Friday, August 5, 2022

መንጠራራትና ሀሰታዊ ትርከት አዋቂነትን አያላብስም!! (አኒስ አብዱላሂ)
ስለ ታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሀሳብ ስለሚቀርቡት የተሳሳቱ ትንታኔዎች

„I believe we have a good chance of discovering

the laws that governs the entire universe”

Stephen Hawking

ከ አኒሳ አብዱላሂ

02.08 2022 ዓ.ም.

ክፍል አራት

ከዚህ አለም በሞት ከተለየን አራት አመት የሞላው እውቁ ሊቃውንት ስቴፈን ሃውኪንግ የተናገረው ሙሉ በሙሉ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ የሚጋራው ነው።

እስቲ በቅድሚያ ስለ ታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብን በሚመለከት እነ ሽፈራው ሉሉና እንዳሻው ቡናሬ አለን የሚሉትን የተቃውሞ አስተያየት ከጀመሩት አረፍተ ነገር እንነሳ።

“ቁስ አካል፣ ኃይልና ቦታ (Matter, Energy and Space) በአንድ ላይ በአንድ ነጥብ ተከማችቶ መገኘት ፍንዳታ እንዳስክተለ ይተርካል” በሚል አረፈተ ነገር በታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሀሳብ ላይ ያላቸውን የተቃውሞ አስተያየት የሚጀምሩት ሽፈራው ሉሉና እንግዳሸት ቡናሬ የትኛው ተመራማሪ? የት ቦታ? መቼ? በየትኛው መፅሄት እንደታተመ? ፍንዳታው ቀድሞውኑስ ምን አይነት እንደሆነ ሳይገልፁ እንዲያው በደፈናው የራሳቸውን የተሳሳተ ፍረጃ እርግጠኛ አስመስለውና አላብሰው የምሁራዊነትን ካባ ለማጥለቅ ተፍጨርጭረዋል ግና አልተሳካላቸውም እንጂ። የፍንዳታው ምክንያት ክምችት ሳይሆን ሌላ ነውና። ይህ እንግዲህ ወደ ኋላ በሰፊው የምንመለከተው ቢሆንም ባጭሩ ግን ስለሚተቹት ፅንሰ ሃሳብ በሚገባ ካለመረዳት የሚመነጭ አጉል አውቃለሁ ባይነትና ጥራዝ ነጠቅነት የተጠናወተው አመለካከት ከመሆን የሚያልፍ አለመሆኑን ከወዲሁ መጥቀስ ግን አግባብነት ያለው ነው።

ሲቀጥሉም “ዩኒቨርስ እየሰፋ ከሆነ ከአንድ ነጥብ መነሳት አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ የተመሰረተ ነው” ይሉና “ይህ አስተሳሰብ ዩኒቨርስ ከአንድ ነጥብ ከፍንዳታ ከተነሳ አሁን ያለውን በጣም የተቀናጀ፣ የጋላክሲዎች፣ የፕላኔቶች፣ ከዋክብቶች ኡደት እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ለማስረዳት አይችልም” ብለው የደንቆሮ ድንቁርናቸውን ያረጋግጣሉ። በማያውቁትና በቅጡ ባልገባቸው ከተሳሳተ አስተያየት ተነስተው ጉዞአቸውን በተሳሳተ ድምዳሜ ላይ በመንተራስ ፍሬቻ በሌለው መኪና ላይ ተሳፍረው ከእውነት ጋር የተጣላ ድምዳሜ በጉያቸው ሸጉጠው በሚያስደንቅ ሁናቴ ወደ ገደል የሚወስድን የቁልቁለት መንገድ ተሳፋሪ ሆነው እናገኛቸዋለን። ቀደም ብለው ተማሪ በነበሩበት ወቅት ስላልገባቸው ፅንሰ ሃሳብ ጥያቄ ለማቅረብ እንዳልደፈሩ ሁሉ አሁንም ቀድሞዉንስ መቼ አስረዱን ብለው ለሚመለከታቸው ክፍሎች የሚፈልጉትን ጥያቄዎች ሳያቀርቡ? ሳይጠይቁና ሊቀርብላቸው የሚችለውንም ትንታኔ ለማየትና ለማንበብ ብሎም ለመረዳት ገቱ ሳይኖራቸው በራሳቸው እምቢባይነት ተኮፍሰውና በትዕቢት ተወጥረው ፅንሰ ሃሳቡ “ማስረዳት አይችልም” ሲሉ በርግጥም ጥራዝነጠቅነት ውርደትን አስከታይ መሆኑን ባለመገንዘብ የተደረሰበት ድምዳሜ በመሆኑ አይፈረድባቸውም። ድንቁርና እንዴት ድፍረትን እንደሚያላብስ ግን በምስሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። በውነቱ የበርካታ አመታት የብዙ ሊቃውንቶች የጋራ ውጤት የሆነ ፅንሰ ሃሳብን በዚህ አይነት መልክ ጥላሸት መቀባትና ለመጋፋት መጣር የራስን አላዋቂነትና በባዶ ጭንቅላት መንጠራራት ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምንም አይነት ሊተረጎም አይችልም።

George Anthony Gamow የቀድሞ ሩሲያዊ የኋላ አሜሪካዊ በተለያዩ የፊዚክስ ዘርፎችና ለታላቁ ፍንዳታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተው ሊቃውንት ጋሞው በአሁኑ ወቅት በህይወት ቢኖርና የነ ሽፈራውን አስተያየት ለማንበብ ቢችል የራሱንና የበርካታ የሙያ ጓደኞቹን የምርምር ውጤት አላግባብ በዚህ አይነት ሁናቴ መዘለፍ እንዴት እንደሚያቅለሸልሸው ስናስብ በርግጥም አፈሩ ይቅለለህ እያልን በሱ አንደበትና በሱ የተባ ብዕር መልስ እየሰጠን ዘላለማዊ እንቅልፉን ከመረበሽ ለማዳን የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን። እነሽፈራው በቅጡ ውስጣዊ ይዘቱ ባልገባቸው ፅንሰ ሀሳብ ላይ ተደናግረው አንባቢዎቻቸውን በማደናገር ወደ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እየተሸጋገሩ ነውና ነገሩ ይህ አያስጨንቃቸውም.. ለምን ብለው። እንዲያውም ይባስ ብለው “ዑደቱ በፍንዳታ ተፈጠረ ብሎ ማመን እግዚአብሄር የሌለበት እምነት ነው” በማለት ያው የለመዱትን የጥላሸት ጅራፋቸውን ሲያስጮሁ መሰል ጩኸት መስማት የለመድነው ነውና የሚደነብር እንደሌለ ሊያውቁት በተገባ ነበር። ሆኖም የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነውና አደብ እንዲገዙ ካልተደረጉ የፖለቲካ ሥልጣንን ለመቆጠጠር ከቻሉማ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሲታሰብ ከሌሎች ሀገሮች ተመክሮ የምናውቀው ነውና በውነትም ያስፈራል፤ ይዘገንናል። ይሰቀጥጣል። ለዚህም ነው በስጋት ብቻ ሳንወሰን ነቅተናል እኛም ጉርጓድ ምሰናል እያልን መልስ ለማቅረብ የተገደድነው።

ቀደም ብሎ በገፅ 21 ላይ “ለምሳሌ የስበት (Gravity) መኖርን፣ የመሬት ስበት፣ የጨረቃ ስበት፣ ወዘተ መኖሩን ሳይንስ ያስረዳል፤ ተረድቶም ብዙ ለሰው ልጅ ጠቀሜታም ጎጂም የሚሆኑ ነገሮች ተፈልስፈዋል። በሳይንስ የሰው ልጅ ይህንን ቢረዳም ባይረዳም (ይህንን ስርብ ደረዝ ይጨመርበት) ስበትን እግዚአብሄር የፈጠረው ስለሆነ ያለ ነው። ሳይንስ የስበት ህግን ያስረዳ እንጂ፣ አለማት በስበት ህግ እንዲኖሩ የፈጠረው አምላካችን እንዴት ታላቅና ረቂቅ መሆኑን ተረድተን አምላካችንን የበለጠ እንድናወድሰውና እንድናከብረው ይረዳናል።“ ብለው በልባቸው ውስጥ ያለውን እንዲህ እርግፍ አድርገው በማያወላዳ ሁናቴ ሲያስቀምጡ ታዲያ ጫጫታው ለምንስ አስፈለገ? “ሳይንስ የስበት ሕግን ያስረዳ እንጂ” ካሉ ያ ሁሉ የጥያቄ ማዥጎድጎድ ምንስ ተፈልጎ ነው የቀረቡት? የመንፈሳዊውን እንጂ የቁስ አካል አለምን ለመራመር መብት ሰጥተው አልነበረም እንዴ? ባለማወደስና ባለማክበር ገሃነም የሚያስገባ በነሱ አስተሳሰብ ከሆነ የምርጫ ጉዳይ ነውና እነርሱን ሊያስጨንቃቸው አይገባም። እናንተ የፈለጋችሁትን ተፈላሰፉ፣ ተመራመሩ፣ እኛ የምንቀበለው የራሳችንን እምነት ብቻ ነው ማለት ከሆነም ታዲያ ይመቻችኋ!! ታዲያ ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር እንካሰላንቲያ መግጠሙ ለምን አስፈለጋችሁ? አቀረባችሁ?

ለማንኛውም በርግጥም ስለ ስበት ብቻ ሳይሆን ስለ ቋሚ የተፈጥሮ ሕጎች በቂ ግንዛቤ ቢኖራችሁ ኖሮ ይህንን ሁሉ ጥያቄዎች ማዥጎድጎድ ባላስፈለጋችሁ ነበር። የናንተኑ አነጋገር ልበደርና “የዲያቢሎስ “ ጠኔ በእውቀት ጠል ሰፈር እንጂ ለእውቀት ክብርና አድናቆት ሰጪዎች ዘንድ ድርሽም እንደማይል በምሳሌነታችሁ ልትጠቀሱ የምችሉ በመሆናችሁ ምስጋና ይድረሳችሁ። የሚገርመው ግን ሳይንቲስቶቹ በስንት ልፋት ያገኙትን ውጤት ድሮ እኛ እናውቀዋለን በመፅሃፋችን ተገልፆ ይገኛል እየተባለ በሳይንስ ላይ መዘባበት መልካም ጠባይነትን መላበስ ሳይሆን በርግጥም ዲያቢሎሱ ካለ በዲያቢሎስ ጠኔ መጠመቅና መታወክ ነው። መድኃኒት የሌለው በሽታ የሚያስከትለው ጠንቅ። ለኪርዬሽን ሳይንስ በአጀንዳ አስፋፃሚነት ተኮፍሰው ያውም ምንም የራሳቸው የሆነ የግል አስተዋፅዖ ባላበረከቱበት መሰማራቱ፣ እናመልከዋለን በሚሉት ፈጣሪም ዘንድ እኮ የሚመስገን ተግባር ሳይሆን የሚያስኮንን ነውና አፍን ለጎም፣ እጅን ሰብሰብ ማድረግና ማስተዋልን መሰነቅ የግድ እንደሚል ሊያውቁት ይገባ ነበር። በባዕድ አጀንዳ አስፈፃሚነት አትክሰሰን የሚሉ ከሆነ አለመሆናቸውን መጣጥፋቸውን አርመው በአዲስ በማቅረብ መታረማቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል። አይ ካሉ ክሱ የጠና ይሆናል። ለነገሩ የተፈጥሮ ሳይንስን ጥላሸት መቀባትን በእጅጉ ከሚጋሩት ውስጥ መ/ር ዶ/ር ዘበነ ለማና መሰሎች ይገኙበታል። የጥላቻ ናዳ አፍ እንዳመጣ ማውረድ የድንቁርና ኃይል መሆኑን ከማመላካት ውጪ የሚያስገኘው ጠቀሜታ በፍፁም የለም፣ ሊኖርም አይችልም። ትዝብትን ያከናንባል እንጂ። ለማንኛውም ወደፊት ረጋ ብለን ስለነሱ የምንለውን እንላለንና እስከዛው ድረስ ገቱን ይስጠን።

ታዲያ ከጥያቄዎቻቸው መዥጎድጎድ ባሻገር በተለያዩ ገፆቻቸው የሸነቆሯቸው የጥላቻ ናዳዎች ማንን ለማስፈራራት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም በኦሪት ዘመን የሚኖር እንዲሁም የተባለውን፣ የሚሰማውን፣ የሚነገረውን እንዳለ ተቀብሎ የሚያምን ትውልድ በአሁኑ ወቅት እንደሌለ አለማወቃቸው ከማስገረምም አልፎ የሚያስደንቅ ነው። ለዚህም ነው እያስተጋቡት ያለው ተቃውሞ ትውልድን ለማስተማሪያ ሳይሆን የሕዝብንና ትውልድን አስተሳሰብ በነሱ የግል አጀንዳ ለመቅረፅ የታሰበ መሟገቻ ከመሆን የማይልፍ ነው ተብሎ የሚገለፀው። ይህ ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ባስገኘው እውቀት ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ ውይይት ለማድረግ መጣር ሳይሆን እንደ ተራ የፖለቲካ ካድሬ ስውር አጀንዳ ያላቸውና ሊቃውንት ነን ባዮች የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንደ ገደል ማሚቶ ማስተጋባት ካልሆነ በስተቀር በምንስ ሊተረጎም ይችላል? እነ ሽፈራው ለእምነታቸው ሽንጣቸውን ገትረው መከራከር የግል መብታቸው ነው። ማመን ማለት ደግሞ በጭራሽ ማወቅ ሊሆን አይችልም። የእምነትን ሚና በቅጡ አለመረዳት ይሆናል። አማኝ ጀብደኝነት የተጠናወተው በእምነቱ “ኃያልነት” ተመክቶ ከሌላው በበለጠ ሁሉን አውቃለሁ ማለት ሲጀምር አጓጉላዊ እምነት (Superstitious) ነው የሚሆነው። ስለሆነም የእምነታቸውን “ትክክለኝነት” ለማረጋገጥና ተቀባይነት እናገኝበታለን ሲሉ በቅጡ ባልተገነዘቡት የሳይንስ ፅንሰ ሀሳብ ላይ በመንጠልጠል እንዳሻ የእህያ እርግጫ የመሰለ ድርጊት እየተራገጡ መዘባረቅ ግን የአምባገነናዊነት መገለጫ ነውና በፍፁም አይፈቀድም። አደጋ አስከታይ ነውና።

ለማንኛውም “የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ የዩኒቨርስ መስፋትን ለዝግመተ ለውጥ ድጋፍ ያስገኛል በሚል ለመተርጎም የቀረበ ነው “ የሚለውን ከምሁራዊ ውይይት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለውና ንቃት የጎደለው እንቶፈንቶ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንቶችን በሁሉም አይነት የማይመጥን አመለካከት ባቀረቡበት አንደበት ተመለሰው እንደገና “ ለምን ይሰፋል? ምንስ ያሰፋዋል? ለመስፋት መነሾ የሆነው ምንድን ነው? ከአንድ ቦታ ነው ወይ የተነሳው? የፈነዳስ ነገር እንዴት ከዝብርቅርቅነታቸው ወደ አስደናቂ ትስስርና ዑደት እንዴት ሊመጣ ቻለ? በፍንዳታ የተስተካከለ ዑደት ሊመጣ ይችላል ወይ? ይህንንስ በተግባር ማሳየት ይቻላል ወይ? ወዘተ ... ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል 29 “ የተሰኙ ጥያቄዎችን እያዥጎደጎዱ በሚያስደንቅ ፍጥነት “ለዚህ መልስ በፍንዳታ ማግኘት አልተቻለም” እየሉ እነሱው ጠያቂ፣ እነሱው መልስ ሰጪ ሆነው ይቀርባሉ። ያናድዳል፣ ያበሳጫል። የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ደግሞ ይቻላል፤ ተችሏልም በማለት በመረጃ የተደገፈ መሟገቻውን ያቀርባል።

ለመሆኑ ግን እስቲ አንድ ጥያቄ እናቅርብላቸው። በየትኛው የምርምር ውጤታቸው ላይ ተንተርሰው ነው “በፍንዳታው መልስ ማግኘት አልተቻለም” በማለት ከዚህ ከባድና መፈናፈኛ ከሌለው ድምዳሜ ሊደርሱ የቻሉት? ማጠየቂያዎቻቸውስ ምንድን ናቸው? በውነቱ ጤናማ አዕምሮ ላለው መልሱን ጠለቅ ብሎ ለሚመረምር ማንኝውም ዜጋ ምንም አይነት መረጃ ባልቀረበበት ሁናቴ እንዲህ ፍፁምነት ያለው ድምዳሜ ማቅረብስ ምንስ ያመላክታል? የአቅራቢዎቹን የእውቀት ደረጃ እጅግ አናሳ መሆኑን ከማመላከት ውጪ። ምናልባትም ራስን ከምሁራን ተርታ በማሰለፍና በመመደብ ደጋፊና ተቀባይ ለማግኘት የታለመ የቅዠት ሕልም ከመሆን አይልፍም። በርግጥም ደግሞ ወቅቱ የኦሪት ዘመን አይደለምና አንባቢያን የተፃፈን አንብበው ለመገንዘብ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ስላለን የሕልም ቅዠታቸውን እንዳለሙ ይቀሯታል እንጂ የሚመኙትን አያገኙቷም። በመሆኑም አንድም የተፈጥሮ ሳይንስ የምርምር ውጤቶችን ባላነበቡበት ወይንም ደግሞ ለእድገቱ ምንም አይነት የግል አስተዋፅዖ ባላበረከቱበት አንድን ፅንሰ ሃሳብና አቅራቢዎችን ግን ጥላሸት ለመቀባት የሚሄዱበት መንገድና እይታ ተንኮል የተሞላበት ፌዝ ከመሆን የማያልፍ ቢሆንም በቸልታ የምናልፈው ጉዳይ ሊሆን አይችልም። እንዳመጣጡ ተገቢው መልስ እንዲደርስ ይደረጋል እንጂ።

ስለሆነም ትኩረታችንን ወደ ተነሳንበት ርዕሳችን ከማድረጋችን በፊት አንባቢን ለማሳወቅ የምፈልገው አንድ ወሳኝ ቁም ነገር አለ። ስለ ታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ በመጠኑም ቢሆን የተሟላ ግንዛቤ ለማግኘት አንባቢ ይቻለው ዘንድ በተራ ቁጥር 29 ራሳቸው በዋቢነት ከጠቀሱት በእንግሊዝኛ ከተፃፈው ባለ 17 ገፅ ባሻገር፤ The Origin of the Universe DeYoung J.C. Whitecomb 13 ገፆች ያሉት፣ እንዲሁም ጊዜ ካላችሁ ለዶክተር ዲግሪ መመረቂያ የተፃፈ Creationism at the grass roots A study of a local creationist Institution. By Paul J. Wendel በ May 2008 ይፋ የሆነ መጣጥፍ እንዲሁም የኖቬል ተሸላሚና የበርካታ መጣጥፎችና መፅሃፍቶች አቅራቢና ተወዳጅ ከሆነው Stephen Weinberg ለምሳሌ The first 3 minutes. A modern view of the Origin of the Universe. (2nd edition Basics Books 1993) ና በሁለተኛነት ስለ ኳንተን ሜካኒክ ያሳተመውን መፅሃፍ እንዲሁም በሚገባ ለመረዳት ሰፋ ያለ የከፈተኛ የሂሳብ ትምህርት ጠያቂ ቢሆንም በእውቁ የኖቬል ተሸላሚ በሆነው የፊዚክስ ሊቃውንቱ የተደረሱ P. J. E Peebles Priciples of Physical Cosmology (Princeton U. Press 1993) ሌሎች ስድስት መፅሃፍቶቹን ብታነቧቸው የነሽፈራው ሉሉና ከጀርባቸው ለሚገኙት የበላይ ጠባቂዎቻቸው ማንነትንና ምንነት በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ይረዳችኋል የምል ግምት የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ስላለው ምክሩን በአክብሮት ለአንባቢዎች ይለግሳል።

የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳቡን በሚመለከት ከሥሙ ጀምሮ ውስጣዊ ይዘቱን በተዛባ አስተያየት ላይ በመመርኮዝ የሚሰጡ ትክክልና እርግጠኝነት የሌላቸው ድምዳሜዎች እየተሰራጩ በመሆናቸው ፅንሰ ሃሳቡ በተጨባጭ ስለምን እንደሚተነትን? ለምንስ እንደተፀነሰ፣ እንዴትስ አንደተፀነስ፣ ማስረጃዎቹ ምን እንደሆኑ ማቅረብ ጥራት ያለው ግንዛቤ ለማግኘት ይረዳል። ፅንሰ ሃሳቡን አስመልክቶ ለሕትመት የቀረቡና በተለያዩ ድረገፆች የወጡ፣ መጠነ ሰፊነት ያላቸውና በእጅጉኑ የተለያዩ ሃሳቦችን የሚያንፀባርቁ፣ አንዳንዶቹ መረጃዎች ለተራው ዜጋ ቀርቶ ለሙያተኞችም በጥሩ ሁናቴ ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሆኑ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ከራሱ ተመክሮ የተገነዘባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ እንዲያውም ማንኛውም አንባቢ እንዲረዳ በማለት አቅልለው እንዲፃፉ የተደረጉት በስህተት የተሞሉ ሲሆኑ ጥላሸት ቀቢዎችም አልጠፉም።

እርግጥ ነው። የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ የዘመናዊ ኮስሞሎጂ ዋና መሰረታዊ ሃሳብ ነው ተብሎ ለፅንሰቱ በተለያየ ደረጃ አስተዋፅዖ ባበረከቱ በርካታ የሳይንስ ሊቃውንቶች ዘንድ ተበክሮ የሚገለፅ ነው። የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ በጣም የታወቀ ቢሆንም በዛው መጠንም ከላይ እንደተጠቆመው በተሳሳተ መልክ ለማቅረብ የሚሞክሩ፣ ጭራሱኑም ሊረዱት የማይፈልጉ በተለይም ኃይማኖታዊ አጀንዳ ያላቸው ክፍሎች በርካታ ናቸው። በነ ሽፈራው ሉሉና እንግዳሸት ቡናሬ የቀረበውም እንቶፈንቶ ከዚህ የተለየ አይደለም። ታላቁ ፍንዳታ ከፍተኛ ከበሬታን ያገኙ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ሳይቀሩ በመጣጥፎቻቸው በተሳሳተ ሁናቴ ሲገልፁ ይስተዋላል። በተለይም ፍንዳታው የተከሰተው ቀድሞውኑ በነበረ ሕዋና ጊዜ ውስጥ ሳይሆን (ይህንን በሚገባ ማስተዋል ይገባል) ሕዋ፣ ጊዜና፣ ቁስ አካል የተፀነሱበት ወቅት(ክስተት) መሆኑን ለመገንዘብ ግራ የተጋቡ መኖራቸው አይካድም። ከስህተቶች ውስጥ አንደኛው ከዚህ ከተሳሳተ እሳቤ የሚጀምር ነው።

ፍንዳታ የሚለው ቃልም ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤን የሚሰጥ ነው። ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ሆይል የተባለው ሊቃውንት ሲሆን ፍላጎቱ ፅንሰ ሃሳቡን ሥም ለመስጠት ሳይሆን በተፎካካሪነት ያለውን የራሱን ስቴዲ ስቴት ፅንሰ ሃሳቡን መሰረት ለማስያዝ በአሉታዊ ጎኑ ለመጠቀም በማሰብ ነበር። ግና እሱ በተመኘውና በፈለገው መንገድ ሳይሆን ቀረና ተቃዋሚዎቹ ቃሉን ቀለብ አርገው ለራሳቸው ፅንሰ ሃሳብ በሚስማማ ሁናቴ ሊጠቀሙበት ችለዋል። ፍንዳታ ቅፅበታዊና እጅግ ፈጣን ከብርሃን ፍጥነትም በላቀ ሁኔታ የህዋ መስፋትን አመላካች እንጂ የተዘበራረቀና ጥቃቅን ንጥረ አካላት በተለያየ አቅጣጫ የተስፈነጠሩበት ሁናቴን አያመላክትም። (ይህንን አስመልክቶ በተጨባጭ ለማሳየት በጣም እጅግ አናሳ በሆነ 10-30 -33 ፍርስራሽ ደቂቃ ውስጥ ለአፅናፈ አለም መነሾ የሆነቺው እጅግ በጣም ትንሽ ቅንጣት በ 1030 እጥፍ ትስፋፋለች። ይህ ማለት 1 ሴንቲሜትር ርዝማኔ ያላት የገንዘብ ሳንቲም የሚልኪዌይ ጋላክሲን 10 ሚሊዮን እጥፍ ለመስፋፋት የተቻለበት ሁናቴ ነው የተከሰተው።) ለህዋው በዚህ ሁናቴ መስፋፋት በማስረጃነት እየቀረበ ያለው ፍንዳታው ከተከሰተ ከ 400 000 አመት በኋላ የተፀነሰውና በቅሪትነት የሚታወቀው CMBR (Cosmic Microwave Background Radiation) ተብሎ የሚጠራው ነው። በተለያዩ ምርምሮች የተገኙት ውጤቶች ልዩነት ቢያሳዩም በጣም ኢምንት 1/10000 ናቸው። ይህም በሌላ በኩል የቀድሞ አፅናፈ አለም በምስቅልቅል የታጀበ እንዳልነበር የሚያመላክት ነው።

የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ በርግጥም ያለ ጥርጥር ስለ መነሾ የሚገልፅ፣ ስለ ቁስ አካላት መነሹ፣ ስለ ንጥረ አካላት መነሾ፣ ስለ ባክግራውንድ ኮስሚክ ዌቭ ሬዴዬኤሽን መነሾ፣ በአፅናፈ አለም ውስጥ ስለሚገኘው ቅርፅ ወዘተ የሚተነትን ነው።

የታላቁ ፍንጋታ ፅንሰ ሃሳብ በበርካታ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዘንድ ተአሚነት ለማግኘት የበቃው ሽፈራውና ጓደኛው እንደሚያናፍሱት ባልተረጋገጠ በተራ ወሬ ሳይሆን በምናባዊ ግምታዊ ትንበያ (hypothesis) አስተሳሰብ ያቀረባቸው አስተያየቶች ሁሉ በተግባር ተፈትነውና ተጨባጩን ሁናቴ አግባብነት ባለውና በትክክል ለመተንተን በመቻሉ እንደሆነ በርካታዎች የሚስማሙበት ነው። ምናባዊ ግምታዊ ትንበያን ምሁራኑ ሲገለፁት እንዲህ ይሉታል። A hypothesis (plural: hypotheses), in a scientific context, is a testable statement about the relationship between two or more variables or a proposed explanation for some observed phenomenon. In a scientific experiment or study, the hypothesis is a brief summation of the researcher's prediction of the study's findings, which may be supported or not by the outcome. Hypothesis testing is the core of the scientific method. 1 (1. What is hypothesis? Definition from Whatais.com) በግርድፉ ሲተረጎም ምናባዊ ግምታዊ ትንበያ በሳይንሳዊ አገባብ ዙሪያ ያለ፣ ስለ ሁለት ወይንም ከዛም ለሚያልፉ ተለዋዋጭ ሁናቴዎች ወይንም ደግሞ ተመርምረው ውጤት ለተገኘላቸው ክስተቶች ለማጣራት የሚቀርቡ ማስረጃዎችን እንደገና ማየትን የሚመለከት ነው። በሳይንሳዊ ምርምር ወይም ጥናት ምናባዊ ግምታዊ አስተያየት የተመራማሪዉን እጥር ምጥን ያለ አጠቃላይ ግምጋሜ ወይንም ጥናታዊ ውጤት የሚገልፅ ሲሆን ውጤቱም አዎንታዊ አለበለዚያም የአሉታዊነት እይታ የሚያርፍበት ነው። ምናባዊ ግምታዊ አስተያየት ለሳይንሳዊ ምርምር ዋና መሰረት ነው በማለት ይገልፁታል።

ለፅንሰ ሃሳቡ ተአሚነት መገኘት ተበክረው ከሚገለፁት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

1. ከፍልስፍና አንፃር ለምሳሌ ከፍንዳታው በፊት ምን ነበር? የአፅናፈ አለም ዳርቻውስ ምንድን ነው? የመሳሰሉ ጊዜንና ጉልበት አጥፊ፣ እንዲሁም ማቆሚያም ሆነ ማጣፊያ የሌላቸውና መልሰው ተመላልሰው በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ከወዲሁ ይገታል።

2. የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ ትክክለኛነቱ ከጥንሰሱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተለያዩ ጥናታዊ ምርምሮች በተረጋገጠው የእውቁ አልበርት አይንሽታይን አጠቃላይ አንፃራዊ ንድፈ ሃሳብ ቀመር ላይ በመመርኮዝ የተፀነሰ በመሆኑ ለተአሚነቱ የራሱ አስተዋፅዖ ማበርከቱ ሌላው ወሳኝ ነጥብ እንደሆነ ይገለፃል።

3. የንኡስ ንጥረ አካላት ስርጭትን የሚመለከት ሲሆን ክብደታቸው በቀላልነት የሚገመቱት ንጥረ አካላት በአፅናፈ አለም ውስጥ በብዛት መገኘት ሌላው ነጥብ ነው። የትኞቹን ንጥረ ነገሮች በአፅናፈ አለም ውስጥ እንደሚፀነሱ ለማወቅ እንደሚቻል አስቀድሞውኑ ግምታዊ ትንበያ (hypothesis) በማቅረብ ብቻ ሳይሆን በምርምርም ያረጋገጠ መሆኑ በተጨማሪነት የሚጠቀስ ነጥብ ነው።

4. በጣም እርቀት ላይ ስለሚገኙ ከዋክብትና የሚፈነጥቁት የብርሃን ጨረር የሞገዳቸው መርዘምን በሚመለከት በጥሩ ሁናቴና ግልፅነት ባለው መልኩ የሚተነትን መሆኑ ሌላው ተጠቃሽ ነጥብ ነው። ኤድዊን ሃብል የተባለው ሊቃውንት በሚሊኪስትሪት ሥም የሚታወቀው ጋላክሲ ብቸኛው የከዋክብቶች ስብስብ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በብርሃን ሞከድ መርዘምም ምክንያት (ረድ ሺፍት)ከኛ መሬት አንፃር ሲታይ እየራቁን ብቻ ሳይሆን በራቁ ቁጥርም የሚርቁበት ፍጥነት በ እጥፍ እንደሚጨምር ባደረገው ጥናታዊ ምርምር ለማሳየት መቻሉ ነበር። ጋላክሲዎቹ በሕዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሳይሆን (መሬት በፀሃይ ዙሪያ እንደምትሽከረከረው አይነት ሳይሆን) የተንሳፈፉበት ሕዋ ራሱ እየተስፋፋ በመሄድ ምክንያት የሚፈጠር ክስተት ነው። በሌላ በክሉ ሁሉም ከዋክብቶች በአንድ ላይ በጠቋራው ጥልቀት ዙሪያ የሚሽከረከሩበት ፍጥነት እምብዛም ከግምት የሚገባ ባለመሆኑ ከነሱ የሚፈነጠቀው ብርሃን ላይ የሚያስከትለው ተፅ ዕኖ እሚንት ነው።

5. የመጨረሻው ነጥብ ከፍተኛ የቁጥር ትምህርት እውቀትንና ግንዛቤን የሚጠይቅ በመሆኑ አንባቢያን በዚህ በኩል ፍላጎት ካላቸው ሊረዱት በሚችሉት የባዕድ ቋንቋ ለምሳሌ Diracs Large Number Hypothesis ድረ ገፅ ገብታችሁ ብታነቡት ስለ ፅንሰ ሃሳቡ ግንዛቤያችሁን ያሰፋል የምል ሙሉ እምነት ስላለው መጠቀሱ ብቻ የሚበቃ ነውና እንድትመለከቱት ይጋብዛል።

የተነሳንበትን ርዕስ ጠለቅ ብለን በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱትን እድገቶች ስናጤን ለምሳሌ ጊዮርገስ ለሜትር (Georges Lemaitre) የተባለ ቤልጂጋዊ ቄስና የፊዚክስ ሊቃውንት በ 1927 ዓ.ም የአይንሽታይንን አጠቃላይ አንፃራዊ ፅንሰ ሃሳብና የሩሲያዊውን የሂሳብ ሊቃውንት የአሌክሳንደር ፍሪድማን የፎርሙላ ቀመር (Friedman Equation) በመጠቀም ቋሚነት የሌለው አፅናፈ አለም በሚመለከት መነሾ የግዴታ ይኖረዋል የሚል የራሱን ግምታዊ ፅንሰ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል። ይህም ያለ ምክንያት አልነበረም። በዚያን ወቅት በተቃራኒነትም ሆነ በተፎካካሪነት ይቀርብ የነበረው የሊቃውንቱ ፍሬድ ሆይልና የሙያ ባልደረቦቹ ስቴዲ ስቴት ሞደል የተሰኘውና የሚታወቀው ነበር። በሁለቱ ፅንፀ ሃሳቦቹ ላይ የሚደረጉት የምርምር ጥናቶች እየተካሄዱ በነበሩበት ወቅት በለሜትር ቀርቦ የነበረውን የመጀመሪያውን ፅንሰ ሃሳብ ማለትም ቋሚነት የሌለው አፅናፈ አለምን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ መረጃ በ1964 ዓ.ም. በአርኖልድ ፒ. ፔንሲያስና ሮበርት ዉድሮው ዊልሰን በተባሉ ሊቃውንቶች በድንገተኝነት ያገኙት ባክግራዉንድ ሬዲዬሽንስ የሞገድ ጨረር መገኘትና ለዚህም ውጤታቸው የኖቬል ሽልማት በማግኘት የእውቅና ማዕረግ መቸራቸው የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ ምርምር ሂደቱንና የቆመበትን መሰረተ ድንጋይ የበለጠ እያጠናከረው ይሄዳል።

በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ሊቃውንቶች እውቅና ያገኘው ኮስሞሎጊያዊ የሞዴል ቀመር እንደሚገልፀውም የአፅናፈ አለም መፈጠር መነሾ የሆነው ቀመር ቁስ አካል፣ ሕዋና ጊዜ በእምቅታ በአንድ ላይ የተዋቀሩበት ሁናቴ በመገኘቱ ብቻ አላቆመም። በዚህም ውጤት ላይ በመመርኮዝና በዘመናዊ ሳተላይት (WMPD) በመደገፍ በተደረገው ጥናታዊ ምርምር የተገኘው ውጤትም የእፅናፈ አለም እድሜ 13.7 ሚሊያርድ አመት እንደሆነ ለማረጋገጥ የተቻለበት ፅንሰ ሃሳብ ነው። በ 1992 ዓ.ም ደግሞ በባክግራውንድ ሬዲዬሽን ላይ እንዲሁ በሳተላይት የተደገፈ ምርምር የተገኘው ውጤት እንደሚያመላክተው በለሜትረ ቀርቦ የነበረውን አፅናፈ አለም መነሾ አለው የሚለውን የፍንዳታ ግምታዊ አስተሳሰቡ ትክክለኛነት ለመረጃው በርዕሱ የተሰማሩ ተመራማሪዎች ቁጥር በእጅጉ መበራከት የበለጠ ግለት እየጨመረ መሄዱ ተቀናቃኞቹ ሳይቀሩ መስካሪ ሆነው ሊቀርቡ መገደዳቸው የሚያመላክተው ይህንኑ እንጂ ሌላ አልነበርም፣ አይደለምም።

ማጠቃለያ

እንግዲህ የጋሞው ፈለገን በመከተል የታላቁ ፍንዳታ ፅንሀሳብን ለማግኘት ሊቃውንቶቹ የተጓዙበት ሂደት በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት አፅናፈ አለም ተነስተን በምንባዊ እሳቤ የኋሊት በማሰብ የተገኘው ግንዛቤ የዛሬ 15 ሚሊያርድ አመት የነበረው የአፅናፈ አለም መነሾው እጅግ ከፍተኛ እፍግታና እንዲሁም ከፍተኛ ሙቀት እንደነበረው ተረድተናል። ቀጥለንም በዚህ ሁናቴ ቁስ አካላት ፅንሳቸው ለነበሩት የተለያዩ ጥቃቅን ንጥረ አካላት (ኤሌክትሮን፣ ፕሮቶን፣ አፕ ና ዳውን ኳርክስ የተሰኙት እንዲሁም ተቃራኒ ጠባይ ካላቸው አቻዎቻቸው ጋር በሚያደርጉት ፍትጊያ ደግሞ የአይንሽታይንን ቀመር በመጠቀም የተገነዘብነው ኢነርጂ ሊፈጠር እንደሚችል አውቀናል። ይህ ሊቃውንቶቹ ፕላዝማ ብለው በሚጠሩት ውስጥ ጥቃቅን ንጥረ አካላት ታምቀው የሚገኙበት ፣ ሬዲዬሽን (የኃይል ፍንጣቂ ከተፀነሰበት ቦታ ተነስቶ በጉዞው እክል እስካላጋጠመው ድረስ በቀጥታ የሚጓዝ) ያለበት፣ አራቱ የተፈጥሮ ሕጎች ምንም አይነት ተፅዕኖ ማሳደር የማይችሉበት እንደነበርም ተረድተናል። ጨለማ የሰፈነበት ሁናቴ ነበር ማለት ነው።

የታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሃሳብ በጣም ጥቃቅን ንጥረ አካላት በሚገኙበት አለም ውስጥ ተፈጥሯቸውንና የሚያደርጉትን የርስ በርስ ግንኙነት በምርምር የተገኘውን ውጤት በትላልቅ ጋላክሲዎችም ጋር አገናኝቶ ጥናታዊ ምርምር ለማደርግና ለማወቅ ይቻላል የሚለውን ሃሳብ ሰንቀው የተነሱት ሊቃውንቶች በርግጥም ጥረታቸው ተሳክቶ የሚያስደንቁ እውቅናዎችን ለመላበስ በቅተዋል። ቀደም ብለን የጠቀስነው ሊቃውንቱ ጋሞው ቀደም ብሎ ካቀረበው ምናባዊ በተቃራኒው በማሰላሰል ምን ሊከሰት እንደሚችል ረጅም ጊዜያትን የፈጀ ምርምር ከሙያ ጓደኛው ራልፍ አልፈር ጋር በመተባበር ያገኙት ውጤት በሃይድሮጅንና በሄሊየም መካከል H2/He ሊኖር የሚችለው የዝምድና ግንኙነት አስር ለአንድ እንደሆነ ነበር። በተጨባጭ የተገኘውም ውጤት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነበር። ራልፍ አልፈር ከሌላ የሙያ ባልደረባው ጋር በመሆን ያደረገው ጥናታዊ ምርምር ቁስ አካላት እጅግ በጣም ከፍተኛ ሙቀት በሚላበሱበት ወቅት ከፕላዝማ ውጭ ሌላ ሊሆን እንደማይችል መግለፁና በተጨባጭም መረጋገጡ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከታቸው የሚጠቀሱ ናቸው።

በመጨረሻም ምስጋና ለሊቃውንቱ ፕላንክ ይሁንና ሌሎች ሊቃውንቶች ወደኋሊት በማሰብ ያለሙትን የጥቃቅን ንጥረ አካላት ምንነትን የገለፀበት ቀመር ማግኘቱ

(ርዝመቷን = 1,61 . 10 -33 cm፣

ክብደቷን = 2.18 10-5 g፣

ሙቀቷን = 1,41 .10 32 0Kelvin እንዲሁም የ እፍግታው መጠኗ

= 5,2 1093 g/cm3 ) ለታላቁ ፍንዳታ ፅንሰ ሀሳብ መዳበር እጅግ ባለውለታ ሊሆን የበቃ ሊቃውንት ነበር።

የአፅናፈ አለም መስፋፋት ከላይ እንደተገለጸው በጣም እጅግ በጣም ፍርስራሽ ሴኮንዶች ውስጥ ጀምሮ ያለውን ሂደት በተመለከተ የአንባቢን ጊዜ አጉል መሻማት፣ የዚህን መጣጥፍ ኢላማ የሚጋፋና የመስኩን ባለሙያዎች በዋናነት የሚመለከት በመሆኑ በስምነት ደረጃዎች የተከፈለና እያንዳንዳቸውም በጥልቀት መታየት ያለባቸው መሆኑ ጠቅሶ ይህንን መጣጥፍ መደምደሙ አግባብነት ያለው ይሆናል። አንባቢያን ወደፊት መቀጠል ከፈለጉ የተለያዩ ድረገፆችንና የኮስሞሎጂ መፅሃፍቶችን ቢያገላብጡ መልካም ይሆናል። በመጨረሻም በፅንሰ ሃሳቡ ላይ የምናቀርበው ትችት ይህ ማክተሚያው ነውና ሽፈራዉ ሉሉና እንዳሻው ቡናሬ መሰሎችም እንዲሁ ይሰሙ እንደሆነ በጥልቀት እንዲያስቡበት አንድ ምክር ልለግሳቸው። በፈላጭ ቆራጭነት ላይ የተመሰረተ እምነትና በምርምርና አርቆ አስተዋይነት በተላበሰ የተፈጥሮ ሳይንስ መካከል መሰረታዊ ልዩነት አለ። ተፈጥሮ ሳይንስ ያሸንፋል የሚሰራ ነውና!! በጥሞና አስተውሉት።

የመጨረሻውና በክፍል 5 እስከምንገናኝ ድረስ

መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!!
https://amharic-zehabesha.com/archives/176458

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...