Wednesday, June 22, 2022
ቃል በተግባር ይገለጽ - ከተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን
ስኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም.
በአንድ አገር የፖለቲካ ሂደት ዉስጥ ላለዉ የዴሞክራሲ እድገትም ሆነ ዉድቀት ምሁራን፣ የሕዝብ አንቂዎች እና የአደባባይ ስዎች በመባል የሚታወቁ ታዋቂ ግለስቦች የየራሳቸዉ ድርሻ አላቸዉ። እነዚህ ግለስቦች በሚያፈልቋቸዉ አዳዲስ ሀሳቦች እና በሚሰነዝሯቸዉ የሰላ ትችቶች የሕዝብን ንቃተ ህሊና በማሳደግ መንግስት የሚከተለዉን የተሳሳተ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ እንዲቀይር ወይም እንዲያሻሽል ተጽኖ ይፈጥራሉ። በሌላ ጎን ደግሞ መንግስት በሕዝብ ላይ የሚያደርስዉን በደል፣ የሰባዊ መብት ጥስት እና የሕግ የበላይነትን አለማክበር እያዩ ድምጻቸዉን ካላሰሙ በሀገሪቱ ላይ ለሚደርሰዉ የዲሞክራሲ ዉድቀት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ከተጠያቂነት አያመልጡም።
እንደነዚህ ያሉ ግለስቦች በመንግስት ተቋማት ዉስጥ የማገልገል እድል ሲገጥማቸዉ በዉጭ ሆነዉ ለፍትሕ፣ ለሕግ የበላይነት እና ለዲሞክራሲ መጎልበት ሲያበርክቱት ከነበረዉ አስተዋጽዎ በበለጠ ተጨባጭ እና አመርቂ ለዉጥ እንዲመጣ ቀጥተኛ ተሳትፎ እና ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ፡ ያጋጠማቸዉን እድል በአግባቡ ካለመጠቀም ወይንም ከሥልጣን ጥመኝነት የተነሳ ስለሕግ የበላይነት እና ስለዲሞክራሲ የነበራቸዉን እቋም እና አመለካከት በመዘንጋት ሲተቹት እና ሲጸየፉት ከነበረዉ አስተሳሰብ ጋር እጅ እና ጓንት ሆነዉ ከተገኙ ለዲሞክራሲው ዉድቀት ተባባሪ ይሆናሉ።
ከዚህ በመነሳት ይህንን ጽሑፍ እንድንጽፍ መነሻ ምክንያታችን ወደ ሆነዉ ጉዳይ እንገባለን። ይሄዉም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተመርጠዉ የመገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባላት እንዲሆኑ የታጩትን ዘጠኝ እጩዎች እራሱ ምክር ቤቱ በ 2013 ዓ.ም. ያወጣዉን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በሚጻረር መልኩ በወቅቱ ከተገኙት 243 የምክር ቤቱ አባላት በ 11 ተቃዉሞ፣ በ17 ድምፅ ተዓቅቦ እና በቀሪዉ አብላጫ ድምጽ ሹመታቸዉን ያፀደቀበት ሕግ ነዉ።
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/13 አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ፤ ማንኛዉም ሰዉ የቦርድ አባል ለመሆን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይንም ተቀጣሪ ያልሆነ መሆን እንዳለበት በግልጽ ተደንግጎ እያለ በማን አለብኝነት በሚመስል መልኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረቡት ዘጠኝ እጩዎች መካከል በወቅቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር) የብልጽግና ፓርቲ አባል እንደሆኑ እያታወቀ ሹመታቸዉን አጽድቋል። ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ማድርጉ የሕግ ጥሰት ብቻ ሳይሆን መንግስት የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ በተቋሟት ዉስጥ ለማስረጽ እና ብሎም ለመቆጣጠር ያደረገዉ ግልጽ ጣልቃ ገብነት ነዉ።
ይህን አይን ያወጣ የሕግ ጥሰት በመቃወም ምክር ቤቱ ዉሳኔዉን እንዲያርም የሲቪል ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም የግል ሚዲያዎች እና ማሕበረሰብ አንቂዎች በተደጋጋሚ ያቀረቡትን የሕግ ይከበር ጥያቄ፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤትም ሆነ የሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዉ በሕግ ጥሰቱ ቀጥለዉበታል።
በእንደዚህ ያለ አስቸጋሪ ወቅት ነዉ ከላይ እንዳስፈርነዉ ምሁራን እና ታዋቂ ግለስቦች እድሉን አግኝተዉ በመንግስት ተቋማት ዉስጥ ማገልገል ሲጀምሩ በሀገሪቱ ዉስጥ ለሚፈጠረዉ የዲሞክራሲ እድገትም ሆነ ዉድቀት ተሳትፏቸዉ ወሳኝ ሚና የሚኖረዉ። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነዉ ለመገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባልነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ታጭተዉ ሹመታቸዉ ከፀደቀላቸዉ ዘጠኝ እጩዎች መካከል ባላቸዉ እዉቀት እና በማሕበረሰብ አንቂነታቸዉ ከሚታወቁት የዘመናችን ሰዎች፡ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) እና ወዳጄነህ ማዕረነ(ዶ/ር) ይገኙበታል።
እነዚህ ሁለት ታዋቂ ሰዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ ዉስጥ ስላለዉ የወቅቱ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮችን አስመልክተዉ ባቀረቧቸዉ ጽሕፎች፣ ባደረጓቸዉ ቃለ ምልልሶች እና የአደባባይ ንግግሮች በማሕበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት እና ተደማጭነትን አትርፈዋል። ይህንንም ከመገንዘብ ይመስላል፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ እነዚህ ምሁራን ያካበቱትን እዉቀት እና ልምድ የመንግስት ታቋም በሆነዉ በመገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባላት በመሆን ሀገራቸዉን እንዲያገለግሉ በእጩነት ያቀረቧቸዉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን በማድረጋቸዉ ሊመሰገኑ ይገባል። እንዲሁም ተሿሚዎቹ በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን እድል በመጠቀም ለሚዲያ ነጻነት እና ለዲሞክራሲ እድገት ተግተዉ በመስራት የተጣለባቸዉን ኃላፊነት በመወጣት የየድርሻቸዉን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።
ከሚያበርክቱትም ድርሻ እንዱ እና ዋነኛዉ ነዉ ብለን የምናምነዉ ለሕግ የበላይነት ዘብ መቆምን ነዉ። ይህም ስለሆነ፡ የብዙኃን መገናኛ አዋጅ የሚደነግገዉን ሕግ በመጣስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፈጸመዉ የሕግ ጥስት ተሿሚዎቹ በወቅቱ ተጠያቂ ባይሆኑም የእጩዎች ሹመት መጽደቁን ተከትሎ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እና በሚዲያ ለተነሳዉ የሕግ ይከበር ተቃዉሞ እዉቅና በመስጠት ተገቢዉን የእርምት እርምጃ እስካሁን ሊውስዱ ይገባ ነበር። በቅድሚያ፡ ሁለቱ ያለ አግባብ የተሾሙት የቦርድ አባላት ሕግ ተጥሶ የተሾሙ መሆናቸዉን ተገንዝበዉ በራሳቸዉ ፈቃድ ከቦርድ አባልነታቸዉ መልቀቅ ነበረባቸዉ። ሆኖም ግን ይህን ባለማድረጋቸዉ የተቀሩት የቦርድ አባላት ለተፈጸመዉ የሕግ ጥሰት መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ ሁለቱን የቦርድ አባላት በተለዋጭ እጩዎች እንዲተካ፤ ካልሆነ ግን፡ ለሕግ የበላይነት መከበር ሲሉ ሁሉም በፈቃዳቸዉ ከሹመታቸዉ በመልቀቅ እጃቸዉን አንስተዉ የሀገሪቱን ሕግ ጠብቀዉ ሊያስጠብቁ ለማረጋገጥ የገቡትን ቃለ መሐላ አክብረዉ የተጣለባቸዉን የዜግነት እና የሞራል ግዴታ በተወጡ ነበር።
የአንድ ተቋም ጥንካሬዉም ሆነ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆኑ በዋነኛነት የሚለካዉ በሚመሩት ሰዎች ችሎታ፣ ብቃት እና ገለልተኝነት ልክ ነዉ። ከዚህ ተነስተን በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰአት እራሱ በተደጋጋሚ ሕግን የጣሰ መንግስት፤ በጦር መሣሪያ ማስመዝገብ ሽፋን ወደ ሕግ ማስከበር ፈሊጥ ትሸጋግሮ በመላዉ ሀገሪቱ በሚመስል መልኩ በተለይም ደግሞ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ወታደራዊ ዘመቻዉን እያፋፋመ ነዉ። በዚህ ባለፉት ሁለት ሳምንታት እንኳን እራሱ መንግስት በስጠዉ መረጃ በአማራ ክልል ብቻ ከ4,500 ባላይ ዜጎችን በተጠርጣሪነት ለእስር ሲዳራጉ፡ ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ተገድለዋል። በተልይም ደግሞ፡ መንግስትን በሰላ ብዕራቸዉ የሚተቹ ጉምቱ ጋዜጠኞቸ እና ታዋቂ የማህበረሰብ አንቂዎቸ እንደ እሽባሪ ያለ ሕግ አግባብ በተገኙበት ታፍነዉ ታስረዋል። መንግስት እነዚህን ጋዜጠኞች በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/13 መሰረት ሕጉን ተከትሎ ክስ መመስረት ሲገባዉ፡ ዉሉ ያልታወቀ ተለዋዋጭ ዉንጀላ እያቀረበ በተለዋጭ ቀጠሮ የመገናኛ ብዙኃን እካል የሆኑትን ጋዜጠኞች ለችግር ሲዳርግ፤ ከላይ ስማቸዉን የዘረዘርነዉ ተሿሚ የቦርድ አባላቱ ድምጻቸዉን አላሰሙም።
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረዉ ለዲሞክራሲ እድገት እና መጎልበት በሁሉም የባለ ድርሻ አካላት የሚደረጉ ተሳትፎዉች ከፍተኛ ሚና አላቸዉ። በይበልጥ ግን የሚስነዘሩ ሀሳቦች እና በአደባባይ የሚተላለፉ ንግግሮች በተግባር ቢገለጹ ሚዛን ይደፋሉ። ይህም ስለሆነ እነዚህ ተሿሚ የቦርድ አባላት፡ በተለይም ደግሞ ሁለቱ የማሕበረሰብ አንቂ እና የአደባባይ ስዎች ሲጽፏቸዉ እና ሲናገሯቸዉ የነበረዉን ተግባራዊ በማድረግ የቦርድ አባላቱ በራሳቸዉ ፈቃድ ከስልጣናቸዉ እንዲለቁ የመሪነቱን ሚና በመጫወት ለሕግ ያበላይነት እና ለዲሞክራሲዉ እድገት የብኩላቸዉን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል።
ይህን ኃላፊነት አለመቀበል ሕዝብ ለፖለቲከኞች፣ ለመሐበረስብ አንቂዎቸ እና ለሙህራን ያለዉን ከፍተኛ ግምት የሚያሳጣ እና በፖለቲካ ሂደቱ ላይ እምነት እንዳይኖረዉ ያደርጋል። በይበልጥም፡ መንግስትን ተጠያቂ እንዳይሆን በመተባበር የሕግ ጥስቱን እንዲገፋበት ፈቃድ መስጠት ይሆናል። በአንጻሩ ግን ከሥልጣናችሁ ብትለቁ፡ ድፍረታችሁን፣ እና የመርህ ሰዉ መሆናችሁን የተመለከተ ተተኪዉ ትዉልድ፡ በራሱ ዘመን ለሚገጥመዉ የሕይወት ፈተና የመፍቻ ቁልፍ፤ ለህልዉናዉ ጥንካሬ ስንቅ ይሆነዋል። አለበለዚያ ግን፡ የታሪክ ተወቃሽ እና የግብዝነት ምሳሌ ትሆናላችሁ።
ከዚህ በመነሳት ለሕግ የበላይነት መከበር ስትሉ የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ እያበረታታን ስማችሁ ከዚህ በታች የተዘረዘረዉ ጠቅላላዉ የቦርድ አባላት ሥልጣናችሁን በፈቃዳችሁ እንድትለቁ በአጽንዎት እንጠይቃለን።
- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ስብሳቢ (በአሁን ሰአት የጠ/ሚ የደኅንነት እማካሪ)
- እምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ከቱሪዚም ሚኒስቴር፤ አባል
- እምባሳደር ሀስን እብዱልቃድር ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል፤ አባል
- አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ አባል
- በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ አባል
- መሣይ ገ/ማሪያም (ዶ/ር)ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ አባል
- ወዳጀነህ ማዕረን (ዶ/ር) አማካሪ፤ አባል
- ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከሃይማኖት ተቋማት፤ አባል
- ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ክሃይማኖት ትቋማት፤ አባል
አስተያየት፡ ከተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን
https://bit.ly/3HZMZ4l
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
https://youtu.be/VUfa5eupQTc?si=Zm73w18dFB27xlqD https://youtu.be/LcFmz2Xq5MY?si=7uP6VZsd2ksEulUf https://youtu.be/7dUVmj8go7s?si=Px...
-
Contact information: Girma Berhanu Department of Education and Special Education (Professor) University of Gothenburg Box 300, SE 405 ...
-
Yonas Biru, PhD In the last fifty some years, four governments have ruled Ethiopia. Emperor Haile Selassie lasted in office for 44 years. ...
-
#image_title አበዉ ኢትዮጵያዉያን "የወንድ ልጂ ሞቱ የተናገረዉን ወይም የሰራዉን የረሳ ዕለት ነዉ ይላሉ "፡፡ ዕዉነት ብቻ ሳይሆን ህያዉ እና በተግባር የተገለፀ ነባር ሀቅ ነዉ ፡፡ ዛሬ በአገራችን ...
No comments:
Post a Comment