Wednesday, August 24, 2022

አዲስ አበባ የኹሉምና ለኹሉም እንጂ የጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ማስፈጻሚያ አይደለችም

አዲስ አበባ የኹሉምና ለኹሉም እንጂ የጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ማስፈጻሚያ አይደለችም
ባለቤት አልባነት ተጫጭኗት እንደዛሬው ሳይሆን “አዲስ አበባ” ሲባል የሰላም ከተማነቷ፣ እንደነ ኒዮርክ፣ ጀኔቫ፣… ከኸሉም የዓለም ማዕዘናት መሪዎች ተሰባስበው ጉዳያቸውን የሚመክሩባት፣ አፍሪካውያን በባርበት ቀንበር ሲማቅቁ የነጻነታቸው ቀንድል ሆና የትግሉን ፊደል ሀ ሁ… ያስቆጠረች ከተማ ነበረች። አዲስ አበባ ጎልታ የጣችው  በሕንጻዋ ሰማይ ጠቀስነት፣ በቪላዎቿ ዐይነ ገብነት፣ በመንገዶቿ ማማር፣ በቴክኖሎጂ ርቀቷ ሳይሆን በነዋሪዎቹ እንግዳ ተቀባይነትና አይበገሬነት፣ በሰላማዊነቷ፣ በተስማሚው የአየር ንብረቷና በቁርጠኛ መሪዎቿ ነበር። ቀደም ያለውን ነገር ትተን በ1879 ዓ.ም በብርሃናተ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ከተቆረቆረች ወዲህ እንኳን አዲስ አበባ እንደ ስሟ እንድታብብ ጠጠር ያልወረወረ ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ኹሉም ኢትዮጵያዊ  በነባርነት ኖሮባታል፣ ኹሉም ዋና ከተማውን ላለማስደፈር ተዋድቆላታል፣ ኹሉም ሠርቷታል እና “ኹሉም” በኩራት “የእኔ” ይላታል፡፡ ዛሬ ላይ አዲስ አበባ አይደለም የመላው ኢትዮጵያውያን የመላው አፍሪካውያን ዋና ከተማ ሁናለች፡፡

ወደጥልቁ ታሪክ ትንተና ሳንገባ በሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በ1987 ዓ.ም የጸደቀው ሕገ መንግስት እንኳን አዲስ አበባ በቻርተር እንድትተዳደር ከደነገገ በኋላ በአጠቃላይ 54,000 (ሃምሳ አራት ሺህ) ሄክታር ስፋት ነበራት፡፡ ይህም አዲስ አበባ መስተዳደር ውስጥ ባሉ 10 ክ/ከተሞችን እና 23 የዙሪያ ቀበሌዎችን ጨምሮ ነው፡፡ ይሄ አኃዝ በ 1995 ዓ.ም 10ኛው የከተማዋ መሪ እቅድ ሲጸድቅ ወደ 52,000 (ሃምሳ ኹለት ሺህ) ሄክታር ዝቅ ብሏል፡፡ ይሄ ማለት ኹለት ልደታ ክ/ከተማን የሚያህሉ ክ/ከተሞች ጠፍተውባታል፡፡ ምን አልባት ዓለም ላይ ስለሌሎች ነጻነት እተዋደቀች ይህን ያህል ሙዳ ሥጋ(መሬት) የጠፋባት ብቸኛ ከተማ ሳትሆን አትቀርም፡፡ አኹን ላይ ይሄ አኃዝ በስንት ሺህ ሄክታር ቀንሶ እንደሆነ ማን ያውቃል?! ይባስ ብሎ አኹን አኹን ከነ “ቦሰት” ወረዳም ጋር እየተነጻተረች ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠን “ልዩ ጥቅም” እጅግ በመለጠጥ ከተማዋን የመጠቅለል ወይም ጥቅም አልባ ማድረግ በሚመስል አካሄድ እተሠራ ያለው ደባ ከተማይቱን ከሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ጋር ተጋግዞ ለከፋ አደጋ እያጋለጣት ነው።

ባልተገባ መንገድና ላልተገባቸው መታወቂያ ይታደላል(ዴሞግራፊ ቅየራ ብለውታል)፣ ዘረፋና ግድያው ተባብሷል፣ ነዋሪዎች በሕገወጦች ይዘረፋሉ፣ ማቆሚያ በሌለው የኑሮ ውድነት ይሰቃያሉ፣ የከተማይቱ ታሪካዊ ቅርሶች በማን አለብኝነት ይፈርሳሉ፣ ሕዝብ ከሌለው ላይ እየቆጠበ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒዬሞች)  ለፖለቲካ ሸሪኮች እንደግል ንብረት ይታደላሉ፣ ከሕግ ውጭ የአጎራባች ክልል ሰንደቅ ዓላማን በትምህርት ቤቶች በመስቀል፣ የክልሉን መዝሙር ዘምሩ በሚል ትምህርት ቤቶችን የአምባጓሮ መፍለቂያ ሆነዋል፤ ከአጎራባች ክልሎች ሰዎች ወደከተማዋ እንዳይገቡ ዘብ አቁመዋል(በብቸኛ ተቆርቋሪነት የሚያጠቡ እናቶችንና አዛውንቶች “ወደየመጣችሁበት ተመለሱ” ተብለዋል)፣ ከዘር ፍጅት ተርፈው በእግሬ አውጭኝ ከተማዋ የደረሱ አቅመ ደካሞች በአንድ ፊሽካ ከከተማዋ ተባረዋል፡፡ይህን ሕገወጥ አሠራር የሚቃወሙትን አካላት ከሕዝብ ጋር ለማጣለትና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደረደረውንና ከተማዋን ለመገንባት ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር የራሱን ደማቅ አሻራ ያኖረውን የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ለማጋጨት ጸብ አጫሪ ንግግሮችን ሆነ ብሎ በመናገር በግልጽ ቅስቀሳ እየተደረገ ይገኛል። ጊዜያዊ ስልጣንን መከታ አድርገው መሬት እየሸጡ እየለወጡ መኪና ሲቀያይሩ፣ ጠጅና ጮማ ሲያወራርዱ ያልጠሩትን ሕዝብ ክፉ ሥራቸው ሲጋለጥ መሸጎጫ በማድረግ ከጮማው ጠልተውት ከሞታቸው ይጠሩታል፡፡ “ላይጠግን አይሠብርም እንዲሉ” ሕዝብ ዘላቂ ጥቅሙንና ዝምድናውን ያውቃልና አይቷቸዋል፣ እምቢ ብሏቸዋልም፡፡

ይህ ኹሉ ደባ አልበቃ ብሎ ሕዝብ የኑሮው ውድነት መቸ ይቀልልኛል? ለልጆቼ ትምህርት ቤት ምን ልክፈል? የናረውን ነዳጅ ወጪ እንዴት ልሸፍን? ለመብራት ከየት አምጥቸ ልክፈል? ትራንስፖርት ወጪዬን እንዴት ልሸፍን? አንጀቴን አሥሬ ያስተማርኩት ልጄ መቸ ይቀጠርልኝ ይሆን? አልበላም ብዬ በቆጠብኳት ኮንዶሞኒዬም መቸ ይደርሰኝ ይሆን? እያለ ሲያብሰለስል ምን አልባትም የወሰን ማካለል በመባለት የመጨረሻው ካርድ ተመዞለታል፤  የከተማዋን ነዋሪዎች አልፎም መላው ኢትዮጵያውያንን የሚያውክ አካሄድ በገዢው መንግስት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እየተፈጸመ ነው። ውሳኔው የቦታ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚታይበት መንገድም ፈጽሞ ስሕተት ሲሆን ከቦታ በዘለለ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱን ነዋሪዎች መብት የሚጥስ ድርጊት ነው። የአስተዳደር ወሰን ግጭቶችንን ጨምሮ ሌሎች የጸብ መነሻና የፍትሕ ብሎም የሰላም እጦት ምክንያት የሆኑ መሰል ጉዳዮች በሕዝባዊ ውይይት፣ በተጀመረው ሀገራዊ መግባባት ሥር መፍታት ሲገባ በገዢው ፓርቲ እየተፈጸመ ያለው ሕገወጥ ድርጊት ሀገራችንን ከድጡ ወደማጡ የሚያስገባ ተግባር መሆኑን ተገንዝበናል። በሌላ በኩል አዲስ አበባ የኹሉምና ለኹሉም ሳትሆን የግለሰቦች መጫዎቻ ካርድ ሆናለች፡፡ ስለሆነም፡-

በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ይካሔዳል የተባለው ሂደቱን ያልጠበቀ፣ ሕግን ያልተከተለ የወሰን ማካለል በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን፡፡

ማከለሉ ጊዜው ነው ከተባለ እንኳን ሕዝብ በውል ተወያይቶ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናቱን እንዲያቀርብና በግልጽነት ወደተግባር እንዲገባ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

የመንግስት ባለስልጠናት ሕዝቡን ወደግጭት ከሚመሩ እንቅስቃሴዎችና ንግግሮች እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ውስጥ ለሚሠራቸው የትኛውም በጎ ሥራዎች ድጋፍና እውቅና ያለን ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የከተማዋ መገለጫና ምንነት የሆኑ፣ ያለፈው ትውልድ አሻራ ማሳያ ታሪካዊ ቅርሶችን ከማፍረስ እንዲቆጠብ በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡

በከተማዋ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ የጠራራ ጸሐይ ዝርፊያ፣ ግድያና የመሬት ቅርምት በየኔነትና በዘላቂነት እንዲፈቱ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

የ1997 ዓ.ም የባለሦስት መኝታ ቤት የጋራ መኖሪያ ቆጣቢዎች ላይ የተፈጸመባቸው በደል ፍትሕ እንዲሰጠው በጥብቅ እናሳስባለን።

በመጨረሻም የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ እንደወትሮው ኹሉ የየአካባቢህን እንቅስቃሴ በትኩረት እንድትከታተል፣ መረጃ እንድታቀብል ብሎም ዘብ እንድትቆም ወንድማዊ ጥሪያችንን እናስተላለፋልን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

 

እናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ

ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
https://amharic-zehabesha.com/archives/176705

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...