Tuesday, August 9, 2022

ክልል ሲሉ ክልል ስንል! - አገሬ አዲስ
ነሓሴ 3 ቀን 2014 ዓም(09-08-2022)

የአገራት ክልል ድንበራቸው ነው። ኢትዮጵያም  የያዘችው መሬት በዳር ድንበሯ የወሰን መስመር ወይም ምልክት የተከለለ ነው።በአገር ውስጥ የሚደረገው አስተዳደራዊ ክፍፍል በክፍለሃገር ወይም በጆግራፊያዊ አቀማመጥ ሰሜን፣ምዕራብ፣ደቡብና ምሥራቅ ተብሎ መዋቀሩ የከባቢን ችግርና ሥራ በቅርቡ ለመከታተል የሚረዳ እንጂ የአገርን ልዑላዊነትና የሕዝብ ስብጥርነቱን የሚቀናቀንና የሚቀይር አይደለም።ሁሉም ዜጋ  በተመቸውና በፈለገው ቦታ ሄዶ የመኖርና የመሥራት መብቱን አያሳጣውም። የሰሜኑ ደቡብ ቢሄድ የለም የአንተ ቦታህ ሰሜን ነው ተብሎ አይባረርም።እንደ ነባሩ ሕዝብ አዲስ መጡም በዜግነቱ እኩል መብት አለው።የመኖር ብቻም ሳይሆን በዛ ከባቢ የኤኮኖሚ፣የፖለቲካና የማህበረሰብ እንቅሳቃሴ ውስጥ የመሳተፍና ፣የመወሰን መብቱ የተጠበቀ ነው።

ከዚህ የአገር ክልል ወይም ድንበር የተለዬው ሌላው ደግሞ በጎሳ ማንነት  የአገር አካል የሆነውን ከባቢ ቆርሶ ለመውሰድ ከክፉ ዓላማ በመነሳት  ክልል ብሎ የመሰዬሙ አካሄድ ነው።የሕዝቡን አንድነት ሰባብሮ የእኔ በማለት ሌላውን ባዳና ጠላት አድርጎ በመፈረጅ በተባበረ ሕዝብ የቆመን አገር ለመበታተን የሚከናወን የባዕዳን ሴራ ተሸካሚ የሆነ ቡድን የሚያራምደው ህሳቤ ነው።በዚህ ህሳቤ የተዘፈቁ አገራት የቀውስና የጦርነት ሜዳ ከመሆን ባለፈ ለእድገትና ለሰላም አልበቁም ።

ከ32 ዓመታት በፊት የጎሰኞች ቡድን የኢትዮጵያን መንግሥታዊ መዋቅር ከመቆጣጠሩ በፊት የነበረው የጠቅላይ ግዛቶች በዃላም በደርግ ዘመን የክፍላተሃገሮች አወቃቀር በአስተዳዳሪዎቹና በሰፈነው አምባ ገነናዊና ጸረ ሕዝብ ስርዓት ምክንያት የሚፈለገው እድገት ሳይመጣ ቀረ እንጂ አገራዊ አወቃቀሩ ያመጣው ውድቀት አልነበረም።በአውራጃ፣በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የተዋቀረው ከባቢ ነዋሪ ሕዝብ በቅርበት ጉዳዩ እንዲፈጸምለት አመች ሁኔታን ፈጠረለት እንጂ አሁን የክልል ከተማ በሚሏቸው የሩቅ መንገድ ጉዞ በሚጠይቀው ማእከል እንዲንከራተት አላደረገውም ነበር።የሕዝቡ ጥያቄ የመንግሥትን ሃላፊነት የያዙት ባለሥልጣኖች ሥራቸውን በሚገባ እንዲሠሩለት እንጂ በጎሳዬ የተለዬ መሬትና አካባቢ ይኑረኝ ብሎ  አልጠዬቀም ነበር።የሕዝቡን መማረርና ብሶት መጠቀሚያ በማድረግ የራሳቸውን አገር የመበታተን ዓላማ ይዘው የመጡት አገር በቀል ጠላቶች ከውጭ ሃይሎች ጋር በመተባበር ያሰፈኑት የጎሳ ማንነትንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ አገራዊ የክልል አወቃቀር ያደረሰውን ስብራትና አደጋ በዘመኑ ያለፉት ሁሉ ያውቁታል።ከኢትዮጵያውያኑም  አልፎ ሌሎች አገራት በራሳቸው ላይ እንዳይደርስ አጥብቀው የሚያወግዙትና የሚከላከሉት የነጣጥለህ ግዛ አፓርታይድ ስርዓት ነው።አንዳንዶቹም በችግሩ ውስጥ ያለፉት ፣ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ ፣ከነዚህም የተማሩት ጋና፣ታንዛንያና ኡጋንዳ በሕገመንግሥታቸው የጎሳ ፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ፣በአገራዊ ዜግነት ማንነቱ እንጂ በጎሳው ማንነት እንዳይደራጅ ከልክለዋል።በኢትዮጵያም ያሉ የአገራቸውን አንድነት የሚሹ ወገኖች የጎሳን ፖለቲካና አሁን የሰፈነውን የጎሳ ሥርዓት ከማውገዝ አልፈው እዬታገሉት ነው።ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም በዬጊዜው እያደገ መጥቷል። በአንጻሩ በጎሳ ስም ክልል ሆነው ለመጠቀም የሚሹ ብልጣብልጦች ከኢትዮጵያዊነት ማማ ላይ ወርደው የጎሳ ማንነትን ታፔላ ተሸክመው ክልል ለመሆን ሲታገሉ እናያለን።እነዚህ አገር ጠሎች ለጎሳ ማህበረሰባቸው ጥቅም የቆሙ መስለው በክልል ስም የሚመደበውን ባጀት እንደሌሎቹ አቻዎቻቸው  ለመቀራመትና የከባቢያቸውን መሬት ቸብችቦ ሃብት ለማሰብሰብ ካለ እኩይ ዓላማ በመነሳት ነው።ሁሉም ዜጋ ለደረሰበት ኢፍትሃዊ በደልና ላለበት የችግር ኑሮ የዳረጉት ለሕዝብ የማያስቡ ስግብግቦችና አገር ጠሌዎች በዘረጉት ስርዓትና  የሥልጣኑ ባለቤት በመሆናቸው እንጂ ኢትዮጵያዊ  በመሆኑ የወረደበት መአትና የፈጣሪ ቁጣ አይደለም።እነዚህን አገር አጥፊዎች ከሚመሩበት የጎሳ ፖለቲካና መመሪያ ካደረጉት የጥፋት ሰነዳቸው ጋር ካልተወገዱ በክልል ላይ ክልል ቢደምሩት መፍትሔ አይሆንም። ቀድመው ክልል የሆኑት ለተሻለ ኑሮ ቀርቶ መለስተኛ ሰብአዊ መብታቸውም አልተከበረም።ተገንጥለው አገር የመሠረቱትም በቡሃ ላይ ቆረቆር ሆነባቸው እንጂ የመብታቸው ጌታና የተሻለ አገር ዜጎች ለመሆን አልበቁም።ከስደትና ከድህነት አልተላቀቁም።ውጤቱ ከሗላቀር ሥርዓት ወደ ባሰ ዃላቀርና አምባገነናዊ ሥርዓት መግባት ነው።ባጭሩ ከምጣዱ ወደ እሳቱ የመውደቅ ያህል ነው።

ሁሉም በዬፊናው ያለቅሳል፣በኑሮው ይማረራል።የጋራ ችግሩን ግን በጋራ ለመወጣት አልቻለም።ለዚያም እንዳይበቃ በራሱ የጎሳ ቋንቋ እየተናገሩ ኢትዮጵያዊ  ስነልቦናውን የሚሰልቡ ጨካኞች መኖራቸው ነው። በጋራ የሚደርስን ችግር በጋራ ለመወጣት ትብብር ቢኖር ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ካለበት የስቃይና የስጋት ኑሮ በተላቀቀና ሌሎች አገሮች ከደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ በደረሰ ነበር።ያም እንኳን ቅንጦት ቢሆንም ከስጋትና ከጭንቀት ተላቆ የዜግነትና ሰብአዊ መብቱ ተከብሮለት ከመሰደድ ይልቅ  በፈለገበት ያገሩ መሬት ላይ እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ለመሥራትና ለመኖር በቻለ ነበር።

የጎሰኞች ክልል ውጤቱ የከፋ መሆኑን የሚክድ የለም።የክልልን መባዛት እንደ ዴሞክራሲያዊ መብት መመልከት ያመጣው ጣጣ ነው።በክልል መነጣጠል ነዋሪውን የሚጠቅምና  ለአገራዊ አንድነት የሚረዳ ሳይሆን የአገርን አንድነት የሚቦረቡርና በብዙ ሚጢጢ መንደሮች የብዙ አገሮች ባንዲራ እንዲውለበለብና እርስ በራሱ እዬተዋጋ እንዲኖር የሚያደርግ የባዕዳን ሴራ ውጤት ነው።ውጤቱንም እያዬነው ነው።ባዕዳን ለሚፈልጉት የጥቅም ወረራ ደካማና የተፈረካከሰ አገር ቢኖርላቸው ይመርጣሉ።አንድነት ያለው ሕዝብ የብረት አጥር ነው፤በቀላሉ ሊገረስሱት አይችሉም።ኢትዮጵያንም ሳትደፈርና ሳትበታተን ያቆያት የሕዝቡ ጠንካራ አንድነት ነበር።አሁን ግን ያ የሕዝብ አንድነት  በውስጥ ባንዳዎች ተቦርቡሮ ባዕዳን የሚወስኑባት አገር ሆናለች።

የክልልን ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ አድርጎ ማዬትና ማቀንቀን አሁን የሚታዬውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሂደት መደገፍ ማለት ነው። ሕዝብ የሚተላለቅበትን መንገድ መቀዬስ ማለት ነው።በአጭሩ የጥፋት መንገድን መምረጥ ማለት ነው።ዴሞክራሲ የሚጠቀሙበት እንጂ የሚጎዱበትንና የሚጎዱበትን ምርጫ መቀበል ማለት አይደለም።አንድ ሰው እራሴን ላጠፋ ነው ብሎ ቢነሳ በርታ ተብሎ ገመድ ወይም ሳንጃ አይሰጡትም።ያንን ማድረግ ወንጀል ነው፤እራስንም ማጥፋት ወንጀል ነው።የገዳይ ተባባሪ መሆንም ወንጀል  ነው።መግደልን ወንጀል የሚያደርገው በሌላው ላይ በመፈጸሙ ብቻ ሳይሆን የራስንም ህይወት ለማጥፋት መነሳቱና ማድረጉም ጭምር ነው።የአንድ ሰው ሞት ለቤተሰቡ ከዛም ለማህበረሰቡ ጉዳትና እጦት ነው። ለወጣቱም ትውልድ የመጥፎ ድርጊት ምሳሌ መሆን ነው።እራስን ለመግደል የገፋፋን ችግር ከማሶገድ ይልቅ ለችግሩ እጅ ሰጥቶ መሸሽ ማለት ነው።ችግርን ይጋፈጡታል እንጂ አይሸሹለትም!በትግል ዓለም የሚከሰተውን በመሸሽና በማፈግፈግ መካከልም ያለን ልዩነት ማወቅ ተገቢ ነው ።ሃይልን ለማሰባሰብና ይበልጥ ተደራጅቶ ለመግጠም ሲባል ስልታዊ ማፈግፈግ(Tactical retreat) ማድረግ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም።ጠላት ሲያይል ማፈግፈግ ከበለጠ ጥቃት ያድናል።ይህንን ስል ግን አገርን ለማዳን ወደ ክልል መውረድ ተገቢ  እንዳልሆነና ክልል መፈልፈሉ ከአገራዊ ስልታዊ ማፈግፈግ ጋር እንዳይታይ አደራ እላለሁ።

ክልል መፈልፈሉ ለአገር አንድነት መሰናክልና ለመፍረስ የሚረዳ የመንጠሪያ እርከን ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ክልሉ ከኬንያ፣ከጅቡቲ፣ከሶማሊያ የሚለዬው የወሰን መስመር  ወይም ድንበር እንጂ የክፍላተ ሃገርን ሕዝብ በጎሳ ማንነቱ ነጣጥሎ የሚጠቀጠቁበት የጎሳ በረት አይደለም።በክልል ላይ ክልል መቀፍቀፉም መደመር ሳይሆን ከኢትዮጵያዊነት ማማ ላይ የሚያወርድ የመቀነስ ሂደት ነው። የአብይ አህመድ መንግሥት ግን ክልልን የእኩልነትና የአንድነት ብሎም የመደመር ውጤትና  የዴሞክራሲ ከፍታ አድርጎ በመስበክ ይመጻደቅበታል።ሌሎቹም ያስተጋባሉ።

ቀደም ሲል በወላይታ በሰሞኑ ደግሞ በጉራጌ ተወላጆች በኩል የሚታዬውክልል የመሆን  ግብግብ የዚሁ ነጸብራቅ ነው።ለኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሆነው የጉራጌ ማህበረሰብ በስሙ ሊነግዱበት የሚቅበዘበዙትን የሥርዓቱ አወዳሾች ወግዱ ሊላቸው ይገባል።ሌላውም እንዲሁ።የክልልን ማንነት መቀበል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከተሸረበው የሴራ መረብ ውስጥ መግባትና መተብተብ ማለት ነው።ክልል ይኑረኝ ማለት አገርን እንደ ሰንጋ ለመቃረጥ የተሳለውን ካራ መሸክምና የድርሻዬን  ቦጭቄ ልውሰድ ማለት ነው። ለተራው የትግራይ ተወላጅ ክልል በመሆኑ ያገኘው ጥቅም የለም፣የአማራውም፣የአፋሩም፣የኦሮሞውም፣የሶማሌውም፣ የሲዳማውም …ወዘተ እንዲሁ።ተጠቃሚዎቹ በክልል ስም ሥልጣን ይዘው የሚበዘብዙት ጨካኞች ብቻ ናቸው።ለሕዝቡማ የተረፈው ቢኖር በጦርነት ውስጥ ገብቶ መጨፋጨፍና በጠላትነት ጎራ ተሰልፎ ለመሪዎቹ ጥቅምና  የሥልጣን ዕድሜ መሞትና መግደል ብቻ ነው።በዚህ ሂደት ስንቱ እረገፈ? ቤቱ ይቁጠረው!ከሚመጣው ተመሳሳይ ወይም ከባሰ አደጋ ለመዳን ለእስከ አሁኑ አደጋና መከራ  ምክንያት የሆኑትን በጎሳው ስም የሚነግዱትን አረመኔዎች ከትከሻ ላይ አውርዶ በጥፋታቸው መቅጣት ሲቻል ብቻ ነው።ከጎሳ ፖለቲካ ተላቆ የአንድ አገር ዜግነት ፖለቲካ ማራመድ ሲቻል ነው።ለዚያም ሁሉንም ማለትም በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነውንና ለደረሰው ውድቀት ተጠያቂ ያልሆነው የማህበረሰብ ወኪል ያካተተ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነው።

በወንጀለኞቹ መካከል የሚደረገው ውይይትና ስምምነት የሰፈነውን አገር አጥፊ ቡድንና ሥርዓት እንዲቀጥል ከማድረግ በቀር የተሻለ ሥርዓት አያሰፍንም፣ሕዝቡን ከስደትና ከርሃብ ብሎም ከእርስ በርስ ግጭት አያወጣም።ሰላምና እኩልነት እንዲሰፍን አይረዳም።ኢትዮጵያንም ከመፈራረስ አያድንም።

በጎሰኞች ክልል ምክንያት ለዘመናት አብረው የኖሩ፣የተዋለዱና በቤተሰብ ደረጃ የዘለቁ ማህበረሰቦች በቋንቋ ማንነታቸው ተለያይተው እርስ በርሳቸው የሚጋደሉበት ምክንያት ሆኗል።ለዚህ ደቡብ ተብሎ የሚጠራው ክልል ምሳሌ ነው።ዛሬ ይህ ክልል ተሰነጣጥቆ ብዙ ክልሎች ሆኗል።ያልሆኑትም ለመሆን እዬወተወቱ ነው።ብዙ ክልል መሆኑ ብዙ ችግሮችን ይዞበት መጣ እንጂ የነበረበትን ችግር አላቃለለለትም።አሁንም በጎሰኞች  የተፈጠረው ክልል ካልፈረሰና፣የጎሰኞች ፖለቲካ ህሳቤ ከነኮተቱ  ካልተወገደ ኢትዮጵያ ከአገርነት ወደ መንደርነት የመለወጧ አደጋ ከፍተኛ ነው።የሚታዬውም አቅጣጫ ያንኑ የሚያመላክት ነው።በክልልም ሆነ በመንደር ሰላም የሌለው እርስ በርሱ እዬተጋደለ የሚኖር ደሃ ሕዝብ ሆኖ ይቀራል እንጂ ለሚፈልገውና ለሚመኘው የተሻለ ሰላማዊ ኑሮ አይበቃም።እንኳንስ ተለያይተው እዬተጋደሉ ይቅርና አንድም ሆኖ ለማደግ ብዙ ፈተናዎችንና የውጭ ተጽእኖችን ለማለፍ የሚጠይቀው ዋጋ ቀላል አይደለም።

ካለው ምስቅልቅልና አገራዊ አደጋ ለመውጣት፣ከሁሉም በፊት ግን ብሔራዊ መግባባት ሊኖር ይገባል፤ለዚያም የዬጎሳው ተወላጆች ምሁራን፣የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች(ወንዶችና ሴቶች)የኪነት ባለሙያዎች፣ የመሪነቱን ሚና ሊጫወቱ ይገባል።

ለሃይማኖቱም ሆነ ለዜግነት መብቱና እኩልነቱ በቅድሚያ አገርና ሕዝባዊ ሥርዓት ሲኖር ነው።

የጎሰኞች ክልል ይፍረስ! የኢትዮጵያ አገራዊ ክልል(ዳርድንበር )ይከበር!!ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስከብር የሽግግር መንግሥት ይቋቋም!!!

አገሬ አዲስ

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/176516

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...