Sunday, July 31, 2022

የአልሸባብ የጥቃት ሙከራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን  ለቀጠናውና ለምእራቡ አለምም የማስጠንቀቂያ ደወልነው
ሀምሌ  24, 2014  (July 31,2022)

አክሊሉ ወንድአፈረው (ethioandenet@bell.net)

ህወሀት በትግራይ ክልል ተመድቦ ያገለግል በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ (መብረቃዊ)  ጥቃት ፈጽሞ ኢትዮጰያ በታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ ውስጣዊ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጰያ ላይ ታላቅ ሁለገብ  ተጽእኖ እያሳደረች ነው፡፡ ይህም የኢትዮጰያን አንጻራዊ መዳከም በአንጻሩም የአልሸባብን መጠናከር አልፎ ተርፎም የሰሞኑን የቀጥታ ወረራ ሙከራ አስከትሏል፡፡ ይህ ሁኔታ በቀጣይ ሊያስከትል የሚችለውን እንደምታ መመርመርና አስቸኳይ የርምት እርምጃ መውስድ አጣዳፊ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተችው እና እየተጫወተች የምትገኘው አሜሪካ ነች፡፡ አሜሪካ የትግራይን አማጺ ሀይል ፣ ሀወውሀትን፣ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ካከካሄደ በዃላ መልሶ እንዲያንሰራራና ከተቻለም ወደ ሥልጣን እንዲመለስ የሚረዳ እጅግ ብዙ ተግባሮችን ሰርታለች፡፡

ለምሳሌም በኢኮኖሚው መስክ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን አጋሮቿንም አስተባብራ ለኢትዮጰያ እርዳታ እንንዳይሰጡ በማድረግ ኢኮኖሚዋ እንዲደቅ ተድርጓል፡፡ ከእርዳታቸው አልፎ የንግድ ስምምነቶችን ( ለምሳሌ አገዋ) በመሰረዝ ቀና ማለት ጀምሮ የነበረውን የእንዱስትሪ መስክ  አሽመድምደውታል፡፡ይህም በኢትዮጰያ ቀድም ሲልም አስከፊ የነበረውን በተለይም የሴቶችንና የወጣቶችን ሰራ አጥነት እጅግ ከፍ አድርጎታል፡፡

በዲፐሎማሲው መስክ ኢትዮጰያ ለ 13 ጊዜ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት አጀንዳ ሆና እንድትወቀስ ብቻ ሳይሆን ቢቻላቸው ታላቅ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ የተባበሩት መንግስታት ዉሳኔ እንዲተላለፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ እያንዳንዱ ስብሰባ የተጠራውም በአሜሪካ ወይም በሸሪኮቿ ነበር፡፡ ይህ ሙከራቸው በቻይና፣ሩስያ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮችና በህንድ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ቢሁንም ታላቅ ጉዳትን አድርሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጰያ በአፍሪካም ጭምር ተቀባይነቷ ላይ ታላቅ ተጽእኖ እንዲደርስባት በተለይም በግብጽ ግፊት ልማቷን እንኳ እንዳትገፋበት በተለያዩ ጎረቤቶቿ ተደጋጋሚ የማስፈራራትና የሴራ ኢላማ እንድትሆን ብዙ ተሞክሯል፡፡ የሱዳንን የደቡብ ሱዳንን የጅቡቲ፣ የዛምቢያን ወዘተ ጉዳይ ማንሳት መረጃ ይፈነጥቃል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚደንት ትራምፐ በይፋ የህዳሴ ግድብ በግብጽ እንዲመታ ጥሪ አድርገው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሀወሀትን አና ሌሎች የውስጥ ህይሎችን (ለምሳሌ በጉምዝ፣ በኦሮሚያ  ጋምቤላ) በወታደራዊ ሀይል ያሻቸውን በህዝብ ላይ ለመጫን ትልቅ ወረራ እንዲፈጸሙ በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ ገፋፍቶ (አበረታትቶ)  እነሆ ኢትዮጰያ ታላቅ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡

በትግራይ የተከሰተውብ እና ኳላም ወደ መሀል አገር የገፋውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጰያ ሰራዊት ያለውን ሀይሉን ወደ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎና አፋር  ሰላዞረ  በምስራቅ የሀገራችን ክፍል አል ሸባብ ላይ የነበረው ትኩረትና ቀድሞ የማጥቃት ተግባሩ  እንደ ቀደምት አመታት እንዳይቀጥል  ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጰያ የደህንነት ክፍል ትኩረቱን ያሰጉኛል ባላቸው የውስጥ ሀይሎች ለምሳሌ በፋኖ ላይ ያደረገ በመሆኑ በአልሸባብ ላይ በሚደረገው ክትትል እና ሴራውን ቀድሞ ማክሸፍ ላይ  ተጨማሪ ክፍተትን ፈጥሯል፡፡

አል ሸባብ ከላይ የተዘረዘረውን እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሸረሸረ የመጣውን የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይን ድጋፍ  በማየት ሁኔታ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ራሱን እጅግ አጠናክሮ ቀደም ሲል ተዋጊዎቹን አሾልኮ ለማስገባት አሁን ደግሞ በግልጽ ኢትዮጰያን በሰፊው ለመውረር ሙከራ አድርጓል፡፡ ይህ ወረራ ቢቀለበስም፣ የሚያመለክተው ግን የምእራቡ እስትራተጂ ለአልሸባብ መጠናከር ታላቅ አስተዋጸኦን እንዳደረገ ነው፡፡

ይህ ጉዳይ አደገኛነቱ ለኢትዮጰያ ብቻ ሳይሆን ለመላ ቀጠናው፣ ለቀሪው አፍሪካና ለምእራቡ አለምም ጭምር ነው፡፡

ባለፉት 2 አመታት የተለያዩ የሀይማኖት ጽንፈኞች ከአልሻባብና ከቦኮ ሀራም ጋር ተባብረወና ተናበው ከሞዛምቢክ እስከ ኮንጎ ታንዛንያና ኬንያ ጭምር መስፋፋታቸው  ጥቃትም ማካሄዳቸው ይታወቃል፡፡

የሀይማኖት ጸንፈኞች በምእራብ አፍሪካም ከናይጀሪያ እስከ ማሊ አጎራባች ሀገሮች እየትሰፋፉ እንደሆነ ከሌሎች ቦታዎች ሁሉአፍሪካን መአከል አድርጎ ለማስፋፋትና፣ ለመጠናከር እንደሚጥሩ ይታወቃል፡፡

ይህን ሁሉ በግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ የምእራቡ መንግስታት በኢትዮጰያ ላይ የሚያደርጉት እጅግ ጽንፍ የያዘ ተጸእኖና ግፊት ምን እያስከተለ እንደሆነ ኢትዮጰያን ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ሀገራት እና የራሳቸውንም ጸጥታና ጥቅም እጅግ እየጎዳ እንደሆነ ተገንዝበው አሥቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡ በዚህ አንጻር፡ ሁኔታውን ለመቀልበስ፡

- በኢትዮጰያ ላይ የጣሉትን የእርዳታ ክልከላ ባስቸኳይ ሊያነሱ ይገባል

- በንግዱ አንጻር ያስተላለፉትን የንግድ መአቀብ ሊያነሱ ይገባል

- ቀደም ሲሉ ይሰጡ የነበረውን እና ከአለፈው ሁለት አመት ወዲህ የከለከሉትን የወታደራዊ ወይም የጸጥታ ትብብር ሊያድሱና ተገቢውን የገንዘብ እና ሊሎችም ድጋፍ ሊቀጥሉ ይገባል

- በዲፐሎማቲክ መስኩ የሚያደርጉትን ቀጥተኛ የሆነና ተዘዋዋሪ ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ ሊያቆሙ ይገባል፡፡

- በኢትዮጰያ የውስጥ በፖለቲካ የሚያደርጉትን ቀጥተኛና ተዛዋሪ  ጣልቃ ገብነት ሊያስተካክሉና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ት አ ዛዝ መስጠትን ባስቸኳይ ሊያቆሙ ይገባል፡፡

- የኢትዮጰያ ወስጣዊ ፖለቲካ እጅግ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን ሲበዛ ውስብስብ መሆኑን በግንዛቤ ውስጥ በማስገባትም ከጣልቃ ገብነት ውጭ ቅራኔን በውይይት ለመፍታት የቴክኔክ እና የማቴርያል ድጋፍ መሰጠት፣ የተወሰኑ ተቃዋሚወችን የማጠናከር እርምጃ መስሎ ከሚታይ አካሄድ ራስን ማቀብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

- የአልሽባብ እና ሌሎችም ጽንፈኞች ጥቃትና አደጋ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ የቀጠናው መንግስታት በጋራ እንዲቆሙ ማበረታታ እንጂ ማደናቀፍ ከቶውንም አይገባም፡፡

የኢትዮጰያ መበታተን የማይገዳቸው ሀይሎች ከአልሸባብ ጋር የሚግባቡበት  አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጰያን ቢቻል ማፍረስ ባይቻል በቀውስ ውስጥ እንድትቀጥል ማድረግ ነው፡፡ የተበታተነችም ሆነች በቀውስ ውስጥ የምትቆይ ኢትዮጰያ ለሁለቱም ክፍሎች አላማ ሰኬት ነው፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጰያ እንደ ሶማሊያ ብትሆን ለኢትዮጰያውያን፣ ለቀጠናውም ሆነ ለምእራቡ አለም ደህነነት እጅግ አደገኛ ነው፡፡

የምእራቡ አለም መንግስታት ተወካዮች በኢትዮጰያ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ ምስቅልቅል በአግባቡ በመረዳት በማንኛውም እርምጃቸው ወገንተኛ እንዳልሆኑ ለማሳየት ማንኛውንም ኢፊሴላዊ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ሁሉን አቀፍ በሆነው በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት በኩል ቢሆን የተመረጠ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በምእራብ መንግስታት ላይ የሚታየውን ወገንተኝነት እና የእምነት መሸርሸር ቀስ በቀስ ለመጠገን ይቻል ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ አሁንም የምእራቡ መንግስታት የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ጋር ብቻ የሚያሳዩትን ቅርርብ በሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች እና በህዝብም ላይ የሚኖረውን አሉታዊ እይታ ሊያጤኑ ይገባል፡፡ ላለፉት ሁለት አመታት የታየው ከመስመር የወጣና ልኡላዊነትን የሚጋፋ ግንኙነት የሚያስተላልፈው መልእክት ኢትዮጰያን አሳንሶና አጋር የሌላት አድርጎ የሚያቀርብ እጅግ አፍራሽ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ የኢትዮጰያ ገዥ ፓርቲ፣ ብልጽግና የምእራቡን መንግስታት ተጸእኖ መላላት ያላግባብ እንዳይተረጉመው እና የህዝብን መብት ለመርገጥ እንዳይጠቀምበት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የመብት ጥስትና ረገጣውን ከቀጠል የተፈለገውን ሀገራዊ መረጋጋትና የአልሸባብንም ጥቃትና መስፋፋት ማምከን  እጅግ ይከብዳል፡፡

በተጨማሪም የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ የምእራቡ መንግስታት ፖሊስ አይደለም እና የዶክተር አብይ መንግስት ራሱን የእስካሁን ፖሊሲና ተግባሩን ገምግሞ ሰሀተቶቹን በተግባር አርሞ ወስብስብ ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ ለመፍታት በአዲስ መንፈስ ለመንቀሳቀስ (reset  ) ቁርጠኛና አስቸኳይ እርምጃዎችን በተጨባጭ ሊወስድ ይገባል፡፡

በዚህ አኳያ ምራባውያኑ በመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበት ምህዳር እንዲዘጋጅ እናም ተግባራዊ አንዲሆን ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት ሁኔታን  መነጋገር እና በጋራ ማመቻቸት  ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጰያ ውስጥ መብትን ሳያከብሩ ሰላምን እውን ማደረግ በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ እጅግ ከባድ ነው፡፡

የአሁኑ የአልሸባብ የወረራ ሙከራ ለኢትዮጰያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ሆነ ለምእራቡ ሀገራት ታላቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡ የምእራቡ አለም በኢትዮጰያ ላይ ያሳደረው ወደር የለሽ ተጸእኖ  ከመንግስት የተለያዩ ስህተቶችና ፖሊሲዎች ጋር ተደማምሮ እነሆ አፍራሽ ጎኑ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ባስቸኳይ መቀልበስ ጠቀሜታው ለምእራቡ አለም ለቀጠናውና ለኢትዮጰያም ጭምር ነው፡፡ ሁኔታው እጅግ አጣዳፊ ትኩረትንም የሚሻ ነው፡፡
https://amharic-zehabesha.com/archives/176387

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...