Friday, October 28, 2022
1ኛ/ መንደርደሪያ፤
በመጀመሪያ የሰዉ ህይወት ዉድና ቅዱስ መሆኑን አንርሳ። ህይወት በግፍ እየተቀጠፈ ሰላም አይኖርም። ሰላም ከሌለ ዕድገት አይታሰብም። መሞት፤ መፈናቀል፤ መሰደድ፤ ልመናና ሰቆቃ ብቻ ይሆናል ዕጣ ፈንታችን፤ ከሆነም እጅግ ሰንብቷል። አገራችን ሰፊ ሆና ሳለች አላስፈላጊ ችግሮችን ስንጋብዝ ምንኛ ግብዞች ነን? ትልቁ ኃጢያት ታሪክን ማዛባት ነዉ። የዉሸት ትርክቶች ለከባድ ጥቃቶች ጋርደዉናል። ሳናዉቅ ራሳችንን እያጠፋን እንገኛለን። እንንቃ፤ ሁላችንም እንደሰዉ እናስብበት፤ ህይወት አጭር ናት፤ ታሪክ ይታዘበናል፤ ንስሐ እንግባ፤ እንተቃቀፍ፤ እንተባበር፤ ሙሉ ትኩረት ለሰላም፤ ለልማትና ለዕድገት እንስጥ። በተለይ የኃይማኖት መሪዎች፤ የሀገር ሺማግሌዎች፤ ምሁራን፤ ወጣቶችና ሀገር መሪዎች በጥልቀት አስቡበትና የመፍትሔ አካል ሁኑ። እነዚህን ችግሮችና የሚታዩኝን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለዉ ሳቀርብ በጥሞና እንድትመለከቱልኝና ገንቢ ሚና እንድትጫወቱ በፈጣሪያችን ስም እለምናችኋለሁ።
2ኛ/ ለሰዉ ህይወት ክብር ይኑረን
ራሳችሁን፤ ወገኖቻችሁንና ጓደኞቻችሁን እንደምትወዱ ሌሎችም እንደዚሁ አፍቃሪዎች አሏቸዉ። የአንዱ ህይወት ከሌላዉ ፈጽሞ አይበልጥም፤ አያንስም። በእግዚአብሔር ለምናምን ሁሉ እርሱ በአምሳሉ የፈጠረን ህዝቦች ነን። የማሰብ አእምሮ ሰጥቶናል። ክፉና ደጉን እንድንለይ አብቅቶናል። ግን የዜጋ ደም በከንቱ እየፈሰሰ ይገኛል። ቅዱስ ሕይወት በገፍ እየጠፋ ይገኛል። ከዋናዎቹ ሕግጋት መካከል ‘አትግደል’ ይላል፤ ‘ባልንጄራህን ከራስህ አስበልጠህ ዉደድ ይላል’። ዛሬ ግን ሰዉ እንደቅጠል በግፍ እየረገፈ ይገኛል። እንደዚህ ዓይነቱ ዝርፊያ፤ ማፈናቀልና መግደል ከዬት የመጣ ነዉ? ሕግና ሥርዓት በሚከበሩባቸዉ ሀገራት ዉሾችና ድመቶች እንኳ መብት አላቸዉ። የአስተዳደሮች ብልሹነት እንደሆነ እንጂ በጭቁኑ ህዝባችን መካከል ጠላትነት አልነበረም። ይሄ አማራ፤ ይሄ ኦሮሞ፤ ይሄ ትግሬ፤ ወዘተ የሚለዉ ክፍፍል በቅርቡ የተፈጠረ የከፋፍሎ መግዣ ተንኮልና የዉሸት ትርክት ነዉ። ያለዉን ተካፍሎ ጥሮ ግሮ የሚያድር ብርቱ ህዝብ ነበር። አሁን ከመተላለቃችን በፊት ያንን መልካም ምግባር መልሰን መገንባት ይኖርብናል። መፍትሔ የሚመጣዉ ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል፤ በዜጎች መካከል ጥሩ ጉርብትናና ወዳጅነት ሲኖር፤ ዜጎች በነፃ ተዟዙረዉ የመስፈር፤ የመሥራት፤ የመነገድ፤ ወዘተ መብታቸዉ ሲጠበቅላቸዉ ነዉ። ለብዙ ሺ ዓመታት በሰላም የኖርነዉ በዚያ መልክ ነበርና።
3ኛ/ ሰላም ሳይኖር ዕድገት አይታሰብም
ሁል ጊዜ ስንደምናገረዉ፤ ቸሩ አምላካችን መርጦ የፈጠራት ሀገር ናት። ሁሉንም አሟልቶ ሰጥቷታል፤ የምድራችን ስፋት፤ የወንዞቻችን፤ የሃይቆቻችንና የጅረቶቻችን ብዛት፤ የህዝባችን ታታሪነት፤ ብርታትና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት መሆኑን ስመለከትና ዛሬ የወደቅንበትን ደረጃ ስመለከት እጅግ በጣም አዝናለሁ። ዛሪ በዓለም ላይ ከሁሉም በታች ሆነን በአሳፋሪ ደረጃ ላይ እንገኛለን። በልጅነታችን ስንማርና ለዲሞክራሲ ስንታገል ዉዲቷ ሀገራችንን ከራስዋም አልፋ ለጎረቤት ሀገሮች ጭምር የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ ነበር። ይቻልም ነበር።
ገበሬዉ በሰላም ወጥቶ ካላረሰ መልካም ምርት ከዬት ይመጣል? ነጋዴዉ በነፃ ተንቀሳቅሶ ካልነገደ እንዴት ሊያተርፍ ይችላል? ተማሪ በነፃነት ወጥቶ ጥሩ ትምህርት ካላገኘ ህይወቱ እንዴት ሊሻሻል ይችላል? እስከመቼ ድረስ ይሰደዱ? ይሰቃዩ? ይዋረዱ? አሁን እኮ ያልተበተኑበት ምድር የለም። በመንገድ፤ በበረሃና በባህር ላይ የቀሩትም ብዙ ናቸዉ።
በመፍትሔ ምትክ ችግር መፍጠር ለምን አስፈለገ? በዕድገት ምትክ ዉድመት ለምን ተመረጠ? የዉሸት ትርክትና መርዝ ከመርጨት ሃቆች ለምን አይመሰከሩም? የሕገ መንግሥቱ ከፋፋይ መዘዞች ሀገር ለማፍረስ እንጂ ለመገንባት አይደለም። ጠንካራ አንድነትን ሳይሆን ከዞን ወደክልል፤ ከክልል ወደመገንጠል፤ ወዘተ የሚጋብዝ ሀገር አፍራሽ ነዉ። በዚህ መልክ ከቀጠልን ግድቡ እራሱ ብዙ ዋስትና አይኖረዉም።
4ኛ/ ህብረት ከሌለን በዉጪ ታሪካዊ ጠላቶች እንጠቃለን።
የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ፍላጎት በደንብ እናቃለን። በነፃነታችንና በብርታታችን ምክንያት ቂም ከያዙብን በጣም ቆይተዋለል። አፍሪቃን በባርነትና በቅኝ አገዛዝ የበዘበዙ ኃይሎች አይተኙልንም፤ ለምን? አፄ ቴዎድሮች በመቅደላ እጅ አልሰጡም። አፄ ዮሐናስ በመተማ ላይ ህይወታቸዉን ሰዉተዋል። በአፄ ምኒልክ መሪነትና በጠቅላላዉ ህዝባችን ትብብር በአድዋ ላይ አሳፍረናቸዋል። በማይጨዉ ወረራ ዘመን ጎበዝ አርበኞቻችን ለ5 ዓመታት ከባድ ትግል በማድረግና ከባድ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል የዉድ ሀገራችንን ነፃነት አስጠብቀዉልናል። ለአፍሪቃዉያን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መዉጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገናል። ካሪቢያኖች ቀና ብለዉ እንዲሄዱ ኩራት ሰጥተናቸዋል። ትብብር በነበረን ወቅት በእግዚአብሔር ኃይል እነዚያን ድሎች ሁሉ ተጎናጽፈናል። በውስጣችን ስንከፋፈልና ስንባላ ግን ለጥቃት እንዳረጋለን። በ1991 ዓ/ም በለንደን ላይ ስብሰባ ጠሩ፤ መሪዉ ሄርማን ኮህን ነበር። በስብሰባዉ ላይ ኅብረ-ብሄራዊ ፓርቲ እንዲሳተፍ አልተፈቀደም። ለሦስት ቀናት የታሰበዉ ኮንፈረንስ በግማሽ ቀን ተጠናቀቀ፤ ወያኔ ወደ አዲስ አበባ፤ ሸዓቢያ ወደ አስመራ። ይሄንን ያደረጉት ለትግራይና ለኤርትራ ህዝብ በመቆርቆር ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነበር።
ግብፅ እንኳን የኛን ዉሀ እየጠጣችና በኛ አፈር እያመረተች ምስጋና የሚባል ነገር አታዉቅም። እኛ ዉሃና አፈር አልከለከልናት። እርሷ ግን ወንዛችንን ገድበን ከጭለማ እንዳንወጣ ታስፈራራናለች። ሱዳን ከርሷ ጋር በመተባበር ድንበራችንን እየደፈረች ትገኛለች። መፍትሔዉ ዉስጣዊ አንድነትና ሰላም ማስፈን ብቻ ነዉ። በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዉስጥ መሆናችንን ባንዘነጋ መልካም ነዉ። ካለዚያ ታሪክም እግረዚአብሔርም ይፈርዱባቸዋል፤ ልጆቻቸዉም ያፍሩባቸዋል።
ስለዚህ አሁን በሰላም፤ በልማትና በዕድገት ላይ እንድናተኩር አደራ እላችኋለሁ። እግዚአብሔር ይጨመርበት።
ዶ/ር በቀለ ገሠሠ (drbekeleg@gmail.com)
https://amharic-zehabesha.com/archives/177555
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment