Friday, July 1, 2022
ወዴት እያመራን ነው? - ባይሳ ዋቅ-ወያ1
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣
ለአሥር ዓመት ያህል ሳላቋርጥ በትምሕርቴና በሙያዬ፣ እንዲሁም ከዓለም አካባቢ በቀሰምኩት ልምድ ላይ ተመሥርቼ አገሪቷ ላይ እያንዣበበ ስላለው አደጋ በተደጋጋሚ መፍትሔ ተኮር መጣጥፎችን ስጽፍ ነበር። ሳያድለን ቀርቶ፣ ለመገዳደል እንጂ ተነጋግሮ ሃሳብን በሃሳብ ሞግቶ አሸናፊውን ሃሳብ በተግባር አውሎ ያገሪቷን ኅልውናና የሕዝቦቿን አብሮነት ለማጠንከር የሚተጋ ፖሊቲከኛ፣ አክቲቪስት ወይም የምሑራን ቡድን በማጣቴ መጻፉና መወትወቱን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቁሜ ነበር። አገራችን ወደ የርስ በእርስ ግጭት ወይንም ጦርነት እያመራች ነውና ተነጋግረን ከዚህ አደጋ እንታደጋት ብዬ “የርስ በርስ ጦርነት መንሥዔውና መፍትሔው” በሚል ርዕስ ሰፋና ጠለቅ ያለ ጽሁፍ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሜ፣ የችግሩ መንሥዔም መፍትሔም ናቸው ብዬ ለማምንበት ሁሉ አካፍዬ አንዳችም የተጨበጠና “መድረክ ፈጥረን ስለ መፍትሔው እንወያይ” የሚል ግለ ሰብም ቡድንም ስላላገኘሁ፣ ሰሚ የማላገኝበት ከንቱ ልፋት ሆኖብኝ፣ ምናልባት ሌላ ዘዴ ይገኝ እንደሁ እስቲ ጊዜዬን ወስጄ ላስብበት ብዬ ለጊዜው “ብዕሬን ሰቅዬ” ነበር።
ብዕሬን እንደገና እንዳነሳ ያስገደደኝ ጉዳይ ሰሞኑን በወለጋ የተከሰተው አሰቃቂው ጭፍጨፋ ነው። ለሶስት አሥርተ ዓመታት ያሕል ከሙያዬ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በተለያዩ የግጭት ቀጠናዎች ተዘዋውሬ በሠራሁባቸው ዓመታት፣ ብዙ ግድያዎችንና፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ያየሁ ቢሆንም፣ በገዛ አገሬ እንዲህ ዓይነት ነገር ይደርሳል ብዬ ግን አንድም ቀን አምኜበት አላውቅም። ከሙያዬ ከተሰናበትኩ በኋላና የአገራችንን ፖሊቲካና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ ከቅርብ ሆኜ ማስተዋል ከጀመርኩ በኋላ ግን፣ ይዋል ይደር እንጂ አንድ ቀን አንድ ቦታ ላይ እንዲህ ዓይነቱ በስፋቱም ሆነ በጥልቀቱ ካለፉት ሁሉ የከፋ የጅምላ ጭፍጨፋ በአገራችን እንደሚካሄድ ይታየኝ ነበር። አሁን ደርሶ “ሊሆን ይችላል ብዬ የተነበይኩት ሆኖ ሳገኘው” ግን እጅግ በጣም አሰቀቀኝ። እጅግ በጣም ዘግናኝና አስቃቂ ጭፍጨፋ! የትም ይሁን የት፣ ማንም ይፈጽመው ማን፣ በማንም የሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይገባ አረመኔያዊ ድርጊት ስለሆነ፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊወገዝ የሚገባ ወንጀል ነው። ስለሆነም ወንጀለኞቹ ያላንዳች መዘግየት ለፍርድ ቀርበው በሕግ በተደነገገው መሠረት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በያለንበት ማሳሰብ አለብን። ከዚህ በፊት ለተፈጸሙት ከባድ የሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ወንጀሎች (የአማራ ክልል ባለ ሥልጣናት ግድያ፣ የኤንጅኔር ስመኝ፣ የሓጫሉ ሁንዴሳ፣ የጄኔራል ጻዕረ፣ በጅምላ ወገንን በእሳት ያጋዩትን፣ ወጣቱን በአደባባይ የረሸኑትን ወዘተ) አንድም ግለሰብ ወይም ቡድን ለፍርድ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት ያገኘ ወንጀለኛ ስላላየሁና፣ ዛሬ በምዕራብ ወለጋ ወገኖቻችንን በጅምላ የጨፈጨፉትን ግለሰቦች ወይም ቡድኖችን መንግሥት ለፍርድ ያቀርባል የሚል አንዳች እምነት ባይኖረኝም፣ መቼም አገሪቷን እመራለሁ የሚል መንግሥት በቦታው ስላለ፣ እነዚህን ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብና ግልጽነት ባለው መንገድ የፍርድ ሂደቱ እንዲካሄድ መጠየቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ መሆን አለበት እላለሁ።
አዎ! ለተጨፈጨፉት ወገኖቻችን የኅሊና ጸሎት ማድረግ፣ ለተጠቁ ወገኖች የዕርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የተቃውሞ ሰልፍ ማዘጋጀት፣ የዓለም አቀፍ ማኅበረ ሰቡን ማነቃቃት ወዘተ እጅግ በጣም አስፈላጊና መደረግ ያለባቸው ሰብዓዊ ድርጊቶች ቢሆኑም፣ ዛሬ ለተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል እንደዉ ኅሊናችንን ለጊዜው ለማደንዘዝ ይረዳን እንደው እንጂ ለዚህና ለወደፊትም ሊፈጸሙ ስለሚችሉ ተመሳሳይ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ አያመጡም። መፍትሔው ከዚህ ዘለግ ይላል። ችግር ሲፈጠር ብቻ በሰብዓዊ ግልፍተኝነት ስሜት ተመርተንና የተፈጸመውን ግድያና ጭፍጨፋ ብቻ አውግዘን ወደየቤታችን የምንመለስ ከሆነ፣ ሰቆቃችን በዚህ አያበቃም። ጥልቅ ብሔራዊ ቀውስ ውስጥ ነው ያለነው። ይህንን አገራዊ ቀውስ ደግሞ፣ ዕንባችንን እንደ ምንም ብለን ካበስን በኋላ፣ አንድ ላይ ተቀምጠን በቀናነት ተወያይተንበት ሕዝባችንን ከተመሳሳይ አደጋ የምናድንበትን ዘዴ መቀየስ አለብን። ዘወትር እንደምለው፣ ለዚህ ሁሉ አደጋ ተጠያቂው የአማራ፣ የኦሮሞና የትግራይ ጽንፈኛ ኤሊቶችና ምሁራን፣ የፖሊቲካ ሥልጣን ጥመኞችና በነዚህ ቡድን በሚጫረው እሳት ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፉና የሚያራግቡ አክቲቪስቶችና የሚዲያ ተቋማት ባላቤቶች ዩቲዩቤሮች ናቸው። ከዘጠና ዘጠኝ በመቶ በላይ የሚሆነው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፣ ሳይድለው ቀርቶ፣ ለነዚህ የፖሊቲካ ሥልጣን ጥመኞችና የብሔር ጽንፈኞች መናጆ ሆነ እንጂ፣ ከሌላ ብሔር ተወላጅ ጋር አብሮ ይኖር እንደ ነበረ ሁሉ ለወደፊትም አብሮ ለመኖር አንዳችም ችግር የለበትም።
ደጋግሜ እንዳልኩት፣ የዛሬውን ችግራችንን ለመቅረፍ እንዲረዳን፣ በመጀመርያ ደረጃ ላይ ማተኮር ያለብን፣ በችግሮቻችን መገለጫዎች (symtoms) ላይ ሳይሆን ለዚህ ሁሉ ችግር በዳረጉን መሠረታዊ ምክንያቶች (root causes) ጎልጉሎ ማውጣት ላይ መሆን አለበት። የመሠረታዊ ችግሮቻችንን ምክንያቶች ከሥሩ ጎልጉለን ካላወጣን ደግሞ አቶ ሓዲስ ዓለማየሁ ከታኅሳሱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ በንጉሡ ትዕዛዝ መሠረት፣ “መፈንቅለ መንግሥቱ ለምን ተከሰተ” የሚለውን ጥያቄ በጥልቅ
አጥንተው ባቀረቡት ዘገባ ላይ እንዳካተቱት፣ “ለማናቸውም ነገር መነሻ የሆነው ሥሩ እንደ ተደበቀ ተቀምጦ ከላይ የሚታየውን ቅርንጫፉን ብቻ ቢጨፈጭፉትና ለጊዜው እንኳ የጠፋ ቢመስል፣ የተመቸ ጊዜ ሲያገኝ የተደበቀው ሥር ዳብሮ ተስፋፍቶ ለማጥፋትም እንደሚያስቸግር ሆኖ በብዛትና በብርታት ይነሳል። ይህ እንዳይሆን፣ መነሻ የሆነው ምክንያት ደህኖ ሆኖ ተመርምሮ ከታወቀ በኋላ ሁለተኛ እንዳይቆጠቁጥና እንዳይቀጥል ከሥሩ መቆፈርና ነቅሎ መጣል ነው እንጂ ከላይ ቅርንጫፉን መጨፍጨፍ ምንም ያህል ጠቃሚ አይሆንም”። ሙሉ በሙሉ እስማማበታለሁ። ስለሆነም፣ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ ሁሌም ለዘላቂ መፍትሔ ፍለጋ ይረዳሉ ከምላቸው ደርዘን ሃሳቦቼ ውስጥ ለጊዜው አንዱን ብቻ ላነሳ እፈልጋለሁ። ሌሎቹን ደግሞ፣ የዚህኛውን ዙር ሃዘናችንን ከጨረስን በኋላ ፈጣሪ አድሎን አንጻራዊ ሰላም አግኝተን ረጋ ብለን ማንበብ የምንችልበት ደረጃ ላይ ስንደርስ በዝርዝር እመለስበታለሁ። በዚህኛው ዙር ላይ ላተኩር የፈለግሁት ተወያይቶ አለመግባባትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ባሕል ለማዳበር ስለ አለመቻላችን ነው። በኔ ግምት፣ ይህ ዋናው አገራዊ ችግራችን ነው።
አለመግባባትን በጉልበት ሳይሆን በውይይት የመፍታት ባሕል ለማዳበር አለመቻላችን እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው። ከአንዳንድ የደቡብ ሕዝቦቻችን አንጻራዊ የውይይት ባሕል በስተቀር፣ ሌላው በሙሉ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ የላቀ ትምሕርት ያገኘውም ሆነ ፊደል ያልቆጠረው ሰፊው ሕዝባችን፣ ፈጣሪ በለገሰን ጭንቅላት ሳይሆን አለመግባባትን ኋላ ቀር በሆነው ጡንቻ ብቻ የመቅረፍ ባሕል ያዳበርን ሕዝቦች ነን። ኋላ ቀር የሆነው የፊውዳል ሥርዓቱን እሴቶች ወርሰን፣ ዕይታችንንና አስተሳሰባችንን የማይጋራውን ወገን መውጋትና አሸንፎም ከድል በኋላ አስገብሮ በሰላም አብሮ የመኖር ሳይሆን፣ ተሸናፊውን በአካልም ሆነ በኅሊና አድቅቀን ዳግመኛ ሰዋዊ ቁመና እንዳይኖረው ማንበርከክ፣ ቅስም መስበር፣ ማዋረድ “የጀግና ባሕል” ይመስለናል። ሳያድለን ቀርቶ ከቴዎድሮስ፣ ዮሃንስ እና ምኒልክ፣ ከደርግ ከኢህአዴግ እና ዛሬም ካለው አገዛዝ የተማርነው ይህንኑ “ጠላት” ተብሎ የተፈረጀውን ተቃዋሚ ቡድንና ግለ ሰብ ዜጋ ማድቀቅና ማሸማቀቅ ነው እንጂ “የጠላትን/የተቃዋሚን” ሃሳብ በሃሳብ የመውጋት ባሕል ለማዳበር አልቻልንም። እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩና ለዘመናዊ ዲሞክራሲያዊ የግጭቶች ማርገቢያና መፍቻ ዘዴዎች ላልተጋለጡ ዜጎቻችን ይቅርና በዲሞክራቲክ አገሮች ውስጥ እንኳ ኖረው ወይም ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያንም ጭምር ይህንኑ “አገር በቀል” የችግር መፍቻ (ጠላትን ማሸነፍና ማድቀቅን) ልምዳችንን እንደ ብቸኛ መፍትሔ አድርገው መቀበላቸውና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በአውሮፓና በአሜሪካ መዲናዎች ሲተጉ ከማየት በላይ እጅግ በጣም አሳሳቢና አሳፋሪ ነገር የለም።
ሁኔታው የሚያሳዝነን ያሕል፣ ባሕሉን ለማዳበር የሚረዳንን ዘዴ ለመቀየስ ደግሞ መፍትሔው፣ በመጀመርያ ደረጃ ከላይ በጠቀስኳቸው ባለ ድርሻ አካላት፣ ከዚያ ወረድ ብሎ ደግሞ በነሱ አማካኝነት፣ በሰፊው ሕዝብ መካከል ጥልቅ ውይይት ሲካሄድ ብቻ ስለሆነ፣ ዛሬ እያንዳዳችን ያጠለቅነውን የማንነት ጭምብል አውልቀን፣ የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ልዩነቶቻን ላይ በግልጽ ተወያይተን፣ ከተቻለ ለመስማማት፣ ካለተቻለም ደግሞ ላለመስማማት ተስማማተን፣ አንዳችን አንዳችንን ሳንገድል፣ በሰላም አብረን የምንኖርበትን አቅጣጫ ለመቀየስ መቻል አለብን። ሌላ ምንም አማራጭ የለንም። በነፍጥ ብርታት ለአገራዊ ቀውስ መፍትሔ የተገኘበት አገር የለም። ለወደፊትም አይኖርም። ዓመጽ ዓመጽን ወልዶ በየተራው ከመገዳደል ባሻገር፣ አገራዊ መፍትሔ ተገኝቶ ሕዝባችን በሰላም ሊኖር አይችልም። ወደድንም ጠላን በአንድ አገር የምንኖር፣ የአንድ አገር ሕዝቦች ነን። የፖሊቲካ ሥልጣን ጥመኞች ሰለባ ሆኖ ነው እንጂ የሰማኒያ አምስቱ የኢትዮጵያ ብሔር ሕዝቦች መካከልማ አንዳችም ለግጭት የሚዳርግ እንኳን ምክንያት ሰበብም የለም። ሁላቸውንም ያለ አንዳች አድልዖ አንድ ላይ በእኩልነት ጠፍሮ የያዘ ድኅነት የሚባል ከይሲ ክስተት ስላለ፣ አብሮነታቸውን በተመለከተ አንዳችም ችግር የለም።
ስለዚህ ወገኖቼ፣ መፍትሔው አንድና አንድ ብቻ ነው። ችግራችንን ለመፍታት የሚረዳን ነፍጥ ሳይሆን መወያየት፣ መወያየት፣ እንደ ገና መወያየት ብቻ ነው። ለዕውነት ስለ ዕውነት በዕውነት የሕዝባችን አንድነትና የኢትዮጵያ ኅልውና የሚያሳስበን ከሆነ ዛሬ ነገ ሳንል፣ መድረክ ፈጥረን በወቅታዊ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ለወቅታዊው ቀውሶቻችን መነሻ ሊሆኑ የሚችሉትን መሠረታዊ ችግሮቻችን ጎልጉለን የምናወጣበት የውይይት መድረኮችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለማመቻቸት በቁርጠኝነት መነሳሳት አለብን። እያንዳንዳችን የየብሔራችንን ጭምብል አጥልቀን ጥግ ጥጉን ይዘን በጎሪጥ የምንተያይና አጋጣሚ ስናገኝ “ሃበሻዊ የአለመግባባትን መፍቻ ዘዴ (ጉልበትን) ተጠቅመን ሌላውን ለማንበርከክ የምናልም ከሆነ ትናንት በከሚሴ፣ ዛሬ ደግሞ በወለጋ የተከሰተው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ነገ ደግሞ በጉሙዝ ወይም በጂንካ መከሰቱ አይቀሬ ነውና ከልብ እናስበብት። ቅንነቱና ፍላጎቱ ጠፋ እንጂ ዕውቀቱንም ችሎታውንም ፈጣሪ ለግሶናል። ትዕግሥትና ብልኃቱን ግን ደጋግሞ ያብዛልን።
*****
- ጸሃፊው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለ ሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለ ሙያ ናቸው።
ጄኔቫ፣ ሰኔ 23 ቀን 2023 ዓ/ም
wakwoya2016@gmail.com
https://amharic-zehabesha.com/archives/173761
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment