የታሪክ ተልእኮውን ለመወጣት አለመቻሉ ወይም አለመፈለጉ አልበቃ ብሎ በሥልጣነ መንበር ላይ ከሚፈራረቁ ሸፍጠኛና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች ጋር እየተገለባበጠ ወይም በፖለቲካ አመንዝራነት አረንቋ ውስጥ እየጓጎጠ የመከራውንና የውርደቱን እድሜ የሚያራዝም ምሁርና ልሂቅ ነኝ ባይ የህብረተሰብ ክፍል ለትውልድ የሚያስተላልፈው የነፃነትና የፍትህ አርበኝነትን ሳይሆን የባርነትንና የውርደትን ቀንበር የመለማመድን አሳፋሪና አስፈሪ ታሪክ ነው።
በዚህ አይነት እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የተዘፈቁ ምሁርና ፖለቲከኛ ተብየዎች ናቸው በሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች በሚቋቋሙ ኮሚሽኖችና በሚቀቡ (በሚሾሙ) ሹመኞች ለዘመናት የዘለቀውንና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማመን ቀርቶ ለማሰብ በሚያስፈራ አኳኋን የቀጠለውን የመከራና የውርደት ዶፍ አስቁሞ ምድረ ገነት የሆነች አገርን (ኢትዮጵያን) እውን ማድረግ እንደሚቻል የትንታኔ ድሪቶ እየደረቱ ሊያሳምኑን የሚሞክሩት።
እናም ይህ ትውልድ ይህንን እጅግ መሪር እውነታ ተጋፍጦ እራሱን የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ባለቤት ለማድረግ በሚያስችለው የጋራ ትግል አደባባይ ላይ በመሰባሰብ መክሮና ተማክሮ የተነሳበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ዓላማ እውን የማድረግ ተልእኮ በድል እስካላጠናቀቀ ድረስ በገንዛ ወገኖቹ የባርነትና የመከራ ቀንበር ሥር እየጓጎጠ ወይም በቁሙ ሞቶ ሳለ እየኖርኩ ነው እያለ እራሱን ከማታለል ክፉ የውድቀት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ፈፅሞ አይቻለውም።
አዎ! በሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ከሚቋቋሙ ኮሚሽን ተብየዎችና ተሿሚ ሥራ አስኪያጆቻቸው መልካምና ዘላቂ መፍትሄ ይመጣልና "የለውጡን ሐዋርያት ከመራቅ ይልቅ መደመር ይኖርብናል” በሚል እጅግ በምሁርነት እና በልሂቅነት ትክክለኛ ትርጉምና ዓላማ ላይ የሚሳለቁትን እጅግ ደካማ ወገኖች በግልፅና በቀጥታ ይብቃችሁና ወደ ትክክለኛው ህሊናችሁ ተመለሱ ለማለት ወኔው የሚያጥረው ትውልድ ዴሞክራሲንና ብልፅግናን መናፈቁ ቅዠት እንጅ ሌላ ሊሆን ከቶ አይችልም።
ለዚህ ግልፅና ቀጥተኛ ሂሳዊ አስተያየቴ መነሻ የሆነኝ የቀድሞው የግንቦት ሰባት (አሁን ኢዜማ የሚባለው) አመረር አባል የነበረው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምንታት በተከታታይ ለአንባቢያን ካቀረባቸው ፅሁፎቹ መካከል በተለይም "በአገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ውሳኔ መወሰን ያለበት ማነው?" በሚል ፅፎ ያስነበበን መጣጥፍ ነው ።
ዓላማዬና ትኩረቴ ግለሰቦች በሚፅፏቸውና በሚናገሯቸው ርእሰ ጉዳዮች ላይ አላስፈላጊ እሰጥ አገባ (unnecessary dialogue) ለመፍጠር አይደለም።
ይልቁንም በተለይ በፖለቲካ ቁመናቸውና አቋማቸው በአንድ በተወሰነ ወቅት የህዝብን ቀልብ ስበዋል ሲባሉ የነበሩ እንደ አቶ ኤፍሬም አይነት ወገኖች ለዘመናት በጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀውን እና አገረ ኢትዮጵያን ምድረ ሲኦል እያደረገ የቀጠለውን ኦህዴድ /ብልፅግና መራሽ አንጃ የሸፍጥና የሴራ ጥሪ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ (የመቶ በመቶ እምነትን በማረጋገጥ) መንፈስ ተቀብለው በመደመር የመከረኛው ህዝብ የመከራና የውርደት ዘመን እንዲራዘም አስተዋፅኦ ያደረጉትንና አሁን ደግሞ ስለ የማጭበርበሪያ ኮሚሽኖችና ስለ አሻንጉሊት ኮሚሽነሮቻቸው “የተቀደሰ ሚና” ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ጨርሶ ሃፍረት የማይሰማቸውን ወገኖች በግልፅና በቀጥታ ነውራችሁ ቅጥ አጥቷልና አስቡበት ማለት የግድ ነው የሚል ፅዕኑ እምነት ስላለኝ መሆኑን ግልፅ ለማድረግ እወዳለሁ።
አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን “የሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎችን የለውጥ ድራማ ወይም ኦርኬስትሬሽን በኮሚሽን ወይም በቦርድ ወይም በኮሚቴ በማስጠናትና በመመካከር ማስተካከል ይቻላል” የሚሉ ምሁርና ፖለቲከኛ ተብየዎችን በግልፅና በቀጥታ ለፖለቲካ አስተሳሰባችሁ ስንኩልነትና ለሞራል ጉስቁልናችሁ ልክ ይኖረው ለማለት ካልቻልን የመከራውና የውርደቱ ፖለቲካ ፈፅሞ ማቆሚያ አይኖረውም። ምክንያቱ ለዘመናት ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴ በሚያሳዝን ሁኔታ የጨነገፈው በለየላቸው ብልሹና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን በአድርባይነት ወይም በፖለቲካ አመንዝራነት አረንቋ ውስጥ በሚዘፈቁና በመዘፈቅ ላይ በሚገኙ ምሁርና ፖለቲከኛ ተብየዎች ጭምር ነውና ።
አቶ ኤፍሬምን ጨምሮ የግንቦት ሰባት ፖለቲከኞች እየማሉና እየተገዘቱ ሲነግሩን የነበረው ራዕያቸው፣ ተልእኳቸው ፣ ዓላመቸውና ግባቸው ሁሉ የተሃድሶ ፍርፋሪ ለቀማ ሳይሆን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ሽግግርና ምሥረታ መሆኑን ነበር። ምንም እንኳ አቶ ኤፍሬም ራሱ በሚያውቀው ምክንያት “ከተሃድሶው ውልደት” በኋላ ብዙም ሳይቆይ በይፋ በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ከመንቀሳቀስ ቢርቅም ከኦህዴድ መራሽ “የለውጥ ሐዋርያት” የፖለቲካ ማእድ ታዳሚነት ግን አልራቀም።
ኦህዴድ መራሹ የኢህአዴግ አንጃ ቡድን ለሩብ ምእተ ዓመት በፍፁም አገልጋይነት ሲያገለግለው የነበረውን ሥርዓት የበለጠ አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንዲቀጥል በማድረግ አገርን ምድረ ሲኦል ሲያደርግ “በፊትም ከማጭበርበሪያነት የሚያልፍ ፋይዳ ያልነበረው ተሃድሶ ተብያችሁ ተፈትኖ ወድቋልና እውነተኛ ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ወደ የሚያስችለው የመፍትሄ መንገድ ተመለሱ” ለማለት የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ልእልና ወኔው ከድቶት ለማጭበርበሪያነት በአዋጅ የተቋቋሙ ኮሚሽኖችና በአሻንጉሊትነት የተሾሙላቸው ኮሚሽነሮች ተብየዎች አገራዊ መፍትሄ ያስገኛሉ በሚል ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብ አባዜ ውስጥ የሚባዝን ወይም የሚርመጠመጥ ትውልድ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን መናፍፈቁ ቅዠት እንጅ እውነት ሊሆን አይችልም።
አቶ ኤፍሬም ማዴቦና መሰሎቹ “ለእውነተኛ ወይም ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ሲሉ ቃል ለምድርና ለሰማይ ብለው ይኖሩባቸው ከነበሩ የውጭ አገራት የተደላደለ ሥራቸውንና ኑሯቸውን ትተው ወደ ኤርትራ የትግል በርሃ እንደወረዱ” በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለማጭበርበሪያነት ባሰለጠኑት አንደበታቸው ሲሰብኩት ለብዙ ዘመን በባዶ ተስፋ ብቻ የኖረው መከረኛ ህዝብ እውነት መስሎት እንደ ብርቅዬ የነፃነት ሐዋርያት ቆጥሮ አጨበጨበላቸው። ይህ አይነት የመከረኛ ህዝብ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ጉጉት ጨርሶ ደንታ ያልሰጣቸውና የማይሰጣቸው የምሁራን ፖለቲከኞች ነን ባዮች ሊፈወስ በማይችልበት አኳኋን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከበሰበሰውና ከከረፋው ኦህዴዳዊ/ብልፅግናዊ ፖለቲካ ሥርዓት ጋር በፖለቲካ አመንዝራነት እየተሻሹ “የጎደለው ነገር ሁሉ በከሚሽን ወይም በቦርድ ወይም በኮሚቴ እየተጠና ይሟላልና ሥርዓቱን እንደ ሥርዓት አምርሮ ከመቃወምና ከመታገል ይልቅ በኢትዮጵያ መሪ ተፈላሳፊነት ተዘጋጅቶ የቀረበውን የመደመር የዘመናችን ታላቅ ፍልስፍና ማጧጧፍ ነው የሚበጀው” የሚል አይነት የትንታኔ ድሪቷቸውን ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ህሊናቸውን ጨርሶ አይጎረብጠውም።
አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “ከድል ማግሥት ከትግል ጓዶቹ” ጋር ወደ አገር ቤት ሲገባ ከኢትዮጵያን ሄራልድ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “በተሃድሶው ላይ እምነታችንን ጥለናል (We placed Trust on the Reform)” ባለው መሠረት ቃሉን ጠብቆ ተፈትኖ አይወዱቁ ውድቀት የወደቀውን ሥርዓት “ይህ ወይም ያኛው ኮሚሽን/ቦርድ/ኮሚቲ ትንሽ የሚጎደለው ነገር አለና ጎዶሎው ከተስተካከለለት በብልፅግና እንብሻበሻለን” በሚል እጅግ የለየለት አድርባይነት ውስጥ መርመጥመጥን የመረጠ ፖለቲከኛ የመሆኑ እውነታ ነው ለዚህ ሂሳዊ አስተያየቴ መነሻ የሆነኝ ።
ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ ሂሳዊ አስተያየቴን ከዚህ በተሻለ ለግልብ ስሜት በሚስማማ አገላለፅ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነበር። ይሁን እንጅ እንደ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ አይነት የበሽታውን ምንጭ ወይም አመንጭ እየሸሹ “የዚህ ኮሚሽን ወይም ቦርድ ወይም ኮሚቲ ትንንሽ ቀዳዳዎች ከተደፈኑለት አገር በሰላምና በብልፅግና ትንበሻበሻለች” የሚል አይነት የትንታኔ ድሪቶ የሚደርቱ ወገኖችን የሄዳችሁበትና እየሄዳችሁበት ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ሽባነትና የሞራል ቁልቁለት ከነውርነት አልፎ እጅግ አደገኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ መሰናክል ነውና ቆም እያላችሁና ትንፋሽ እየወሰዳችሁ ተራመዱ ማለት በእጅጉ አስፈላጊ ነው የሚል ፅዕኑ እምነት ስላለኝ ተሽኮርማሚውን አቀራረብ አልወደድኩትም። አልወደውምም።
ሆን ብሎም ይሁን ባለማወቅ (በድንቁርና) የሚፈፀም የዚህ አይነት ስህተት በተለይም በእንደኛ አይነቱ ከጋራ አገራዊ ማንነት ወርዶ በጎሳ/በመንደር ማንነት አዘቅት ውስጥ በተዘፈቀ የፖለቲካ ሥርዓት ለተጠረነፈ ህዝብ የሚያስከትለው ውጤት በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ ነው። አዎ! እንዲህ አይነት ስህተቶችን ተጨባጭ በሆነ፣ ገንቢነት ባለው ፣ ግልፅነትንና ቀጥተኛነትን በተላበሰ አቀራረብ እንዲታረሙ ለማድረግ የምንሞክርበት አካሄድ በአብዛኛው ተሽኮርማሚነትና ሽባነት የሚያጠቃው የመሆኑ መሪር እውነት ለዘመናት ለመጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ደረጃ ተዘፍቀን ለምንገኝበት አጠቃላይ ውድቀት ዋነኛ ከሁኑ ምክንያቶች አንዱ ነውና ልንዋጋው ይገባል።
አቶ ኤፍሬምን የማውቀው በግል (in person) ሳይሆን አሁን ኢዜማ የተሰኘውና በዚያን ወቅት ግንቦት 7 ይባል የነበረው የፖለቲካ ቡድን አመራር አባል ሆኖ “ከተአምረኛው የተሃድሶ ለውጥ” በኋላ በለውጡ ሐዋርያት ተጠምቆ የመቶ በመቶ የእምነት ቃሉን በመስጠት"በክቡር ሚኒስትርነት" ሹመት ከተንበሻበሸው እና የልሂቅነትን (intellectualism) እውነተኛ ትርጉምና ካረከሱት ወገኖች አንዱ ከሆነው ባልደረባው ዶ/ር ብሃኑ ነጋ ጋር በየስብሰባ አዳራሹ ያደርገውን “የዴሞክራሲ አርበኝነት” ዲስኩሩን በመከታተል ነው። ወደ "ኤርትራ በርሃ " ወረድን ሲሉም ሊያስገኝ የሚችለው የበጎ ለውጥ ፍሬ ብዙም ሊያሳምን የሚችል ባይሆንም ቢያንስ በአንፃራዊነት የተመቻቸ ኑሮንና ቤተሰብን ተሰናብቶ ለመሄድ መወሰን የእራሱ ፈተና አለውና ምናልባትም ለነፃነትና ለፍትህ ፍለጋው ትግል የእራሱን አወንታዊ መነቃቃትን ሊፈጥር ይችላል የሚል ተስፋ ከነበራቸው ወገኖች አንዱ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ ።
ይህንን የምለው ይህ የዛሬው ሂሳዊ አስተያየቴ መነሻ አቶ ኤፍሬም ከሰሞኑ የፃፈው መጣጥፍ ብቻ ሳይሆን እንደማነኛውም የአገሩ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ግለሰብ የፖለቲካችንንና የፖለቲከኞቻችንን አካሄድ የመከታተል ጉዳይ ጭምር መሆኑን ለመግለፅ ነው ።
በተሽኮርማሚነት ብቻ ሳይሆነ ሥር በሰደደና ከመጠን ባለፈ የአድርባይነትና የአስመሳይነት ፖለቲካ ባሀል ክፉኛ የተጎዳው የፖለቲካ እኛነታችን ለዘመናት ከመጣንበትና ግዙፍና መሪር ዋጋ ከተከፈለበት የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ፍለጋ ሃዲድ አንሸራትቶ ይኸውና ለመግለፅ በእጅጉ ከሚያስቸግር አጠቃላይ (ሁለንተናዊ) የቀውስና የውድቀት አረንቋ ውስጥ ዘፍቆናልና ከምር አምርረን ወደ ትክክለኛው መንገድና አቅጣጫ መመለስ ካለብን በግልፅና በቀጥታ ከመነጋገር ነው መጀመር ያለብን ።
እንደ አቶ ኤፍሬም አይነት “ያለ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥዓት ለውጥ ከትግላችን ላንመለስ ቃል ለምድርና ቃል ለሰማይ ይሁንብን” በሚል የምሉና ይገዘቱ የነበሩ ፖለቲከኞችና ምሁራን ነን ባዮች የአብይ አህመድን የሸፍጥና የሴራ የመደመር ፖለቲካ ድርሰት በቅጡ አጤኖ ለመወሰን ፈፅሞ ጊዜና ትእግሥት ሳይወስዱ በተረኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ኦህዴዳዊያን ለሚመራው ብልፅግና ተብየ ገዥ አንጃ ህሊናቸውን ሸጠው ወደ አገር ቤት ከገቡ በኋላም ልክ የሌለው አድርባይነታቸውን በመቶ ለመቶ የእምነት ቃል ያረጋገጡ “የምሁር ፖለቲከኞች” ናቸው። አገር ለንፁሃን ልጆቿ ምድረ ሲኦል ስትሆን አንዳችም ፋይዳ ያለው እርምጃ ሳይወስዱ አሁን ስለ ተአምር ሠሪ ኮሚሽኖችና ኮሚሽነሮች የሚደርቱት የትንታኔና የምክረ ሃሳብ ድሪቶ ጨርሶ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ሽታ የለውም።
እናም እንዲህ አይነት ወገኖችን ያለምንም መሽኮርመም ከተዘፈቃችሁብት የኦህዴድ (ብልፅግና) ርኩስ የፖለቲካ አመንዝራነት ውጡና በተቀደሰ ተግባራዊ ንስሃ የተቀደሰ ሥራ ሥሩ ብሎ እቅጩን ለመንገር ሌላ ተጨማሪ የመከራና የውርደት ጊዜ መጠበቅ የለብንም!
ይህንን ለማለት የፖለቲካና የሞራል ወኔው የሚከዳን ከሆነ እጅግ አስከፊ በሆነው የአልቃሽና ዘፋኝ የፖለቲካ ማንነታችንና እንዴትነታችን እንቀጥላለን። ይህንን አይነት የውድቀት አዙሪት ሰብረን መውጣት ካለብን “ይኸኛው ወይም ያኛው ብልፅግና ሠራሽና መራሽ ኮሚሽን ወይም ቦርድ ወይም ኮሚቲ ትንሽ ማስተካከያ ከተደረለት ታሪክ ሊሠራ ይችላል” ከሚል እጅግ ወራዳና አዋራጅ የምሁርነትና የፖለቲከኛነት አስተሳሰብ አረንቋ ሰብረን መውጣት ይኖርብናል።
አዎ! በአድርባይነትና አስመስሎ የመኖር የፖለቲካ ማንነትና እንዴትነት አዙሪት ውስጥ እየተርመጠመጡ በባለጌና ሴረኛ የኦህዴድ/ብልፅግና ፖለቲከኞች የሚቋቋሙ ኮሚሽኖች እና የሚሾሙ ኮሚሽነሮች “ነፃና ትክክለኛ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የሚያግዝ ሂሳዊ ድጋፍ ማድረግ ነው” በሚል ወራዳ አስተሳሰብ የመከራና የውርደት ሥርዓት እድሜ እንዲረዝም አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን ወገኖች በግልፅ፣ በቀጥታና ገንቢነት ባለው አቋምና ቁመና በቃችሁ ማለት ያለብን ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው መሆን ያለበት ።
ከአጠቃላይ መርህ እና የተወሰኑ ጉድለቶች ያሉበትን የፖለቲካ ሥርዓት ለማስተካከል ከሚደረግ ጥረት አንፃር ሲታይ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ባስነበበን ፅሁፉ ለመዳሰስ፣ ለመተንተን እና ይበጃል የሚለውን ምክረ ሃሳብ ለመሰንዘር ያደረገውን ሙከራ በአወንታዊነት ለመቀበል አያስቸግርም ነበር። ለዘመናት ከተዘፈቀበት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ያለ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጨርሶ ማገገምም ሆነ መታደስ የማይችለው የእኛ አይነቱ የፖለቲካ ሥርዓት በሽታ አጥኝና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚሽን ወይም ቦርድ ወይም ኮሚቴ በሚል የለየለት የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ አካሄድ ይፈታል ብሎ የሚያምን የምሁር ፖለቲከኛ የገንዛ አገሩን ዘመን ጠገብ የፖለቲካ መሪር እውነት በሚገባ ተረድቶታል ወይም ይረደዋል ብሎ ለማመን በእጅጉ ያስቸግራል።
የለውጥ ተብየውን ለምንነትና እንዴትነት በቅጡ ሳያጤኑ እጅግ ለወረደና አዋራጅ ለሆነ “የመቶ በመቶ የመተማመን ፖለቲካ" ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እንደ አቶ ኤፍሬም አይነት ፖለቲከኞች አሁን ደግሞ ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ያቋቋሟቸው ኮሚሽኖችና የሾሟቸው ኮሚሽነሮች አንዳንድ ጉድለቶቻቸው ከተስተካከሉላቸው አገራዊ እርቅና ሰላምን እውን በማድረግ ረገድ "ተአምር ሊሠሩ ይችላሉ" በሚል ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ህሊናቸውን ጨርሶ ቅር አይላቸውም።
የአገራችን ከባዱና አስቀያሚው የፖለቲካ ባህል ዋናውን የአገራዊ በሽታ ምንጭ (ቫይረስ) ትቶ በሚያስከትለው ብርቱ የህመም ስሜት (symptoms of serious or chronic illness) ላይ ሰንካላና ትርጉም የሌለው ሃተታ ወይም ትንተና ላይ የመጠመድ ክፉ አባዜ ነው ። የአቶ ኤፍሬም ሃተታና ምክረ ሃሳብ የሚነግረንም ይህንኑ አስቀያሚ የፖለቲካ ወለፈንዲ አስተሳሰብ (ugly and paradoxical political thinking) ነው። የሥርዓት ለውጥን አጥብቀው የሚፈሩት ሸፍጠኛና ሴረኛ ኦህዴዳዊያን/ብልፅግናዊያን ለጉልቻ ለውጣቸው ሽፋን ይሰጡላቸው ዘንድ በአዋጅ ያቋቋሟቸውን ኮሚሽን ተብየዎችና የሾሙላቸውን ኮሚሽነሮች ትንሽ ጉደለታቸውን በማስተካከል አገርን በእርቅና በሰላም በረከት እንዲያንበሸብሹ ለማድረግ ይቻላል በሚል ከእራሱ አልፎ መከረኛውን ህዝብ ግራ የሚያጋባ ምሁርነትና ፖለቲከኛነት ነውር ነው ካልተባለ የሚያስከትለው ውጤት እስካሁን ካለው በእጅጉ የከፋ ነው የሚሆነው።
አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የለየለትን የገዳይና የአስገደይ የፖለቲካ ቫይረስ አምራቾች (ምንጮች) እና ሌሎች መሣሪያዎቻቸው (የፖለቲካ አመንዝራነት ሸሪኮቻቸው) የሚጫወቱትን ኮሚሽን የማቋቋምና መሰል የማታለያ የፖለቲካ ጨዋታ እንደ እውነተኛ የመፍትሄ መንገድ በመውሰድ "ስለ አቋቋማችሁልን እያመሰገን ህዝብን ይበልጥ ያማልላችሁ ዘንድ አንዳንድ ቀዳዳዎችን ለመድፈን ፈቃዳችሁ ይሆን ዘንድ በአክብሮት እንመክራለን" የሚል የምሁር ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ነውረኝነቱ በግልፅና በቀጥታ ካልተነገረው እራሱን የመፍትሄዎች ሁሉ መክፈቻና መቆለፊያ ቁልፍ አድርጎ ስለሚቆጥር የሚያስከትለው ሁለንተናዊ ቀውስ ከባድ ነው የሚሆነው።
ይህንን እኩይ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልክፍትና የሞራል ድቀት ከምር ተደራጅቶና ተቆጥቶ በቃ የሚል አገራዊ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች የህብረትና የአንድነት ንቅናቄ እስካልተፈጠረ ድረስ የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችን ፍላጎት፣ ዓላማና ግብ ለማሳካት በእራሳቸው በገዥዎች የተፈጠሩ ወይም የሚፈጠሩ ኮሚሽኖች ወይም ቦርዶች ወይም ኮሚቲዎች የመከራውን ዘመን ከማራዘም ያለፈ ህዝባዊ ፋይዳ እንደሌላቸውና እንደማይኖራቸው ለማወቅ ፈፅሞ የተለየ እውቀትን አይጠይቅም።
በእጅጉ ከበሰበሰና ከገማ እንቁላል ጫጩት መጠበቅ ፍፁም የሆነ ድንቁርና (absolute ignorance) እንደሆነ ሁሉ ለዘመናት እጅግ ግዙፍና መሪር በሆነ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከበሰበሰና ከከረፋ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓት ለእውነተኛ አገራዊ እርቅና ሰላም እውን መሆን የሚያስችሉ ኮሚሽኖችና ኮሚሽነሮች ይወለዳሉ ብሎ እንኳን ማመን ማሰብም የለየለት የፖለቲካ ድንቁርና ወይም የአድርባይነት ክፉ ልክፍት እንጅ ከቶ ሌላ ሊሆን አይችልም።
እንደ አቶ ኤፍሬም ያሉ የብልፅግና ወዶ ገብ ፖለቲከኞች የሚሉን ግን “ይቻላል” ነው። ይህ ነው የአብዛኛው የአገራችን ፖለቲከኛና ምሁር ነኝ ባይ እጅግ ሥር የሰደደና በቀላሉ ሊቃለል የማይችል ሆኖ እየቀጠለ ያለው መሪር ፈተና።
በእውነት እንነጋገር ካልን እኮ በእንደዚህ አይነት ሥርዓት የተፈጠሩ እና የገንዝብና ሌላም አስፈላጊ ግብአት የሚሠፈርላቸውን ኮሚሽኖች ይመሩ ዘንድ የተሾሙ ኮሚሽነሮችተ ብየዎች ገዳይና አስገዳይ በሆነው ህገ መንግሥት ተብየ እየማሉና እየተገዘቱ የተቀበሉት ምሁራንና አዋቂዎች ነን የሚሉ ናቸው ። ታዲያ እነዚህ ሰዎች እንኳንስ የእውነተኛ መፍትሄ አፈላላጊዎች ሊሆኑ ለእራሳቸው የህሊና ነፃነት ዳኝነትም ተገዥዎች እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? ፈፅሞ ሊሆኑ አይችሉም! ምክንያቱም የበሽታው ምንጭ (ምክንያት) የሆነው ሥርዓታዊ ቫይረስ ይበልጥ የከፋ እየሆነ በመጣበት መሪር እውነታ ውስጥ የሚያስከትለውን የህመም ስቃይ ለማስታገስ መሞከር ለዘመናት ተሞክሮ ፈፅሞ ያልሠራና ዛሬም ሊሠራ የማይችል መሆኑን አሳምረው እያወቁ የሸፍጠኞችንና የሴረኞችን ቅባተ ሹመት ተቀብተው የመከረኛውን ህዝብ የመከራ ዘመን በማራዘሙ እኩይ ተግባር ላይ ለመሠማራት ፈቅደዋልና ነው።
ለዚህ ነው የእንዲህ አይነቶችን የፖለቲካ አስተሳሰብ ድሃዎችና የሞራል ጎስቆሎች በዝምታ ወይም እጅግ በዘቀጠ የምን አገባኝ አስተሳሰብ ማለፍ በራሱ እጅግ አስቀያሚና አስፈሪ የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነትና የሞራል ዝቅጠት ነውና በፍፁም እንዲቀጠል ሊፈቀድለት አይገባም ብሎ እቅጩን መነጋገር አስፈላጊ የሚሆነው።
እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የእንዲህ አይነት ጨካኝና አስፈሪ የፖለቲካ ኦርኬስትሬሽን ሰለባ የሆኑትና የሚሆኑት ፊደል በመቁጠርና በእድሜ ብቻ ሳይሆን የመከራና የውርደቱን የፖለቲካ ባህልና ሥርዓት በመታገል ረገድም አንቱ የሚያሰኝ ተሞክሮ አለን የሚሉ የመሆናቸው መሪር ወለፈንዲነት (deep [y painful paradox) ነው።
ገዥ ቡድኖች ሆን ብለው ያደረጉትንና ተሿሚዎችም አሜን ብለው የተቀበሉትን የእከክልኝ አክልሃለሁ እጅግ ፃያፍ የፖለቲካ ጨዋታ "እዚህኛው ወይም እዚያኛው ሰነድ ውስጥ ወይም የአፈፃፀም ሂደት ላይ የሚታዩት ቀዳዳዎች ከተደፈኑ በቅርቡ በኮሚሽኑ አዘጋጅነት እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ ታሪካዊ የብልፅግና ቀን ይሆናል " የሚል ወራዳ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን ሊያራግፉብን የሚሞክሩ የምሁራን ፖለቲከኞች እየበዙ እንጅ እየቀነሱ ያለመሄዳቸው ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢና አስፈሪ ነው።
ይህንን አይነት ወራዳ የፖለቲካ አስተሳሰብና ጨዋታ ከምር ለመታገል በቅድሚያ የገንዛ እራስን ህሊና በትክክለኛው ሚዛን ላይ ማግኘትን ይጠይቃል ። ይህ ደግሞ በተራው የራስን የቆሸሸ የፖለቲካ ሰብእና ከምር በሆነ ፀፀትና ይቅርታ ለማፅዳት ፈቃደኛ መሆንን ግድ ይላል ።
አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በግንቦት ሰባት አመራር አባልነቱ አጥብቆና አዘውትሮ ሲያስተጋባው የነበረውን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥዓላማ፣ መርህና ግብ ርግፍ አድርጎ በመተው ህወሃትን ቀንሶ ህወሃት ሠራሹን ጎሳ ተኮር አደገኛ ሥርዓት ይበልጥ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በተረኝነት ላስቀጠለው ኢህአዴጋዊ አንጃ (ኦህዴድ/ብልፅግና) እራሱን አሳልፎ የሰጠ ፖለቲከኛ ነው።
የበላይነቱን ተረኝነት በተቆጣጠሩት ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች የአራት ዓመታት አገዛዝ ወቅት አገር ለንፁሃን ልጆቿ ምድረ ሲኦል ስትሆን እጅግ የወረደ “የተሃድሶው ይስተካከል” ዲስኩርና ጩኸት ከማላዘን አልፎ የበሽታው ሁሉ ምክንያት የሆነውን ሥርዓት እንደ ሥርዓት አስወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን የማድረግ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም ለማለት ወኔው የከዳው የምሁር ፖለቲከኛ ስለ ኮሚሽኖችና ኮሚሽነሮች ችግር ፈችነት ላስተምራችሁ ሲለን ቢያንስ ነውረኝነቱን በግልፅና በቀጥታ ለመንገር የምንቸገር ከሆነ ሌላ ምን አይነት የመከራና የውርደት ታሪክና ትርክት እንደምንጠብቅ አላውቅም ወይም አይገባኝም ።
የሥርዓት ለውጥ እንጅ የጉልቻ ለውጥ ፈፅሞ አይሞከርም በሚል የብእራቸው ቀለም አልበቃ እስከሚላቸው ሲፅፉለትና ለዚሁ ባሰለጠኑት አንደበታቸው ሲደሰኩሩለት የነበረውን መርህና ዓላማ እርግፍ አድርገው በመተው እና በህዝብና ለህዝብ አቋቋምነው የሚሉትን ኢሳት የተሰኘውን መገናኛ ብዙሃን ለተረኛው ኦህዴድ/ብልፅግና በእጅ መንሻነት አሳልፈው በመሥጠት የገዳይነትና የአስገዳይነት ፖለቲካ ሥርዓት መሣሪያ ያደረጉት አቶ ኤፍሬም እና በካቢኔ አባልነትና በሌላም የሥልጣን ሹመት የተንበሻበሹ ጓዶቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ አይነቶችን የምሁር ፖለቲከኞች ነን ባዮች በግልፅና በቀጥታ በገባችሁበት ወራዳና አዋራጅ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ እየጓጎጣችሁ (እየተንደፋደፋችሁ) ስለ ዴሞክራሲና ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምታግተለትሉት የትንታኔ ድሪቶ ጨርሶ ስሜት የለውምና ቆም ብላችሁና ትንፋሽ ስባችሁ በማሰብ ትክክለኛውን ሰው የመሆን ህሊናችሁን ፈልጋችሁ አግኙት ማለት ከተገቢ በላይ ተገቢ ነው።
በዚህ ልክ ለመነጋገር ስንችል ብቻ ነው የበሽታችን ምንጭ (ምክንያት) የሆነውን የሸፍጠኞችና የሴረኞች ሥርዓት በቀጥታ ከመጋፈጥ እየሸሸን ስላስከተለውና እያስከተለ ስላለው አስከፊ የህመም ስቃይ ሌት ተቀን እግዚኦ ከማለትን ክፉ አባዜ (ልማድ) ሰብረን ለመውጣት የምንችለው።
“መንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ በኮሚሽኑ ሥራ ከሂደቱ እስከ ፍፃሜው አስፈላጊውን ድጋፍ ከማቅረብ ውጭ በምንም አይነት ጣልቃ ሊገባ አይገባውም” የሚለው የአቶ ኤፍሬም ሃሳብ በመርህ ደረጃ ወይም በአጠቃላይ እውነትነት ወይም በምዕናባዊነት ካልሆነ በስተቀር በመሬት ካለው ግዙፍና መሪር የአገራችን የፖለቲካ ምንነትና እንዴትነት አንፃር ፈፅሞ ሊሆን የሚችል አይደለም።
አራት ዓመታት ሙሉ አገር በንፁሃን ልጆቿ የደም ጎርፍ ስትጥለቀለቅና በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የቁም ሰቆቃ ስትጨነቅ የችግኝ ተከላ "ኤክስፐርትነቱን" ፣ የመናፈሻ ዶኩሜንታሪ ፊልም ተዋናይነቱን ፣ የእርሻ ላይ ተውኔቱን ፣የሁሉም አይነት ሙያ "አሰልጣኝነቱን"፣ በራሱ በፈጣሪ ተሳላቂነቱን ፣ ሃፍረተ ቢስ የውሸት ፈብራኪነቱን፣ ወዘተ እያቀነባበረና እያዘጋጀ “የታላቅ መሪነቴን ገድል እወቁልኝ” የሚለውን ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ በቀጥታና በግልፅ ነውር ነው ለማለት የሚያስችል ወኔ የጎደለው ምሁር ነኝ ባይ ፖለቲከኛ በዚሁ ጉደኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ መልካም ፈቃድና ቡራኬ የተቋቋሙ ኮሚሽኖችና የተሾሙ ኮሚሽነሮች “የሚጎድላቸውን ጎደሎ አስተካክሎ እውነተኛ የአገራዊ እርቅና ሰላም እውን ማድረጊያ መሣሪያዎች ማድረግ ይቻላል” ብሎ ለማሳመን ሲሞክር እንዳልሰሙና እንዳላዩ ዝም ጭጭ ብሎ ማለፍ የታጋሽነትና የአዋቂነት ማሳያ አይደለም።
የበሽታ ምንጭ (the root cause of disease) የሆነውን የፖለቲካ ሥርዓት ከሥሩ ነቅሎ በመጣል በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት የሚያስችል ሁለንተናዊ የጋራ ጥረት ከማድረግ ይልቅ እያስከተለ ያለውን የህመም ስቃይ በማስታመም አገር ትርጉም ያለው እፎይታ ያገኛል ብሎ ከማሰብና ከማመን የሚከፋ የፖለቲካ አስተሳሰብ ድንቁርና እና የሞራል ዝቅጠት ከቶ የለም። ስለሆነም ከዚህ ክፉ አዙሪት ሰብሮ ሊያወጣን በሚችል የሥርዓት ለውጥ ትግል ላይ መረባረብ ካልቻልን ፖለቲካ ወለዱ መከራና ውርደት ጨርሶ ማቆሚያ አይኖረውም!
እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!
https://amharic-zehabesha.com/archives/177563
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment