Monday, July 25, 2022

“ጉርጥ አደፈጠም ዘለለም ፤ ያው ጉርጥ ነው“ እና ከእውነት ጋር እንታረቅ - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
በኢትዮጵያችን ማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ ፣   በልቡ ውሥጥ ያለውን ንፁህ እውነት ፣ ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ ጮክ ብሎ በአደባባይ “ እኔ ሰውን በሰውነቱ እንጂ በሌላ አላውቀውም ። በአማራነቱ ፣ በትግሬነቱ ፣ በኦሮሞነቱ ፣ በጉራጌነቱ ፣ በሲዳማነቱ ፣ በሱማሌነቱ ፣ በጋምቤላነቱ ፣ በጉምዝነቱ ፣ በሐረሬነቱ ፣ በአፋርነቱ ። ወዘተ ።  ሳይሆን ፣ እንደ እኔ ሰው በመሆኑ ብቻ ነው የማውቀው ። ሰውን ሰው ብሎ ከመጥራት በመግባብያ ቋንቋው ስያሜ መጥራት ሰውን እንደ ግዑዝ ነገር መከፋፈል ነውና ግብዝነትን ያራባል ። አንዱን የሰው ሰብስብ በቋንቋው አንግሶ አንዱን ባርያ እንዲሆን ያሥገድዳል ። በዚህም ሰበብ የማያባራ ግጭት ውስጥ ሰዎች ሰውነታቸውን ክደው እንዲዘፈቁ ያደርጋል ። ትብብርና መደጋገፍ በሚሻው በ21ኛው ክ/ዘ ዘመን መራራቅን እና ጥላቻን ያነብራል ። እናም ይኽ የቋንቋ ሥርዓተ መንግሥት እሥከቀጠለ ጊዜ ደረስ የውጪ ጠላቶቻችን የመጫወቻ ካርድ ሆኖ በማገልገል በሚረጩት ገንዘብ ሰበብ መገዳደላችን የማያባራ ይሆናል ።“ ብሎ ቢናገር ፤ ይኽ እውነቱ  ለሥንቱ ሰው ይገባዋል ?

ከቶስ ተፈጥሮ በሂደት እኛን በክብር ከማሰናበቱ ቀድመን ትርጉም በሌለው ጥላቻ ፣ የተሻለ ለመብላት ብለን ፤ ለተሻለ የግል ኑሮ ብለን ነገ መሞታችን ላይቀር ለምን ዛሬ በስግብግብ አእምሮና በውሸት ቅስቀሳ ተገፋፍተን ጥቂቶች  ብዙሃን ንፁሐንን እንደእኛው ሰው መሆናቸውን እያወቅን በቋንቋ ልዩነት ብቻ ፣ ለምን እንገድላቸዋለን  ?

እኛ እንደ ህዝብ ተራ ሟች በመሆናችን ፤ ከዕውቀት በመራቃችን እና ኃይማኖተኞች ነን እንላለን እንጂ በተግባር ፀረ _ እግዚአብሔር ወይም ፀረ_ ፈጣሪ በመሆናችን ወደጥፋት ሥናመራ ፣ የሚመሩን የአገር አሥተዳዳሪዎች የባሰ በመገዳደላችን  እንድንቀጥል ለምን አሥፈላጊውን ሤጣናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ   ? የሞትን ፅዋ መሪዎች ሣይቀሩ እንደሚጨልጦት ፍፁም ዘንግተው አይደለምን ? በመንግሥት ውሥጥስ  ተራ ሟች ሰዎች አልተሰባሰቡምን ? ከጥቂት ሚኒሥትሮች ውጪስ ሌላው የመንግሥት አካል በታሪክ የሚወሳበት ሰፊ ሥፍራ ይኖረዋልን ? ከቶስ ከመሪው በሥተቀር ማነው በተደጋጋሚ ፣ ሥሙ በደግና በክፉ ሥራው የሚነሳው ? የሚወሰው ?

ራቁት መወለድ ፤ ማደግ ፣ መጎልበት ፣ መጎልመስ ማርጀት ፣ መጃጀት መሞት የተፈጥሮ ሂደት ነው ። ከነዚህ ደረጃዎች ውሥጥ  በአንዱ እያሉም ፣   በህመም መሰቃየት እና መሞት የሁላችንም ዕጣ ፈንታ እንደሆነ መገንዘብም ታላቅ እውቀት ነው  ። የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ከመሞታቸው በፊት ጥይት ባይገድለን ባዮሎጂ ይገለናል ። ያሉት ይኽንን እውነት ይገልፀዋል ። (ጠ/ሚ አብይ አህመድ ታመው ቢሞቱ አዲስና እንግዳ ነገር ከቶም አይሆንም ። ሰው “ ተወለደ  ! “ ሲባል “ ሞተ ! ማለት ነው ። “ የሚባለውም ሞት ሁሌም ከህየሸወት ጌር አብሮ በሠኖሩ ነው ። ምናልባት  የሚቆጨው አንድ መሪ እንደሚሞት አሥቀድሞ በመገንዘብ  መሪ ያለማዘጋጀት ነው ። ለአፍሪካ ፖለቲካ ግን ይኽ አሥፈሪ ና አሣፋሪ መንገድ ከቶም አይደለም ። )

የሰለጠኑት  አገራት መሪዎች ይኽንን እውነት ከመቶ አመት በፊት ተገንዝበውታል ። እናም እንደ ሰው ሞት የማይቀርላቸው በመሆኑ ፣ የመንግሥት ቅብብሎሻቸውን ወገኛ አድርገውታል ። በአፍሪካ ግን ወገኝነት በጣት በሚቆጠሩ የአፍሪካ አገራት  ብቻ ነው ያለው ።

በአውሮፓና አሜሪካ መንግሥታቱን ፣  ተቀናቃኞቻቸው እና ምሁራን በአደባባይ ቢተቿቸው እና ቢያብጠለጥሏቸው “ ለምን ሥሜ በመጥፎ ተነሳ ? “በማለት ዘረፍ አይሉም ።  በመንግሥት ባለሥልጣናት ደርጊት ከበሸቀው  ህዝብ ጋር በመወገን ወቅታዊውን  ፖለቲካዊ ጉዳይና ፣ የህዝቡን ወቅታዊ የፍላጎት ትርታውን  አድምጠው  እያዋዙ ባለሥልጣናቶቻቸውን ተው ፣ እረፉ ይኽ ለዚህ ህዝብና አገር አይመጥንም ። ለእናንተም ቅሌት ነው ፤ በማለት የሚመክሩትን ኮመዲያንን ለምን ቀለድክብኝ በማለት አፍንጫቸውን በቦክስ አይሰብሩም  ። በግራና ቀኙም  ምንም ያህል መራራ እና የሚያንገፈግፍ ተረብ እና የትችት ናዳ ፤ ሸንቋጭ  ሂሥ ና  መዓት  የቃላት ውርጂብኝ ቢያጋጥማቸው ፤ ባለሥልጣናቱ ከሥህተት መንገዳቸው ከመማር ባሻገር ፤ ሂሱን እንደ ስድብ በመቁጠር ፣ መንግሥት ሆኜ ሣለ ፣ ሊሰግድልኝ ሲገባ ትችትና ወቀሳ   በእኔ ላይ በማዝነብ ፣ እውነትን ለህዝብ አሳውቋልና  እንደ ዮኃንስ መጥመቁ አንገቱ ተቋርጦ በሳሕን ይቅረብልኝ አይሉም   ። “ አፍኑት ! “   ብለው ሥውር  ትእዛዝም አይሰጡም  ።

እዚህ አገር አስብቶ ማረድ ፤ ልኩን አሳየው በማለት የራስ ቆዳን በማዋደድ ( ራቁታቸውን እንደተወለዱ ና ራቁታቸውን እንደሚቀበሩ በመካድ ) ዜጎች ተፈጥሮ በሰጣቸው አንደበት ለምን ተናገሩበት ብለው “ ለእግረ ሙቅ “ የሚዳርጉ ህግ አሥፈፃሚዎች ፣  እንዴት እና በማን እንደተቋቋሙ ግልፅ ባይሆንም ፣  ጤነኛና አሥተዋይ አእምሮ ላለው ማንኛውም ዜጋ ጉዳዩ እጅግ  አሣሣቢና አናርኪሲዝምን የሚያሰፍን ነው ። በዙ ጥያቂም ህዝብ እንዳያነሳ ያሥገድዳል  ።

“  በዚች ቅድስት አገር  በመንግሥት አርቆ አሳቢነት የሚተማመኑ ፣   ንፁሐን በማሰባቸው ብቻ ዘብጥያ ለምን ይወርዳሉ  ? እንዴት እውነትን ያለፍርሃት በመናገራቸው ፣ እውነቱ ለሌሎች ጠረዘኛ ፖለቲከኞች የሚጎመዝዝ በመሆኑ ብቻ የተፈጥሮ አንደበታቸው  ይለጎማል  ?   ደግሞስ የቋንቋና የጎሣ ፖለቲካው ያመጣው መሞሻለቅ አይደለም ወይ ? ...  ። ሥንትና ሥንት ተሣዳቢዎች ደረታቸውን ገልብጠው በኩራት በሚራመዱባት አገር ውሥጥ እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ መንግሥትን ለበጎ ሥራ የሚያነሳሳ ፣ ህፀፆቹን ነቅሶ በማውጣት እንዲታረም አሥቀድመው ምክረ ሃሳብ የሚለግሱ ፣ ለበጎ ሥራ ኮርኳሪ አንደበትና ብዕር ያላቸው ዜጎች ለምን ይታሰራሉ ???..... “ በማለት ዘወትር መንግሥትን የሚሞግት ጥያቄ ህዝብ ሲጠይቅ የሚሰማውም ከዚህ እውነት አፃር ነው ። በየደጁና በየቤቱ ። በየትም ሥፍራ ውሸት ሰልችቶናል ። እያለ ነው ህዝብ ።

እንደምታውቁት  ከደርግ የሶሻሊዝም “  የአብዮተኛ “ እና “ የፀረ አብዮተኛ “ ፍረጃ ጀምሮ አውዳሚው ውሸት ወይም ቅጥፈት  እየተለመደ መጥቷል  ። ያኔ በደርግ የሶሻሊዝም ሥርዓት ፣ ንፁሐን ያለ  ፍትህ ፣ ፍርድ ቤት ሣይቀርቡ ፣ በግለሰቦች የግል ውሳኔ ፣ በነፃ እርምጃ ይገደሉ ነበር ። ያም  እኩይ ድርጊት  “በየፍየል  ወጠጤ ... “ ዜማ ታጅቦ   በሬዲዮ ይነገር ነበር ። ይኽ  ትክክል ያልሆነው ፣ ውሸት የሆነው ማብራሪያ በሥሜት ተጆብኖ ፤ በበቀለ ወፍሮ ፤  ለህዝብ   ሲቀርብ ብዙሃኑ “ አሹ  “ ይል ነበር ። ከወታደራዊ  መንግሥት ሥርዓት  በኋላ   ደሞ  ፤ መልኩን ቀይሮ ብቅ ያለው ፤ በሎጂክ እንጂ በመንግሥት ሥርዓትነት በዓለም ቅቡልነት የሌለው የተጨቋኝ እና የጨቋኝ ቋንቋ ትርክትና የተረኝነት መንገድ ነው ። ኢህአዴግ ወያኔ የዚህ ሥርዓት ዋና ተዋናይና የመድረኩ ባለቤት ሆኖ የመጣበት ። ( ...  ። ) የሰው መግባቢያ የሆነን ቋንቋ ሲወለድ ጀምሮ በደም ውሥጥ ያለ  የአንድ ጎሣ ብቻ መግባቢያ አድርጎት አረፈው እና ሰውን በቋንቋ ከፋፍሎ ክልል ብሎ አጥር ሰርቶለት አረፈው ።

በመሠረቱ ቋንቋ የሰዎች በሙሉ ቋንቋ ነው ።  የአንድ ዘውግን እና ጎሣ ቋንቋ ሊሆን አይችልም ። ከተማርከው ፣ በቋንቋው ተናገሪ ቤተሰብ ውስጥ ካደክ ፤ ወይም በልዩ ለዩ አጋጣሚ ከቋንቋው ተናጋሪ ቤተሰብ ጋር ከኖርክ ፤ ቋንቋውን በቀላሉ ታውቃለህ ። አንድ ቋንቋ የእኔ ብቻ ነው ማለት    በመሠረቱ ሥህተት ነው ። ሥለቋንቋ መወለድ ፣ ማደግ እና ዓለማቀፋዊ መሆን ብቻ ሣይሆን ቋንቋ እንደሚወለድ ሁሉ እንደሚሞት ያለማወቅም ነው ። ቋንቋውን በመማር ብቻ የየትኛውም አገር ዜጋ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች የራሱ ማድረግ ይችላል ። ይሁን እንጂ የቀድሞው  የወያኔ ሥርዓት የእነሱ እና የእኛ ቋንቋ በማለት ዜጎችን በቋንቋ መጥራት በመጀመሩ እና ግለሰቦች በቋንቋ ብቻ   ለህብረተሰባቸው የሚፈይዱት አንዳችም ሳይኖር ፤ እውቀቱ ፣ ችሎታው ፣ ክህሎቱ ሳይኖራቸው ፣ በቋንቋ ብቻ ተደራጅተው ፣ ተቧድነው ፣ ኔት ወርክ ፈጥረው ፤ በቀላሉ   ሀብት ለማፍራት የሚያሥችል  ሥልጣን አሥገኘላቸው ። በደርግ የሶሻሊዝም ሥርዓተ መንግሥት “ ሁሉም ጎሣዎች እኩልናቸው ሌብነትም ጥዩፍ ነው “ ተብሎ ተጨቋኝ መደብ አሸናፊ የሆነበትና ኃይልና ሥልጣን የሰፊው ህዝብ ነው ። “ ተብሎ  በገሃድ የተዜመበት ሥርዓት በቋንቋ የበላይነትና ገዢነት ሥም የጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭነት የሚፀባረቅበት መንግሥታዊ ሥርዓትን ይዞ ብቅ አለ ። የወቅቱ  ፕሬዚዳንት  መለሥ ዜናዊ በቋንቋ ሥም የትግሪኛ ተናጋሪዎችን ፈላጭ ቆራጭነት አበሰሩ ። ሌብነት በወጉ ለህወሓት ፓርቲ ጥቅምና ጥቅም ብቻ እንዲውል ተደረገ ። በመለሥ ዜናዊ ዙሪያ ያሉ  ጥቂት የህወሓት ዓባላትም ቢሊዮነር ሆኑ ። በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ና ሀብት በአሜሪካና በአውሮፓ አከማቹ ።

ይኽ ሌብነት መለሥ ከሞቱ በኋላ በሁሉም የኢህአዴግ ዓባል ድርጅቶች ውሥጥ ተስፋፋ ። እና ህብረተሰቡ የሚጠየፈው ሌብነት እጅግ እያበጠ መጣ ። ...

ቀስ ፣ በቀስ  መልካሙ ባህላችንን ፣እሴቶቻችንን እና ኃይማኖተኝነታችን  በእጅጉ ሸረሸረው ። ጥቂት የማይባለው አጋጣሚው የተመቻቸለት ቋንቋኛ ያለምንም ድካም  በአቋራጭ ገንዘብ እያገኘ ቱጃር ለመባልም በቃ ።  እንሆ  ለዛሬው ፈጣሪን ያለመፍራት ደረጃ ጥቂት የማንባለውን  ቋንቀኝነት አደረሰው ።  ሰውን በቋንቋው መከፋፈል ። ሰውን ከፋፍሎ  በየቋንቋው መፈረጅም በእጅጉ ተሥፋፋ ። ከአንድ ቋንቋ ቤተሰብ የተወለደ ግለሰብን እንኳ በነውረኛ ድርጊቱ መኮነን  መላውን የቋንቋውን ቤተሰብ መድፈር እንደሆነ ተቆጥሮ በየመንደሩ የሁከት ፣ የብጥብጥና የመገዳደል ሰበብ ሆኖ ነበር  ።

የእገሌን ልጅ ተናገርክ ፤ ሰደብክ ፤ ነገሩን ፣ ድርጊቱን ኮነንክ ፤ ...አንተ እንትን ሥለሆንክ ። የሚሉ የነገር ሰይፎች እጅግ   በርክተው የስንቱን ንፁሐን አንገት እንደቀነጠሱ ሾርት ሚሞሪ ከሌለን በሥተበር አንረሳም ። የባሰ አውሬነት ደግሞ በቅርቡ  በምዕራብ ና በምሥራቅ ወለጋ ሲከሰት ሰብዓዊነት ጠፍቶ ለዜጎች ሞት የሚቆጭና የሚንገበገብ ባለሥልጣን ጠፋ   ።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ፣ ዛሬ እና አሁን ያልባነንን መቼ እንደምንባንን ከቶም አይገባኝም ። መንግሥት ህዝብን በሚበጀው ወይም ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርገው ፣ ዜግነቱን በሚያሶድደው መንገድ ህዝብን መመራት አለበት እንጂ በጠላቶቻችን በሚዘወሩ ኢ _ ሰው እና ፀረ _ፍቅር በሆኑ ባለነፍጥ ፖለቲከኞች ማስፈራርቾ እሥከመቼ ፓለቲካውን  እያስታመመ አገርን በተረጋጋ ሁኔታ ማሥተዳደሩን በወከባ ይቀጥላል ?

የበለፀጉት አገራት ታሪክ የሚነግረን ጠንካራ መንግሥት ለመገንባት በወታደራዊ ህግ ብቻ የሚመራ መከላከያ ሠራዊት እና የአገርን ጠላቶች አሥቀድሞ በማነፍነፍ ፤ከጥፋት የሚታደግ የሲቪሊና ወታደራዊ ደህንነት አሥቀድሞ መገንባት ያሥፈልጋል ። ( ዛሬም የተጠናከረ የደህንነትና የመከላከያ ተቋም እንዲኖራቸው ለነዚህ ተቋማት የሚያወጡት ወጪ የሠራዊት እንክብካቢያቸው ከፍተኘ ነው ። )  እኛም በአቅማችን ከፍተኛውን በጀት   ለመከላከያ ና ለደህንነት ኃይል በመሥጠት መንግሥትን አጠናክረን ፣ በዜጎች ቅቡልነት ያለው ተከታታይ የሆነ ጠንካራ መንግሥታዊ ተቋማ ሊኖረን ይገባል ። ብዬ አምናለሁ ። በዚህ ረገድ የመንግሥት ጥረት የሚያስመሰግነው ቢሆንም ፣ ከፓለቲካው አንፃር ግን ፈቀቅ ያለ ተጨባጭ ለውጥ በበኩሌ አላየሁም ። መንግስት ዛሬ በከፍተኛ “ የማንን ልመን ? “ ጥርጣሬ ውሥጥ የወደቀም ይመሥላል ።

ዛሬ እና አሁን  መንግሥት እንደግለሰብ ማንን ማመን ማንንስ ያለማመን ጥርጣሬ ውሥጥ ሊወድቅ የቻለው ፣ካለፈው የደርግ አዙሪት ያልወጣ የፓርቲ አባላትን ይዞ ሥለሚጓዝ ነው ። እርግጥ ነው በሥም ፓርቲው ተለውጧል ። በግብር ግን የተለወጠ አንዳች ነገር የለም ። መንግሥት በአንክሮ ከተመለከተ ዘሬም የሚጓዝበት አደረጃጀት ደርግ ከመሠረተው ቀበሌ ና ገበሬ ማህበር የሚነሳ ነው ። ዛሬም የማዘጋጃ  ተቋማዊ ሥርዓት ሳይሆን የካድሬ ቀበሌያዊ አሥተዳደር ነው ።  ዛሬም ፓርቲና መንግሥት አልተለየም ። በመሆኑም በፓርቲ ሥም  ከቀበሌ ጀምሮ በሰው ነፍሥ የሚወሥኑ እግዜሮች ቢኖሩ አይገርምም ። ከደርግ ጀምሮ ነበሩና !!!!!!!!

በበኩሌ መንግሥት ወይም ገዢው ፓርቲ  ለ21 ኛው ክ/ዘ የሚመጥን የመንግሥት ሥርዓት ለማዋለድ አንድ ብርቱ ዘዴ ካልቀየሰ በታሪክ ተወቃሽ ሊሆን የሚችልበት መሥቀለኛ መንገድ ላይ እንዳለ ይታየኛል ።

በተለይም በትግራይ  ያለው ፣ ሰው መሆንን የካደ የሊሂቅ ሥብሥብ አጥፍቶ መጥፋት አላማው ነውና አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ንብረት በሆነው መሬት ፤ በእኔነው ባይነት በብርቱ ይከራከራል ። ይኽንን ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት እኩይ መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ቅቡል የሆነ ልዩ ዘዴ እና ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ አዲስ የዜጎች እኩልነት መንገድን  መንግሥት ሣይዘገይ መቀየሥ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ ። ያ ዘዴም የትግራይ ህዝብ ሰውነትን በካደው ፣ የትግራይ ሊሂቅ ላይ የሚነሳበት እና እሥከወዲያኛው የሚጠራርገው መሆን ይኖርበታል ። ልብ በሉ የትግራይ ህዝብ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ የኢትዮጵያ ግዛት ሁሉ አገሩ መሆኑንን በተጨባጭ ከተረጋገጠለት እጅግ የሚያስደንቅ ኢትዮጵያዊነቱን የወያኔንን ግብአተ መሬት በመፈፀም ያረጋግጣል ።

 

 

 
https://amharic-zehabesha.com/archives/176253

No comments:

Post a Comment

https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD       https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf   https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...