Wednesday, August 17, 2022

የኢትዮጵያ የለዉጥ ጉዞ የዲያስፖራዉ ትዝብቶችና አስተያየቶች - ለማ ደስታ ከኖርዌይ
ነሐሴ 9/2014

በወርሃ ሐምሌ ከሶስት ዓመት ከአጋማሽ የዉጪ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ቤተሰብ ለመጠየቅና ሀገርን ለማየት መልካም አጋጣሚ አግኝተን ነበር። በአዲስ አበባና በማዕከላዊ የደቡብ አከባቢ ( በሀዲያ ዞን ) የአምስት ሳምንታት ቆይታ አድርገን ወደ ዉጪ ሀገር ተመልሰናል። በዚህ ጽሁፍ ወደሀገር ቤት ለመምጣት ካሰብን ጊዜ ጀምሮ የነበረዉንና፣ ወደዚህም መጥተን የታዘብናቸውን መልካም ለዉጦችን፣ አጓጊ ጅማሬዎችንና የታዘብናዉን እጅግ አናዳጅ ጉዳዮችን በማንሳት በቀጣይ የእርምት እርምጃዎች ለሚወስዱ ሀላፊነት ላላቸው አካላትም ይሁን ለህዝቡ እይታዎቻችንን ለማካፋል ነዉ። ጽሁፉም በሀገር ቤት የሚታዩትን ለዉጦችና ችግሮች በዲያስፖራ ልምድና እይታ በማየት ገንቢ፣ እዉቀት ተኮርና ዘለቄታዊ ለዉጥ ለማየት የመነጨ እንደሆነ ከሚል ግንዘቤ ሊታይ ይገባል።

ከኮሮና በኋለ ወደ ትዉልድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ቤተሰብ ጥየቃና ሀገር ለማየት እንደምንሄድ ሲሰሙ ግራ የተጋቡ፣ ፍርሃታችዉን ሳይዋሹ የነገሩንና እቅዳችንን እንዲናጤነዉ የመከሩን ወዳጆች ነበሩን። የሌሎች ሀገር ዜጎች ብቻ ሳይሆኑን ትዉልደ ኢትዮጵያውያንን በዚህ ወቅት ልጆችንን ይዞ ሀገር ቤት መምጣት የማይመከር እንደሆነ አስታዉሰውን ነበር። ወደ ሀገር ቤት ጉዞ ከማድረጋችንን ጥቂት ቀናት በፊት በወለጋ የነበረዉ ሁኔታ፣ በደቡብም በምስራቅም ይሰማ የነበረው ነገር፣ በየማህበራዊ ሜዲያዉ የሚዘወተረዉ የጦርነት ስጋት ወሬ ሁሉ ነገሩ በማስፈራራት የተመላ ነበር። እኛ ግን ሞትም ቢሆን ከቤተሰባችን ጋርና በሀገራችን ነዉ ብለን የትኛዉም ማስፈራሪያ ሀሳባችንን ሳያስለዉጠን፣ እንደተወራበት ሰይሆን ሰላማዊ ወደሆነ ሀገር መጥተን መልካም ጊዜ አሳልፈናል። በእርግጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋዉረን ስላላየን ለሁሉም ሰዉ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በነጻነት መመላለስ ቀላል ነዉ ብሎ ለመናገር ይከብዳል። በተለይም ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ አንጻር በየሰፈሩ ከህግ አግባብ ዉጪ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉ፣ በዘር፣ በቋንቋና በሀይማኖት አድልዎ የሚያደርጉ፣ ጥቃት የሚያደርሱ እንደማይጠፉ መገመት ይቻላል። ነገር ግን ሀብታም ሀገሮች የራሳቸውን ጥቅም ለማረጋገጥና ሀገራችንን ለማራከስ የሚያሰራጩትን የጸጥታና የደህነነት የስጋት መልእክቶችን የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ጠላቶች በማህበራዊ ሚድያ በማራገብ የፈጠሩት የተሳሰታና የተጋነነ የስጋት መልእክት የሀገራችንን ገጽታ ማዛባቱ በግልጽ የሚታይ ሆኗል። ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት

የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስዳቸዉ ጸጥታና ሰላምን የማረጋጋጥ ተግባር ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፣ ህዝቡም ስለሀገሩ ሰላም፣ ደህንነትና ጸጥታ ከአፍራሽ ሀይሎች ሙሾ መስማቱን ትቶ፣ በየአካባቢዉ ጸጥታውን፣ ሰላሙን፣ ህጉንና ስርዓቱን በማረጋጋጡ ረገድ ሀላፊነቱን መወጣት አለበት። ሀገሮች የፈረሱት፣ የሚፈርሱት፣ ስርዓተአልበኝነት የሚነግሰዉ ህዝብ ሀላፊነቱን ዘንግቶ አሊያም ቸል ቢሎ፣ አይመለከተኝም የመንግስት ሀላፊነት ነዉ በሚልበት ወቅትና ቦታ ነዉ። ምንም እንኳን የደቦ ፍርድ፣ ህግን በደቦ ( mob justice) ለማስፈጸም መሞከር ተገቢ ባይሆንም የሀገርን ጸጥታ፣ ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ረገድ ህዝብ መንግስት መሆኑን መረሳት የለበትም። እኔ በምኖርበት ሀገር ሁሉም ለሀገሩ ዘብ ነዉ። ህግ አስከባሪ ኖረ አለኖረ፣ ሰዉ ሁሉ ህግ ያከብራል።ያስከብራልም። ይህ የሀገሪቱ ህዝብ ያልተጻፈ ግን ሁሉም የሚያከብረዉ የስነስርዓት ህግ ነዉ። ህግ የሚጥስና የጋራ ሀብትን አለአግባብ ለራሱ ለማድረግ የሚሞክር ቢኖር ማንም ሰዉ ለምን ታደርጋለህ ብሎ ይጠይቃል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለህግ አካላት ደዉሎ ያስታዉቃል። በሀገራችን የሚሰማዉ የመንገድ ማብራት መስመር፣ የባቡር መሰመር ወዘተ የህዝብና የሀገር ሃብት መሰረቅ፣ የጋራ መሬቶች፣ የከተማ አረንጓዴ ስፍራዎች በሌሊት መቀራመት፣ ሁሉም የመኪና አሽከርካሪ ህግ ሳያከብር መንዳት፣ በግልና በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ወረፋ ጠብቆ አለመስተናገድ የመሳሳሉ የስነስርዓት ህጎች ቸል መባሉ የሀገርን ገጽታ ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ኑሮ አቃዉሷል።

ኢትዮጵያ እንደሀገር፣ ኢትዮጵያዊያን እንደ ህዝብ ብዙ የሚያኮሩ ታሪኮች፣ ድሎችና ገድሎች ባለቤት ነን። ሰፊ ሀገር፣ ብዙ ህዝብ፣ እምቅ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ሃብት ያለን ሀገር ነን። የፍትሓዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከተፈቱ፣ የእዉቀትና የክህሎት ሃብት ከታከለበት በአጭር ጊዜ የድህነት ታሪካችን ተቀይሮ በብልጽግና እንደሚተካ የሚያሰዩ ጅማሮዎችን ተዝበናል። በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት ትላልቅ ፓርኮች፣መጻሕፍት ቤቶች፣ ባንኮች፣ የንግድና የመንግስት ድርጅት ህንጻዎች፣ የአምልኮ ስፍራዎች፣ ስታዲየሞች በእርግጥም አዲስ አበባ በአዲስ መልክ እያበበችና ተስፋ ያላት መሆኑን የሚያሳይ ሆኖ አግኝተናል። ሁሉንም ለመጎብኘት ጊዜ ባናገኝም ከአዲስ አበባ ዉጪ ያሉትን የገበታ ለሀገር ፕሮጄክቶች፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በተለያዩ ክልሎች የተገነቡ የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ የመስኖ ፕሮጄክቶች፣ የከተሞች ማስዋብ ፕሮጄክቶች፣ የእንዱስትሪ ፓርኮች፣ በግንባታ ላይ ያሉ መንገዶችና የፍጥነት መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዪኒቨርሲትዎች፣ ሆስፒታሎች፣ በመላዉ ሀገሪቱ የተቀጣጠለዉ የአረንጓዴ አሻራ ሀገርን መልሶ የማልበስ ትልምና በቅርቡም ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው በምግብ እህል ራስን የመቻልና ግብርናዉን የማዘመን እርምጃዎች ተደምሮ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታ በማታዉቀዉ ሁለንተናዊ ልማትና የለዉጥ ጎዳና ላይ መሆኗን መካድ

አይቻልም። የሚያነድደዉ ግን ብዙ አስደናቂ እምርታዎች የታዩ ቢሆንም ህዝቡ ለዉጦችን የሚያይበት የተዛባ እይታ፣ የመገናኛ ብዙሃን የማስተዋወቅና የመንግስት አካላት የመረጃ አሰጣጥ ችግሮች መኖራቸዉ ነዉ። በአዲስ አበበ ከተማ ዉስጥ እየኖረ የተገነቡትን ነገሮች ያላየ፣ በወሬ የተዛባ መረጃ ይዞ የተቀመጠ ብዙ ህዝብ አለ። በአንዳንድ ቦታዎች የመግቢያ ዋጋ ምናልባት ዉድ እንኳን ቢሆን ለሁሉም በነጻ ክፍት የሆኑ እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ መስቀል አደባባይ፣ ቸርቸል ጎዳናና አብርሆት አሉ። የሚመለከታቸዉ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ሚድያ የተሰሩትን ስራዎች ለሀገር ዉስጥ፣ ለዲያስፖራ መህበረሰባችን፣ ለአህጉራችንና ብሎም ለአለም የማስተዋወቅ ትልቅ ሀላፊነት አለባቸዉ።

የባለፉት ዓመታት የሀገራችን ፈተና የሆነዉን ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም የገዛ ሀገሩን ከወጋዉ ከትሕነግ ጋር እንኳን ሰላም ለመፍጠር ዉይይት ለማካሄድ ዝግጅቶች ማኖሩ፣ በብዙ ሰብዓዊ ቀዉስ ዉስጥ ላለዉ ለትግራይ ክልል ህዝባችን የተሻለ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍሰትና የመልሶ ግንባታ ሀሳቦች እየተንሸራሸሩ መሆናቸዉ ተስፋ ሰጪ ነገር ነዉ። የፖለቲካዉን ባህል ለማስተካከልና ችግሮችን ዘለቄታዊነት ባለዉ መልኩ ለመፍታት እንዲቻልም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ዉይይቶች መጀመራቸዉ አገራችን በእርግጥም በብዙ እየተፈተነችና እያሸነፈች መሆኗን የሚያሳይ ነዉ። ሀገራዊ ምክክሩም አካታች ፣ ሀገር በቀል የሆነ፣ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ህዝቡ ተቀራራቢና በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያግዝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ምንም እንኳን የዘመናት ትግል ያመጣቸዉ ባለራዕይ መሪዎች ሌት ተቀን በመስራት በአጭር ጊዜ ትልልቅ ለዉጦችን በማምጣት የሀገራችን የብልጽግና ተስፋ ከግብ የማድረስ ቁርጠኝነት፣ ብቃትና አቅሙ ያለን መሆኑንን ቢያሳዩንም፣ አንዳንድ ያልተለወጡ፣ አሊያም የከፉ ጉዳዮች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ችግሮቻችን ለይተን ማወቅ፣ አጥርተንና አንጥረን መለየትም ለመፍትሔ ፍለጋ የመጀመሪያ መንገድ ነው። ከዚህ በመቀጠል የታዘብኩትን አንዳንድ ጉዳዮች በትንሹ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የመጀመሪያው ጉዳይ በአዲስ አበባ ይሁን ከዞንና በክልል፣ ህዝብ በሚበዛባቸዉ በከተሞች ይሁን በገጠር መንገዶች የሚታየዉ የሁሉም አይነት ተሽከርካሪ እንቅስቃሴና አጠቃላይ የትራፊክ ባህላችን ነዉ። በሚያሳዝንና በሚያስገርም ሁኔታ የአገራችን የትራፊክ ባህል ህግንና ስርዓትን በመጣስ፣ ለሰዉ ህይወት፣ ለንብረት ሀላፊነት የማይሰማዉ፣ የጉልበተኞች ገድሎ ማለፍ ሩጫ ነዉ። አንዳንድ ቦታ የመንገዶች ጥበት፣ መቆፋፈር ችግር ሲሆን፣ የተሻለ መንገድ ሲኖርም የባለመኪኖች ለከት የለሽ አነዳድ ምነው መንገዶቹ በተቆፋፋሩ የሚያሰኝ ነዉ። ችግሩ የሲኖትራኮችና የትልልቅ መኪኖች ብቻ ሳይሆን ትንንሾቹ ለሁለትና ሶስት እግር ተሽከርካሪዎችም ለከት የለሽነት ነዉ። ሁል ጊዜ በሁሉም ቦታ የትራፊክ ህግ አለማክበር፣ በተገቢዉ ቦታ ቅድሚያ አለመስጠት፣ ግልጽ የሆነ የመንገድ አቅጣጫ ጠቋሚ አለመኖር፣ ህግ ለማስከበር መንገድ ላይ የተሰማራዉ የህግ አካልም ህግን ለራስ ጥቅም ማግኛ ማዋሉ ከመንገዶች ችግርና ከተሽከርካሪዎቻችን ጉድለት ጋር ተደምሮ ኢትዮጵያ ሰዉ ከቤት ወጥቶ ጉዳዩን ፈጽሞ ቤቱ በሰላም ለመመለስ ዋስትና የሌለዉ ሀገር እያደረጋት ነዉ። ከዉጪ ሀገር የሚመጡ እንግዶችማ ኢትዮጵያ ዉስጥ መኪና መንዳት የማይታሰብ ነዉ። በትራፊክ የሚታየዉ የዘሬይቱ ኢትዮጵያ ህዝብ ጸባይ ነጻበራቅ ይሁን? ሁሉም ሌላዉን ረግጦ ለራሱ ለማለፍ ይፈልጋል። ይህንንም ስርዓት የሚያስይዝ አካል የለም። ሚዲያም እንኳን ይህንን ስር-የሰደደ ችግር በማጋለጥ እንዲሻሻል የበኩላቸዉ እያደረጉ አይደለም። የአዲስ አበባና የመላዉ ሀገሪቱ የትራፊክ ባህል ካልተለወጠ የሚጠፋዉ ህይወት፣ ሀብትና ንብረት፣በከንቱ የሚባከነዉ ጊዜ፣ የሀገር ገጽታ መልሶ ለመገንባት ብዙ ዋጋ ይጠይቃል።የትራንስፓርት ሴክተር በስራ ፈጠራ፣ በንግድ፣ በአጠቃላይ ሀገራዊ ልማት፣ ሰላምና እድገት ጉዞ ላይ ያለዉ ወሳኝነት ታይቶ፣ በአሽከርካሪነት ሙያ እዉቀትና ሰነስርዓት ዙርያ፣ በመንገዶች ግንባታ፣ ጥገና፣ ጥበቃና አጠቃቃም፣ በትራፊክ ህግና ስነስርዓት ማክበርና ማስከበር ሂደት ሁሉን ያሳተፈ ህይወት፣ ንብረትና ሀገር አድን የለዉጥ ንቅናቄ ማምጣት የግድ ይላል።

ሁለተኛዉና በቆይታችን የታዘብነዉ አስጨናቂ ጉዳይ ከኑሮ ዉድነት ጋር በአገሪቱ የሚታየዉ የትየለሌ የተራራቀዉ የጥቂት ሃብታሞችና የብዙ ደሆች የኑሮ ደረጅ ልዩነት ነዉ። ምንም እንኳን ከድሮ ጀምሮ ደሃና ሃብታም አብሮ የኖረበት ሀገር ቢሆንም በተለይ በከተሞች አከባቢ የተሻለ ገቢ ያለቸው ሰዎች ቤት በጣም በተጋነነ አደገኛ አጥር፣ በሰላትም የብርጭቆ ስባሪዎችን በኤሌክትሪክ ታጥሮ ሲታይ ህዝባችን ይህን ያህል ተጨካክኗል ለማለት ይጋብዛል። በአንጻሩ ግን ችግሩ ምናልባት የአጥር ገንቢዎችና ሻጮች የፈጥሩት የተጋነነ ስጋትና የተሳሳተ የጥበቃ እሳቤ ይሆናል ብሎ መደምደሙ ያዋጣ ይሆናል እንጂ በአደገኛ አጥር የታጠረ ቤት ሁሉ የወርቅ ክምችት ያለበት እንዳይደለ እሙን ነው። ይሁንና ግን እጥርና አደገኛ አጥርን ማብዛቱ የባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ኢፍትሓዊ የሃብት ክፍፍል፣ የመንግስትን ስልጣን ተጠቅሞ ሃብት የማጋበስ ሌብነት የወለደዉ ጭካኔና ንፉግነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ጥያቄው ጥቂቱ ሃብታም ቤቱን ለምን አጠረ፣ ቆለፈ ሳይሆን፣ ለሌሎች ያልተካፈለና በጥቂቶች እጅ የተሰበሰበ ሃብት ለሀገር ሰላምና ልማት ይሆናል ወይ የሚለዉ ነው። ከዚህ አንጻር ሃብት ያጋበሱ በሃብታቸው ስራ በመፍጠር፣ ግብር በመክፈል ለሌሎችም እንዲዳርስ ካላደረጉ እነርሱና ልጆቻቸዉ ተደላድለዉ ሌላዉ ተርቦ የሚኖርበት ሁኔታ አደገኛ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግስትም የልማት እቅዶቹ ምንም እንኳን አዲስ አበባ ላይ ብዙ ለዉጥ በማሳየት ለሌሎች ክልሎች አርአያ ማሳየት ፈታኝ አማራጭ ቢሆንም፣ ፈተናዉ ተቋቁሞ ቀጣዮች የልማት እቅዶች በመላዉ ሀገሪቱ በፍት ሃዊነት ተሰራጭተው በተለይ አልሚ በሆኑ የገጠሪቱ ክፍሎችም ይሁን መልማት ባለባቸዉ አከባቢዎች እንዲሁም ለመሰረተ ልማት አመቺ ላልሆኑ አካባቢዎችም ልዩ ትኩረት በመስጠት በሀገሪቱ የሚታየዉን የምጣኔ ሃብት ክፍፍል መራራቅ ማጥበብ ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ የሀይማኖቶች ሀገር ናት። ህዝቦቿም ፈጣሪን አክባሪና ፈሪ ናቸዉ። በቆይታችን የገረመን በኢትዮጵያ ዉስጥ ሀይማኖት የተሰጠዉ ትርጉምና ስፍራ ነዉ። ሀይማኖት ህዝብና ሀገርን ለማነጽ ወሳኝ ነዉ። ግን በታሪክ እንደሚታየዉ ደግሞ ሀይማኖት ፖለቲካዊ መሳሪያ ሲሆን፣ ለፖለቲካ ስልጣን ማግኛ፣ ጥፋት መሸፈኛ፣ ደጋፊ ማሰባሰቢያ፣ መቧደኛ ፣ የኔ ያንተ የሚባለዉን ድንበር ለማበጀት ሲዉል ከሀይማኖታዊ ሚናው ወጥቶ ፖላቲካዊ ዳራ ውስጥ ተዋናይ ይሆናል። ይኼ ማለት ሀይማኖት ፖለቲካዊ ሚና የለዉም፣ ፖለቲካኞችም ሀይማኖት ሊኖራቸው አይገባም ለማለት ሳይሆን የሀይማኖትና የፖለቲካ ለየቅልነት፣ ትብብርና ጤናማ ግንኙነት ስርዓት ከልተበጀለት ገደብ መተላለፉ፣ በሀማኖት ጥላ የፖለቲካ ግብ ለማስፈጸም በመሞከር ሀይማኖትን ማጉደፍ፣ ፖለቲካንም ማስነቀፍ ይመጣል። የኢትዮጵያ የሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነትና ግንኙነት ታሪካዊ ክስተቶችን ለሌላ ጊዜ ለዉይይት በይደር በማቆየት፣ እንደታዘብነው ከሆነ በኢትዮጵያ ዉስጥ ሀይማኖትና ሀይማኖተኞችን ከሚናቸዉ ወጥተው በብዙ ጉዳዮች ላይ ከሚገባዉ በላይ ጣልቃ እንዲገቡ የተፈቀደ ሁኔታ ያለ ይመስላል። ማንም ደፍሮ መናገር ስለማይችል በሀይማኖት ስም የሚደረገዉ ድርጊት ሁሉ በዝምታ እየታለፈ፣ ሀይማኖቶችም ሀገርም እየተበደለ ነዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሀይማኖቶች ከመቅደሶቻቸዉ ወጥተው በንግድ ቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በታክሲ ዉስጥ፣ በሆቴል፣ በመገናኛ ብዙሃን በቴሌቬዥን፣ ሬድዮ፣ በእንተርኔት፣ በፓርክና ባልተያዙ መሬቶች፣ በባንክ፣ በእንሹራንስ፣ በሆስፒታሎች፣ በፍርድ ቤቶች ነዉ ያሉት። በህዝባዊና መንግስታዊ ተቋማት የበላይነት ለመያዝ፣ የራስን ወገን ለመጥቀም፣ በበኣላት ድምቀት፣ በድምጽ ማጉያ፣ በቤተመቅደሶች ብዛት፣ ውበትና ከፍታ፣ በልዩ ልዮ በዓላት ዝግጅቶች፣ ብዙ ህዝብ በአንድ በመሰብሰብ፣ በተሰሚነት፣ በፖለቲካ ስልጣን በመቆናጠጥ፣ በቁጥርም በተጽዕኖ ፈጣሪነት በልጠዉ ለመገኘት በሚደረገዉ ግልጽና ህቡዕ ፉክክር የኢትዮጵያ የሀይማኖት ባህል በከፍተኛ ሁኔታ ፖለቲካዊ ቅርጽ ይዟል። በሀይማኖት ድርጅቶች ዉስጥ የሚሰማዉ የስልጣን ሽኩቻም ሀይማኖቶች ካካበቱት የፖለቲካ ጠቀሜታ የመነጨ እንጂ ለሀይማኖት ከመቆርቆር ብቻ የመጣ እንዳይደለ መገመት ይቻላል። ስለሆነም ሀይማኖቶች አሁን ከገቡበት ፖለቲካዊ ሚና ወጥተው በመሬት ጉዳይ፣ በአደባባይ ስያሜ ጉዳይ፣ የሀገርና የህዝብን የወል ህልዉና በነጠላና በራሳቸው ደርዝ ብቻ ከመግለጽ፣ ሀይማኖትን ያለቦታዉ ለስልጣን፣ ለገንዘብ፣ ለሌላም ከማዋል እንዲቆጠቡ የሚያደርግ፣ የዜጎችን ነጻነትና ሰብዓዊ መብት የሚያከብርና የሚያስከብር፣ የሀይማኖትንና የፖለቲካን ለየቅልነትን ጤናማ ግንኙነት መስመር የሚያስዝ በህገመንግስቱ በተቀመጠዉና የአለም አቀፍን ህግጋት እንዲሁም የሁሉንም ሀይማኖቶች አስተምሮ ታሳቢ ያደረገ የሀይማኖት ህግ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። ህጉም በተለይም የቤተእምነቶችን የመሬትና የሃብት አጠቃቀም፣ የበዓላት አከበባር፣ የድምፅ ብክለት፣ የሴቶች፣ የደሆችና የህጻናትን መብት ፣ የሃብትና የንብረት አያያዝና አጠቃቀም፣ የዜጎች ሰብኣዊ መብትና ክብር መጠበቅ፣ የስራ ቀናትና የሀይማኖታዊ ስነስርዓቶች ጉዳይ፣ የህዝብ ደህንነት፣ የሀይማኖቶች ፖለቲካዊ ሚናና በተመለከት ግልጽ መመሪያዎችን መያዝ አለበት። የህዝብና የሀገር ደህንነት፣ጸጥታ፣ ልማት፣ ሰላምና አንድነት የማይሸረሽሩ፣ በስነምግባር የታነጻ ህብረብሄራዊ፣ በልዩነቶች የተዋበች አንዲት ሀገር ለመገንባትና ለማጠናከር ድጋፍ የሚሰጡ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ተቋማትን የሚያጠናክር መሆን ይኖርበታል።

ዉሃ፣ ትምህርት፣ ጤና

አገራችን ኢትዮጵያ የካፒታሊስት ስርዓት እየተከተለች መሆኑን የማያዉቅ አይኖርም። የካፒታሊስት ስርዓት ትልቁ መገለጫዉ ደግሞ ገበያ ተኮር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እየተጠናከረ መሄድ ነው። ከፒታሊዝም በተጠናከረባቸዉ አገሮች ዜጎችና ነዋሪዎች የሚፈልጓቸው አገልግሎት በጥራት በገበያ ይቀርባል። ዜጎችም እንደአቅማቸዉ የሚችሉትን አገልግሎት በክፍያ ይሁን በብድር እየወሰዱ ይገለገላሉ፣ አቅራቢዎችም ምርትና አገልግሎቶችን እየሸጡ ትርፋቸዉን እያገኙ፣ ግብር እየከፈሉ የሀገርን እኮኖሚ ይደግፋሉ። ያም ሆኖ ግን እንደዉሃ፣ ጤና፣ ትምህርት፣መብራት፣ መንገድ፣ የቆሻሻና የፍሳሽ ማስወገድ የመሳሰሉ መሰረታዊ ግልጋሎቶች ከገበያ ዉድድር ባለፈ ለፍትሓዊ የሀገር ግንባታ ፋይዳ የተነሳ ለሁሉ እንዲዳረስ ይሞከራል። በተለይ የዜጎች ማህበራዊ ዋስትና በአንጻራዊ ሁኔታ በተሻለ መልኩ በተረጋጋጠባቸዉ የአዉሮፓ ሀገራት መንግስታት እነዚያን መስረታዊ ግልጋሎቶች በማሟላታቸው ዜጎች የተዳላደለ ኑሮ ለመኖር ችለዋል።

በሀገራችን የተነሱት መንግስታትም የህዝባችንን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማለት የጤና፣ የትምህርት፣ የንጹህ ዉሃ፣ የመብራት፣ የመንገድ ወዘተ ችግሮችን ለማቃለል ብዙ ስራ ሰርተዋል። አሁንም ብዙ ስራዎች እየተሰራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ቴሌኮም ድርጅት በአጭር ጊዜና በቴክኖሎጂ ድጋፍ ከነጉድለቶቹም ግልጋሎቶቹን በፍጥነት እያስፋፋ መሆኑ፣ የዋጋ ሁኔታም በአንጻራዊነት እየተሻሻለ መምጣቱ የሚያበረታታ ነዉ። በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ዙርያ አሁንም እጥረትም የአሰራር ችግሮችም ይስተዋላል። በከተሞች አከባቢ የፍሳሽና የቆሻሻ ማስወገድ ችግር ገና አልተቀረፈም። የመጸዳጃ ቤቶች ችግር በተለይ ለሴቶቻችን የተዘጋጀ አቅርቦት የለም ማለት ይቀላል። በመሰረቱ የመጸዳጃና የንጽህና ጉዳይ ህዝባችንንና ሀገራችንን በሚያስወቅስ ደረጃ ዝቅተኛ ነዉ። የንጽህና አገልግሎት አለመሟላት የሰብዓዊ ክብር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የብዙ በሽታዎች ምክንያት በመሆን ኢኮኖሚንም ሰለሚጎዳ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነዉ። በቆይታችን የታዘብኩት በጣም የሚያስከፋዉ ጉዳይ ቢኖር በሀገሪቱ የተንሰራፈዉ የዉሃ ንግድ ነዉ። ፈጣሪ በነጻ የሰጠን ዉሃ በላስቲክ ታሽጎ መቸብቸቡና ዉሃዉ ከተጠጣ በኋላ ላሲቲኩ በየመንገዱ መጣሉ እጅግ አስገራሚና አሳዛኝ ክስተት ነዉ። የዜጎች ንጹህ የመጠጥ ዉሃ የማግኘት መብትና የመንግስት ባለስልጣናት አገልግሎቱን የማቅረብ ሀለፊነት ተረስቶ፣ ውሃ መጣ ብሎ ደስታ የሚታይበት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ሳይሆን አይቀርም።

ሌላዉ የታዘብነዉ አዲስና እንግዳ ነገር ቢኖር ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድርስ የትምህርት ዘርፍ ለንግድ ክፍት መደረጉ አስቀድሞዉኑ የወደቁዉ የትምህርት ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ብቻ ሳይሆን ገንዘብ ያለዉ በግል ትምህርት ቤት የተሻለ ትምህርት ሲያገኝ ገንዘብ የሌለዉ በመንግስት ትምህርት ቤት ክፍልና ፊደል ይቆጥራል። የጤና ዘርፉም ቢሆን ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚም ክፍት መሆኑን ተከትሎ በየሰፈሩ የግል ክሊኒኮች፣ ሆስፒታሎች፣ የጤና ተቋማት ተስፋፍተዉ፣ የዜጎች ጤንነት ትርፍ ማግኛ መሆኑ ሀገራችን በደሃና በሃብታም መካካል የከፋ ልዩነት የሚደረግበት፣ ገንዘብ ያለዉ በግል፣ ገንዘብ የሌለዉ በመንግስት የሚታከምበት ስርዓት እየተፈጠረ እንደይሆን ያሰጋል።

ትሕነግ ወያኔ ከስልጣን ከወረደ በኋለ የፖለቲካ ስልጣንና የሃብት ክፍፍል ሹኩቻዉ በብሄረሰቦች ስም ሆኗል። የትሕነግና መሰል የፖለቲካ ፍልስፍና የሚከተሉት አቋራጪ ስልጣን ፈላጊ ፖለቲከኞች የፈጠሩት የማንነት ፖለቲካ አሁንም በህግ ያልታገደ ከመሆኑ አንጻር የመንግስት ስልጣን መቆናጠጥ፣ የመሬት ወረራ፣ የስራ እድል፣ ንግድና ስራ ፈጠራ እድሎችም በብሄር መደራጀታቸዉ እሙን ሆኗል። የኦሮሚያ ባንክ፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ የአማራ ባንክ፣ የደቡብ ግሎባል ባንክ ወዘተ እየተባለ፣ ባንክም፣ ልብስም፣ ባህልም፣ በዓልም የብሄር መልክ ይዟል። የብሄርና የሀይማኖት ተኮር ማንነቶች ተኮር መገለጫዎች ለአድልዎ፣ ክፍፍል፣ ለመሳሳብ ለልዩነት ምክንያት እንዳይሆኑ በፖለቲካ ዉሳኔ ማስቆም የግድ ይላል። የሀገራችን ልማትና ብልጽግና የሚረጋገጠዉ ዜጎች በማንነት ሳይሆን በብቃትና

በነጻነት ሲንቀሳቀሱ፣ ሲደራጁ፣ ሲሰሩ ነዉ። የብሄርንና የሀይማኖት ስያሜ የያዙ የንግድ ተቋማት አካታች አይሆኑም። በአገራችን የእንዱስትሪ ልማት በከፍተኛ ሁኔታ አየተስፋፋ እንደሆነ ብናዉቅም ሀገራዊዉ ምርት በሀገራዊዉ ገበያ ቀርቦ፣ በሀገሬዉ ህዝብ ተፈላጊነት ሳያገኝ፣ የህንድ፣ የቱርክ፣ የቻይና፣ የታይላንድ፣ እንዲሁም የአረብ ሀገሮች ርካሽ ምርት ገበያዉን አጥለቅልቋል። የኢትፍሩት ምርት የሆኑትን የብርቱካን ማርማላታ እንኳን በኢትዮጵያ ዉስጥ እንደልብ ማግኘት አለመቻል ምን ያሀል በራሳችን የማምረት አቅም የማንተማመን፣ የሰዉ አድናቂ የራስን ናቂ እንደሆንን ያሳያል። ነጋዴዉ የሚሯሯጠዉ የዉጪ ምንዛሬ አግኝቶ የሀገርን ምርት ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት ሳይሆን ሌላ አላቂና አላስፈላጊ የፍጆታ እቃ ከሆነ አገር አስመጥቶ ለመቸብቸብና ሃብታም ለመሆን ነዉ። በሀገሬ ምርት እኮራለሁ፣ ኢትዮጵያ ታምርት ብለዉ አንድ ቀን የፎከሩ ባልስጣናትም በማግስቱ ከዱባይ ባመጡት ሶፋ ቢሮዎቻዉን አሸብረቀዉ ይታያሉ። የእንዱስትሪ ስትራቴጅያችን ዉጤት በሚያመጣ መልኩ ካልተቀየረ የብልጽግና ህልማችን መዘግየቱ አይቀሬ ነው።

በግብር ከፋይ ህዝብ ገቢ የሚተዳደሩም የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ይሁን ገቢያቸዉን ከማሳደድ ጋር ለሀገር ግንባታ የሚሰሩ የግል ሚዲያዎች የሀገርንና የህዝብን ችግሮች በሚፈቱ ጉዳዮች ትኩረት በማድረግ፣ ባለሙያዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አከላትን በማሳተፍ ተጠያቂነትና፣ ሀላፊነትንና ለዉጥን ለመምጣት በመስራት ፋንታ የፖለቲከኞችን እግር እየተከተሉ ሪፓርት በማድረግ ተጠምደዋል። በሀገራችን የመጣዉ ለዉጥ በብዙ ዘርፎች ለዉጥ ያመጣ ሲሆን የሚዲያ ሴክተር ግን አሁንም መሰረታዊ ተሃድሶና ለዉጥ ያስፈልገዋል።በተለይ ዲያስፖራዉ የዉጪ ሚንዛሬዎችን በህጋዊ መንገድ በማስገባት፣ የእዉቀትና የአሰራር በህሎችን በማስተዋወቅ፣ የሀገርን ምርት፣ ባህልና ጥቅም በዉጪ ሀገሮችት በማስተዋወቅ የሀገርን ገቢ የማሳደግ፣ ጥቅም የማስጠበቅ ትልቅ ታሪካዊ ሀላፊነት አለበት። በስመ ዲያስፖራነት፣ ስነምግበር ከሌላቸዉ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር የሀገርን ሃብት መዝረፍ፣ የደሃን መሬት መንጠቅ፣ በልማት ስም ማጭበርበር የሚያስወቅስ እኩይ ተግባር ነዉ። ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ የዲያስፖራ አባላትም ክብርና ሙገሳ ብቻ ሳይሆን እንደማንም ዜጋ መታየት ሲያስፈልገም መፈተሽ ይኖርባቸዋል።  ወደትውልድ ሀገራችን ያደረገነው ጉዞ በብዙ ደስታ የተሞላ፣ ተስፋችንን ያለመለመ ቢሆንም የምንመኛትን የተሻለች ሀገር ለማየት ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን ያሳየ ነዉ። ለዉጥማ አለ።

እስከአሁን ለመጣዉም ለዉጥ መሪዎች ማመስገን በሚገባቸዉ መልኩ ማመስገን፣ መታረም ባለባቸዉ ጉዳይ የእርምት ሀሳቦችን ማቅረብ ተገቢ ነዉ። በሀሳብ ልዕልና የሀገርን ግንባታ ማፋጠን የሁሉም ሀላፊነት ነው። ተስፋ መቁረጥ የለብንም።
https://amharic-zehabesha.com/archives/176631

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...