Saturday, August 13, 2022

እንዳንደናገር እንጠንቀቅ፣ - ክገብረ አማኑኤል
የአገራችን ህዝብ አሁን ባለው አገዛዝና በወያኔ ዘመን ምን ያህል የከፋ ሥቃይና መከራ እንደተፈራረቀበት ምስክር መጥራት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። በየጊዜው ለደረሰው የህዝብ ጭፍጨፋና ዘር ማጥፋት መከለያ የሚሆኑ ጉዳዮች እየተጋረጡ፣ ህዝቡ የደረሰውን መከራና እልቂት እየረሳ በተፈበረኩ ጉዳዮች ላይ መጠመድ በዘመኑ አባባል ‘’አጀንዳ መሥጠት’’ የመንግሥታችን የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል። ህዝብ ካልተከፋፈለ ለጸረ-ህዝብ አገዛዝ አይመችም። በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ አንዱ ሲነካ ሌላውም ራሱ እንደተነካ እንደሚሰማው አምናለሁ። ሆኖም በየዘመናቱ ከመንግስት በደረሰበት ከፍተኛ ጥቃትና ፈተና የተነሳ ሃይሉን ለመጠቀም ለመሰባሰብ እንዳይችል በመደረጉ ጉዞውንና ትግሉን ከባድ አድርጎታል። ሆኖም ምንዜም ከፈጣሪ በታች፣ ህዝብ አሽናፊ መሆኑን መጠራጠር ደካማነት ነው። የብዙሃኑ የአገራችን ህዝብ ሥነ-ልቡና አንድ በመሆኑ ባንድነት ቆሞ ያለውን አረመኒያዊ ሥራዓት እንደሚጥል ተስፋችን ጽኑ ነው።

በቅርቡ በወለጋ የተካሄደው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አንዲረሳሳ ለማድረግ ከተፈጠሩ ማደናገሪያዎች መካከል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰወር፣ የኮንዶሚኒየም ጉዳይና የሙሰኝነት ጉዳይ ጥቂቶቹ ይመስሉኛል። በወለጋ ለተካሄደው ጭፍጨፋና የንጹሃን ህጻናት፣ እናቶች፣ እህቶችና ወንድሞች ነፍስ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም ቀደም ይህ መንግስት ወደሥልጣን ከመጣበት ዘመን ጀምሮ የተጨፈጨፉትን ወኖቻችንን የምንረሳበት ህሊና የለንም። መንግስትና ተባባሪዎቹ፣ እነዚህን መከራዎች ከህዝቡ ህሊና ለመፋቅና ለዳግም ጭፍጨፋ ለማዘጋጀት የሚደረገው ማደናገሪያ የበለጠ ድርጊቱ የማን ሃላፊነት እንደሆነ እያረጋገጠልን ነው ለማለት ይቻላል።

ይህ ሰዓት ከዚህ የዕልቂት አዙሪት የምንወጣበትንና፣ የህዝብና የግለሰብን መብት የሚከበርበትን ዕውነተኛ ሥርዓት ለማምጣት ከፈጣሪ በታች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ትግል የምናደርግበት ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በአስተዋይነቱ መሪዎቹን በብዙ ርቀት ቀድሞ የሚመራ መሆኑ ሃቅ ነው። ህዝቡ ምንጊዜም የአገሩን አንድነት ለማስጠበቅ፣ መብቱን በእኩልነት ለማስከበር፣ በኢኮኖሚ ዕድገት አገሩን ለማራመድ ለሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረት ለሚደረግ ለውጥ ምንግዜም ዝግጁ መሆኑን  አምናለሁ። ሆኖም ባንጻሩ በአገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ምንያህል ለዚህ ብቁ ህዝብ የሚበጅ ዘላቂ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማምጣት የሚያስችል የአመራር ብቃትና ዘመኑን የሚመጥን የትግል ሥልት እየተከተሉ ነው የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያለበት ጊዜ ነው።

ቀደም ባለው ጽሁፌ ላይ ለመወያያ  እንዲሆን  በሚል ሊታዩ የሚገባቸው ሠላማዊ የትግል ስልቶችን ለመጠቆም ካነሳኋቸው ነጥቦች መካከል ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገባቸው መካከል የሚከተሉት አጽኖት እንዲሰጣቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። በዚህ ረገድ በውጪ ከሚኖሩና ከዕውነት ተቃዋሚዎች የበሰለ አመራር ይጠበቃል። ወቅቱ የትግል ስልቶች በጥልቀት ታይተው መኧሰን ያለባቸው ስልሆኑ ለውይይት አንዲቅርቡና ሌሎች የረቀቁ ስልቶች ሊተለሙ አንደሚገባ ባጽኖት ሊታሰብበት ይገባል።

- ተንሰራፍቶ ያለውን የዘረኝነት ፖለቲካ ከኢትዮጵያ በስተቀር በየትኛውም አገር በህገመንግስት ሰፍሮና ተንሰራፍቶ እንደማይገኝ  ለተቀረው ዓለምም የጥፋት አርዓያ እንዳይሆን በዓለም መድረክ ማጋለጥና እንዲወገዝ ማድረግ፣

- በሥራ ላይ ያሉ የሰብዓዊ መብቶችና ሌሎች ዓለማቀፋዊ ህጎች በኢትዮጵያ እየተጣሱ መሆናቸውን፣ ይልቁንም የሰው ልጅ የመኖር መብት በኢትዮጵያው የዘረኝነት ሥርዓት በአደባባይ የተጣሰ መሆኑንና ሰዎች በየዕለቱ በመንግስት እውቅና እየተገደሉ መሆኑን በማያወላዳ ማስረጃ አስደግፎ በማቅረብ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያን መንግስት በይፋ መክሰስ፣ ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ዓለማቀፍ ክሶችን ማጠንከርና መቀጠል፣

- አገርን የማዳኑን ሥራ ወዳጅ ከሆኑ ሌሎች አገሮች ጋር በመተባባር መሥራት፤ በዚህም ላይ ተቃዋሚዎች ሃይላቸውን በማተባበር የሠለጠነና የረቀቀ ፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ስልትን በመጠቀም መሠረታዊ ለውጥ አንዲመጣ ከህዝቡ ጋር በመሆንና በማስተባበር ጠንካራና ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትና ከተባባሪ የውጭ ሃይሎች ጋር በመሥራት ተግባራዊነቱ እንዲረጋገጥ ማድረግ

እነዚህን የትግል ስልቶች በውጪ አገር ከሚኖር ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ሊያካሄዱ የሚገባ ሲሆን፣ በቅርቡ በእንግሊዝ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጭፍጨፋውን በመቃወም በማድረግ ላይ ያሉት የረሃብ አድማ ዓይነተኛ ታላቅ ምሳሌነት ያለው ስልት መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ነው።

አሁን ለማስታወስ የምወደው ህዝቡና እውነተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደረግ ስላለበት ሁኔታ መወያየትና አቅጣጫን የማመላከት ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው ነው፤ በመሆኑም፣ በሌላ በኩል እውነተኛ ኢትዮጵያዊነትንና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማምጣት ቁርጠኛ የሆኑ ፓርቲዎች ሊያስቡበት በሚከተሉት የትግል ስልቶችን በመቀየስ በሳል አመራር ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል።

- በሰጥቶ መቀበል መርህ በመጠቀም ዓለማቀፍ ጋር ተባብሮ በመስራት በኢትዮጵያ ውስጥ በቅድሚያ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አንዲቆም ማድረግ፤

- በተቻለ መጠን ይህ መንግስት የሚያገኛቸውን ርዳታዎችና ብድሮች ለማስቆም ያላሰለሰ ትግል ማድረግ በኢኮኖሚ፣ ያለውን ሥርዓት ማዳከምና ለዘረፋና ለስርቆት የሚውለውን ሃብት ማሳጣት፣

- በአገር ውስጥ በሚገባ የጠራ የጸረ-ዘረኝነት ሃሳብና አስተምህሮ በተጠናና ለሁሉ ሊዳረስ በሚችል መልክ ማስፋፋት ለዚህም የላቀ ተዓማኒነት ያላቸው የራዲዮ ጣቢያዎችንና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መጠቀም፣

- ኢትዮጵያ ህዝብ ከፖለቲከኞች ወጥመድ ወጥቶ በአገር ውስጥ የሚካሄደው ትግል በሁሉም የኣገራችን ክፍሎች ማራመድ እንዲቻል፣ በተቻለ መጠን የሚሰጠው ትምህርት ህዝባዊ ይዘት ያለው፣ ሆኖ በተለያዩ ቋንቋዎች አንዲሰጥ ማድረግ፤

- እውነተኛውን የኢትዮጵያን ማንነት የሚያከብሩና የሚያራምዱ ታዋቂ አንጋፋ ሰዎችን ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና አሜሪካ ወዘተ. በማስተባበር የትግሉ አጋርና ጠበቃ አንዲሆኑ ማድረግ፣

ከፈጣሪ በታች፣ በተቀናጀ መንገድ በሚደረግ ዘመኑን የሚመጥን ትግል፤  በማካሄድ ባገራችን ውስጥ በቅኝ አገዛዝ ኢትዮጵያን የያዛትን የዘረኝነት ሥርዓት በማያድግም ሁኔታ ልንለውጠው ይገባል።

እውነት ያሸንፋል!

ኢትዮጵያ ባንድነቷ ጸንታ ትኖራለች!

የንጹሃንን ደም በከንቱ ያፈሰሱ በህዝብም በፈጣሪም ፊት ይጠየቃሉ!

ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ያድን! ይባርካትም!

ገብረ አማኑኤል
https://amharic-zehabesha.com/archives/176588

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...