Friday, October 14, 2022

ነፍሴ ቃተተች - በላቸው ገላሁን
ወንድም ወንድሙን ሲቀላ በማይቴ

ጭካኔ ገኖ ሲነግስ በቀዬዬ በመንደር በቤቴ

አምሳለ _ እግዚአብሄር ሰው መሆን ከንቱ ሆኖ

ሥጋው ታርዶ ተቃጥሎ እንደ ትቢያ በኖ

ሞቶም እንኳን ሞቱ አንሶት

ተዘቅዝቆ ሲሰቀልና ሲበለት፤

ቃተተች ከርታታዋ ሩሕ ነፍሴ

ቃል አጣች ምስኪን ጎልዳፋ ምላሴ

እንዲህ ያለ እኩይ ጠያፍ ስራ

ምንስ ተብሎ ሊነገር ለማን ሊወራ።

የሰው ልጅ አንሶ ከቅንጣት ጉድፍ

እየተቀላ በየጥሻው በየጉድባው ሲረግፍ

ሲቆላ ሲጠበስ፤ ሲቀቀል እንደ ንፍሮ

ሲታረድ ሲበለት፤ እንደ በግ እንደ ዶሮ፤

ቃተተች ከርታታዋ ሩሕ ነፍሴ

ቃል አጣች ምስኪን ጎልዳፋ ምላሴ

እንዲህ ያለ እኩይ ጠያፍ ስራ

ምንስ ተብሎ ሊነገር ለማን ሊወራ።

በግዮን በቅምጥ እንዲሁም በኑቢያ

በፋርስ በኤፍራጥስ በየመን በሜሶፖታሚያ

ተምሳሌት ሆና የኖረች ጥነተ ጦቢያ

ዛሬ ቀን ጥሏት ወድቃ ትቢያ

ጭካኔ፤ ደቁርና፤ ረሃብ ስደት በቤቷ ነግሶ

ተርታ ዜጋዋ ከሰው አንሶ አፈር ልሶ

ሳይ እና ስኖረው ስመልከት

ፍቺው ጠፍቶኝ መፈወሻ ዋግምት፤

ቃተተች ከርታታዋ ሩሕ ነፍሴ

ቃል አጣች ምስኪን ጎልዳፋ ምላሴ

እንዲህ ያለ እኩይ ጠያፍ ስራ

ምንስ ተብሎ ሊነገር ለማን ሊወራ።

በላቸው ገላሁን

ጥቅምት 2015

USA

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/177388

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...